ቦርከና ደስክ

World Wide Travel Group

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com) 

አገራችን ኢትዮጵያ ተከታታይ ሥርዓተ መንግስት ያላት፣ የረጂም ጊዜ ታሪክና የገናና ሥልጣኔ ባለቤት የነበረች አገር ናት። የዛሬዋ እንግሊዝ እንደ አገር ከመመስረቷ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት የነበራት ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንደነበረች የሚያመለክቱ አያሌ የታሪክ ማስረጃዎች አሉ። እንግሊዞችና ሌሎችም የአውሮፓ አገሮች አስደናቂ ህንፃዎችንና  አብያተ ክርስቲያናትን ሲሰሩ ኢትዮጵያዊያንም ዓለም አቀፍ ዝና ያተረፉ የአክሱም ሃውልትን፣ ዕጹብ ድንቅ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትንና የጎንደር ቤተ መንግሥትን ሰርተዋል። 

የአውሮፓ ስልጣኔ መሠረት ከሆኑ ዕሴቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ብዙዎቹ የአውሮፓ አገሮች የሚጋሩት የላቲን ፊደል ነው። አገራችን ኢትዮጵያ የራሳቸው ፊደል ካላቸው ጥቂት የዓለም አገሮች ውስጥ አንዷ ናት። እነዚህ የታሪክ ማስረጃዎች የሚነግሩን አንድ ትልቅ እውነት አለ፣ እሱም በታሪክ ወደኋላ ስንሄድ በአንድ ወቅት እንግሊዞችና እኛ ኢትዮጵያዊያን በተመሳሳይ የስልጣኔ ደረጃ ላይ እንደነበርን ነው። ታዲያ እኛን ምን ነክቶን ነው ዛሬ እነሱ መጽዋች እኛ ተመጽዋች የሆነው? ለምንድነው እነሱ ጨረቃ ላይ መኖር ይቻል ይሆን ብለው ወደ ላይ ሲወጡ እኛ እዚሁ ምድር ላይ አብሮ መኖር ያቃተን? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ብዙ መጓዝ የለብንም። እንግሊዝ ውስጥ የዕድገትና ብልፅግና በር የተከፈተው፣ የእንግሊዝ ህዝብ በንጥቂያና ብዙኋኑን በማግለል ላይ የተመሠረተውን የፖለቲካ ሥርዓት አቃፊ በሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ሲቀይረው ነው። ይህንን እንግሊዞች በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምረው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያጠናቀቁትን የፖለቲካ ሂደት እኛ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም አልጀመርንም። በትክክል የሚገባንና ቁጭት ውስጥ ከትቶን የሚያነሳሳን ከሆነ የድህነታችን፣ የተመፅዋችነታችን፣ የመራባችን፣ የኋላ ቀርነታችንና የእርስ በርስ መገዳደላችን ዋናው ምክንያት ለዘመናት አንቆ ከያዘን ነጣቂና አግላይ ከሆነ የኤኮኖሚና  የፖለቲካ ሥርዓት እራሳችንን ማላቀቅ አለመቻላችን ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፈው ግማሽ ምዕተ አመት ሦስት የተለያዩ መንግስታትን ከሥልጣን አስወግዷል፣ በ1967 ዓ.ም. የፊውዳሉን ሥርዓት፣በ1983 ዓ.ም.ወታደራዊውን አገዛዝ፣በ2010 ዓ.ም.ደሞ የህወሓትን የአንድ ብሔር አምባገነን አገዛዝ ከአራት ኪሎ ማባረር ችሏል፣ሆኖም መሰረቱን ፍትህ፣ነጻነት፣እኩልነትና ዲሞክራሲ ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ባለመቻሉ የመጀመሪያውን የመንግስት ለውጥ ካደረገ ከ52 አመታት በኋላ ዛሬም አምባገነንነትን እየታገለ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ በ2010 ዓ.ም. በታሪካችን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እጅግ በጣም ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ አግኝቶ የመጣውና ብዙም ሳይቆይ እራሱን ወደ አንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭ አምባገነንነት የለወጠው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በግልጽ የሚታዩና ጥልቅ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች መፍታት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹን ቀውሶች የሚፈጥረው እሱ እራሱ ነው። ጠሚ አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የወሰዳቸው ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ እርምጃዎች ኢትዮጵያንና ህዝቧን በቀላሉ መውጣት የማይችሉት አዘቅት ውስጥ ይዟቸው ገብቷል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ በየቀኑ ጥልቀቱና ስፋቱ እያደገ ከሚሄድ አዘቅት ውስጥ በአስቸኳይ እራሳችንን የማናወጣ ከሆነ የኢትዮጵያ እንደ አገር ቀጣይነት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይገባል። 

በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ  ስር የሰደደ የብሔር ፖለቲካ አለ፣የብሔር ግጭትና የርስበርስ ጦርነት አለ፣ሰላምና መረጋጋት የለም፣መንግስት ሊፈርስ ትንሽ ነው የቀረው(State Collapse)፣የዘር ማፅዳትና የጦር ወንጀል በየቀኑ ይፈጸማል፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ፣በህዝብ፣ በመንግስትና በፖለቲካ ተዋንያኑ መካከል መተማመን የለም፣ማዕከላዊው መንግስት ደካማ በመሆኑ አንዳንድ ክልሎች ከቁጥጥሩ ውጭ ሆነዋል፣የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በሚከተለው ፍጹም የተሳሳተ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ የተነሳ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በሁሉም አቅጣጫ እየከበቡን ነው፣ ከጎረቤቶቻችን ጋር በሰላም መኖር የማንችልበት ድረጃ ላይ ደርሰናል፣ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ አለ፣ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ኢትዮጵያ የህልውና አደጋ ላይ ናት። ስለዚህ የኢትዮጵያን እንደ አገር ቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና ባጠቃላይ ኢትዮጵያን ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመውሰድ የሽግግር መንግስት በጣም አስፈላጊ ነው።

Advertise here _ borkena

አለም አቀፉን ማህበረሰብ ጨምሮ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያ በሽግግር ሂደት ውስጥ ማለፍ አለባት እያለ ሲወተውቱ፣የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ግን የብሔር ግጭትና የእርስበርስ ጦርነት በሚካሄድባት ኢትዮጵያ ውስጥ አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅቱን ጀምሯል። ትግራይ፣አማራና ኦሮሚያ ውስጥ ዜጎች እንኳን ምርጫ ጣቢያ ሄደው ተወካዮቻቸውን ሊመርጡ ገበያ ወጥተው ምግብ ለመሸመትም በህይወታቸው መቁረጥ አለባቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የመቃወም፣ የመሰብሰብና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የለም፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢሯቸው ውስጥ የቁም እስረኞች ናቸው። ኢትዮጵያ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች የሚገኙባትና ከ5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርት ቤት መሄድ የማይችሉባት አገር ናት። እነዚህ በግልጽ በአይን የሚታዩ ሁኔታዎች አፍ አውጥተው የሚነግሩን ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ሳይውል ሳያድር ሁሉን አቀፍ ወደሆነ የሽግግር ሂደት ውስጥ መግባት እንዳለባት ነው፣ይህ የማይሆን ከሆነ አደጋው መበታተን ሊሆን ይችላል። ይህንን የመበታተን አደጋ ለማዳንና፣ኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለመጀመር የግድ በሽግግር ሂደት ውስጥ ማለፍ አለብን፣በሽግግር ሂደት ውስጥ ማለፍ ካለብን ደሞ የሽግግር መንግስት ያስፈልገናል። 

ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ውድቀትን ለማስቀረት፣ሥር የሰደዱ የፖለቲካ፣ የብሔር እና የጸጥታ ቀውሶችን በቁጥጥር ስር ለማድረግ፣ሠላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ፣ በአምባገነንነትና በዲሞክራሲ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ፣ተቋማዊ ማሻሻያ ለማድረግ፣አገራዊ ዕርቅ ለማድረግና የጦር ወንጀልና የዘር ማጽዳት ወንጅል የፈጸሙ ኃይሎችን ተጠያቂ ለማድረግ የሽግግር መንግስት አማራጭ ሳይሆን አስፈላጊ ነው። ጠቅለል ባለ መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት የሚያስፈልገን በሚከተሉት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው-

