የ130 ኛው የአድዋ ድልን ለማክበር የተዘጋጀ ፅሁፍ (ከዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ)
ቦርከና ደስክቦርከና ደስክ
World Wide Travel Group

አድዋ የአፍሪካ እህጉር የነፃነት ጎህ ቀዳጅ:የጥቁር ህዝብ ኩራት: የማንነታችን ህያው ማስረጃ

ከዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ
የካቲት 23 (የጊዮርጊስ ዕለት) አፄ ምኒሊክ፣ ራስ መንገሻ (የትግራይ ሠራዊት አዛዥ)፣ ራስ መኮንን( የመሃል ጦር አዛዥ)፣ ራስ ሚካኤል( የወሎ ጦር አዛዥ) የዋጉ ገዥ ዋግሹም ጓንጉል፣ የላስታው ራስ ኃይሉ፣ የአምባሰሉ ጃንጥራር አስፋው፣ ራስ ወሌ (የቤገምድር ጦር አዛዥ)፣ ደጅዝማች በሻህ እና ሊቀመኳስ አባተ፣ አድዋ፣ በቅዱስ ገብራል ቤተክርስቲያን ተገኙ። ጸሎት ካደረሱ በኃላ የአቡነ ማቴዎስን ቡራኬ ተቀበሉ። “ ልጆቼ! ዛሬ የፍትህ ዕለት ነው። የእግዚአብሔር ፍርድ የሚፈጸምበት ቀን ነው። ሂዱ! እምነታችሁን፣አገራችሁንና ንጉሳችሁን ተከላከሉ። ኃጢአታችሁን ያስተሰርይላችሁ።” ብለው ባረኩዋቸው:: ሁሉም መስቀል ተሳልመው ወጡ። ንጉስ ተክለሃይማኖት በጣም ሃይማኖተኛ ሰለሆኑ ቁርንባን ለመቀበል ወደ ኋላ ለመቅረት ቢፈልጉም አፄ ምኒልክ ስላጣደፉዋቸው ሁሉም በየግንባራቸው ወደ የሰራዊታቸው ሔዱ።
ሃያ ኪሎ ሜትር ርቆ አድዋ አፋፍ ላይ አምስት የጣሊያን ጀነራሎች የኢትዮጵያን ሰራዊት ለማጥፋት የመጨረሻ ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው : የዘመኑን ወታደራዊ መሃላና ሰላምታ ተለዋውጠው : ወደየግንባራቸው ሔዱ። ጀነራል ባርቲየር፣ የኤርትራ ገዢ፣ ጀነራል አልበርቶኒ፣ ጀነራል አርሞንድ፣ ጀንራል ዳቦርመዳ እና: ጄኔራል አሊና; በጠቅላላው ከባንዳው ሌላ : 17 ብርጌድ የጣሊያን እግረኛ ጦር እና 57 መድፍ ነበራቸው።
- Advertisement –
Advertise here _ borkena
ጦርነቱ ተከፍቶ ስድስት ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አከተመ። ጀንኔራል አርሞንዴ : ከተገደሉት 262 የጣሊያን መኮንኖች አንዱ ነበር። 4000 የጣሊያን ወታደሮች ተገድሉ። 1900 የጣሊያን ወታደሮች፣ ጀነራል አልበርቶኒ ጨምሮ፣ እንዲሁም አንድ ሺህ ባንዳዎች ተማረኩ።
አንቶይ ሙከስ (Antoy Mucus) “የጣሊያን ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ” በሚለው መጽሃፉ እንድገለጠው : “በአውሮፓ የኮሎኒያል ታሪክ ከፍተኛው አንድ ታላቅ ሽንፈት ነበር።”
“It was the greatest single disaster in European colonial history.” The Italian Ethiopian Campaign, Antony Muckes, Random House)
