በመታየት ላይ ያለ

መጨረሻ የተሻሻለው: January 30, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 22/ 2018 ዓ.ም፡– በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጥል በፃፉት ደብዳቤ በክልሉ ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው በመግለጽ፣ ዓለም አቀፍ አሸማጋዮችና የፕሪቶሪያ ሰላም ስምምነት ዋስትና ሰጪዎች በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ አቀረቡ።

ሰልሳይ ወያነ ትግራይ እና የትግራይ ነጻነት ፓርቲ  ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለአሜሪካ፣ ለአውሮፓ ህብረት እና ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አደራዳሪዎችና ለሌሎች ዋስትና ሰጪ አካላት በዳፉት ደብዳቤ፤ እየጨመረ የመጣው ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ውጥረት ደካማ የሆነውን የሰላም ሂደት ሊያናጋው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ሰልሳይ ወያነ ትግራይ በደብዳቤው ክልሉ “ሊቀለበስ በሚችል አደጋ ጫፍ ላይ ይገኛል” ሲል ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ እያጨመረ የመጣው ወታደራዊ ፍጥጫ በህዳር ወር 2022 ዓ.ም. በተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት የተገኘውን ሰላም ሊያፈርስ እንደሚችል አመልክቷል። ፓርቲው አክሎም ባለፉት ዓመታት በጦርነትና በሰብአዊ ቀውስ ውስጥ የቆየው የትግራይ ህዝብ፣ አሁን ደግሞ “ካለፈው እጅግ የከፋ” ሊሆን የሚችል ሌላ ጦርነት ስጋት ተደቅኖበታል ብሏል።

“አደጋውን ለመከላከል ያለው ዕድል በፍጥነት እየጠበበ ነው” ያለው ፓርቲው፣ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዝምታውን መርጦ እርምጃ የማይወስድ ከሆነ ጦርነቱ በትግራይ ብቻ ሳይሆን በመላው የአፍሪካ ቀንድ ላይ ሊቀለበስ የማይችል ጥፋት እንደሚያስከትል አስገንዝቧል።

ድርጅቱ ለውጥረቱ መርገብ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጣልቃ ገብነት እንዲደረግ፣ የትግራይ የግዛት አንድነትና አስተዳደራዊ ወሰኖች እንዲከበሩ፣ ተፈናቃዮች በክብር እንዲመለሱ እንዲሁም የሰላም ስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተሉ ገለልተኛ አካላት ስራቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቋል። ይህ ደብዳቤ ግልባጭ ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና ለፌዴራል መንግስቱ መሆኑ ተመላክቷል ነው።

በተመሳሳይ መልኩ የትግራይ ነጻነት ፓርቲ በህወሓት እና በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት መካከል ያለው ውጥረት እያየለ መምጣቱን በመግለጽ ይህም ለሰላም ስምምነቱ “ከባድ እና ቅጽበታዊ ስጋት” መሆኑን ገልጿል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት ግጭቱን በይፋ ቢያቆምም፣ አፈጻጸሙ ግን “አዝጋሚ፣ ወጥ ያልሆነ እና በቂ ክትትል የማይደረግበት” በመሆኑ አለመተማመን እንዲሰፍን ማድረጉን ፓርቲው አመልክቷል። አደራዳሪ አካላት በዝምታ መቆየታቸው ወታደራዊ እርምጃን እንደ አማራጭ ለሚመለከቱ አካላት ብርታት ሊሰጥ እንደሚችልም አስታውቋል።

ፓርቲው አሸማጋይ አካላት ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር በንቃት እንዲሳተፉ፣ በአንድ ወገን የሚወሰዱ ወታደራዊ እርምጃዎችን የሚከለክሉ ቀይ መስመሮችን በይፋ እንዲያረጋግጡ፣ የክትትልና የማረጋገጫ ስርዓቶችን እንዲያጠናክሩ፣ ለሲቪሎች ጥበቃና ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ቅድሚያ እንዲሰጡ፣ እንዲሁም ስምምነቱን የሚያናጉ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ተጠያቂነት በተገቢው መንገድ እንዲሰፍን ጥሪ አቅርቧል።

ሁለቱም ፓርቲዎች በትግራይ ክልል ሌላ ዙር ጦርነት ከተከሰተ ለዓመታት በግጭት፣ በጅምላ መፈናቀል እና በኢኮኖሚ ውድመት ለደከመው ህዝብ እጅግ አስከፊ እንደሚሆን አጽንዖት ሰጥተዋል። ዳግም ሊቀሰቀስ የሚችለው ግጭት መከላከል የሚቻል መሆኑን በመግለጽ፣ ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት በአስቸኳይ፣ በገለልተኝነት እና በቁርጠኝነት እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ሁለቱም ፓርቲዎች ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ቁርጠኛ መሆናቸውን በመግለጽ፣ አሽማጋት አካላት ያለምንም መዘግየት ተግባራዊ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ስምረት (ስምረት) ፓርቲ ባወጣው መግለጫ፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ እንዲሆን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሁሉን አቀፍ ጫና እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል። ፓርቲው በህወሓት ውስጥ የሚገኝ “የወንጀል ቡድን” ሲል የጠራው አካል ከባድ መሣሪያዎችን ያካተተ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት ለመሰንዘር ዝግጅት እያደረገ ነው በማለት የከሰሰ ሲሆን፣ ይህ ወታደራዊ ዝግጅት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ሊዘልቅ እንደሚችልም ስጋቱን ገልጿል።

እነዚህ መግለጫዎች የወጡት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ውጥረት እጅግ በጨመረበት ወቅት ነው። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ባለፈው ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ ሁሉም ወገኖች ከፍተኛ  መቆጠብ እንዲያሳዩና በከባድ መስዋዕትነት የተገኘውን ሰላም አደጋ ላይ ከሚጥሉ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በፌደራል ኃይሎች እና በትግራይ ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች መከሰታቸውን የሚጠቁሙ ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከትሎ፣ በክልሉ ያለው ስጋት እያየለ መጥቷል። የጸጥታ እና የዲፕሎማሲ ምንጮች ለፈረንሳይ የዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) እንደገለጹት፣ የተከሰተው ግጭት ወደ ተለያዩ የክልሉ አየር ማረፊያዎች የሚደረጉ በረራዎች እንዲሰረዙ ምክንያት ሆኗል። አዲስ ስታንዳርድም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቀሌ፣ አክሱም፣ ሽሬ እና ሁመራ ትላንት ተይዘው የነበሩ በረራዎችን በሙሉ ማሰረዙን ዘግቧል።አስ