  1. የኢትዮጵያን እንደ አገር ቀጣይነት ለማረጋገጥ- የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ፣ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው የሚል ኢትዮጵያን ተከታታይነትና ዘላቂነት እንዳላት አገር ሳይሆን፣ ብሔሮቿ ከፈለጉ የምትቀጥል ካልፈለጉ ደሞ ምንግዜም ልትበታተን የምትችል የብሔሮች ስብስብ አድርጎ የሚመለከት እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ አንቀጽ አለበት። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የብሔር ነጻ አውጭ ድርጅቶች የሚገኙባትና የማያቋርጥ የብሔር ግጭትና የርስበርስ ጦርነት የሚካሄድባት አገር ናት። በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት አይኑ በብሔር ፖለቲካ የታወረና ሁሉንም የፖለቲካ ልዩነቶች በጦርነት ብቻ ለመፍታት የሚሞክር ጦርነት ቀፍቃፊ መንግስት በመሆኑ፣ኢትዮጵያ ከብሔር ግጭት፣ከእርስ በርስ ጦርነትና ከመበታተን አደጋ ወጥታ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ማድረግ እንድትችል የሽግግር መንግስት ያስፈልጋል።
  2. በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚካሄደው ግጭትና ጦርነት ለማቆም- ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚካሄድ የትጥቅ ትግል አለ፣አማራና ኦሮሚያ ክልል በፌዴራል መንግስትና በታጣቂዎች ( ፋኖና ኦነግ-ሸኔ) መካከል የሚካሄደው ጦርነት የብዙ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፣በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከቀያቸው አናቅሏል፣በንብረትና መሰረተ-ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። የትግራይ ህዝብ የሁለት አመቱ ጦርነት ካደረሰበት ከፍተኛ ኤኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ሳያገግም ሦስተኛ ዙር ጦርነት እየታወጀበት ነው። ጋምቤላ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች እንዳሻቸው እየመጡ ሰላማዊ ዜጎችን የሚገድሉበትና የሚዘርፉበት ክልል ከሆነ አመታት ተቆጥረዋል። በሥልጣን ላይ ያለው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት እነዚህ ችግሮች እንዲባባሱ ከማድረግ ውጭ መፍትሄ ሲፈልግ አይታይም። ይህ የሚያሳየን ኢትዮጵያ ውስጥ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ተደራድሮ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስና ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ ያለን ብቸኛ አማራጭ ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር መንግስት ብቻ መሆኑን ነው።
  3. ብሔር ተኮሩን ፌዴራል ሥርዓት ለማሻሻል- መሠረቱን ብሔርና ቋንቋ አድርጎ የተዋቀረው የኢትዮዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት ዛሬ በየቦታው ለሚታዩ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ምክንያት መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። የብሔር ኃይሎች ኢትዮጵያ “የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት” ብለው በተናገሩበት በቀኃስ ሥርዓት ውስጥም ሆነ የብሔር ነጻ አውጪዎች የ17 አመት ጦርነት ባካሄዱበት በደርግ ዘመንም ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔር ብሔረሰቦች ነበሩ፣ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ብሔሮች የግዛት ይገባኛል ሽኩቻ ውስጥ የገቡትና