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ ነገር ሆኖ አያውቅም። ታሪካችን ሁሉ የትግልና የድል ታሪክ ነው። ስለሆነም በተጎናጸፍናቸው ድሎች ምክንያት ወረራውና ጥቃቱ አክትሞ : ትግሉ አበቃ ብለን የተዝናናንበት ወቅት አልነበረም። በታሪካችን ውስጥ ያሳለፍናቸው የድል ዘመናት ሁሉ ወደ አዲስ የትግል ምዕራፍ የሚያሸጋግሩን ነበሩ። የተጎናጸፍናቸው ድሎች ሁሉ ለሚቀጥሉት ትግሎቻችን የሞራል ተሃድሶ ሰጥተውናል። የኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ : በተባበረ ክንድና ኃይል፣ እ.ኤ.አ 1896 በአድዋ ሜዳ ፍልሚያ : በኢጣሊያ ኮሎኒያሊስት ወራሪዎች ላይ የተቀዳጀው ታሪካዊ ድል፣ የተጎናጸፈው ገናና ክብር፣ ብሔራዊ በሆነ መራራ ትግልና መስዋዕትነት የተገኘ፣ የፍጹም አንድነት ውጤትና መግለጫ ነው። ዓላማውም ጠላትን ትምህርት አስተምሮ ወደመጣበት ለመመለስና የኢትዮጵያን ታሪካዊ ህልውና ለማስከበር ነበር።
- Advertisement –
Advertise here _ borkena
በዚህ ዕለት በቅኝ ግዛት ፈላጊው በኢጣሊያ ኢምፔሪያሊስት ተስፋፊ ኃይልና : ነጻነቱንና የግዛቱን አንድነት ላለማስደፈር ምንጊዘም ትጥቁን አላልቶ በማያውቀው የኢትዮጵያ ጀግና ህዝብ መካከል በተካሔደው የአንድ ጀንበር ታሪካዊ ጦርነት ላይ የተገኘው ድልና ክብር ; የብሔራዊ አንድነታችን ወጤት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ አህጉርም የነጻነት ንቅናቄ ጎህ ቀዳ ጅ፣ የጥቁር ህዝቦች መመኪያና የማንነታችን ህያው ማስረጃም ነው። ከዚህ ከቀይ ባህርና ከግብፅና ሱዳን በኩል: በኢትዮጲያ ምድር ላይ በግልጽ ከተሰነዘረው ወረራና ብሎም ከኮሎኒያሊስቶች ተከታታይ አደጋ ለመዳን የነበረው ብቸኛ አማራጭ የኢትዮጲያ ህዝብ ብሔራዊ አንድነት፣ ድርጅትና ዝግጅት መሆኑን በጥልቀት የተገነዘቡት አፄ ቴዎድሮስ ነበሩ። ስለሆነም ቴዎድሮስ ለብሔራዊ አንድነትና ትግል መሰረትና መሳሪያ ሊሆን የሚችል አንድና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ለመገንባት ባካሔዱት ታሪካዊ በውጭ የተደገፈ የውስጥ ትንንቅ: እ.ኤ.አ በ1847 የኢትዮጲያን ህዝብ በአንድ ብሔራዊ መንግሥትና መሪ ሥር በማሰባሰብ በሃገሪቱ የአንድነት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ከፈተ።
አጸ ቴዎድሮስ እራሳቸው ኮሎኒያሊዝም እስከመጨረሻው ለመታገል ባደረጉት ትግል፣ በትግላቸው በተገኙት በርካታ ድሎችና እሳቸውም በሞቱት የክብር ሞት ለኢትዮጵያችን ታላቅ ድል አጎናጽፈዋል። ከዘመኑ መጀመሪያ፣ ከ1847 ጀምሮ በየጊዜው በተነሱብን ወራሪዎች ላይ ድልን እንድንጎናጸፍ ወሳኝ አስተዋጻኦ ያደረጉት አፄ ቴዎድሮስ: በመራራ ትግላቸው ብሔራዊ አንድነትና ማዕከላዊ መንግስት በመመስረታቸው ነው። አፄ ቴዎድሮስ ይህንን ታላቅ ዓላማ ይዘው ቢነሱም፣ እጅግ በጣም ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ በሆነው በቀይ ባህር አካባቢ ሃብታምና ኃያል የሆነውንና እየጠነከረ የመጣውን የኢትዮጵያን ህዝብ አገር ወዳድነትና ጀግንነት ለማየት የማይፈልጉ ወራሪዎችና ኢምፔሪያሊስቶች የእኚህን ታላቅ መሪ የአገር ግንባታ ዓላማና ዘመቻ በመቃወም በአገሪቱ ብሔራዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግባት ጀመሩ። የአፄ ቴዎድሮስ ህይወት ይህንን በመሰለ የኮሎኒያሊስቶች አሻጥር ቢቀሰፍም፣ በአርማቸው የተገንባው የኢትዮጲያ ማዕከላዊ መንግስትና ህብረተሰብ፣ የራሳቸውን ዓላማና ፈለግ በተከተሉት በአፄ ዮሃንስ መሪነት ከውስጥ መሰሪዎችና ከእንግሊዝ ወራሪዎች እንቅፋትና አሻጥር አምልጦ፣ እ.ኤ.አ በ1868 እና በ1881፣ በጉንደት፣ በጉራዕና በመተማ ጦር ሜዳዎች የግብጽንና የሱዳንን ወራሪዎች በመድምሰስ የአገሩን ብሔራዊ ነጻነትና አንድነት ከአደጋ አትርፎ ድልን ተጎናጸፈ።
በአፄ ቴዎድሮስ ብሔራዊ መንግስት ሥር ተደራጅቶ፣ በአፄ ዮሃንስ የተጠናከረው የኢትዮጵያ ህዝብ በዳግማዊ ምኒልክ መሪነትና አዝማችነት፣ ታላቅ ጸረ ኮሎኒያሊስት ድል አስመዝግቧል። ከኢትዮጵያ በስተቀር በዘመኑ መላው የአፍሪካና የእሲያ አህጉራት ህዝቦች ፣ ህንድን : ቻይናን: ላቲን አሜሪካንን ጨምሮ : ረግጦ የገዛውን ኮሎኒያሊስት ወራሪ ኃይል በታላቁ የአድዋ ጦርነት ላይ ደምስሶ የአገሩን ብሔራዊ ነጻነትና አንድነት ከከፍተኛ አደጋ ከማዳኑም በላይ በዓለም ላይ የመጀመሪያውን ጸረ ኮሎኒያሊስት የትግልና የድል ታሪክ አስመዘገበ። ይህ ማለት በመላው በመላው አለም ተመቻችቶ የስፈረውን የእውሮፖን ኮሎኒያሊዝምን አንድም ሀይል ሳይደፍረው የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪክ ለመጅመሪያ ጊዜ: የተባበረ ክንዱን አንስቶ ደምሶታል::ይህ የጀግንነትና የመስዕዋትነት ውጤት የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነትና ትብብር የማይገሰስ፣ ጠንካራ ኃይል መሆኑን በተግባር ለዓለም አስመዘገበ፣: አስተማረ።
በዚህ ታሪካዊ የአደዋ ጦርነትና የድሉ ዋዜማ ላይ: ኮሎሊያሊስቶችና ኢምፔሪያሊስቶች :የኢትዮጲያ የአያሌ ሺህ ዓመታት ብሔራዊ አንድነትና ነጻነት ወደ ፍጻሜ እንደደረሰ፣ ቀኝ ግዛት በአገሪቱ ህዝብ ትክሻ ላይ እንደሚወድቅ፣ እንዳለቀለት ጉዳይ ቆጥረው ነበር። ይህንን ከንቱ ምኞት አውርተው አስወርተዋል። ለዚህም የተለያዩ ምክኒያቶችና ግምገማ ነበራቸው።
- Advertisement –
- ከ1881 እስከ 1885 ድረስ በአገር አቀፍ ደረጃ ተስፋፍቶ የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ረሃብና እልቂት ከፍተኛ የህይወትና የሃብት ጥፋት አድርሶ ስለነበር፣
- በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የእንግሊዝና የፈረንሳይ ኢምፔሪያሊስቶች የሀረርን ክፍል ሀገር ለመቀራመት ትልቅ ሴራ በመገንባት ላይ ስለነበሩ፣
