
ከአሜሪካ ጋር ፍጥጫ ውስጥ የምትገኘው ኢራን በኦማን ባሕር አቅራቢያ እና በሰሜን ሕንድ ውቅያኖስ ላይ ከሩሲያ ጋር የባሕር ኃይል ወደታራዊ ልምምድ ልታደርግ ነው።
ጭምቅ ሃሳብ
- “አስቸጋሪ” የተባለው የዩክሬን-ሩሲያ ድርድር ያለ ውጤት ተጠናቀቀ
- ጋቦን “ሐሰተኛ መረጃ እያተሰራጩ ነው” በሚል ማኅበራዊ ሚዲያን አገደች
- ሶማሊላንድ የኤርዶዋንን የአዲስ አበባ ንግግር “ተቀባይነት የሌለው” ስትል ነቀፈች
- “ኢራናውያን ገና ያልተቀበሏቸው፤ ትራምፕ ቀይ መስመር ያሏቸው ነጥቦች አሉ”- የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት
- ኢራን፤ ኒውክሌርን በተመለከተ “በዋነኛ መርሆች” ላይ ከአሜሪካ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን አስታወቀች
- የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቀይ ባሕር እና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ከኬንያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተወያዩ
የቀጥታ ሽፋን
- 18 የካቲት 2026የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ጊዜ ለተጨማሪ ጊዜ ተራዘመ
የፎቶው ባለመብት,HoPRየምስሉ መግለጫ,የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ዶ/ር)የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የጀመረውን ሥራ እንዲያጠናቅቅ ተጨማሪ የስምንት ወራት የሥራ ጊዜ እንዲሰጠው ወሰነ።ለሦስት ዓመት የሥራ ዘመን የተቋቋመው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ ሁኔታ በተካሄደ የምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ የሥራ ጊዜው ለአንድ ዓመት እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል።የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ የካቲት 11/2018 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የኮሚሽኑን የአራት ዓመታት የሥራ ሪፖርት በማድመጥ ውይይት ካደረገ በኋላ ነው የሥራ ጊዜው ለተጨማሪ ስምንት ወራት እንዲራዘም የወሰነው።የካቲት 14/2014 ዓ.ም. ተቋቁሞ ሥራ የጀመረው ኮሚሽኑ የተራዘመለት የአንድ ዓመት የሥራ ጊዜ የካቲት 14/2018 ዓ.ም. የሚያበቃ በመሆኑ የቀሩ ሥራዎችን ለማከናወን ከየካቲት 15/2018 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ቀጣይ ዓመት ጥቅምት አጋማሽ የሥራ ጊዜው ተራዝሟል።በዶ/ር መስፍን አርአያ የሚመራው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ምከክር እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል።ነገር ግን ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ እና የምክክር ጉባዔውን ለማካሄድ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው በጠየቀው መሠረት የሥራ ጊዜ ተራዝሟል።ያጋሩ, የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ጊዜ ለተጨማሪ ጊዜ ተራዘመ - 18 የካቲት 2026ኢራን እና ሩሲያ የጋራ የባሕር ኃይል ወታደራዊ ልምምድ ሊያደርጉ ነው
የፎቶው ባለመብት,IRNAየምስሉ መግለጫ,የሩሲያ እና የኢራን ባሕር ኃይል ባለሥልጣናትከአሜሪካ ጋር ፍጥጫ ውስጥ የምትገኘው ኢራን በኦማን ባሕር አቅራቢያ እና በሰሜን ሕንድ ውቅያኖስ ላይ ከሩሲያ ጋር የባሕር ኃይል ወደታራዊ ልምምድ ልታደርግ ነው።ወታደራዊ ልምምዱን በተመለከተ ቃል አቀባይ የሆኑት ሪር አድሚራል ሐሳን ማግሱድሉ በሰጡት መግለጫ ልምምዱ በአራን ባሕር ኃይክ አስተናጋጅነት የሚካሄድ ነው። “ዋነኛ ዓላማውም በኦማን ባሕር እና በሴማነዊ ሕንድ ውቅያኖስ አስተማማኝ የባሕር ላይ ግንኙነት እና ደኅንነትን ማስጠበቅ ነው” ብለዋል።በልምምዱ የሁለቱ አገራት ባሕር ኃይሎች በቅንጅት በቀጣናው የባሕር ላይ እንቅስቃሴ ስጋት የሆኑ ተግባራትን መከላከል በተለይም የንግድ እና ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን መጠበቅ እንዲሁም የባሕር ላይ ሽብርተኝነትን መዋጋት መሆኑ ተገልጿል።ይህ ሐሙስ ይጀመራል የተባለው የባሕር ላይ ወታደራዊ ልምምድ የሚካሄደው የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ የባሕር ኃይል ልመምድ ካደረገ ከቀናት በኋላ ነው።በተጨማሪም ኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እየዛተች ያለችው አሜሪካ ግዙፍ አውሮፕላን ጫኝ እና ሌሎች የጦር መርከቦችን ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ እያሰማራች ባለችበት ጊዜ የሚካሄድ ወታደራዊ ልምምድ ነው።ኢራን እና አሜሪካ በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ኦማን እና ስዊትዘርላንድ ውስጥ ሁለት ዙር ድርድር ያደረጉ ሲሆን፣ ሦስተኛ ዙር ንግግር በቀጣይ እንደሚያደርጉ እየተነገረ ነው።ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን በኒውክሌር መራሃ ግብሯ እና በረጅም ርቀት ሚሳኤሎች ግንባታዋ ላይ የሚቀርብላትን ሃሳብ የማትቀበል ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚጠብቃት ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።ኢራን በበኩሏ የኒውክሌር ግንባታዋ ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ እንደሚውሉ በተደጋጋሚ እየገለጸች ሲሆን፣ ለድርድር የማታቀርባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ይፋ ከማድረጓ በተጨማሪ ጥቃት የሚፈጸምባት ከሆነ የምትሰጠው አጸፋ ከባድ እንደሚሆን አስጠንቅቃለች።ያጋሩ, ኢራን እና ሩሲያ የጋራ የባሕር ኃይል ወታደራዊ ልምምድ ሊያደርጉ ነው - 18 የካቲት 2026“አስቸጋሪ” የተባለው የዩክሬን-ሩሲያ ድርድር ያለ ውጤት ተጠናቀቀ
