
Yared Hailemariam ·Follow
መልዕክተ ቅዳሜ፤
War Hawks ልሂቃን እና ጦር ሰባቂ ፖለቲከኞች፤
++++++
ጦር ሰባቂ፣ ግጭት ጠማቂ፣ በትንሽ በትልቁ ጉልበታቸውን መፈተን የሚፈልጉ የፖለቲካ መሪዎች ባሉበት አገር፤ war hawks (ጦርነት ቀስቃሽ እና ግጭት አራጋቢ) ልሂቃን ሲታከሉበት ያ አገር መቸም ቢሆን ሰላም አይኖረውም፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ የገጠማት ፈተና ይሄው ይመስለኛል፡፡ የአገሪቱ ፖለቲከኞች በተለይም በሥልጣን ዙሪያ ያሉት፤ የሄዱትንም ሆነ ያሉትን ጨምሮ ጦርነትን የችግር ሁሉ መፍቻ፣ ጠላቶቻቸውን ማጥፊያ ወይም ማንበርከኪያ፣ ጉልበታቸውን መፈተሻ እና ሥልጣናቸውን ማራዘሚያ አድርገው ስለሚቆጥሩ በትንሽ በትልቁ ይዋጣልን ማለት መለያቸው ነው፡፡ ይህን የፖለቲከኞቹን እብደት የሚያባብሱ እና ትንሽ ኮሽ ባለ ቁጥር ሰላምን፣ ውይይትን እና ድርድርን ከመስበክ ይልቅ ጎራ ለይተውና አንድ ወገን ይዘው ግጭትን የሚያራግቡ፣ ፖለቲከኞችን ለግጭት የሚያደፋፍሩ፣ የሚያበረታቱ፣ በሃሳብ፣ በገንዘብና በእውቀት ግጭትን የሚደግፉ ልሂቃን ቁጥራቸው በርከት ሲል ደሞ የሰላም ድምጾች ይታፈናሉ፡፡ ስለ ሰላም የሚሰብኩ ኢላማ ይደረጋሉ፣ ነጫ እርግብም ትሰየፋለች።
ኢትዮጵያ ዛሬ የገጠማት ፈተና በአንድ ወገን ያለጦርነት ፖለቲካ መስራት የማይችሉ እና ግጭትን ዋና የፖለቲካ መሳሪያቸው ያደረጉ ጭንጋፍ የህውሃት እና የብልጽግና መሪዎች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዳር ቆመው የእሳቱን ወላፈን በርቀት እያዩ ህውሃትን ወይም አብይን ደግፈው ግፋ በለው እያሉ ጦርነትን የሚያራግቡ እና የሚያበረታቱ ልሂቃን አገሪቱ ማባሪያ በሌለው ግጭት ውስጥ እንድትማቅቅ እያደረጓት ነው፡፡ ስለ ጦረኞቹ ፖለቲከኞች ብዙ ጊዜ ደጋግሜ ስለጻፍኩና ስለተናገርኩ የዛሬ ትኩረቴ War Hawks ልሂቃን ላይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄዱ ጦርነቶች ወይም ግጭቶች እና አሁንም በመካሄድ ላይ ያሉ ጦርነቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የልሂቃን ድጋፍ የተቸራቸው ናቸው፡፡ ከዩንቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች አንስቶ በርካታ ምሁራን፣ ቄሱ፣ ሼሁ፣ ፓስተሩ፣ የአገር ሽማግሌው፣ ባለሃብቱ፣ ጋዜጠኛው እና የማሕበረሰብ አንቂ የሚባሉት ሳይቀሩ ፖለቲከኞች እርስ በርስ መነጋገር እና ሥልጡን ፖለቲካ መስራት አቅቷቸው ልዩነታቸውን በጡንቻና በአፈሙዝ ለመፍታት ሲሰናዱ የዘረዘርኳቸው ልሂቃን ሰልፋቸውን አሳምረው ከአንዱ ወይም ከሌላው ተፋላሚ ፖለቲከኛ ጀርባ ሆነው ጦርነቱን በቃላት ከመቀላቀል አልፈው ይባርካሉ፡፡ ግጭት አባባሽ የሆኑ ትዕርክቶችን፣ ትንታኔዎችን፣ አመክንዮዎችን፣ ማበረታቻዎችን ይዘው ከየመሸጉበት ጉድጓድ በመውጣት ከፖለቲከኞቹ ጎን ይቆማሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ጸባችን ሁሌም መራር፣ ቶሎ የማይበርድ፣ ብዙ ደም አፋሳሽ እና አገር አውዳሚ የሚሆነውም ለዚህ ይመስለኛል፡፡
ጦርነት አያስፈልግም፣ አያዋጣንም፣ አንተም ተው አንተም ተው፣ ሰላም ይስፈን የሚሉ ድምጽች ይታፈናሉ ወይም ጥቂት ከመሆናቸው የተነሳ አድማጭ የላቸውም፡፡ በመንጋ ልሂቃን እና በጦረኛ ፖለቲከኞች ጩኸት የሰላም ድምጾች ሁሉ ይዋጣሉ፡፡ እንዴት አንድ የዩንቨርሲቲ ፕሮፌሰር፣ እንዴት አንድ በእውቀት ዘልቆ የተማረ ሰው፣ እንዴት አንድ የሃይማኖት አባት፣ እንዴት አንድ የአገር ሽማግሌ፣ እንዴት አንድ ባለሃብት፣ እንዴት አንድ ጋዜጠኛ፣ እንዴት አንድ የሲቪክ ማህበር መሪ ጦርነትን ደግፎ ከከሸፉ ፖለቲከኞች ጎን ቆሞ ግጭትን ያራግባል???