ከክልሌ ውጣልኝ በሚል እርስበርስ መገዳደል የጀመሩት ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፌዴራሊዝም (Ethnic Federalism) ከተመሰረተ በኋላ ነው፣ ወይም ብሔር ብሔረሰቦች እራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ጀመሩ በተባለበት በህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓት ውስጥ ነው — ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ደሞ የዚህ ሥርዓት ተቀጥላ ነው። የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት የፌዴራል ሥርዓቱን አወቃቀር ለማሻሳል ህገ መንግስታዊ ዕርምጃ መውሰድ የሚችስል ህዝባዊ ተአማኒነት የለውም፣ ደሞም ህገ መንግስት ማሻሻልን የመሰለ ትልቅ አገራዊ እርምጃ ለመውሰድ አገራዊ ሃላፊነት መሰከም ካቃተውና በአንድ ፓርቲ ከሚመራ አገዛዝ ይልቅ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የሚወክል የሽግግር መንግስት የበለጠ ተቀባይነትና ተአማኒነት ይኖረዋል።
  4. ህገ መንግስቱን ለማሻሻል- በ1987 ዓም በስራ ላይ የዋለውንና ዛሬ በስራ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ህገ መንግስት በተመለከተ ሁለት ነገሮችን ማለት ይቻላል፣ አንደኛ- ባለፉት 31 አመታት ህወሓት/ኢህአዴግ እንደጻፈው ህገ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ ለሁለት ከፍሎ ያከራከረ ሌላ ምንም ነገር የለም፣ሁለተኛ፣ይህ ህገ መንግስት ፌዴራል ዲሞክራሲያዊት ሪፑብሊክ ኢትዮጵያን ከፈጠረ ጀምሮ ኢትዮጵያ የአለማችን የብሔር ግጭት ተምሳሌት ሆናለች። ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በኢትዮጵያዊያን መካከል አጥር ሰርቶ የለያየን የብሔር ፌዴራሊዝም እንዲቀጥል የሚፈልግ መንግስት ስለሆነ እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ አንድ አገር ህዝብ አብሮ የሚያኖረንን ማህበራዊ ኮንትራት እንደገና መጻፍ አለብን፣ይህንን ለማድረግ ያለን ብቸኛ አማራጭ ደሞ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ መንግስቱ ይሻሻል ወይስ ይለወጥ የማለት ህዝባዊ መሰረት የሚኖረው ኢትዮጵያዊያን ተስማምተው የፈጠሩት የሽግግር መንግስት ሲኖር ብቻ ነው።
  5. አገሪቱን ያናጋት ኢኮኖሚያዊና ሰብአዊ ቀውስ እንዲያበቃ- ኢትዮጵያ በአንድ በኩል ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ጋር ተስማምታ ተግባራዊ ባደረገቻቸው የኤኮኖሚ ፖሊሲዎች የተነሳ፣በሌላ በኩል ደሞ የአሜሪካና የሌሎችም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እርዳታ በመቀነሱ የተነሳ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ቀውስና፣ ስፋቱና ጥልቀቱ በየቀኑ እየጨመረ የሚሄድ የረሃብና የድህነት አደጋ ውስጥ ገብታለች። ጦርነት በሚካሄድባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ሁሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ተፈናቅሏል፣ የዞን፣የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከጥቅም ውጭ ሆኗል፣የእርሻ ቦታዎች የጦርነት አውድማ ሆነዋል፣ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋሞች ተዘግተዋል ወይም ወድመዋል። የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ኢትዮጵያን ከዚህ ትልቅ ቀውስ ውስጥ ያወጣል ብሎ መጠበቅ የችግሩን ትክክለኛ ባለቤት አለመረዳት ነው። ስለዚህ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ በፍጥነት ለመውጣት የሚያስፈልገን፣ትኩረቱን ትርጉም የለሽ ምርጫ ላይ ያደረገ መንግስት ሳይሆን፣ትኩረቱ ሰላም፣መረጋጋትና ሰብዓዊ ተደራሽነት ላይ የሆነ የሽግግር መንግስት ነው።
