ኢሕአፓ/eprp 

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር ጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም የክልሉን ቅርንጫፍ ማስተባበርያ ጽ/ቤት የሚመሩ አመራሮችን መምረጡ ይታወሳል።

በትናንትናው ዕለትም አመራሮቹ ከዚህ ቀደም በባህርዳር ከተማ የነበረውን ጽ/ቤት ቀበሌ 16 ኪዳነምሕረት ቤተክርስትያን ፊት ለፊት ወደሚገኘው ዋንዛዬ ሪልስቴት ህንጻ 2ኛ ፎቅ ቢሮ ቁጥር 202 በማዘዋወር በይፋ በመመረቅ ከፍተዋል።

በጽ/ቤቱ ምርቃት የፓርቲው የቀድሞ አንጋፋ የኢሕአሠ አባላትና የኢሕአፓ አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።

በዕለቱ አዲሰ ከተመረጡት የክልሉ የኢሕአፓ አመራሮች በክልሉ አሁናዊ ሁኔታ መሠረት አድርገው ቀደም ብለው ያጠኑት ጥናት ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ቀጣይ የሚደረገውን ሠላማዊ ትግል ከእስካሁኑም በበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ተስማምተዋል።

ክልሉ ሙሉ በሚባል ደረጃ የጦርነት አውድማ መሆኑን ተከትሎ የአያሌ ንፁሃን ሞት፣ መፈናቀል፣ የህፃናት ከትምህርት ገበታ መቅረት እና መሰል አሰቃቂ በደሎችን በየቀኑ መስማት የተለመደ ተግባር ሆኗል።

ይህንና ሌሎች አሁናዊ ግፎችን ለማስቆም ከመታገል አንፃር አዲሱ የክልሉ አመራር ወደ ማህበረሰቡ በመውረድ ታላቅ ትግል ለማድረግ እንደተዘጋጀና ይህንን ሀገርና ህዝብ የሚያድን ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ደግሞ በሁሉም አቅጣጫ የሚገኝ የአማራ ህዝብ በአባልነት፣ በደጋፊነት እንዲሁም በሚደረገው ሰላማዊ ትግል ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ ያስተላልፋል።

ኢሕአፓ ልክ እንደሁልጊዜው በመላው ኢትዮጵያ

1. በንፁሃን ላይ እየደረሠ ያለው እልቂት በአስቸኳይ እንዲቆም

2. ጦርነት እንዲቆምና በመርህ ላይ የተመሰረተና በትክክልም የህዝቡን የህልውና ስጋቱን ያማከለ እውነተኛ ፖለቲካዊ ድርድር እንዲደረግ

3. ማንነት ተኮር ማፈናቀልና ማዋከብ እንዲያበቃ

4. ማንነት ተኮር እስር እንዲቆምና በማንነታቸው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች እና ንጹሀን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንደ ሚቀጥል እየገለጸ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ጽኑ አጋርነትም ለማስታወስ ይወዳል።