February 2, 2026

ቦርከና ደስክ

World Wide Travel Group
ወልቃይት ጠገዴ _ Welkait Tegede

ከወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

በትናንትናዉ ዕለት ማለትም ጥር 22 ቀን 2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን አገራዊ ምርጫ አስመልክቶ የምርጫ ክልል እና ምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝር መረጃ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። በዚህ መሠረት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን  <<ምዕራብ ትግራይ>>  በሚል ምድብ ሥር ተጠቅሰዉ ተመልክተናል። እንዲሁም ምርጫ  ቦርዱ ለወደፊቱ በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በመዳሰስ እና በመገምገም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ተጨማሪ መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል። 

ዳሩ ግን የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነትና ወሰን ጥያቄ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለፌደሬሽን ምክር ቤት፣ ለትግራይ ክልል ምክር ቤት እና አስተዳደር እንዲሁም ለአማራ ክልል መንግሥት መቅረቡ ይታወቃል። በመሆኑም ሕወሓት በድርጅቱ ውሳኔ አካባቢውን ከ1984 ዓ.ም. ሕገ መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት በጉልበት እና ከወልቃይት ጠገዴ የአማራ ሕዝብ ፍላጎት እና ፈቃድ ውጪ ወደ ትግራይ ክልል ማካለሉ ይታወሳል። ስለሆነም አካባቢያችን ለሦስት ዐሥር ዓመታት አማራዊ ማንነቱ ተደፍጥጦ እና የትግራይ ማንነት ተጭኖበት መቆየቱ ይታወቃል። 

ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በአገራችን የሰሜኑ ጦርነት ሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት ማለትም ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በተወሰደዉ እርምጃ ከሕወሓት አገዛዝ ነጻ በመውጣት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በዞን ደረጃ ተደራጅቶ በ4 የገጠር ወረዳዎች፣ 5 ከተማ መስተዳድሮች እና 93 ቀበሌዎች ይዞ ራሱን በራሱ በማስተዳደር ላይ ይገኛል። በተጨማሪም ከነጻነት ማግስት በአቶ አደም ፈራሕ የኢፌዴሪ ፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ‐ጉባኤ የተመራ ልዑክ ቡድን ስለ አካባቢዎቹ የሕዝብ ፍላጎት እና ሁኔታ ዳሰሳዊ ጥናት በማድረግ ሪፖርት ማድረጋቸውም አይዘነጋም። 

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ ”አማራ ነን እንጂ አማራ እንሁን አላልንም!” በሚል መሪ ቃል በተደጋጋሚ ድምጹን በተለያየ መንገድ ማሰማቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ስለሆነም ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚደረገዉ አገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከወዲሁ የበኩላችን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናችንን እያረጋገጥን፤ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ላለፉት 5 አመታት በአማራ ክልል አስተዳደር ሥር ሆኖ መቆየቱ እየታወቀ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትግራይ ክልል የምዕራብ ትግራይ ምርጫ ክልል ሥር አድርጎ መመደቡን ተገቢነት ስለሌለው፤ ቦርዱ ይህንን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ዞኑ በአማራ ክልል ሥር ሆኖ ምርጫ እንዲያካሄድ ስንል በአክብሮት እየጠቅን ከህዝባችን ፍላጎት ውጪ የሚደረግ አካሂድ የማንቀበል መሆኑ ከወዲሁ እንገልፃለን።

Advertise here _ borkena

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ 

ጥር 23/2018 ዓ.ም.

 ሁመራ