  6. ከቀን ወደ ቀን እየጠበበ የሚሄደውን የፖለቲካና ሲቪክ ምህዳር ለማስፋት- ኢትዮጵያ ጠሚ አቢይ አህመድ የሚፈልገው ነገር ሁሉ የሚሆንባት እሱ የማይፈልገው ከሆነ ግን ምንም ነገር የማይሆንባት አገር ከሆነች አምስት አመታት ተቆጥረዋል። አቢይ አህመድ የማይፈልጋቸው የአገር ውስጥና የውጭ ሜዲያዎች ታግደዋል፣ጋዜጠኞች ታስረዋል፣ከአገር ተባርረዋል ወይም ተሰድደዋል፣የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና ሲቭክ ማህበራት ፈቃድ ተሰርዟል። ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት ይቁም ብለው ሠላማዊ ሠልፍ የጠሩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ታስረዋል፣ባጠቃላይ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካና የሲቪል ምህዳር እየጠበበ ሄዶ እንኳን መናገር ማንንም የማያስተንፍስ ሆኗል። የፕሬስ ነፃነትን ዛሬ ካለበት ቦታ ዜጎች መንግስትን ከመቃወም ጀምሮ በነጻነት ማሰብና ያሰቡትን በነጻነት ማንሸራሸር የሚችሉበት ቦታ ላይ ለማድረስና፣የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት መንቀሳቀስ የሚችሉበት ምህዳር ለመፍጠር፣በተለይ ደሞ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ቁልፍ የሆኑ ተቋማትን(ምርጫ ቦርድና የፍትህ አካላት) በአዲስ መልክ ለመገንባት የሽግግር መንግስት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።
  7. እውነተኛ ብሔራዊ እርቅ ለማስፈን- ኢትዮጵያ የቀይሽብር ወንጀል፣የጦር ወንጀል፣የዘር ማጽዳት ወንጀልና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባትና ዛሬም በየቀኑ የሚፈጸምባት አገር ናት። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በአገረ-መንግስቱ ግንባታ ሂደት፣ባለፈው የኢትዮጵያ ታሪክ፣በስራ ላይ ባለው ህገ መንግስት፣በፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀርና ባጠቃላይ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት በሚለው ጥያቄ ላይ የማይግባባ የፖለቲካ ልህቅ የሚገኝባት አገር ናት። በሥልጣን ላይ ያለው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ለእነዚህ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያቀርብ ዕድል ተሰጥቶት ዕድሉን አለመጠቀሙ ብቻ ሳይሆን አንዳዶቹ ችግሮች እንዲባባሱና ይበልጥ እንዲወሳሰቡ አድርጓል። ካሁን በኋላ ኢትዮጵያ በአገራዊ ምክክር፣በሽግግር ግዜ ፍትህና በእውነትና እርቅ ሂደቶች ውስጥ እንድታልፍ ለማድረግ ቅቡልነቱም ህጋዊነቱም የሚኖረው ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ብቻ ነው።
  8. ተቋማዊ ማሻሻያዎች ለማድረግ– ኢትዮጵያ ነፃና ገለልተኛ ተቋሞች የሌሉባት አገር ናት። ፍርድ ቤቶች፣የፖሊስና የደህንነት ተቋሞች አራት ኪሎን የተቆጣጠረ ሁሉ ህዝብን ቀጥቅጦ ለመግዛት የሚጠቀምባቸው የማጥቂያ መሳሪያዎች ናቸው። ህዝብ በከፈለው ግብር የሚተዳደሩ ሜዲያዎች የገዢው ፓርቲ የፕሮፓንዳ መሳሪያዎች ናቸው። ምርጫ ቦርድ ገዢው ፓርቲ በየአምስት አመቱ እንዲመረጥ ለማድረግ የተቋቋመ ተቋም ነው። በሥልጣን ላይ ያለው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት እነዚህ ተቋሞች የሱን የሥልጣን ዘመን እስካረዘሙለት ድረስ ምንም አይነት መሻሻያ እንዲያደርጉና ዝህባዊ መልክ እንዲይዙ ማድረግ አይፈልግም። ስለዚህ ያለን ብቸኛ አማራጭ ነፃና ገለልተኛ ተቋማትን ያለምንም ጠልቃ ገብነት ህዝብንና አገርን እንዲያገለግሉ አድርጎ መገንባት የሚችል ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ማቁቋም ነው።

