
7 ታህሳስ 2025
ኬቪን ካሮል እና ዴቢ ዌበር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት በአውሮፓውያኑ 1967 ነበር። ሁለቱም በአስራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቲያትር ቡድኖች አባላት ነበሩ። እንደተያያዩ የፍቅር ስሜት ተሰምቷቸዋል።
“እኔ ወንዶች ብቻ የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነበርኩ። ዴቢም የሴቶች ብቻ ትምህርት ቤት ነበረች” ሲሉ ካሮል ለቢቢሲ አውትሉክ ፕሮግራም ተናግረዋል። “የተዋናይ መረጣ ሲካሄድ በጋራ አንድ አዳራሽ ውስጥ ነበርን። ጓደኛዬን ‘ያንቺን ልጅ አየሃት? ለትምህርት ቤት የዳንስ ፕሮግራም እወስዳታለሁ’ አልኩት” በማለት ያስታውሳሉ።
ዌበርም በበኩላቸው፤ “ለተዋናይ መረጣው ከሌላ ትምህርት ቤት ከመጡት ሴቶች አንዳቸውንም ስለማላውቅ አዳራሹ ውስጥ ብቻዬን ተቀምጬ ነበር። እርሱን እንዳየሁት ግን አስታውሳለሁ። ካየኋቸው ወንዶች በሙሉ ቆንጆው ነበር” ይላሉ።
ካሮል እና ዌበር አንድ ላይ ወደ ዳንስ ፕሮግራሙ በመሄድ ብቻ አላበቁም፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የሚነጣጠሉ ሰዎች አልሆኑም። አንድ ጊዜ ለመጋባት ቀላል የሆነ ሂደት ወዳለበት ሜሪላንድ ለመጥፋት ጭምር አቅደው ነበር።
ኋላ ግን ነገሮች ተቀያየሩ። ዌበር ማርገዟ ህልማቸውን ቀጨው። 40 ዓመት ለሚሆን ጊዜ እንዲለያዩም ምክንያት ሆነ
ዛሬ በድጋሚ ተገናኝተዋል። በወጣትነታቸው ሊቀጥሉት ያልቻሉትን ፍቅር እያጣጣሙ መሆኑን ይናገራሉ። እዚህ የደረሱበት መንገድ ግን የሆሊውድ ፊልም ይወጣዋል።
ያልተጠበቀ ዜና
በወቅቱ ከነበረው ማኅበራዊ ምልከታ አንጻር ሲታይ፤ የዌበር ቤተሰቦች ልጃቸው እንዳረገዘች ሲነገራቸው ያሳዩት ድጋፍ እምብዛም ያልተለመደ ነበር።
“በጣም ፍቅር ነበራቸው። ኬቪንን ይወዱት ነበር። ምርጥ ሰው እንደሆነ ያውቁ ነበር። እናም በጣም እንዋደድ ነበር” ሲሉ ዌበር ለቢቢሲ ተናግረዋል። “የዚያን ጊዜ ግን ለሚያረግዙ ታዳጊ ሴቶች የነበረው ሁኔታ የተለየ ነበር” ይላሉ።