የፎቶው ባለመብት,Reutersየሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም ያለመው አሜሪካ ያሸማገለችው ውይይት ያለ ምንም ውጤት ተጠናቀቀ።በስዊትዘርላንድ ጄኔቫ የተካሄደው የሦስትዮሽ ንግግር ማክሰኞ ዕለት አመሻሽ ላይ ቢጀምርም ረቡዕ ግን መካሄድ የቻለው ለሁለት ሰዓት ብቻ ነው።የአሜሪካው አምባሳደር ስቲቭ ዊትኮፍ በውይይቱ ላይ ያላቸውን ተስፋ ተናግረው የነበረ ቢሆንም፤ የሩሲያም ሆነ የዩክሬን ተደራዳሪዎች “አስቸጋሪ” መሆናቸውን ገልጸዋል።ሞስኮ እና ኪየቭ በአራት ዓመታት ግጭት ውስጥ ቁልፍ በሆኑ የግዛት ጉዳዮች እና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ አሁንም ድረስ ልዩነት አላቸው።የነበረው ውይይት አስቸጋሪ እንደነበር ያመኑት የሞስኮ ተደራዳሪ ቭላድሚር ሜዲንስኪ፣ ድርድሩ “የተለመደው ዓይነት” እንደነበር እና ሌላ ስብሰባ በቅርቡ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪም ድርድሩን በሁለቱ ወገኖች አቋም ልዩነት የተነሳ “ቀላል አልነበረም” ሲሉ ተናግረዋል።የዩክሬን ተደራዳሪ ሩስቴም ኡሜሮቭ በውይይቱ ምንም እንኳ ለውጥ ባይታይም “ከፍተኛ እና ጥልቅ” በማለት “በዚህ ደረጃ” ምንም ዓይነት ዝርዝር ጉዳዮችን ይፋ ማድረግ እንደማይቻል ተናግረዋል።”ይህ በሁሉም ወገኖች መካከል ስምምነት እና በቂ ጊዜ የሚፈልግ ውስብስብ ሥራ ነው” ሲሉ ኡሜሮቭ ተናግረዋል።የውይይቱ ማብቃቱ ከመነገሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ዜሌንስኪ ሩሲያ “ወደ መጨረሻው ደረጃ ሊደርስ የሚችል ድርድርን ለማዘግየት እየሞከረች ነው” ሲል ከስሰዋል።የሩሲያ እና የዩክሬን ልዑካን ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በጥር ወር አሜሪካ አቡዳቢ ላይ ባዘጋጀችው የድርድር መድረክ ላይ ነበር።ይህም በጥቂት ወራት ውስጥ የመጀመሪያውን የእስረኞች ልውውጥ ማድረግ አስችሏል። ረቡዕ ዕለት ዜሌንስኪ ሌላ የእስረኛ ልውውጥ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሚካሄደው ጦርነት እንዲያበቃ ለማድረግ የሚደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ይመራሉ።ያጋሩ, “አስቸጋሪ” የተባለው የዩክሬን-ሩሲያ ድርድር ያለ ውጤት ተጠናቀቀ - 18 የካቲት 2026ጋቦን “ሐሰተኛ መረጃ እያተሰራጩ ነው” በሚል ማኅበራዊ ሚዲያን አገደች
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesበማዕከላዊ የአፍሪካ ክፍል የምትገኘው ጋቦን መገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የማኅበራዊ ሚዲያዎችን በአገሪቱ ውስጥ ግጭትን እያባባሱ እና መከፋፈልን እያሰፉ ነው በሚል ላልተወሰነ ጊዜ አገደ።ማክሰኞ ምሽት በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የአገሪቱ ከፍተኛ ኮሚዩኒኬሽን ባለሥልጣን “ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት”፤ “የኦንላይን ዘለፋ” እንዲሁም “ያለፈቃድ የግል መረጃን ማሠራጨት” ለውሳኔዎቹ ምክንያት መሆናቸውን ገልጿል።የባለሥልጣኑ ቃል አቀባይ ዤን ክላውዴ ሜንዶሜ የትኛው የማኅበራዊ ሚዲያ በዚህ ውሳኔ እርምጃ እንደሚወሰድበት ግልጽ ባያደርጉም በአገሪቱ ውስጥ ግን ዋትስአፕ፣ ቲክ ቶክ እና ፌስ ቡክ ዝነኛ ናቸው።አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት የሚያስተዳድሩት ጄነራል ብሪስ ኦሊጉኢ ንጉማ እአአ በ2023 ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ካካሄዱ በኋላ ባለፈው ዓመት የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸንፈዋል።የ50 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ከመምህራኖች እና ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።ረቡዕ ዕለት ረፋዱ ላይ ማኅበራዊ ሚዲያዎቹ መቋረጣቸውን ተጠቃሚዎች ተናግረዋል።ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው ከሆነ የተወሰኑ ተጠቃሚዎች ፌስቡክ እና ቲክቶክን መጠቀም አልቻሉም።ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት ጋቦን ማኅበራዊ ሚዲያዎች በወጣቱ ዘንድ ለመዝናኛም ሆነ ለሥራ ከፍተኛ ተቀባይነት አላቸው።በዋና ከተማዋ ሊብራቪሌ የሚኖር ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ የምግብ ቤት ባለቤት ንግዱን የሚያስተዋውቅባቸው ማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች መታገዳቸው ሥራው ላይ እንቅፋት እንደሚፈጥርበት ተናግሯል።ያጋሩ, ጋቦን “ሐሰተኛ መረጃ እያተሰራጩ ነው” በሚል ማኅበራዊ ሚዲያን አገደች - 18 የካቲት 2026ሶማሊላንድ የኤርዶዋንን የአዲስ አበባ ንግግር “ተቀባይነት የሌለው” ስትል ነቀፈች
