
ከ 8 ሰአት በፊት
በአሜሪካ አየር መንገዶች የሚደረጉ በረራዎችን እንዲቀንሱ ከተነገራቸው በኋላ ቅዳሜ ዕለት ከአሜሪካ የሚነሱ፣ የሚገቡ እንዲሁም በአገር ውስጥ የሚደረጉ ከ1 ሺህ 400 በላይ በረራዎች ተሰረዙ።
የአየር ጉዞ ቅነሳ የተደረገው የአገሪቱ ምክር ቤት በመጪው በጀት ዓመት የመንግሥት አገልግሎትን ለመደገፍ በወጣው ረቂቅ ላይ መስማማት ባለመቻላቸው ምክንያት የፌደራል መንግሥት ተቋማት በመዘጋታቸው ነው።
እንደ የበረራ ተቆጣጣሪው ፍላይትአዌር ከሆነ አርብ ዕለት ከ7 ሺህ በላይ በረራዎች የዘገዩ ሲሆን ቅዳሜ ዕለት ቁጥሩ ዝቅ ብሎ ወደ 6 ሺህ የሚጠጉ በረራዎች መዘግየት አጋጥሟቸዋል።
ይህ የሆነው የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር፣ የፌደራል ተቋማት በተዘጉ ጊዜ ያለ ክፍያ እየሰሩ ያሉ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ድካም አጋጥሟቸዋል በሚል ሥራ በሚበዛባቸው 40 የአገሪቷ አየር ማረፊያዎች የአየር ጉዞ አቅምን በ10 በመቶ እንደሚቀንስ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ካስታወቀ በኋላ ነው።
ሪፐብሊካን እና ዴሞክራቶች ከባለፈው ወር አንስቶ የቀጠለውን የፌደራል ተቋማት መዘጋትን ማስቆም በሚቻልበት ጉዳይ ላይ በሃሳብ ተከፋፍለዋል።
ሪፐብሊካኖች እና ዴሞክራቶች በገንዘብ ድጋፍ መፍትሔ ላይ እስካሁን መግባባት ባለመቻላቸው በአገሪቷ ታሪክ ያጋጠመው ረዥሙ የፌደራል መንግሥት ተቋማት መዘጋት ቅዳሜ ዕለት 39ኛ ቀኑን ይዟል።
የምግብ ዕርዳታ ክፍያዎች መቋረጥ እና የበረራ መስተጓጎሎች ባጋጠሙበት ወቅት የተቋማት መዘጋት በአሜሪካውያን ዘንድ ስጋት የፈጠረ ሲሆን፣ የምክር ቤት አባላት ተቋማቱ እንዲከፈቱ የሁለትዮሽ ድርድሮችን ለማካሄድ ዋሽንግተን ይገኛሉ።
የአሜሪካ አየር መንገድ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ የዋሽንግተን ዲሲ መሪዎች አፋጣኝ መፍትሔ ላይ እንዲደርሱ አሳስቧል።
