
መምህር ኢንጂነር ታሪኩ አበራ ·Follow
·
† የግእዝ ቋንቋ ታሪካዊ አመጣጥና ጥቅሙ †
★ ግእዝ ሞቷል የሚሉት ሙታነ አዕምሮ ናቸው።ግእዝ 70 ሚሊየን ሕዝብ በየቀኑ አምልኮ የሚፈጽምበት፣የ 120 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የሦስት ሺ ዘመን ሕያው ታሪክ ተሰድሮ የተቀመጠበት ጠንካራና ሕያው ቋንቋ ነው።★
ቋንቋ ማለት መግባቢያ ማለት ነው ፡፡ የግእዝ ቋንቋ አመጣጥ ከአንዳንድ ቀደምት የታሪክ ጸሓፊዎችና የግእዝ ቋንቋ መጻሕፍትን ጽፈው ካስረከቡን ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶችና የቋንቋው ባለቤቶች እንደምንረዳው፦ የግእዝ ቋንቋ አመጣጥ በኢትዮጵያ መነሻ ሊሆነን የሚችለው ክርስቶስ ከመወለዱ ከ800 ዓመት ጀምሮ ነገደ ሴም (የሴም ዘሮች/ወገኖች) ቋንቋቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ሴማዊ ቋንቋ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ቋንቋ ሆኗል። ነገደ ሴም ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ቋንቋቸውን በመግባቢያነት አሳድገው፣ ሥነ ጽሑፋቸውን አስፋፍተው በባቢሎን ፣ በአካድና በአሶር ይኖሩ ነበር፡፡ በኋላ ግን ለሁለት ተከፍለው ግማሾቹ ሴማውያን ሰሜንና ምሥራቅ እስያን፣ ግማሾቹ ሴማውያን ደግሞ ደቡብ እስያን ይዘው ይኖሩ ነበር፡፡
የሰሜን እስያ ሴማውያን ቋንቋ (የአካድ ቋንቋ)፦ አርማይክ፣ ዕብራይስጥን እና ፊንቄን ሲያስገኝ የደቡብ እስያ ሴማውያን ቋንቋም (አካድ ቋንቋ)፦ ሳባን ግእዝንና የተለያዩ በኢትዮጵያ ውስጥ በመግባቢያነት የምንጠቀምባቸውን ሴማውያን ቋንቋዎች አስግኝቷል፡፡ በደቡብ እስያ ይኖሩ የነበሩ ነገደ ሴም በተለያየ ምክንያት እየፈለሱ ወደ ደቡብ ዐረብ ወደ የመንና ወደ አካባቢዋ መጥተዋል ከዝያም ፈልሰው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በአክሱምና በአካባቢዋ ሰፍረው ይዘዋቸው ከመጡት ቋንቋዎቻቸው መካከል በታሪክ ጎልተው የሚታወቁና አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩትና በአሁኑ ሰዓትም በአገልግሎት ላይ የሚገኙት ቋንቋዎች የሳባ እና የግእዝ ቋንቋዎች ናቸው፡፡
ነገደ ሴም(ሴማውያን) ቋንቋዎቻቸውን /ሳባና ግእዝን/ ከነገደ ካም ቋንቋ ጋር አስማምተው በመያዝ ሁሉንም ቋንቋዎች ሲናገሯቸው ኖረው ነበር፡፡ በኋላ ግን ሳባና ግእዝ እየተለመዱና እየተስፋፉ እየዳበሩም ከመሄዳቸው የተነሣ የነገደ ካምን ቋንቋ እየዋጡት መጥተው ሁለቱ ሳባ እና ግእዝ ቋንቋዎች ብቻ ሀገራዊ ቋንቋዎች ይሆኑ ጀመር እየቆዩ ግን ሁለቱ (ሳባና ግእዝ) በጣም ተመሳሳይና ተቀራራቢ በመሆናቸው እንደ አንድ ቋንቋ ሆነው ይነገሩ ጀመር፡፡ ይኸም ጽሑፉ (ፊደሉ) በሳባ እንዲጻፍ እና መነጋገሪያ ቋንቋውን ደግሞ በግእዝ እንዲሆን በመደረጉ ነው፡፡ ነገደ ሴም በሳባ ቋንቋቸው ሳባውያን፤በግእዝ ቋንቋቸው ደግሞ አግአዝያን ተብለው የሚጠሩት ከዚህ መነሻነት ነበር፡፡