የሽግግር መንግስት እንዴት ይመሰረታል?

ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዳይፈጠር ምክንያት ከሆኑ ነገሮች አንዱ፣የተለያዩ የፖለቲካና ማህበራዊ ባለድርሻዎች እርስበርስ የማይገናኙ መሆናቸውና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር መሃሉ ባዶ መሆኑ ነው፣ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ የመሃል ፖለቲካ የሚያራምዱ ኃይሎች አለመኖራቸው ነው (Absnece of Centripetal political forces).። ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመጀመሪያው ትልቅ ስራ እነዚህን- በአንድ ቤት ውስጥ ተራርቀው በየራሳቸው ክፍል የሚኖሩትን ባለድርሻዎች ተወያይተውና በመካከላቸው የሚገኙ ልዩነቶችን እጥብበው ወደ ሳሎን ክፍል እንዲመጡ ማድረግ ነው። እንዴት? ከታች ያሉትን 3 ሠንጠረዦች ይመልከቱ

Advertise here _ borkena

ሁለተኛ- እነዚህ ወደ መሃል የመጡ ባለድርሻዎቺ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ  ተወያይተው ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው

ሦስተኛ- ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዴት መፈጠር አለበት በሚለው ጥያቄ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው 

አራተኛ- እነዚህ የተለያዩ ባለድርሻዎች የሽግግር መንግስት እንዴት መፈጠር አለበት በሚለው ጥያቄ ላይ ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የታጠቁ ኃይሎች (ህወሓት፣ፋኖ፣ኦነግ-ሸኔ፣ኦብነግ፣ጋህነግ እና ቤህነን) ጋር ንግግር መጀመር አለባቸው።

ኢትዮጵያ ዉስጥ የሽግግር መንግስት ሊፈጠር የሚችልባቸው ቢሆንሶች(Senarios)

– Advertisement –

አገራችን ኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ያስፈልጋታል ወይ በሚለው ጥያቄ ላይ አብዛኛው ተቃዋሚ ኃይልና የኢትዮጵያ እንደ አገር ቀጣይነት በሚያሳስባቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል ልዩነት የለም፣ልዩነት ቢኖር እንዴትና በነማነው የሽግግሩ መንግስት የሚፈጠረው በሚለው ጥያቄ ላይ ነው። ጠሚ አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ የወሰዳቸው ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ እርምጃዎች ኢትዮጵያንና ህዝቧን በቀላሉ መውጣት የማይችሉት አዘቅት ውስጥ ይዟቸው ገብቷል። ከዚህ በየቀኑ ጥልቀቱና ስፋቱ እያደገ ከሚሄድ አዘቅት ውስጥ በአስቸኳይ እራሳችንን የማናወጣ ከሆነ የኢትዮጵያ እንደ አገር ቀጣይነት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይገባል። ይህንን አደጋ ለመከላከል የመጀመሪያው እርምጃ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ነው።

ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ አመታትን ያስቆጠረ ሥርዓተ መንግስት ያላት አገር ብትሆንም፣ኢትዮጵያ ውስጥ በግልጽ የሚታየው የፖለቲካ ባህል ነፍጥን እንጂ ውይይትና ድርድርን የሚጋብዝ አይደለም። ባለፉት 50 አመታት በግልፅ እንዳየነው ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን ለመፍታት ጠመንጃ ተሸክመን ጫካ ገብቶ መታገል እንጂ በጠረቤዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ ተወያይቶና ተደራድሮ ልዩነቶችን መፍታት ምርጫችን ሆኖ አያውቅም። ዛሬ ላይ ግን ከአሮጌውና ከውጤት አልባው የጠመንጃ ባህላችን ተላቅቀን የውይይትና የድርድር ባህል እንድንለማመድ አገራችን ኢትዮጵያ የገባችበት  ውስብስብ ሁኔታ ያስገድደናል። ይህ ግዳጅ አገርን ለማዳን የሚደረግ ግዳጅ ነውና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሙሉ ልቡ ሊቀበለው ይገባል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው የሚካሄደው ጦርንት እያፈናቀለ፣እየገደለና እያሳደደ ያለው ኦሮሞ፣አማራ፣ትግሬ፣ሱማሌ፣ሲዳማ፣ወላይታ፣ጋምቤላ ወዘተ ሳይል ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ነው። ጠሚ አቢይ አህመድ በፈጠራት ኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ አጥነት፣በድህነት፣በኑሮ ውድነት፣በረሃብና በቤት አልባነት የሚሰቃየው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። ስቃዩ፣በደሉና መከራው ብሔር አይለይም፣ ከእነዚህ ሰው ሰራሽ ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ግን ለመገላገል የምናደርገው ጥረትም በብሔር ሊለያየን አይገባም፣አዎ በፍጹም አይገባም!!!

