
መስከረም ጌታቸው /Meskerem Getachew ·Follow
ቆይ ስንት ጎጃም ነው ያለው?
ሕዝቡ አንዴ በጦርነት አንዴ በእገታ አንዴ በኑሮ ውድነት ያለበት መንገላታት ይበቃዋል-ቢያንስ ሃይማኖቱንና ባሕሉን ተውለት፡፡ ለወጣችሁበት ማኅበረሰብ ምንም ማድረግ ባትችሉ ዝም በሉ እንጂ አጋጣሚ ተጠቅማችሁ አትሸቅጡበት፡፡
በግሌ ጥበብንና ጥበበኞችን አደንቃለሁ፤ የሰዎችን ተሰጥዖ ቦታ እሰጣለሁ፤ መበረታታት እንዳለበትም አምናለሁ፡፡
ነገር ግን በሥመ ጥበብ እና በሥመ መዝናኛ የአንድ ሕዝብ ባሕል እና ሃይማኖት በዚህ ደረጃ ክብሩን ሲያጣ ማየት አልፈልግም፡፡
ያውም የተወለድሁበት፣ያደግሁበት፣ ራሴን የኖርሁበት ባሕል እንዲህ በራሱ ልጆች የገንዘብ መሰብሰቢያ ሁኖ ሲጨማለቅ ማየት ያማል!
ወዳጆቼ እነዚህ “ተዋነይ” በሚል ዩቱዩብ ቻናል በኩል በድራማ፣ፊልሞችና ሙዚቃዎች የጎጃም ባሕልና ሃይማኖት የሚያራክሱ ወጣቶችን ምከሯቸው እንጂ አታጨብጭቡላቸው፡፡ በተለይም ለጎጃም ሕዝብ ክብርና ፍቅር ያላችሁ ሁሉ በእያንዳንዷ ሳቃችሁና ይሁንታችሁ ውስጥ ለሕዝቡ ንቀት እንዳይሆንባችሁ ተጠንቀቁ፡፡
መጀመሪያ ሁለተኛም ሳይ ልጆች ናቸው እንደኮሜዲ አስበው ነው እያልሁ ነበር፡፡ ግን ዓመታት ተቆጠሩ…ጭራሽ ከአገር ውጭም ልንመጣ ነው ጠብቁን የሚል አየሁ፡፡ ይገርማል ሕዝብን እየሰደቡ ዓለምአቀፍ ጉዞም አለ?
ባይሆን እኔ ያደግሁበት ነውና እውነቱን ልንገራችሁ፡-
አማራ እንደሁሉም ኢትዮጵያዊ በየእምነቱ ፈጣሪውን የሚፈራ ነው፤ ባሕሉን አክባሪ፤ አገሩን ወዳጅ ነው፡፡
የጎጃም እናቶች ለባሎቻችው ትልቅ ክብር ያላቸው ባል የቤት ራስ ብለው አክብረው አስከብረው የሚኖሩ እንጂ የቤቱ ራስ እኔ ነኝ ብለው ጠዋት ማታ ባላቸውን በዱላ የሚቀጠቅጡ ወይ ንቀታቸውን በጸያፍ ስድቦች የሚገልጹ አይደሉም፡፡ ጭራሽ እግራቸውን አንስተው እንደእንስሳ የሚራገጡ እናቶች የሉንም፡፡
የጎጃም አባወራዎች ትዳራቸውን አክባሪ እንጂ ዝሙትን ናፋቂና አበረታች አይደሉም፡፡ ከእነቃላቸውም ከፈለጋችሁ የሕግ ሚስት እና የሕግ ባሏ ወይ ሚስቱ መባል ትልቅ ክብር የሚሰጥበት ማኅበረሰብ እንጂ በየጥሻ እና በመጠጥ ቤቱ ክብር መስጠትን የሚያበረታቱ አይደሉም፡፡ እንዳውም ይጸየፉታል፡፡
ሃይማኖተኞች ናቸው- በየእምነታቸውም ፈጣሪያቸውን ፈሪ! ለሃይማኖት አባቶቻቸው ያላቸው ክብር ይለያል፡፡ ካህናት የእግዚአብሔር ዐይኖች ናቸው የሚለውን ትምህርት አምነው ፤ተደርጎላቸው የሚኖሩ እንጂ አባቶችን የሚያጣጥሉ አይደሉም፡፡
ሠርቶ መለወጥን የሚያበረታቱ ከአፈር ጋር ሲታገሉ ውለው የሚድሩ፣ ጅግኖችን የሚያወድሱ እንጂ በየሠፈሩ ሴቶችን ሲያስሱ የሚዉሉትን ወይ በሴት ፀብ ዱላ ሲመዙ የሚውሉትን የሚያሞግሱ አይደሉም፡፡
ከምንም በላይ የጎጃም ሕዝብ የማኅበረሰብ መዋቅር ጠንቅቆ የሚያውቅ የሚያከብር ነው፡፡ በተዋረድ መከበር ያለበትን አክብሮ ታናናሹን ዝቅ ብሎ አስተምሮ ለኢትዮጵያ ድንቅ ባሕል፣ ታሪክ እና ጥበብን ያዋጣ ሕዝብ ነው፡፡
እናም የዚህ ቻናል ባለቤቶች ስለምታምኑት እምነት ፈጣሪ ስትሉ እባካችሁ አንድ ሕዝብ በሚዲያ በዚህ መንገድ አታስተዋውቁ፡፡ እንዲህ ያለ ቀልድና መዝናኛ ይቅርባቸሁ፡፡ በኮሜዲ ሥራም እኮ መልካም ነገር ማስተዋወቅ ይቻላል።
እነጌትነት እንየው የመሠሉ የሀገር ጥበብ ዋርካዎች የወጡበት አካባቢ እኮ ነው ያላችሁት። አርአያ የሌላችሁ አትምሰሉ እንጂ።
አንድ ሕዝብ በሃይማኖቱ ፣በባሕሉ እና በታሪኩ የሚደረግ ቅሰጣ ከማንነት ግድያ የሚተናነስ አይደለም፡፡ ገንዘቡ ይቅርባችሁ የሚጸጽታችሁን ነገር አታድርጉ! ወይስ ስንት ጎጃም ነው ያለው? እኛ የማናውቀው ለእናንተ ብቻ የተገለጠ አለ እንዴ?
አቅም አላችሁ ተሰጥዖ አላችሁ፡፡ ያን እግዚአብሔር የሰጣችሁን ጸጋም ለመልካም ነገር ተጠቀሙበት!
“አድናቂ” ነን የምትሉም የምታደንቅቱን ለዩ፡፡
ሀገርን እንዲህ እንደዋዛ እየሳቅን እንዳንሸኛት!
