February 10, 2026

ሰሞኑን “ከአንዳንድ” የአማራ ክልል አካባቢዎች የመከላከያ ሰራዊትን መውጣትን ተከትሎ፤ የአማራ ክልልን ህዝብ “ለዳግም ሰብአዊ ቀውስ የሚዳርግ ሁነት ተከስቷል” ሲል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አስታወቀ። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ባለው ነባራዊ ሁኔታ “የተመጠነ” “የጸጥታ አካላት ስምሪት ያለመኖር” እና “የሕግ ማስከበር ስራዎች መላላት”፤ የክልሉን ህዝብ “ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈሉት ነው” ሲልም ፓርቲው ገልጿል።
አብን ይህን የገለጸው፤ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ክልላዊ፣ ሀገራዊ እና ቀጠናዊ ወቅታዊ አጀንዳዎችን በተመለከተ ካደረገው ውይይት በኋላ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 3፣ 2018 ምሽት ባወጣው የአቋም መግለጫ ነው። ፓርቲው በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ ይፋ ባደረገው በዚሁ መግለጫው፤ በአማራ ክልል “ባለፉት ጥቂት ጊዜያት” ታይቶ የነበረው “አንጻራዊ መረጋጋት” ከሰሞኑ “አይሎ” በታየ “የትጥቅ እንቅስቃሴ” መቀየሩን አትቷል።
ፓርቲው መግለጫውን ያወጣው፤ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ “የፋኖ ኃይሎች” አንዳንድ አካባቢዎችን እየተቆጣጠሩ መሆኑ እየተነገረ ባለበት ወቅት ነው። “የፋኖ ኃይሎች” ስፍራዎቹን የተቆጣጠሩት፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከነበሩባቸው አካባቢዎች መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ እንደሆነ ከስፍራዎቹ የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።

አብን በዛሬው መግለጫው የመከላከያ ሰራዊት ከአንዳንድ አካባቢዎች “መነቃነቁን” አረጋግጧል። ይህን ተከትሎ ከሰሞኑ “አይሎ” የታየው እንቅስቃሴ፤ የአማራን ህዝብ “ለከፋ የሰብአዊ ቀውስ፣ ለደህንነት ስጋት፣ ለኢኮኖሚ ድቀት አልፎም ለህልውና አደጋ የሚያጋልጥ” እንደሆነ አብን በመግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል።
እንቅስቃሴው የአማራን ህዝብ ትግል “ማዕከል አልባ በማድረግ” ጥያቄዎቹን “ከስርዓታዊ ማዕቀፍ የሚያወጣ” እንደሆነ የገለጸው ፓርቲው፤ ይህም የክልሉን ህዝብ “የሃሳብ መሪ የሚያሳጣ”፣ “ተቋም እና መንግስት አልባ የሚያደርግ” መሆኑን አመልክቷል። “የግጭት እና የጦርነት ፖለቲካ” ለአማራ ክልል ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች “መልስ የማያስገኝ” እንደሆነም አብን አስገንዝቧል።
ይህን አይነቱ ፖለቲካ “የታሪካዊ ጠላቶች እኩይ ዓላማ ማስፈጸሚያ ነው” ብሎ እንደሚያምንም አብን በመግለጫው ላይ አስፍሯል። ፓርቲው “ታሪካዊ ጠላቶች” ሲል የጠራቸውን አካላት ማንነት በግልጽ ባይጠቅስም፤ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው “የትጥቅ እንቅስቃሴ” በኢትዮጵያ እና በአማራ ህዝብ ላይ “የሚጋሩት ጠላትነት ያስተሳሰራቸው” ኃይሎች የተሰማሩበት እንደሆነ ግን በመግለጫው ከመወንጀል ወደ ኋላ አላለም።