የዛሬ አምስት አመት በህውሃት እና በፌደራል መንግስቱ በኩል ጦርነቱ እንደተጀመረ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለ ልሂቃን ዋና የጦርነቱ አራጋቢ በመሆን አገሪቱን ቢያንስ ከግማሽ ሚሊዮን ሰው በላይ ላሳጣት ጦርነት ትልቁን አስተዋጽዎ አድርጓል፡፡ ከፕሮፌሰሮቹም፣ ከቄሶቹም፣ ከሼሆቹም፣ ከባለሃብቱም፣ ከብዙ ጋዜጠኞችና የሲቪም ማህበራት መሪዎች ይልቅ አንድ ታሪኩ ጋንኪሴ (ዲሽታ ጊኔ) ተሽሎ ሰው ሆኖ ቢገኝም አሳዳጁ በዝቶ መከራውን አይቷል፡፡ ጦርነቱ እንደተጀመረ ሰሞን የዛሬው የብልጽግና የደህንነት ቢሮ ሃላፊ የሆነው እና ያኔ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ የፖለቲካ አማካሪ መሰለኝ የነበረው አቶ ሬድዋን ሁሴን አገር በቀል የሲቪክ ማህበራትን በኤሊያና ሆቴል ሰብስቦን የተናገረን ነገር ትዝ አለኝ፡፡ መንግስት ሕግ ለማስከበር ህውሃት ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አውቃችሁ ከዛሬ ጀምሮ ይህን ሕገወጥ አካል ጁንታ ብላችሁ እንድትጠሩት እና ሽብርተኛ ስለሆነ መንግስት የሚፈጽመውን እርምጃ ያለምንም ማቅማማት እንድትደግፉ ነው የጠራናችሁ አለን፡፡ እኔ ይህን ንግግሩን እንደሰማው ከግማሽ ሰአት በላይ ሳልቆይ አዳራሹን ጥዬ ወጣሁ፡፡ እጅግ በርካታ የሚባሉ የሲቪክ ማሕበራት መሪዎች፤ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችን የሚመሩ ሳይቀሩ አዳራሽ ውስጥ እየፎከሩ እንዝመት፣ ህውሃትን እናወግዛለን፣ ከመንግስት ጎን እንቆማለን የሚሉ መፈክር አዘል ንግግሮችን ያሰሙ ነበር፡፡ ልክ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈረም ደግሞ እነዚሁ ሰዎች ዋና የሰላም ሰባኪ መስለው ነጭ እርግብ ይዘው ተከሰቱ፡፡
አሁንም ሰሞኑን የተጀመረውን ግጭት ተከትሎ እነዚሁ War Hawks ልሂቃን ከያሉበት እየወጡ ፍለጠው፣ ቁረጠው፣ በለው ማለታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ባለፈው ጦርነት ከሃሰት የፕሮፓጋንዳ ወሬ ከመፈብረክ አንስቶ ግጭቶቹን በማባባስ ትልቅ ሚና የተጫወቱት ልሂቃን መካከል የላቀ የውሸት እና የጥላቻ የፕሮፖጋንዳ አበርክቶ ላደረጉት ሰዎች በሰላሙ ጊዜ የመከላከያ የክብር ኒሻን ሽልማትና እውቅና ተበርክቶላቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ በጦርነቱ ወቅት የዶ/ር ደብረጽዮን አንገት ተቆርጦ የሆነ ቤተክርስቲያን ውስጥ መገኘቱን አረጋግጠናል ብለው ሰበር ዜና የሰሩ ሰዎች ዘንድሮ ምን ይሉን ይሆን?
ለማንኛውም ልሂቅም የፖለቲካ መሪም የከሸፈበት አገር መከራው ብዙ ነው፡፡ ልሂቅም ፖለቲከኛውም ጽብ አጫሪ፣ ግጭት ጠንሳሽና ጸረ ሰላም በሆነበር አገር የግጭት አዙሪት አይበጠስም ይከራል እንጂ፡፡ ኢትዮጵያ እጅግ ጨካኝና አምባገነን በሆነው አብይ አህመድ፣ ከታሪክና ከውድቀታቸው በማይማሩ ጨካኝ የህውሃት መሪዎች እና War Hawks ልሂቃን እጅ እስካልወጣች ድረስ ሚሊዮኖች በጦርነት ያልቃሉ፣ ሚሊዮኖች ከቅያቸው ይፈናቀላሉ፣ ሚሊዮኖች የአካል ጉዳተኞች ይሆናሉ፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች እና ሕጻናት የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ ይሆናሉ፣ ከጦርነት የተረፉና ያመለጡ ወጣቶች አገራቸውን ጥለው ይሸሻሉ፣ የአገር ሃብት ይወድማል፡፡
እንግዲህ ለፖለቲከኞችም ሆነ ለWar Hawks ልሂቃን ልቦና እስኪሰጣቸው ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ እናንተ ጠንስሳችሁ በምታቀጣጥሉት ጦርነት ውስጥ እራሴንም ሆነ ልጆቼን አልማግድም በማለት በአንድ ድምጽ እምቢኝ ለጦርነት! ጦርነት በቃኝ1 የግፍ አገዛዝ በቃኝ! ብሎ በመነሳት ሊታገላቸው ይገባል፡፡
መልካም ሰንበት!