የፎቶው ባለመብት,Somaliland Presidential Officeሶማሊላንድ፤ የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ትናንት በአዲስ አበባ ያደረጉት ንግግር “ተቀባይነት የሌለው፤ በሶማሊላንድ እና ቀጣናዊ አጋሮቿ መካከል ያለውን ግንኙት የሚያውክ” ስትል ነቀፈች።ኤርዶዋን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ኢትዮጵያ ሳሉ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው የአገርነት ዕውቅና “ለሶማሊላንድም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ምንም ጥቅም” አይኖረውም ብለዋል።ለዚህም ሶማሊላንድ በሰጠችው ምላሽ “በአፍሪካ ቀንድ ያሉ አገራት የውጭ ጉዳይ የፖሊሲ ውሳኔዎች የቀጣናው መንግሥታት እና የሕዝቡ መሆን አለባቸው” ብላለች።ከሶማሊላንድ የወጣው መግለጫ “የውጭ ተገዳዳሪ ኃይሎች በቀጣናው ገብተው መረጋጋት እና ትብብር መታወክ የለበትም” ይላል።በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግብዣ አዲስ አበባ የገቡት ኤርዶዋን፤ ኢትዮጵያ በምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ውስጥ በተለይም “ለአገራት ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ትኩረት እንደምትሰጥ” ተናግረዋል።”በዚህ ረገድ እስራኤል ለሶማሊላንድ ዕውቅና መስጠቷ ለሶማሊላንድም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ምንም ጥቅም እንደማይኖረው በድጋሚ መግለጽ እወዳለሁ” ሲሉ እስራኤል ታኅሣሥ መጨረሻ የወሰደችውን እርምጃ ተችተዋል።ሶማሊላንድ ባወጣችው መግለጫ፤ ቱርክ “የቀጣናውን ውጥረት የሚያባብስ” አቋም ከማንጸባረቅ እንድትታቀብ አሳስባለች።ቱርክ “የጋራ ትብብርን” እንዲሁም “ሉዓላዊ ውሳኔ ሰጭነትን” እንድታከብርም ሶማሊላንድ ጠይቃለች።መግለጫው፤ “ሶማሊላንድ ከቀጣናው እና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአገርነት ዕውቅና ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና ዴሞክራሲያዊ መሠረት ያለው ነው” ብሏል።ያጋሩ, ሶማሊላንድ የኤርዶዋንን የአዲስ አበባ ንግግር “ተቀባይነት የሌለው” ስትል ነቀፈች - 18 የካቲት 2026“ኢራናውያን ገና ያልተቀበሏቸው፤ ትራምፕ ቀይ መስመር ያሏቸው ነጥቦች አሉ”- የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesየአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከኢራን ጋር የተደረገው ድርድር “አንዳንድ ጉዳዮችን በተመለከተ በጥሩ ሁኔታ መሄዱን” ተናገሩ።“በሌላ በኩል፤ ፕሬዝዳንቱ ቀይ መስመር ብለው ያስቀመጧቸው እና ኢራናውያን ገና ያልተቀበሏቸው ነጥቦችም አሉ” ሲሉ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።ጄዲ ቫንስ አክለውም “ሥራችንን እንቀጥላለን። ነገር ግን ዲፕሎማሲ ሊደርስበት የሚችለው ጥግ መሄዱን የሚወስኑት ትራምፕ ናቸው” ብለዋል።ፕሬዝዳንት ዶናልድት ትራምፕ፤ ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ዲፕሎማሲ እና ሌሎች አማራጮችንም እየተጠቀሙ እንደሆነ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።“ሁሉም አማራጮች ጠረጴዛው ላይ ናቸው። ኢራን ሽብርን መደገፍ እንድታቆም እንፈልጋለን። የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ እንቅስቃሴ ነው። ከዚህ የበለጠው ስጋት ግን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ነው” ሲሉም አክለዋል።ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ እንደማትፈልግ ብትናገርም “ይሄ እውነት እንዳልሆነ እናውቃለን” ብለዋል ጄዲ ቫንስ።“የኒውክሌር የጦር መሣሪያ እንደሚፈልጉ የሚጠቁሙ ብዙ ድርጊዎች ፈጽመዋል። ግባችን ይሄ እንዳይሳካ ማድረግ ነው” ሲሉም የአገራቸውን አቋም አስታውቀዋል።ያጋሩ, “ኢራናውያን ገና ያልተቀበሏቸው፤ ትራምፕ ቀይ መስመር ያሏቸው ነጥቦች አሉ”- የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት - 18 የካቲት 2026ኢራን፤ ኒውክሌርን በተመለከተ “በዋነኛ መርሆች” ላይ ከአሜሪካ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን አስታወቀች
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesየምስሉ መግለጫ,የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺኢራን፤ የኒውክሌር መርሃ ግብሯን በተመለከተ ከአሜሪካ ጋር “በዋነኛ መርሆች” ላይ እንደተግባቡ አስታወቀች።ሁለቱ አገራት በጄኔቫ ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት ካደረጉ በኋላ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ እንደተናገሩት፤ የኒውክሌር “ዋነኛ መርሆችን” በተመለከተ መግባባት ላይ ተደርሷል። አሜሪካም “በውይይቱ መሻሻል ታይቷል” ስትል ገልጻለች።የአሸማጋይዋ ኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አልቡሳዲ “የጋራ ግቦችን በመለየት እና የቴክኒክ ጉዳዮችን በተመለከተ ድርድሩ ጥሩ መሻሻል ታይቶበታል” ብለዋል።የኢራን መንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ስትዝት ቆይታለች።አሜሪካ እና የአውሮፓ አጋሮቿ፤ ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ልትገነባ ነው ቢሉም ቴህራን በተደጋጋሚ አስተባብላለች።አሜሪካ እና ኢራን ከሚደራደሩባቸው ነጥቦች ዋነኛው የኒውክሌር ጉዳይ ነው።አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን “መሻሻል ቢኖርም ብዙ የምንወያይባቸው ዝርዝር ነጥቦች አሉ። የምንለያይባቸውን ነጥቦች በተመለከተ ኢራናውያን በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ምክረ ሐሳም ይዘው እንደሚመጡ ገልጸዋል” ሲሉ ስለ ድርድሩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በበኩላቸው “አንዳንድ ጉዳዮችን በተመለከተ ድርድሩ በጥሩ ሁኔታ ተካሂዷል። ፕሬዝዳንቱ ቀይ መስመር ብለው ያስቀመጧቸው እና ኢራናውያን ገና ያልተቀበሏቸው ነጥቦችም አሉ” ሲሉ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።ያጋሩ, ኢራን፤ ኒውክሌርን በተመለከተ “በዋነኛ መርሆች” ላይ ከአሜሪካ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን አስታወቀች - 17 የካቲት 2026አያቶላ ኻሜኒ “የዓለም ኃያሉ ሠራዊት መልሶ እንዳይነሳ ሆኖ ሊመታ ይችላል” ሲሉ አስጠነቀቁ