እነዚህ ኃይሎች “አንድም የአማራን ህዝብ ዘላለማዊ ዕረፍት የመንሳት ዓላማቸውን ለማሳካት፣ በሌላ በኩል ሀገር ለማፍረስ የእጅ አዙር አመራር የሚሰጡበት እና የሚሳተፉበት እየሆነ መምጣቱን ተገንዝበናል” ብሏል አብን። የትጥቅ እንቅስቃሴውን “ለኢኮኖሚ ዓላማ የሚጠቀሙ” አካላት እንዳሉም ፓርቲው በመግለጫው ከስሷል።
“[የትጥቅ] እንቅስቃሴው የህዝባችን ውጫዊና የውስጥ ጠላቶች በራሳቸው አቅም ማሳካት ያልቻሉትን እኩይ ዓላማ እንዲያስፈጽሙ በር እየከፈተ ያለ እና የህዝቡ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንዲዘነጉም እንዲወሳሰቡም የሚያደርግ መሆኑ ስራ አስፈጸሚ ኮሚቴው አስምሮበታል” ሲል አብን በዛሬው መግለጫው ላይ አትቷል።
የአብን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ካደረገው ውይይት በኋላ፤ የትጥቅ እንቅስቃሴ እያደረጉ ላሉ ኃይሎች፣ ለመላው የአማራ እና የክልሉ ሕዝብ እንዲሁም ለፌደራል እና የአማራ ክልል መንግሥታት ጥሪዎች አቅርቧል። ፓርቲው በስም ላልጠቀሳቸው ታጣቂ ኃይሎች ባስተላለፈው ጥሪ፤ የሰላም አማራጭን እና የፖለቲካ መፍትሄ እንዲቀበሉን አሳስቧል።

ፓርቲው የአማራ ህዝብ “በዘላቂ ሰላሙ እና ህልውና” ላይ የተጋረጠውን “አሁናዊ አደጋ” በልኩ ተጋፍጦ “ራሱን አርነት እንዲያወጣም” ጠይቋል። “ሕዝባችን ከዚህ ታሪካዊ ቀውስ ለመላቀቅ የሚያደርገው ትግል ከግብ እንዲደርስ ያላሰለሰ ጥረት እንደምናደርግ ለማረጋገጥ እንወዳለን” ሲልም አብን አቋሙን አስታውቋል።
አብን የፌደራል እና የአማራ ክልል መንግሥታት “የህግና የፖለቲካ ኃላፊነቶችን እንዲወጡ” ከዚህ ቀደም ሲያቀርብ የነበረውን ጥሪ አሁንም በድጋሚ ለማቅረብ መገደዱን በመግለጫው ላይ አንስቷል። የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደረገ፣ እንደ የአካባቢዎቹ ነባራዊ ሁኔታ “የተመጠነ” የጸጥታ አካላት ስምሪት “አለመኖር” እና የህግ ማስከበር ሥራዎች “መላላት” “ከፍተኛ ዋጋ ማስከፈሉን” ፓርቲው በመግለጫው ላይ አመልክቷል።
የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ የጠየቀው አብን፤ ህዝቡ የራሱን ሰላም እንዲያስከብር ተቋማዊ “የማብቃት ሥራዎችን በማከናወን” ሰብአዊ ደህንነትን የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል። ሁለቱ አካላት የልማት ፕሮጀክቶችን በማስጀመር እና የመልካም አስተዳደር ስርዓቱን በማሻሻል “ለሰላም መስፈን መደላድሎች” እንዲፈጠሩ እንዲያደርጉም አብን ጥሪውን አቅርቧል።
በክልሉ ባለው የጸጥታ ሁኔታ “ተዋናይ” ከሆኑ አካላት ውስጥ “ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር የተሰለፉ” እና በሕዝቡ ላይ የማይሽር ክህደት የፈጸሙ” ኃይሎች እንዳሉ አብን ወንጅሏል። በአንጻሩ “ከጠላት ጋር [የሚደረግን] ያልተቀደሰ ጋብቻን የተጸየፉ ኃይሎች” እንዳሉም ፓርቲው በመግለጫው ጠቅሷል። ሁለቱ ኃይሎች “በተለያየ ሚዛን እንዲለኩ” የጠይቀው አብን፤ የሚቀርብላቸው የመፍትሔ አማራጭም “በየፈርጃቸው እንዲሆን” አሳስቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
