
ከ 7 ሰአት በፊት
አሜሪካ ግዙፉ የጦር መርከቧን ጨምሮ ወሳኝ የባሕር ኃይል ተዋጊ መርከቦቿን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ካስጠጋች ቀናት ተቆጥረዋል። በዚህም ከዛሬ ነገ በኢራን ላይ ጥቃት ልትፈጽም ትጭላለች የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
በእርግጥ አሜሪካ ፕሬዝዳንቷ ሲዝቱ እንደቆዩት ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ ዒላማ የምታደርጋቸው ቦታዎች በአብዛኛው የሚገመቱ ቢሆንም፤ የሚያስከትለውን ውጤት መተንበይ አይቻልም።
ሆኖም እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ከቴህራን ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ኃይሎች ጥቃት እንዲፈፅሙ ለማዘዝ ወስነዋል። ይህ ከሆነ ምን ሊከሰት ይችላል?
1. የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር
የአሜሪካ የአየር እና የባሕር ኃይሎች የተወሰኑ እና የተለዩ ዒላማዎች ላይ ብቻ ጥቃት ከፈፀሙ ኢራን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ልትሸጋገር ትችል ይሆናል።
ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ጥቃቱ የተወሰኑ፣ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ወታደሮች እና በአብዮታዊ ዘቡ ሥር በሚንቀሳቀሱ የባሲጅ ታጣቂዎች ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ እንዲሁም በባልስቲክ ሚሳዔሎች መተኮሻ እና ማከማቻ ቦታዎች እንዲሁም የኢራን የኒውክሌር ማዕከላት ላይ ብቻ ከተፈፀመ ነው።
በዚህ ምክንያት ቀድሞውኑ የተዳከመው አገዛዝ ወድቆ ኢራን ሌላውን ዓለም መቀላቀል ወደምትችልበት ትክክለኛ የዲሞክራሲ ሥርዓት ልትሸጋገር ትችላለች።
ይህ ብሩህ የሆነው መላምት ነው።
ምክንያቱም የምዕራቡ ጦር በኢራቅ እና በሊቢያ ጣልቃ መግባቱ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርን አላመጣም። ምንም እንኳም ጣልቃ ገብነቱ በሁለቱም አገራት የነበረውን አምባገነን ሥርዓት ማስወገድ ቢችልም ለዓመታት አለመረጋጋትን እና ደም መፋሰስን አስከትሏል።
የራሷን አብዮት ያስነሳችው ሶሪያም ብትሆን ያለ ምንም የምዕራባውያን የጦር ድጋፍ ነው በ2024 ፕሬዚደንት ባሻር አል አሳድን ከሥልጣን ማስወገድ የቻለችው።

2. አገዛዙ ይተርፋል፤ ፖሊሲዎቹን ያሻሽላል
ይህ ” የቬንዙዌላ ሞዴል” ሊባል ይችላል። በቅርቡ አሜሪካ በቬንዙዌላ ላይ የወሰደችው ፈጣን እና ከባድ አገዛዙ እንዲቆይ ነገር ግን ፖሊሲዎቹ እንዲቀየሩ አድርጓል።
ኢራን አሁን ባለችበት ሁኔታ ይህ ማለት በርካታ ኢራናውያን ዘንድ የማይወደደው የእስላማዊ ሪፐብሊክ አገዛዝ ተርፎ፤ ነገር ግን በመካከለኛው ምሥራቅ ላሉ ታጣቂዎች ድጋፍ እንዳያደርግ ወይም በአገር ውስጥ የኒውክሌር እና የባሊስቲክ ሚሳዔል ፕሮግራሞቹን ለማቋረጥ እንዲሁም ተቃውሞን ማፈኑን እንዲያቆም ይገደዳል።
ይህ ይሆናል ብሎ ማሰብ ግን ከባድ ነው። ምክንያቱም እስላማዊው ሪፐብሊክ አገዛዝ ለ47 ዓመታት ያህል ይህን ሲቃወም ነው የቆየው። አሁንም አቅጣጫውን የሚቀይር አይመስልም።
3. አገዛዙ ይወድቃል፤ በወታደራዊ አስተዳደር ይተካል
ይህ ብዙዎች ሊሆን ይችላል ብለው የሚያስቡት ነው።
አሁን ያለው አገዛዝ በብዙዎች ዘንድ የሚደገፍ ባለመሆኑ እና ባለፉት ዓመታት በአገሪቷ በሚካሄዱ ተከታታይ ተቃውሞዎች እየተዳከመ መጥቷል። ሆኖም አሁንም ግዙፍ እና ሰፊ የደኅንነት ሥርዓት አለው።
ተቃዋሚዎች አገዛዙን እስካሁን መገልበጥ ያልቻሉትም ከጎናቸው የሚቆሙ የፀጥታ ኃይሎች ባለመኖራቸው ነው።
እነዚህ ታማኝ የሆኑ ኃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ በሚጠቀሙት “ጭካኔ የተሞላበት እና ያልተገደበ ኃይል” ምክንያት አገዛዙ ሥልጣን ላይ እንዲቆይ አድርገውታል።
በመሆኑም አሜሪካ ከምትፈፅመው ጥቃት በኋላ የሚፈጠረውን ግራ መጋባት ተከተሎ ኢራን በእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በተገነባ ጠንካራ ወታደራዊ አስተዳደር ትመራለች ተብሎ ይታሳበል።