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesየኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ “የዓለም ኃያሉ ሠራዊት መልሶ እንዳይነሳ ሆኖ ሊመታ እንደሚችል” በመግለጽ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምላሽ ሰጡ።ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር ከተፈጠረው ፍጥጫ ጋር በተያያዘ የአሜሪካን ጦር ሠራዊት ኃያልነት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ሰንብተዋል።በአገራቸው ዙሪያ የጦር መርከቦቿን እያስጠጋች ያለቸው አሜሪካ፤ ኢራን የሚቀርቡላትን ቅድመ ሁኔታዎች በመቀበል ከስምምነት ካልደረሰች እርምጃ እንደሚወሰድባት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሲዝቱ ቆይተዋል።ይህንን በተመለከተ ኻሜኒ በሰጡት ምላሽ “የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሠራዊታቸው በዓለም ላይ ጠንካራው እንደሆነ በተደጋጋሚ ይናገራሉ። ጠንካራ የተባለ ሠራዊት አንዳንድ ጊዜ እንዳይነሳ ተደርጎ ክፍኛ ሊመታ ይችላል” በማለት አስጠንቅቀዋል።ጠቅላይ መሪው ጨምረውም አሜሪካ የጦር መርከቦችን ወደ ኢራን መላኳን በተደጋጋሚ እየገለጸች መሆኗን በመጥቀስ “መርከቦች አደገኛ መሣሪያዎች ናቸው፤ ነገር ግን የበለጠ አደገኛው ነገር እነዚህን መርከቦች ከባሕር ሥር እንዲሰምጡ የሚያደርገው የጦር መሣሪያ ነው” በማለት የአሜሪካ መርከቦች የሚገጥማቸውን ምላሽ አመልክተዋል።አሜሪካ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በዓለም ላይ ካሉ ትልቅ አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከቦች መካከል አብርሃም ሊንከን የተባለውን በኢራን አቅራቢያ በሚገኘው ባሕር ላይ ያሰማራች ሲሆን፣ በቬንዙዌላ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ውስጥ ተሳታፊ የነበረው ጄራርድ ፎርድ መርከብ ደግሞ ወደ ባሕረ ሰላጤው እንዲያመራ አዝዛለች።ከእነዚህ ግዙፍ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርኮቦች በተጨማሪ ሌሎች በርካታ የአሜሪካ የጦር መርከቦች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተሰማርተዋል።ያጋሩ, አያቶላ ኻሜኒ “የዓለም ኃያሉ ሠራዊት መልሶ እንዳይነሳ ሆኖ ሊመታ ይችላል” ሲሉ አስጠነቀቁ - 17 የካቲት 2026የቱርክ ፕሬዝዳንት ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ
የፎቶው ባለመብት,Abiy Ahmed Ali/FBየቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲብ ታይፕ ኤርዶዋን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግብዣ መሠረት ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተዋል።ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ማክሰኞ የካቲት 10/2018 ዓ. ም. አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ የሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ጽሕፈት ቤታቸው አስታውቋል።ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ከሚያደርጉት ውይይት በተጨማሪ የተለያዩ የስምምነት ሰነዶች እንደሚፈረም ይጠበቃል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋንን ከተቀበሉ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በሰፈረው መልዕክት ላይ ጉብኝቱ “በቱርክ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ጥልቅ የአጋርነት ጥንካሬ የሚያንጸባርቅ ነው” በማለት የአገራቱን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር ውጤታማ ውይይት እንዲደረግ ምኞታቸውን ገልጸዋል።ያጋሩ, የቱርክ ፕሬዝዳንት ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ - 17 የካቲት 2026ታዋቂው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ጀሲ ጃክሰን በ84 ዓመታቸው አረፉ
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesየምስሉ መግለጫ,ጀሲ ጃክሰን፤ ከማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር ጋር በመሆን ለጥቁር አሜሪካውያን መብት በጽኑ ታግለዋልታዋቂው አሜሪካዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ጀሲ ጃክሰን በ84 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።ቤተሰቦቻቸው ባወጡት መግለጫ “አባታችን ታላቅ መሪ ነበር። ለቤተሰባችን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ለሚገኙ ጭቁኖች እና ድምጻቸው ለታፈነ ሰዎችን ጭምር ጠባቂ ነበር” ብለዋል።እንደ አውሮፓውያኑ በ1960ዎቹ ጀሲ ጃክሰን ከማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር ጋር በመሆን ለጥቁር አሜሪካውያን መብት በጽኑ ታግለዋል።በአውሮፓውያኑ በ1984 እና በ1988 የዴሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩም ነበሩ።ጀሲ ጃክሰን በ2017 ፓርኪንሰንስ የተባለ በሽታ እንደያዛቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ያለፈው ኅዳር ላይ ሆስፒታል ገብተውም ነበር።በሰብአዊ መብት ንቅናቄ ውስጥ አብረዋቸው የሠሩት የመብት ተሟጋች ሬቨረንድ አል ሻርፕተን “አገሪቱን እና ዓለምን የለወጠ ሰው ነው። ፖሊሲ እና ሕግ አስቀይሯል። ሕልማችን እንዳይሞት ጠብቆ ለልጆቻችን አውርሷል” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር እንደ አውሮፓውያኑ በ1968 ቴነሲ ውስጥ በተገደለበት ወቅት ከጀሲ ጃክሰን ጋር አብረው ነበሩ።በ1941 ሳውዝ ካሮላይና የተወለዱት ጀሲ ጃክሰን፤ ከወጣትነታቸው አንስቶ በፖለቲካው ንቁ ተሳታፊ ነበሩ።በ1971 ‘ኦፕሬሽን ፑሽ’ የተሰኘ የማኅበራዊ ፍትሕ እና የመብት ተሟጋች ተቋም መሥርተዋል።ያጋሩ, ታዋቂው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ጀሲ ጃክሰን በ84 ዓመታቸው አረፉ - 17 የካቲት 2026ሁለተኛ ቀኑን በያዘው የኬንያ ሠራተኞች አድማ ምክንያት በረራዎች ከ20 ሰዓት በላይ ተቋረጡ