እኛ ኢትዮጵያዊያን የተሰራብንን የልዩነት ግድግዳ አፍርሰን አንድ ላይ ከቆምን ችግሮቻችን ከኛ በታች ናቸው። ሦስት የተለያዩ መንግስታትን ከሥልጣን አስወግደናል፣ለኛ የሚበጅና በምርጫ አምጥተን በምርጫ ማስወገድ የምንችለው መንግስት የሚገኝበትን የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር ግን አልቻልንም። በአስቸኳይ መወገድ ያለበትን የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት ከማስወገዳችን በፊት ግን ከዚህ ቀድም ያልሰራነውን አንድ ትልቅና ወሳኝ ሥራ መስራት አለብን፣ ይህ ወሳኝ ሥራ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ከመወገዱ በፊት ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ነው። በእርግጥ ዛሬ አገራችን በምትገኝበት ሁኔታ ውስጥ የሽግግር መንግስት ማቋቋም በጣም አስቸጋሪና ፈታኝ ስራ ነው፣ሆኖም ፈተናውና ችግሩ ይህንን ስራ ሳንሰራ ቀርተን እኛም አገራችንም ከሚደርስብን አደጋ በጣም ያነሰ ነው። 

በዛሬዋ የተለያዩ የታጠቁ ኃይሎች በሚገኙባትና በፌዴራሉ መንግስትና በእነዚህ የታጠቁ ኃይሎች መካከል ጦርነት በሚካሄድባት ኢትዮጵያ ውስጥ የታጠቁ ኃይሎችን ያላካተተ ወይም የእነሱን ሙሉ ስምምነት ያላገኘ የሽግግር ሂደት መጀመር አይቻልም። በተለይ አማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ኦነግ-ሸኔና ህወሓትን ከግምት ውስጥ ሳናስገባ ስለሽግግር መንግስት ማሰብ አንችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዴት ይመሰረታል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ ቢሆንሶችን (Cenarios) አስቀምጠን መመልከት እንችላለን፣ነገርግን በእያንዳንዱ ቢሆንስ ውስጥ የታጠቁ ኃይሎችን ከግምት ውስጥ ካላስገባን የምናስቀምጠው ቢሆንስ ከምኞት ያለፈ አይሆንም። ለምሳሌ፣የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በትጥቅና በህዝባዊ እምቢተኝነት በሚካሄደው ትግል ግብአተ መሬቱ ሲደርስ፣ የተለያዩ ባለድርሻዎችን ጋብዞ ያንን በተደጋጋሚ አያስፈልግም ያለውን የሽግግር ሂደት ማስጀመር ይችላል፣ነገር ግን ከተጋበዙት ባለድርሻዎች ውስጥ የታጠቁ ኃይሎች ከሌሉበት እነዚህ ኃይሎች የሽግግሩን ሂዳት ከመጀመሩ በፊት ወይም ከተጀመረ በኋላ የማሰናከል ከፍተኛ ችሎታ አላቸው። 

ቢሆንስ አንድ-

የታጠቁ ኃይሎች ግንባር ፈጥረው ግንባሩ የተለያዩ ባለድርሻዎችን (ሲቪል፣ወታደራዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ) ያሰባስባል። ይህ የባለድርሻዎች ስብስብ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ከመውደቁ በፊት ተወያይቶ/ተደራድሮ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ያቋቁማል። ይህ የሽግግር መንግስት ነው ለጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት የድርድር ጥያቄ ማቅረብ ያለበት። ጥያቄው ተቀባይነት ካገኘና ድርድሩ ከተሳካ፣ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት የሽግግሩ አባል ይሆንና ለሽግግሩ መንግስት ሥልጣን ያስረክባል። ጥያቄው ተቀባይነት ካላገኘ ወይም ድርድሩ ካልተሳካ ግን የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ያለው ዕድል በኃይል መወገድ ብቻ ነው።