ለዚህም መረጃ የሚሆኑን ሳባና ግእዝ ቋንቋዎች ተጽፈውባቸው የሚገኙት ጥንታውያን የኢትዮጵያ ቅርሶች እንደ የአክሱምና የላሊበላ ሐውልቶች በየሐ እናበአዱሊስ ወዘተ ….. የተለያዩ በድንጋይ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎችና ቅርጻ ቅርጾች እስከ አሁን ቆመው የሚገኙ የዚህ ቋሚና ግልጽ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ የሳባና የግእዝ ቋንቋዎች በዚህ ሁኔታ እስከ 324 ዓ.ም. አካባቢ ድረስ አብረው ሲነገሩ ቆይተዋል በኋላ ግን የሳባ ቋንቋ እየተዳከመና በግእዝ ቋንቋ እየተዋጠ ይሄድ ጀመር እንደ ምንም እየተንገዳገደ እስከ 350 ዓ.ም. ቆይቶ ከዚህ በኋላ ከሥነ ጽሑፍ ከመነጋገሪያነትም ፈጽሞ ቀረ የግእዝ ቋንቋ ግን ከ324 ዓ.ም ጀምሮ ብቸኛ ሀገራዊ ቋንቋ በመሆን እስከ 12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም የአማርኛ ቋንቋ ከግእዝ ቋንቋ ተወልዶ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ እስኪ መጣ ድረስ የግእዝ ቋንቋ በስፋት ሲያገለግል እንደ ነበር የታሪክ ጸሐፊዎች በግልጽ አስቀምጠዋል፡፡
አሁን እየተጠቀምንበት ያለው አማርኛ ቋንቋ ሆሄያቱ የግእዝ ፊደላት ናቸው።በአማርኛ ቋንቋ እየጻፉ ግእዝ አያስፈልግም የሚሉ ሰዎች በዕውቀት ድርቀት የሚሰቃዩ ናቸው።
★ ግእዝን ለምን እናጠናለን? ★
ኢትዮጵያውያን በመሆናችን ግእዝ ቋንቋ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቋንቋ በመሆኑ የግእዝን ቋንቋ ማወቃችን በብዙ ጥበብ የተሞሉ መጻሕፍትን ለማወቅና ለመመርመር ትልቅ ጥቅም ያለው በመሆኑ ስለ ኢትዮጵያ ምንነት ማወቅ ከፈለግን ግእዝ ቋንቋ መማር እጅግ አስፈላጊ ነው። የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያሳዩ ብዙ መጻሕፍት የተጻፉት በግእዝ ቋንቋ ነው። ብዙ ሊቃውንት የግእዝ ቋንቋን ዘመን የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን ነበር ይላሉ።
ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ግእዝ ቋንቋ የሐገራችን ጥንታዊ ቋንቋ ከመሆኑ በተጨማሪ ጥበብ ሥጋዊና ጥበብ መንፈሳዊ ለማወቅ መሠረታዊ እና ቁልፍ ነገር ነው። በግእዝ ቋንቋ ብዙ ጥልቅ ዕውቀት ተጽፎ ይገኛል ስለ ከበሩ ማዕድናት፣ስለ ተለያዩ ፈዋሽ ዕፅዋት፣ስለ ሥነ ፈለክ፣ ስለ ድንቅ ሃገራዊ ታሪኮችና ሌሎችም ሃገራዊ ጉዳዮች በግእዝ ተጽፎ ይገኛል።የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት በብዛት የተጻፉት በግእዝ ቋንቋ ነው አብዛኛዎቹ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ወደ አማርኛ አልተተረጎሙም።
የቅዱስ ያሬድ የዜማ ድርሰቶችም በሙሉ የተደረሱት በግእዝ ቋንቋ ነው ዜማ ለመማር የሚፈልግ ሰው መጀመሪያ ግእዝን ቢማር የመጻሕፍቱን ምሥጢር እንዲረዳ ስለሚያግዘው ከዜማው በፊት ቋንቋውን አስቀድሞ እንዲማር ይመከራል። ዜማ ሲዜም የግእዝ ንባባት ስርዓትን ጠብቆ ነው።
የግእዝ ቋንቋን ጥቅም ያወቁ ብዙ የውጪ አገር ዜጎች እንኳን የኢትዮጵያን ጥበብና እውቀት ለመረዳት ግእዝ ቋንቋን ያጠናሉ ሃያ ስምንት የሚሆኑ አገራት ግእዝ ቋንቋን በየዩኒቨርስቲያቸው ይሰጣሉ።
ስለዚህም ግእዝ ቋንቋን መማር ብዙ ጥበብና ዕውቀት የሚሰጡ መጻሕፍትን ለማወቅ በእጅጉ ይጠቅማል።
ግእዝ ተማሩ