የፎቶው ባለመብት,Reutersየምስሉ መግለጫ,በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች በረራቸው ተሰርዟልበኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው ዋነኛ የአገሪቱ አውሮፕላን ማረፊያ ከ20 ሰዓት በላይ በረራ በማቋረጡ ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች ጉዟቸው እንደተስጓጎለ ተገለጸ።በአፍሪካ በርካታ ተጓዦችን ከሚያስተናግዱ አየር ማረፊያዎች መካከል አንዱ በሆነው ጆሞ ኬንያታ አውሮፕላን ማረፊያ፤ ሠራተኞች ለሁለተኛ ቀን የቀጠለ አድማ በማድረጋቸው በረራዎች ተሰርዘዋል።ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለትምህርት ሊጓዝ የነበረው እና በረራው የተሰረዘበት ጃክ ኦኮት የተባለ ተጓዥ “ከ20 ሰዓት በላይ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ቆይቻለሁ። በሰው ተጨናንቋል” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።የኬንያ አብራሪዎች ማኅበር “የተፈጠረው መስተጓጎል ከአብራሪዎች የሥራ እና እረፍት ጊዜ ጋር የሚጣረስ ነው” ብሏል።የሥራ ማቆም አድማው ከበረራ ደኅንነት ጥበቃ ጋር እንዳይጣረስ እንደሚሰጋም ማኅበሩ አስታውቋል።የኬንያ አቪየሽን ሠራተኞች ማኅበር ከሳምንት በፊት የሥራ ማቆም አድማ እንደሚኖር ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።የበረራ ሠራተኞችን ክፍያቸው እንዲሁም የሥራ ሁኔታቸው የማይሻሻል ከሆነ ሥራ የማቆም አድማ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።የማኅበሩ ዋና ፀሐፊ ሞስ ንዲማ “ይሄ በቀላሉ የሚታይ አድማ ሳይሆን ሙሉ ኢንዱስትሪውን የሚመለከት ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።ያጋሩ, ሁለተኛ ቀኑን በያዘው የኬንያ ሠራተኞች አድማ ምክንያት በረራዎች ከ20 ሰዓት በላይ ተቋረጡ - 17 የካቲት 2026ዩክሬን የወታደሮቿን ዘር በማቀዝቀዣ እንዲቀመጥ ገንዘብ እንደምትደጉም ተገለፀ
በጦርነት ወታደሮቿን እያጣች ያለችው ዩክሬን የወታደሮቿን ዘር በማቀዝቀዣ ለማስቀመጥ ድጎማ እየሰጠች ነው።በ2022 የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ሲጀምር የግል የስነ ተዋልዶ ክሊኒኮች ሴት ወታደሮች እንቁላላቸውን ወንዶች ደግሞ የዘር ፈሳሻቸውን እንዲያስቀምጡ አማራጭ አቅርበዋል።በ2013 ይህንን ለመቆጣጠር የተነሳው የዩክሬን ምክር ቤት ለአገልግሎቱ በገንዘብ ለመደጎም ሕግ አውጥቷል።ሕጉን ካረቀቁት የምክር ቤት አባላት አንዷ የሆኑት ኦክሳና ዲሚትሪቭ “ወታደሮቻችን ወደፊታችንን እየተከላከሉ ነው፤ ነገር ግን የእነርሱን [ወደፊት] ሊያጡ ይችላሉ። ስለዚህ ዕድል መስጠት ነው የፈለግነው” ብለዋልየሁሉም ወታደሮች ናሙና ከሞቱ እስከ ሦስት ዓመት ድረስ በነፃ የሚቀመጥ ሲሆን፤ የትዳር አጋሮቻቸው እንዲጠቀሙት አስቀድሞ በጽሑፍ ፈቃድ ካላቸው ለመፀነስ መጠቀም ይችላሉ ተብሏል።እርምጃው ከጦርነቱ በፊት ዩክሬንን የገጠማትን የስነ ሕዝብ ቀውስ እና ከጦርነቱ በኋላ ወጣቶቿ ተገድለውባት የተባባሰውን ችግር ለመፍታት ያለመ እንደሆነ ተነግሯል።ያጋሩ, ዩክሬን የወታደሮቿን ዘር በማቀዝቀዣ እንዲቀመጥ ገንዘብ እንደምትደጉም ተገለፀ - 17 የካቲት 2026የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቀይ ባሕር እና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ከኬንያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተወያዩ
የፎቶው ባለመብት,Ministry of Foreign Affairs Kenyaየግብፅ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ከኬንያ ባለሥልጣናት ጋር በቀይ ባሕር እና በአፍሪካ ቀንድ አሁናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያየ።በግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ እና የውኃ ሐብት እና መስኖ ሚኒስትር ሃኒ ስዊላም የተመራ ከፍተኛ ልዑክ የካቲት 9/2018 ዓ.ም. ኬንያን ጎብኝቷል።የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከኬንያ ዋና የምክር ቤት ፀሐፊ ሙሳሊያ ሙሳቫዲ እና ሌሎችም ከፍተኛ ሹሞች ጋር በቀይ ባሕር እና የአፍሪካ ቀንድ አሁናዊ ሁኔታዎች ላይ መወያየተቻውን ካይሮ አስታውቃለች።የግብፅ ውኃ ሐብት እና መስኖ ሚኒስቴር ንግግሩን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት በቀጣናው በዋናነት ደግሞ በሶማሊያ እና ሱዳን ሰላም እና መረጋጋትን መመለስ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሐሳብ መለዋወጣቸው ተጠቁሟል።ሁለቱ ወገኖች ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር የመከላከያ እና የተቀናጀ የውሃ ሐብት አስተዳደርን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ላይ ለመተባበር ተስማምተዋል።የናይል ወንዝን ዘላቂነት ለመጠበቅ እና የጋራ ሐብትነቱን ለማስጠበቅ በጥምረት መስራት አስፈላጊ ስለመሆኑ ሁለቱም ወገኞች እውቅና እንደሰጡ ተመላክቷል።አገራቱ “ሁሉም የናይል ተፋሰስ አገራት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አድርጎ በውሃ ደኅንነት፣ በማኅበረ ኢኮኖሚ እድገት እና በስነ ምህዳር ጥበቃ በጋራ ለመስራት” ስለማሰባቸው ተጠቅሷል።ያጋሩ, የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቀይ ባሕር እና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ከኬንያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተወያዩ - 17 የካቲት 2026ናይጄሪያ በዩክሬን ዜጎቿ ሞተው መገኘታቸውን ተከትሎ ማስጠንቀቂያ አወጣች
