
ኢሕአፓ/eprp ·Follow
የታገቱ ወገኖቻችን በአስቸኳይ ይለቀቁ ዘንድ እንጠይቃለን!
*ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ*
ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ደራ ጉንደ መስቀል በመጓዝ ላይ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎች በሙሉ ጥር 27 ቀን 2018 ዓ.ም ታግተው መወሰዳቸውን የሚገልጹ መረጃዎች እየወጡ ነው።
በእገታው ወቅት አንዲት የ6 ወር ህፃን ከእናቷ ተነጥላ የት እንደደረሰች እስካሁን አይታወቅም። የዚህችን ህፃን አሁናዊ ሁኔታ እና የቤተሰቦቿ ስቃይ ለማሰብ እንኳን ይከብዳል።
እንዲህ ያሉ የሰላማዊ ሰዎች የሚደረጉ ተደጋጋሚ እገታዎች የየዕለት ዜና ከሆኑ 7 አመታትን አስቆጥረዋል። ሁኔታውን አስከፊ የሚያደርገው ደግሞየዜጎችን ደህንነት እና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀሰ ነፃነት የሚገታ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ንጹሃን ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ነው።
ይህ አሳዛኝ ተግባር እንዳይፈጸም የመከላከል ሃላፊነት በዋናነት የመንግስት ቢሆንም፤ መንግስት የዜጎቹ ደህንነት ከመጠበቅ ይልቅ በተቃራኒ መቆሙን በተደጋጋሚ አይተናል።
በጉዳዩ ዙሪያ መንግስት ካሳየው ቸልተኝነት እና ‘ምን አገባኝ?!’ ባይነት በመነሳት መሠል ድርጊቶች የሚፈጸሙት በመንግስታዊ መዋቅር ነው ብለን እንድናስብ አድርጎናል።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ የሚመለከታቸው አካላት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ እና አጠቃላይ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ግድ ይለናል የሚሉ አለማቀፍ ተቋማት ለታገቱት ንጹሃን ድምፅ እንዲሆኑ እና የታጋች ዜጎች ህይወት ለማዳን ጥረት እንዲደረግ፣ ይህን መሰል ህገወጥ ድርጊቶችም መቋጫ እንዲበጅላቸው መፍትሄውን እንዲያፈላልጉ በአስቸኳይ ይጠይቃል።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ
ጥር 29 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
