February 10, 2026

የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያውያን ላይ በጣለው የጉዞ እገዳ ምክንያት ወደ አሜሪካ ከተሞች የሚጓዙ መንገደኞች ቁጥር በመቀነሱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ተናገሩ። አየር መንገዱ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 4.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንም ዋና ስራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።
አቶ መስፍን ይህን ያሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸምን በተመለከተ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 3፤ 2018 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል በሰጡበት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። አየር መንገዱ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 10.64 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገዱን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ በዚሁ ጊዜ ውስጥ 451 ሺህ ቶን ጭነት ማጓጓዙን አመልክተዋል።
መንግስታዊው ተቋም ባለፈው መንፈቅ ዓመት ከመንገደኞች ማጓጓዝ እና ከጭነት አገልግሎት ያገኘው አጠቃላይ ገቢ፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ14 በመቶ ብልጫ እንዳለው አቶ መስፍን አስታውቀዋል። አየር መንገዱ ካገኘው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 22 በመቶው ከዕቃ ጭነት (ካርጎ) የተገኘ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አየር መንገዱ ባለፈው ግማሽ ዓመት ውስጥ ሰባት አዳዲስ አውሮፕላኖችን መረከቡ ለገቢው መጨመር አስተዋጽኦ ማድረጉን አክለዋል። ሆኖም አሁንም ቢሆን አየር መንገዱ የአውሮፕላን እጥረት እንዳለበት ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
አቶ መስፍን በዛሬው መግለጫቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገቢ ከተጠቀሰው በላይ ከፍ እንዳይል ያደረጉ ምክንያቶችንም አንስተዋል። በተቋሙ ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ካሳደሩ ምክንያቶች መካከልም የአሜሪካ መንግስት የጣላቸው የጉዞ እቀባዎችን ጠቅሰዋል።
አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ75 ሀገራት ዜጎች የፍልሰት ቪዛ (immigrant visa) መስጠት እንደምታቆም የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባለፈው ጥር ወር አስታውቆ ነበር። ይህ ውሳኔ የሚመለከታቸው፤ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ዜጎቻቸው “ተቀባይነት በሌለው መጠን” ከመንግስት ድጎማ የሚቀበሉ ሀገራትን እንደሆነ መስሪያ ቤቱ በወቅቱ ገልጿል።

የእነዚህ ሀገራት ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደ አሜሪካ እንዲገቡ የሚፈቅደውን የቪዛ አሰጣጥ የሚያቆመው ውሳኔ፤ ከጥር 13፤ 2018 ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል። ከእዚህ ውሳኔ አንድ ወር አስቀድሞ የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት ሚኒስትር ክሪስቲ ኖም፤ በተለምዶ “ዲቪ” በመባል በሚታወቀው የፍልሰተኞች የዳይቨርሲቲ ቪዛ ፕሮግራም ላይ እገዳ መጣላቸው ይታወሳል።
ሚኒስትሯ የእገዳ ትዕዛዙን ያስተላለፉት፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት መሆኑንም ገልጸዋል። እገዳው በ“ዲቪ” ፕሮግራም ምክንያት አሜሪካውያን “ጉዳት እንዳይደርስባቸው” ለማረጋገጥ እንደሆነም ክሪስቲ በወቅቱ አስታውቀው ነበር።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ “የአሜሪካ መንግሥት በየጊዜው ከጉዞ ጋር በተያያዘ የሚያወጣቸው እገዳዎች ወደ አሜሪካ ከተሞች በሚጓጓዙ መንገደኞቻችን ላይ ተጽዕኖ አሳድሮብናል” ሲሉ በዛሬው መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል። ከየካቲት እስከ ግንቦት ባሉት አራት ወራት ውስጥ ወደ አሜሪካ የሚጓዙ መንገደኞች ቁጥር እንደሚቀንስ ቢጠበቅም፤ የአሜሪካ መንግስት በየጊዜው የሚጥላቸው የቪዛ እና ጉዞ ገደቦች ግን ችግሩን ማባባሱን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