የፎቶው ባለመብት,Reutersናይጄሪያውያን በሌላ አገር ጦርነት ውስጥ በውትድርና ተቀጥረው እንዲሳተፉ በሚካሄድ ሕገወጥ ምልመላ እንዳይታለሉ የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስቸኳይ ማስጠንቀቂያ አወጣ።ሚኒስቴሩ ማስጠንቀቂያውን ያወጣው የዩክሬን ባለሥልጣናት ባለፈው ዓመት በጦርነት እንደተገደሉ የገለጿቸውን የሁለት ናይጄሪያውያን አስከሬን እንዳገኙ ከተናገሩ በኋላ ነው።ናይጄሪያ የግለሰቦቹን ሞት ባታረጋግጥም እሁድ ዕለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኪሚቢ ኢሞሞቲሚ ኤቢንፋ ባወጡት መግለጫ “በእንደዚህ አይነት አሳዛኝ ሁኔታዎች ሰለባ የሆኑ በርካታ ናይጄሪያውያን ተታልለው ወታደራዊ አገልግሎት ኮንትራቶችን እንዲፈርሙ ከተገደዱ በኋላ ወደ ውጊያ ቀጠናዎች ተሰማርተዋል” ብለዋል።ኬንያ ለዜጎቿ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ አውጥታለች።እንደ ናይጄሪያ ባለሥልጣናት ገለጻ፣ የምርመራ እና የደህንነት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት አንዳንድ ዜጎች ጥሩ ክፍያ የሚከፈልበት የሥራ ዕድል፣ የደህንነት ሥራ፣ የትምህርት ዕድሎች ወይም የፍልሰት ማበረታቻዎች እንደሚሰጡ ቃል ተገብቶላቸው ወደ ጦርነት ቀጠናዎች ተወስደዋል።በአንዳንድ አጋጣሚዎች፣ ተጎጂዎች ተገቢው የሕግ ምክር ሳይሰጣቸው በውጭ ቋንቋዎች የተጻፉ ውሎችን እንዲፈርሙ ይገደዱ ነበር፣ እና የጉዞ ሰነዶቻቸው ወደ ሚሄዱበት አገር እንደደረሱ ይወሰድባቸዋል ተብሏል።በመሃል ያሉ ደላሎችም የቱሪስት ወይም ሌሎች ወታደራዊ ያልሆኑ ቪዛዎችን በመጠቀም ጉዞ እንደሚያመቻቹ ይነገራል።ኤቢንፋ ናይጄሪያውያን እንደዚህ አይነት መደለያዎችን እንዳይቀበሉ አስጠንቅቀዋል። ይህም ሕይወትን አደጋ ላይ ከመጣል ባለፈ የናይጄሪያን እና ዓለም አቀፍ የቅጥረኛ እንቅስቃሴዎችን እና የውጭ ዜጎችን ስለመመልመል የሚደነግጉ ሕጎችን ሊጥሱ እንደሚችሉ አፅንዖት ሰጥቷል።የናይጄሪያ መንግሥት እነዚህን ጉዳዮች ለመመርመር እና የሕዝብ ግንዛቤን ለማሳደግ ከቀጠናው እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።በውጭ አገር የሚገኙት የዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎች የቆንስላ ድጋፍን ለማጠናከር እና ለዜጎች ማሰሳሰቢያ እንዲያስተላልፉ ተነግሯቸዋል።የዩክሬን የስለላ ድርጅት ከ36 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ከ1,400 በላይ ግለሰቦች ለሩሲያ እንዲዋጉ መመልመላቸውን ይገምታል። ዩክሬን ራሷ አፍሪካውያንን ጨምሮ የውጭ ዜጎችን ለመመልመል በመሞከሯ ቀደም ሲል ትችት ገጥሟታል።የአፍሪካ መንግሥታት ዜጎቻቸውን በተደጋጋሚ እያስጠነቀቁ እና ወደ ግጭቱ ተታልለው የገቡ ዜጎቻቸውን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየሰሩ ነው።ያጋሩ, ናይጄሪያ በዩክሬን ዜጎቿ ሞተው መገኘታቸውን ተከትሎ ማስጠንቀቂያ አወጣች - 17 የካቲት 2026ከኢራን ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ “በተዘዋዋሪ” እሳተፋለሁ – ዶናልድ ትራምፕ
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesየአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ እና ኢራን ድርድር በጄኔቫ ከመጀመሩ በፊት “በተዘዋዋሪ እሳተፋለሁ” ሲሉ ተናገሩ።በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረገው ድርድር “አይሳካም” ብለው ያስቡ እንደሆን የተጠየቁት ፕሬዚዳንቱ፣ “ከስምምነት ላይ መድረስ የሚፈልጉ ይመስለኛል። ባለመስማማት የሚመጣውን መዘዝ መቀበል የሚፈልጉ አይመስለኝም” ብለዋል።“ኢራን እጅግ ጠንካራ ተደራዳሪ ናት። ለበጎም ሆነ ለክፉ” ያሉት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት “መጥፎ ተደራዳሪ ናት፤ ምክንያቱም የኒውክሌር ተቋማቷን ለማውደም ቢ-2 ጦር አውሮፕላንን ከመላካችን በፊት ልንስማማ እንችል ነበር ። አሁን ግን የበለጠ ኃላፊነት የሚሰማቸው ይመስለኛል። ስምምነት ላይ መድረስ ይፈልጋሉ” ብለዋል።ፕሬዚዳንቱ ይህንን ከተናገሩ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በድርድሩ ላይ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።ቃል አቀባዩ ዩናይትድ ስቴትስ ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ አሁን “የበለጠ ምክንያታዊ ነች” ሲሉ ተደምጠዋል።በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሚደረገው ሁለተኛ ዙር ድርድር ማክሰኞ በጄኔቫ ይጀመራል።የእስራኤሉ ቤንያሚን ኔታንያሁ ከድርድሩ መጀመር አስቀድመው የኢራን ዩራኒየም ማበልጸጊያን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እና የበለፀገው ዩራኒየም ሙሉ በሙሉ ከአገሪቱ እንዲወጣ በድርድሩ ላይ መካተት አለበት ሲሉ ተናግረው ነበር።አክለውም ድርድሩ የኢራን ባሌስቲክ ሚሳዔልን ማካተት አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር።ያጋሩ, ከኢራን ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ “በተዘዋዋሪ” እሳተፋለሁ – ዶናልድ ትራምፕ - 16 የካቲት 2026የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ከኢራን አቅራቢያ እንደሚገኝ የሳተላይት ምሥል አመለከተ
