
እናት ፓርቲ
በኦሮሚያ ክልል፣ በምሥራቅ አርሲ ዞን፣ መርቲ ወረዳ፣ ፈረቀሳ ቀበሌ ትናንት የካቲት 17 ቀን 2018 ዓ.ም፣ ምሽት 3፡00 ጀምሮ በተፈጸመ የተቀናጀ ጭፍጨፋ እስከአኹን ባለን መረጃ 4 ሰዎች የተገደሉ ሲኾን፣ 2 በጠና ቆስለዋል፣ 2 ተይዘው ተወስደው የደረሱበት አልታወቀም፣ ከ 10 በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል፣ የገበሬው የእህል ጎተራን ጨምሮ በርካታ ንብረት ወድሟል፡፡
ገዳዮች ቀብር ጭምር ክልክለው ነበር የሚሉት ምንጮቻችን አኹንም በቅርብ ርቀት ላይ ኾነው የገበሬውን በሬ እያረዱ እየበሉ እየጨፈሩ ነው፡፡ ከልካይም፣ ቀጪም የለም፡፡ ግድያውም ሃይማኖት ለይቶ የተፈጸመ ነው፤ ሕዝቡ ራሱን እንዳይከላከል በመንግሥት መሣሪያውን እንዲያወርድ ተድርጓል፤ እጃችንን አጣጥፈን ሞታችንን መጠበቅ ኾኗል ኑሯችን ብለዋል ነዋሪዎች።
መንግሥት ሕዝቡን የመጠበቅ ሥራውን ቢረሳው የአካባቢው ማኅበረሰብ በሕጋዊ መንገድ ታጥቆ ራሱን እንዲከላከል አማራጭ ይቅረብለት በሚል በተደጋጋሚ ብንወተውትም ሰሚ አልተገኘም።
ፓርቲያችን ግድያውን በጽኑ ያወግዛል። ለሞቱትም እረፍተ ነፍስን እየተመኘን ለአካባቢው ማኅበረሰብም መጽናናትን ይመኛል። ተይዘው የተወሰዱ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ እንዲለቀቁና ሕዝቡ በሕጋዊ መንገድ ተደራጅቶ ራሱን እንዲከላከል ኹኔታዎች በፍጥነት እንዲመቻቹለት በጥብቅ እናሳስባለን።
ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
እናት ፓርቲ
የካቲት ፲፰ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