ይህ ቢሆንስ እውን እንዲሆን፣የታጠቁ ኃይሎች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ከማስወገድ ባሻገር ኢትዮጵያ ውስጥ መፈጠር ያለበት የሽግግር መንግስት የተለያዩ የአገሪቱን ባለድርሻዎች ማካተት እንዳለበትና እያንዳንዱ ባለድርሻ በሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደት ውስጥም ሆነ፣በሽግግሩ መንግስት ውስጥ የሚኖራቸው ተሳትፎ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ለመሆኑ በሙል ልብ መቀበል አለባቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝባዊ እምቢተኝነትና በትጥቅ የሚደረገው ትግል የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረስ አለበት። ከዚህ በተጨማሪ ለጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት የድርድር ጥያቄ የሚያቀርበው የሽግግር መንግስት አካታችና የትኛውም ባለድርሻ በበላይነት የማይቆጣጠረው መሆን አለበት።

ቢሆንስ ሁለት

አገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻዎች ጥምረት ፈጥረው ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዴት ይፈጠራል በሚለው ጥያቄ ላይ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። እነዚህ ባለድርሻዎች ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ተገናኝተው በወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳዮች፣ በሽግግር መንግስት አስፈላጊነትና እንዴት ይፈጠራል በሚለው ጥያቄ ላይ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። የዚህ ስምምነት ውጤት የታጠቁ ኃይሎችና የሲቪል ባለድርሻዎች ጥምረት ይሆናል። ይህ ጥምረት ለጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት እሱ እራሱ ተሳታፊ የሚሆንበት የሽግግር መንግስት እንዲፈጠር ጥሪ ያቀርባል። መንግስት ጥሪውን ከተቀበለ ጥምረቱና መንግስት ሰፋ ያለውን ባለድርሻ ያካተተ የሽግግር መንግስት ይመስርታሉ፣መንግስት ጥሪውን ካልተቀበለ የሽግግር መንግስት መመስረቱ አይቀርም፣ይህ የሽግግር መንግስት የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በኃይል ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ ወደ ሥልጣን ይመጣል።

ይህ ቢሆንስ እውን እንዲሆን፣በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት እየተዳከመ ሄዶ የታጠቁ ኃይሎች ግልፅ የበላይነት ሊኖራቸው ይገባል።

ቢሆንስ ሦስት

ኢትዮጵያ ውስጥ የፌዴራል ኃይሎች ከአማራ ኃይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ ከገቡ ሦስት አመት ተቆጥሯል፣ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሽምቅ ውጊያ ከተጀመረ አመታት ተቆጥረዋል፣አሁን ደሞ የኢትዮጵያ መንግስት ከትግራይ ኃይሎችና ከጎረቤት ኤርትራ ጋር ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብቷል። ይህ ውጥረት ከፈነዳ ሱዳን ውስጥ ከሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ጋር የአፍሪካን ቀንድ ባጠቃላይ ምስራቅ አፍሪካን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ይዞ ሊገባ ስለሚችል፣ አለም አቀፉ ማህበረሰብ (አሜሪካ፣የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት) ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት እንዲፈጠር የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት ማስገደድ ይችላሉ። በተለይም ከኤርትራና ከትግራይ ጋር የሚደረገው ጦርነት የኢትዮጵያን ውስጣዊ ክፍፍል በፍጥነት ስሌሚያባብሰውና ከፍተኛ የዜጎች ሞት፣መፈናቀልና ስደት ስለሚከሰት፣አለም አቀፉ ማህበረሰብ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አድርጎ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ተወግዶ የሽግግር መንግስት ሥልጣኑን እንዲረከብ ሊያደርግ ይችላል።

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian NewsBorkena English

ኤክስ ፡ @zborkena