የምስሉ መግለጫ,አብረሃም ሊንከን የጦር መርከብአሜሪካ፤ ኢራን በምታካሂደው የኒውክሌር መርሃ ግብር ምክንያት ጫና እያበረታችባት ባለበት በአሁኑ ወቅት ግዙፍ የጦር መርከቦችን በኢራን ዙሪያ እያሰማራች ነው።የቢቢሲ የመረጃ አጣሪያ ቡድን ቢቢሲ ቬሪፋይ፤ በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይም በኢራን አቅራቢያ እየተጠናከረ ያለውን የአሜሪካን ወደታራዊ ኃይል በቅርበት እየተከታተለ ነው።ከሦስት ሳምንት በፊት የአሜሪካ ግዙፍ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከብ ወደ ባሕረ ሰላጤው አካባቢ መድረሱ ከተዘገበ በኋላ ቢቢሲ ትናንት እሑድ በተነሳ የሳተላይት ምሥል አማካኝነት መርከቡ የት እንደሚገኝ አረጋግጧል።መርከቡ ወደ አካባቢው ከተሰማራ ከሦስት ሳምንታት በላይ ቢሆንም እስከ ትናንት ድረስ ግን ከሳተላይት የምሥል ዕይታ ውጪ ሆኖ ቆይቶ ነበር።በብዛት የመርከቦችን ቦታ ለመለየት ከሚውለው እና ዩሮፒያን ሴንቲኔል-2 ከተባለው ለሕዝብ ይፋ ከሆነውን ሳተላይት የተገኘ ምሥልን በመጠቀም ባደረጋው ማጣራት፤ አብረሃም ሊንከን የጦር መርከብ ከኢራን አቅራቢያ ከኦማን የባሕር ዳርቻ 240 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ እንዳለ ቢቢሲ አረጋግጧል።የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጄራርድ ፎርድ የተባለው ሁለተኛ ግዙፍ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ አብረሃም ሊንከንን በመቀላቀል ከሌሎች ወታደራዊ መሣሪያዎች ጋር ወደ ቀጣናው መሰማራታቸውን አረጋግጠዋል።ያጋሩ, የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ከኢራን አቅራቢያ እንደሚገኝ የሳተላይት ምሥል አመለከተ - 16 የካቲት 2026የኢራን አብዮታዊ ዘብ የባሕር ላይ ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ ጀመረ
የፎቶው ባለመብት,Getty Imagesየምስሉ መግለጫ,የኢራን አብዮታዊ ዘብ ፈጣን ጀልባየኢራን አብዮታዊ ዘብ በአገሪቱ ላይ ሊቃጣ የሚችል ወደታራዊ ጥቃትን ለመከላከል ያለውን ዝግጁነት ለመፈተሽ ቁልፍ በሆነው የሆርሙዝ ሰርጥ ልምምድ ማድረግ መጀመሩን አስታወቀ።ይህ ወታደራዊ ልምምድ መካሄድ የጀመረው በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ሁለተኛ ዙር ድርድር ጄኔቭ፣ ስዊትዘርላንድ ውስጥ ሊካሄድ በተቃረበበት እና አሜሪካ በኢራን አቅራቢያ ግዙፍ ወታደራዊ መርከቦቿን እያጠናከረች ባለበት ጊዜ ነው።ለድርድር ወደ ጄኔቭ ያመሩት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፤ ኢራን ለማስፈራሪያ እንደማትንበረከክ በመግለጽ “ትክክለኛ፣ ፍትሐዊ እና ሚዛናዊ ስምምነት” እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ኢራን እስካሁን ያዳበረችውን ለኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሊውሉ የሚችሉ የዩራኒየም ውጤቶችን እና የማብላያ ማዕከላቷን በሙሉ ማስወገድ እንዳለባት አስጠንቅቀዋል።ያጋሩ, የኢራን አብዮታዊ ዘብ የባሕር ላይ ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ ጀመረ - 16 የካቲት 2026የኢራን እና የአሜሪካ ድርድር የነዳጅ፣ የማዕድን እና የጦር መሣሪያን እንደሚያካትት ተገለጸ
የፎቶው ባለመብት,Reutersኢራን ከአሜሪካ ጋር የኒውክሌር ስምምነት ላይ በመድረስ ሁለቱንም አገራት በምጣኔ ሃብት ተጠቃሚ የሚያደርግ መንገድን የመከተል ዕቅድ እንዳላት አንድ ኢራናዊ ዲፕሎማት ተናገሩ።ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ ዲፕሎማቱ የኢራንን አቋም ያስታወቁት ከአሜሪካ ጋር ሁለተኛ ዙር ውይይት ከመደረጉ ከቀናት በፊት ነው።ከዚህ ቀደም የተደረገው ውይይት ሁለቱ ባላንጣ አገራት በቴህራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ ያላቸውን ልዩነት ለማጥበብ እና ግጭትን ለማስወገድ የሞከሩበት እንደነበር ተዘግቧል።የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለሮይተርስ እንደተናገሩት፤ አሜሪካ ሁለተኛውን ግዙፍ የጦር መርከብ ወደ ቀጣናው ያስጠጋች ሲሆን፤ አገራቱ ስምምነት ላይ የማይደርሱ ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል።የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምርጫቸው በዲፕሎማሲ እና ድርድር እልባት ማግኘት ነው።“ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ መድረስ የቻለ ባይኖርም እንሞክራለን” ሲሉ ማርኮ ሩቢዮ ተናግረዋል።አሜሪካ ኢራን ላይ እርምጃ ከወሰደች ኢራን በምላሹ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ መቀመጫዎች ላይ ጥቃት እንደምትሰነዝር ዝታለች። ትናንት ግን ኢራን የተለሳለሰ አቋም አንጸባርቃለች።በኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የምጣኔ ሃብት ዲፕሎማሲ ምክትል ዳይሬክተር ሐሚድ ጋንባሪ “ስምምነቱ ዘላቂነት እንዲኖረው አሜሪካም በምጣኔ ሃብት ተጠቃሚ መሆን አለባት” ብለዋል።“በነዳጅ፣ በማዕድን እና በአየር ጦር መሣሪያ ግዢም ያሉን የጋራ ፍላጎቶች የድርድሩ አካል ናቸው” ሲሉም የአገራቸውን አቋም ይፋ አድርገዋል።በአውሮፓውያኑ በ2015 የተፈረመው የኒውክሌር ስምምነት የአሜሪካን ጥቅም ያስጠበቀ እንዳልሆነ አክለዋል።ትራምፕ በ2018 አሜሪካን ከስምምነቱ ማስወጣታቸው ይታወሳል።ያጋሩ, የኢራን እና የአሜሪካ ድርድር የነዳጅ፣ የማዕድን እና የጦር መሣሪያን እንደሚያካትት ተገለጸ - 16 የካቲት 2026የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኃላፊ ጋር ተወያዩ