4. ኢራን በአሜሪካ ኃይሎች እና ጎረቤቶቿ ላይ የአፀፋ ጥቃት ትሰነዝራለች
ኢራን “ጣቶቿ ቃታ ላይ” መሆናቸውን በመግለጽ ከአሜሪካ ለሚፈፀምባት ጥቃት የአፀፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ዝታለች።
ሆኖም ያላት ኃይል ከአሜሪካ የባሕር እና የአየር ኃይል ጋር ሊወዳደር እንደማይችል ግልጽ ቢሆንም አሁንም በዋሻዎች፣ ከመሬት በታች ወይም ራቅ ባሉ ተራራዎች ውስጥ ተደብቀው በሚገኙ የባልስቲክ ሚሳዔሎች እና ድሮኖች የአፀፋ ምላሽ ልትሰጥ ትችላለች።
በአረብ ባሕረ ሰላጤ በኩል በሚገኙ በባህሬን እና በኳታር የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮች እንዲሁም መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ልትፈፅምም ትችላለች።
ከፈለገችም “የአሜሪካ ጥቃቶች ተሳታፊ ናቸው” ብላ በምታስባቸው እንደ ዮርዳኖስ ወይም እስራኤል ያሉ አገራትን አንዳንድ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ማድረግ ትችላለች።
በአውሮፓውያኑ 2019 በኢራቅ ውስጥ በኢራን የሚደገፉ ሚሊሻዎች እንደተፈፀመ በተነገረው እና በሳዑዲ አራምኮ የፔትሮኬሚካል ተቋማት ላይ የተፈፀመው አውዳሚ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት ሳዑዲዎች ለኢራን ሚሳዔሎች ምን ያህል ተጋላጭ እንደሆኑ አሳይቷል።
ሁሉም የአሜሪካ አጋር የሆኑት በአረብ ባሕረ ሰላጤ ላይ የሚገኙ የኢራን ጎረቤቶችም የአሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ በእነሱ ላይ ጦስ ይዞ ሊመጣ ይችላል ብለው እየተጨነቁ ነው።

5. ኢራን በባሕረ ሰላጤው ቦምብ በመቅበር አጸፋ ትሰጣለች
ይህ ከአውሮፓውያኑ 1980 እስከ 1988 ባሉት ዓመታት በተካሄደው የኢራን እና ኢራቅ ጦርነት ጀምሮ ኢራን የመርከብ መስመሮች ላይ ቦምብ የቀበረች ሲሆን፣ በሮያል የባሕር ፈንጅ አምካኞች እስከሚፀዱ ድረስ ለዓለም አቀፍ የመርከብ ጉዞ እና የነዳጅ አቅርቦት ስጋት ሆኖ ቆይቷል።
በኢራን እና በኦማን መካከል የሚገኘው ጠባቡ የሆርሙዝ ሰርጥ ለዓለም ንግድ ወሳኝ ቦታ ነው።
ወደ 20 በመቶ የሚሆነው የዓለም የተጣራ የተፈጥሮ ጋዝ እንዲሁም ከ20 እስከ 25 በመቶ የሚደርሰው ነዳጅ ዘይት እና የነዳጅ ተረፈ ምርቶች በየዓመቱ የሚያልፈው በዚሁ ወሽመጥ ነው።
ኢራን በፍጥነት የባሕር ቦምቦችን ለመቅበር ልምምድ ጀምራለች። ይህን ካደረገች የዓለም ንግድ እና የነዳጅ ዋጋ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው።

