ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር፣ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም እና የአየር ኃይሉ አዛዥ
የምስሉ መግለጫ,የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር፣ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም እና የአየር ኃይሉ አዛዥ ሰሞኑን በተከበረው የአየር ኃይሉ 90ኛ ዓመት በዓል ወቅት

28 ጥር 2026

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ክብረ በዓልን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር፤ እንደ አውሮፓውያኑ በ2030 የኢትዮጵያ አየር ኃይልን አቅም ወደ አምስተኛው ትውልድ ለማሻገር ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል።

አምስተኛው ትውልድ ወይም (fifth-generation) ዘመነኛ የውጊያ አቅም ያላቸው ምጡቅ የጦር መሣሪያዎችን ያካትታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አቅም የሚገኝበትን ዘመናዊ ቁመና በመግለጽ አገሪቱን ለሚገዳደሩ ኃይሎች ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል።

“ሚግ-21 ላይ ቆመው የቀሩ” ላሏቸው አገራትም ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን እና ጥቅሟን ለማስጠበቅ በተንጠቀቅ የሚጠባበቅ ጠንካራ አየር ኃይል እንዳላት የሚጠቁም ንግግር አድርገዋል።

በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በዘመናዊ መሣሪያ እንዲሁም በሰው ኃይልም ከአራተኛው ትውልድ ወደ አምስተኛው ትውልድ እንደሚሻገርም አስረግጠው ተናግረዋል።

የአየር ኃይልን 90ኛ ዓመት በማስመልከት በተዘጋጀው የአቪዬሽን ዐውደ ርዕይ ላይ የአየር ኃይሉ ዘመናዊ አውሮፕላች ለጉብኝት በቅተዋል። አየር ኃይል ተቋማዊ ብቃቱን የሚያሳዩ ትዕይንቶችም አቅርቧል።

የጦርነት አዙሪት በማይርቀው የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ሱዳን በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ፣ ደቡብ ሱዳን በውጥረት ውስጥ ትገኛለች። ከጊዜ ወደ ጊዜ ግንኙነታቸው እየሻከረ የመጣው ኢትዮጵያ እና ኤርትራም የጦርነት ስጋት እያንዣበባቸው ነው።

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ እና ጎረቤት አገራት ያላቸው የአየር ኃይል እንዴት ይነጻጸራል? የሚለውን ይህ ዘገባ ይፋዊ ዓለም አቀፍ መረጃን መሠረት አድርጎ ይዳስሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
የምስሉ መግለጫ,ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአየር ኃይሉ በዓል ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት

145 አገራትን በአጠቃላይ ወታደራዊ አቋማቸው ያነጻጸረው ግሎባል ፋየርፓወር (Global Firepower) የአፍሪካ ቀንድ አገራት አየር ኃይል አቋምን ባላቸው መሣሪያ እና ዝግጁነት አወዳድሯል።

አገራቱ ያላቸውን አጠቃላይ ወታደራዊ ኃይል ለማወዳደር በተጠቀማቸው ወደ 60 የሚጠጉ መስፈርቶች አማካኝነት መዝኖ ነጥብ (PowerIndex) ሰጥቷቸዋል።

ከግምት ውስጥ ከገቡ መስፈርቶች መካከል ወታደራዊ ቁመና፣ የፋይናንስ አቅም እና ሎጅስቲክስ ይጠቀሳሉ።

በ2026 የተከለሰ መረጃን መሠረት በማድረግ የአየር ኃይል እና የባሕር ኃይልን ጨምሮ የአገተት አጠቃላይ ወታደራዊ አቅም ተለክቷል።

አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ሕንድ እና ደቡብ ኮርያ በወታደራዊ አቅም ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ላይቤርያ፣ ሱሪናም፣ ሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ፣ ቤሊዝ እና ቡታን በዝርዝሩ መጨረሻ ላይ የሚገኙ አምስት አገራት ናቸው።

ወደ አፍሪካ ቀንድ ስንመጣ በዝርዝሩ ውስጥ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ተካትተዋል።

የአየር ኃይሎችን ጥንካሬ እንዲሁም የመሣሪያ ክምችት እና ዝግጁነት ለማነጻጸር ዘጠኝ ዝርዝሮች ቀርበዋል።

ከእነዚህም መካከል አጠቃላይ የአውሮፕላን ብዛት (Aircraft Total)፣ ተዋጊዎች (Fighters) እና የተዋጊዎች ዓይነት (Attack Types) ይጠቀሳሉ።

አውሮፕላኖች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ጨምሮ ሌሎችም የአየር ኃይል መሣሪያዎች እንዲሁም የተዋጊዎች ማሠልጠኛ አውሮፕላኖች ይገኙበታል።

በተጨማሪም ልዩ ተልዕኮ የሚፈጽሙ አውሮፕላኖች (Special Mission) እና የተዋጊ አውሮፕላኖች ነዳጅ ጫኝ/አመላላሽ (Tanker Fleet) ተካተዋል።

በመጨረሻም ሄሊኮፕተሮች (Helicopters) እና ጥቃት የሚፈጽሙ ሄሊኮፕተሮች (Attack Helicopters) በዝርዝሩ ተጠቅሰዋል።

ግሎባል ፋየርፓወር ያካተታቸው መረጃዎች ለመጨረሻ ጊዜ በድረ ገጹ ላይ የወጡት በአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት 2026 መግቢያ ላይ ነው።