የፎቶው ባለመብት,xየምስሉ መግለጫ,የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ እና የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ራፈኤል ግሮሲበነገው ዕለት ከአሜሪካ ጋር ለሚያደርጉት ድርድር ጄኔቫ የሚገኙት የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ፣ ከዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጋር ተገናኝተው ተወያዩ።ራፈኤል ግሮሲ በኤክሰ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕከት ከኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መገናኘታቸውን ገልጸው “ነገ በጄኔቫ ለሚካሄደው ድርድር ዝግጅት በዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተናል” ብለዋል።አራጋቺ ጄኔቫ ከደረሱ ከሰዓታት በኋላ በኤክስ ገጻቸው ላይ “ከአገራችን የኒውክሌር ባለሙያዎች ጋር ለዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ራፋኤል ግሮሲን አገኛቸዋለሁ” ብለው ነበር።የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በተጨማሪም ወደ ጄኔቫ የሆኑት “ፍትሃዊ እና ሚዛናዊ የሆነ ሰምምነት ላይ ለመድረስ” የሚያስችሉ ተጨባች ሃሳቦችን በመያዝ መሆኑን ተናግረዋል።በኢራን እና ዩናይትድ ስቴትስ መካከል የሚደረገው ሁለተኛው ዙር ድርድር ነገ በጄኔቫ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።በትናንትናው ዕለት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ማንኛውም ከኢራን ጋር የሚደረግ ስምምነት ያበለጸገቻቸው ዩራኒየምን ሙሉ በሙሉ የሚያስወግድ መሆን አለበት ሲሉ አስጠንቅቀዋል።በተጨማሪም ስምምነቱ የኢራን ባሌስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራምንም ማካተት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።ያጋሩ, የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኃላፊ ጋር ተወያዩ - 16 የካቲት 2026የመንግሥታቱ ድርጅት በደቡብ ሱዳን ግጭት ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን ገለፀ
የፎቶው ባለመብት,AFP via Getty Imagesየተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) በደቡብ ሱዳን በተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል ያገረሸውን ግጭት ተከትሎ በርካታ ሰዎች ተጎድተው በአኮቦ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ገለፀ።ድርጅቱ ባለፈው አርብ ባወጣው መግለጫ በአኮቦ ካውንቲ፣ በሰሜን ጆንግሌይ በደቡብ ሱዳን መከላከያ እና የሱዳን ሕዝቦች ነጻነት እንቅስቃሴ/ተቃዋሚ መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት የቆሰሉ ሕሙማንን የሰብአዊ ድርጅቶች እንክብካቤ እያደረጉ መሆኑን ገልጿል።ድርጅቱ በርካታ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሕይወት አድን የሆነ ሕክምና ለማግኘት እንዲችሉ ወደ ተሻለ የሕክምና ተቋም የሚሄዱበት መንገድ ባለመኖሩ “አስተማማኝ ባልሆነ ሁኔታ” ውስጥ ይቆያሉ ሲል አስጠንቅቋል።ኦቻ እየተባባሰ የመጣው ግጭት እና በጆንጌሊ የተፈጸመው የአየር ጥቃት ወደ 280,000 ሰዎችን ከቀያቸው ማፈናቀሉን ገልጿል።የተፈናቃዮች ቁጥር ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚያስፈልገውን ሰብዓዊ እርዳታ ጨምሮታል ሲል ኦቻ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።12 የጤና ተቋማት መዘረፋቸውን እና በከፊል መውደማቸው ያስታወቀው ኦቻ፣ ይህም አስፈላጊ የጤና አገልግሎቶችን አስተጓጉሏል፤ እንዲሁም ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች የሚሰጠውን እንክብካቤ ገድቧል ብሏል።በመንግሥት እና ለማቻር ታማኝ በሆኑ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት ደቡብ ሱዳን በሚቀጥለው ዓመት ታሕሳስ ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀች ነው።ደቡብ ሱዳን በአውሮፓውያኑ 2011 ነው ከሱዳን ተገንጥላ የዓለማችን በዕድሜ ትንሿ ሀገር የሆነችው።ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር የአገሪቱ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት ሲሆኑ ሪክ ማቻር ደግሞ የመጀመሪያው ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ።ነገር ግን ከሁለት ዓመት በኋላ ፕሬዝዳንት ኪር ሙሉ ካቢኒያቸውን አባረው ማቻር መፈንቅለ መንግሥት እያሴሩ ነው ብለው ከወቀሱ በኋላ በአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ተቀሰቀሰ።በዚህ አምስት ዓመት በዘለቀ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች ሲገደሉ፤ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለዋል።በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል በ2018 የሰላም ስምምነት ተፈርሞ፣ ሁለቱም አካላት አዲስ ሕገ-መንግሥት ለማፅደቅ፣ ምርጫ ለማካሄድ፣ የጦር ኃይሎቻቸውን ለማዋሃድ እንደሁም የሕዝብ ቆጠራ ለማካሄድ እና የታጠቁ ኃይሎችን መሳሪያ ለማስፈታት ተስማምተዋል።ነገር ግን እስካሁን ከስምምነቱ ማዕቀፎች አንዱም ተፈፃሚ አልሆነም። በሀገሪቱ የተለያዩ ግጭቶች መከሰታቸውም ቀጥሏል።ያጋሩ, የመንግሥታቱ ድርጅት በደቡብ ሱዳን ግጭት ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን ገለፀ