6. ኢራን የአሜሪካን ግዙፍ የጦር መርከብን በማስመጥ አፀፋ ትሰጣለች
አንድ የአሜሪካ መርከበኛ በባሕረ ሰላጤው በሚገኝ የጦር መርከብ ላይ ሆኖ ኢራን “የተቀናጀ ጥቃት” ትፈፅማለች የሚል ስጋት እንዳሳሰበው ገልጿል።
ኢራን በአንድ ወይም በብዙ ዒላማዎች ላይ በርካታ ፈንጂዎችን በድሮኖች እና በፈጣን ባሕር ሰርጓጅ የጦር ጀልባዎች የምትተኩስበት ቦታ ይህ ነው። በዚህም ምክንያት የአሜሪካ የባሕር ኃይል መከላከያዎች ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማስወገድ አይችሉም።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጥበቃም ከዓመታት በፊት በባሕረ ሰላጤው ውስጥ የነበረውን ባህላዊ ባሕር ኃይል በሌሎች ተክቷል። የተወሰኑ አዛዦቹም በሻህ ወቅት በዳርትማውዝ ሥልጠና ወስደዋል።
የኢራን የባሕር ኃይል አባላት በሥልጠናቸው ያተኮሩት “ባልተለመደ ወይም ያልተመጣጠነ ጦርነት” ላይ ሲሆን፣ ዋናው ጠላታቸው የሆነውም የአሜሪካ የባሕር ኃይል አምስተኛውን የጦር መርከብ በማጥፋት ወይም በማሳለፍ ሊያገኛቸው የሚችላቸውን ቴክኒካዊ ጠቀሜታዎች እየተመለከተ ነው።
መርከበኞቹን በመያዝ የጦር መርከቡን ማስመጥ ደግሞ ለአሜሪካ ትልቅ ውርደት ነው የሚሆነው።
ይህ የማይመስል ቢሆንም በአውሮፓውያኑ 2000 በቢሊዮን ዶላር በሚገመተው የሚሳዔል አውዳሚ የጦር መርከብ በባሕረ ሰላጤው ነዳጅ እየሞላ ሳለ በአል ቃኢዳ የአጥፍቶ ማጥፋት ጥቃት ተፈፅሞበት 17 የአሜሪካ መርከበኞች ተገድለዋል።
ከዚህም በፊት በአውሮፓውያኑ 1987 የኢራቅ ጄት አብራሪ ሁለት ኤክሶሴት ሚሳዔሎችን ዩኤስኤስ ስታርክ በተባለ የአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ በመተኮስ 37 መርከበኞችን ገድሏል።

7. አገዛዙ ይንኮታኮታል፤ ቀውስ ይፈጠራል
ይህ የተደቀነ እውነተኛ አደጋ ሲሆን፣ የጎረቤቶቿ ኳታር እና ሳዑዲ አረቢያ ዋነኛ ስጋቶች ውስጥ አንዱ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ልክ በሶሪያ፣ በየመን እና በሊቢያ እንደታየው የእርስ በርስ ጦርነት ሊከሰት ይችላል።
በሚፈጠረው ትርምስ እና ሁከት ውስጥም የሚፈጠረውን የኃይል ክፍተት ተከትሎ ኩርዶች፣ ባሉች እና ሌሎች በቁጥር አናሳ ጎሳዎች ሕዝባቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ሊፈጠር የሚችለው ውጥረት ወደ የትጥቅ ግጭት ሊያመራ የሚችልበት አደጋ አለ።
ይህም በኢራን የውክልና ጦርነት በቀጣናው ጥቃቶችን ያስተናገደቸው እና በኒውክሌር ፕሮግራሟ የኅልውና ስጋት የገባት እስራኤል ብቻ ሳትሆን አብዛኞቹን የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን ሊያስደስት ይችላል።
ነገር ግን ትልቋ እና 93 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት የመካከለኛው ምሥራቅ አገር ወደ ትርምስ ውስጥ እንዲሁም የሰብዓዊ እና የስደተኝነት ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ማንም ሰው አይፈልግም።
አሁን ላይ ትልቁ አደጋ ፕሬዚደንት ትራምፕ ከፍተኛ ኃይላቸውን ወደ ኢራን ድንበር ካስጠጉ በኋላ እርምጃ ለመውሰድ ወይም ኪሳራቸውን ለመጋፈጥ መወሰናቸው ነው።
ጦርነት የሚጀመረው ግልጽ የሆነ መጨረሻው ሳይታወቅ ቢሆንም፤ ሊገመት የማይችል ጎጂ ውጤት ማስከተሉ የማይቀር ነው።