ይህ የአገራት ወታደራዊ አቅምን የሚመዝነው ተቋም መረጃዎችን የሚያጠናቅረው የተለያዩ ይፋዊ የመረጃ ምንጮችን መሠረት በማድረግ በመሆኑ አገራት በምሥጢር የሚይዟቸውን መረጃዎች አያካትትም።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሄሊኮፕተሮች
የምስሉ መግለጫ,የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሄሊኮፕተሮች

ኢትዮጵያ

ከ145 አገራት መካከል በወታደራዊ አቅም 47ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ግሎባል ፋየርፓወር ለአገራት በሚሰጠው የኃይል ምዘና ነጥብ (PowerIndex) ላይ ለኢትዮጵያ 0.8525 ተሰጥቷል።

እጅግ በጣም ጠንካራ ተደርጎ የሚወሰደው ነጥብ 0.0000 ሲሆን፤ በዝርዝሩ በአንደኛነት የተቀመጠችው አሜሪካን እንደ ማነጻጸሪያ ብንወስድ የተሰጣት ነጥብ 0.0741 ነው።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በዝርዝሩ ከነበራት ሥፍራ ከፍ ያለች ሲሆን፤ ያለው አጠቃላይ የአየር ኃይል አውሮፕላኖች መጠን (Aircraft Total) 104 (ከ145 አገራት 66ኛ) መሆኑ ተመልክቷል።

ግሎባል ፋየርፓወር ባስቀመጣቸው በእያንዳንዱ ዝርዝሮች ላይ ዝግጁነትን (Readiness) ይመዝናል።

ዝግጁነት የሚለካው ከአሜሪካ አየር ኃይል 75% አማካኝ ነጥብ አንጻር እንደሆነ ድረ ገጹ ይጠቁማል። ይህም አጠቃላይ የሠራዊት ዝግጁነት፣ የመሣሪያ ዘመናዊነት፣ የመሣሪያ እድሳት እና የመሳሰሉትን ያካትታል።

አገሪቱ ካላት አጠቃላይ የአየር መሣሪያ አንጻር እያንዳንዱ ዓይነት ምን ያህሉን ድርሻ እንደሚሸፍን ለመጠቆም በመቶኛ ተሰልቶ ተቀምጧል።

በእያንዳንዱ መስፈርት ኢትዮጵያ ከ145 አገራት ጋር ተወዳድራም ነጥብ ተሰጥቷታል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዋጊ አውሮፕላን
የምስሉ መግለጫ,የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዋጊ አውሮፕላን

ኤርትራ

ኤርትራ በወታደራዊ አቅም ከ145 አገራት መካከል 119ኛ ሥፍራ ላይ ትገኛለች። ለአገራት በሚሰጠው የኃይል ምዘና ነጥብ (PowerIndex) ላይ ለኤርትራ 2.6841 ተሰጥቷል።

ኤርትራ ከዚህ ቀደም በዝርዝሩ ከነበራት ሥፍራ ከፍ ማለቷ ተገልጿል።

ሶማሊያ

በአጠቃላይ ወታደራዊ አቅም ከ145 አገራት 137ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ሶማሊያ ናት።

ለአገራት በሚሰጠው የኃይል ምዘና ነጥብ (PowerIndex) ላይ ለሶማሊያ 3.7393 ተሰጥቷል።

ከዚህ ቀደም በዝርዝሩ ከነበራት ሥፍራ ከፍ ማለቷን የግሎባል ፋየርፓወር ድረ ገጽ ይጠቁማል።

ሱዳን

ሱዳን፤ ከ145 አገራት መካከል በወታደራዊ 66ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ለአገራት በሚሰጠው የኃይል ምዘና ነጥብ (PowerIndex) ላይ 1.3563 ተሰጥቷል።

ከዚህ ቀደም ከነበረችበት ሥፍራ ከፍ ብላ ትገኛለች።

ኬንያ

ከ145 አገራት መካከል በወታደራዊ 84ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው አገር ኬንያ ናት። ለአገራት በሚሰጠው የኃይል ምዘና ነጥብ (PowerIndex) ላይ 1.8588 ተሰጥቷል።

ከዚህ ቀደም ከነበረችበት ዝቅ ማለቷን የግሎባል ፋየርፓወር ድረ ገጽ ያሳያል።

ደቡብ ሱዳን

ከ145 አገራት መካከል በወታደራዊ 113ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው አገር ደቡብ ሱዳን ናት።

ለአገራት በሚሰጠው የኃይል ምዘና ነጥብ (PowerIndex) ላይ 2.4645 ተሰጥቷል።

ከዚህ ቀደም የነበረችበት ሥፍራ ዘንድሮም አልተለወጠም።

አጠቃላይ ወታደራዊ አቅም

በ2026 ግሎባል ፋየር ፓወር የአገራት ወታደራዊ አቅም ደረጃ ዝርዝር ውስጥ ከ54ቱ የአፍሪካ አገራት 38ቱ ብቻ የተካተቱ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆነችው ጂቡቲ ካልተካተቱት ውስጥ ናት።

በአጠቃላይ ወታደራዊ አቅም ሲታይ ከአፍሪካ ከአንድ እስከ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ግብፅ፣ አልጄሪያ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ ናቸው።

ከኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት መካከል ከአፍሪካ በወታደራዊ አቅም ጥንካሬ ሱዳን 9ኛ፣ ኬንያ 12ኛ፣ ደቡብ ሱዳን 23ኛ፣ ኤርትራ 25ኛ እና ሶማሊያ 34ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።