- እንግሊዝ በአገሪቱ ምዕራባዊ ጠረፍ በሱዳን : በሰሜን ግብፅን :በደቡብ በኩል ደግሞ ኬኒያን አጣምራ: በቅኝ ግዛትነት ይዛ : የአባይን ምንጭ ሀገሮች ብትቅጣጠርም: ኡትዮጵያን በቀጥታ ለመውረር እንደማይችል አውቆ በተዘዋዋሪ መንገድ ለመቆጣጠር ከባድ ሴራ ዝግጅት ውስጥ ስለነበረች:
- በሃሰተኛ ውጫሌ ውል መሰረት የአውሮፓ ኃያላን አገሮች አገሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የኢጣሊያን ቀኝ ግዛት ትሆናለች በሚል እምነትና ምኞት ተገፍተው ከኢትዮጵያ ጋር ምንም ዓይነት የንግድና የዲፕሎማቲክ ግንኙነቶችን ስምምንት ለማድረግ ፍቃድኞች ባለመሆናቸው፣
- የጀብደኛው የኢጣሊያ ኮሎኒያሊስት ወታደሮች ኢትዮጵያን በጦር ኃይል አሸንፈው፣ አፄ ምኒልክንና እተጌ ጣይቱን በሰንሰለት አስረው፣ በምርኮኛነት ወደ ሮም ለመውሰድ በከንቱ ምኞት አብደው በከፍተኛ ዝግጅት ላይ ስለነበሩ ነው።
ይህ በእዚህ እንዳለ በ1883 በኢጣሊያንኛው የውጫሌ ውል ትርጉም ውስጥ ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ አስመስሎ ያቀረበው አንቀጽ መለወጥ : የኢጣሊያንን ክብር በአውሮፓ ኃያላን ዘንድ የሚያዋርድ ይሆናል በማለት የኢጣሊያን ወኪል አንቶኒዮ : አፄ ምኒልክ ለዚሁ ጉዳዩ በጠሩት ጉባኤ ፊት ተመጻደቀ። አፄ ምኒልክና እተጌ ጣይቱ : እኛም በራሳችን ቋንቋ ከተሰራው የውል ትርጉም ሌላ መሆኑና ብሎም ነጻ ህዝብ መሆናችንን ኃያላን ለሚባሉ መንግስታት ሁሉ ስለአስታወቅን፣ በኢጣሊያንኛ ትርጉም የተጻፈው የውሉ አንቀጽ ብሔራዊ ነጻነታችንንና ክብራችንን የሚነካ ስለሆን በግድ መለወጥ አለበት ሲሉ የኢትዮጰያን ታሪካዊ ጸረ ኮሎኒያሊስት ፅረ ኢምፔሪያሊስት አቆም አረጋገጡ።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የውጫሌ ውል ፍጻሜና የአድዋ ጦርነት ዋዜማ ሆነ። የኢትዮጵያ መሪዎችና የጦር አለቆች ከንጉሰ ነገስቱና ከእተጌ ጣይቱ ጀምሮ በሰሜንና በደቡብ ለወሳኙ ፍልሚያ ራሳቸውንና የጦር ሰራዊታቸውን ማዘጋጀት ጀመሩ። የኢትዮጵያ ህዝብ በጾታ፣ በእድሜ፣ በዘር በጎጥ :በጎሳ፣ በሃይማኖት፣ በሙያና በመደብ ሳይወሰን ለጸረ ኮሎኒያሊስቱ ጦርነት አስፈላጊውን ዝግጅት አከናወነ። ለወሳኙ ብሔራዊ ትግልና ድል፣ ለዚህ ብሔራዊ የነጻነትና የታሪክ ጥበቃ ፍልሚያ ዝግጅት በጦርነቱ ያልተሳተፉ ኢትዮጵያን ሁሉ : በፈቃደኝነት ያደረጎቸው አስተዋጽኦዎች ለወገን ክብር ታሪክ ባለድርሻ አድርጎአቸዋል።
ከውጭ ጠላት ጋር አብረን እናት አገራችንን አንወጋም በማለት መሳሪያቸውን ወደአሰለፋቸው ጠላት አዙረው የማይረሳ ብሔራዊ ግዳጅ ፈጽመው ካለፉት የኤርትራ ጀግኖች መካከል እነ ባህታ ሃጎስና እነ አውሎዓለምን በክብር እናስታውሳቸዋለን። በወሎ ደጃዝማች ጎንጉል ዘገየ የተባሉት ሽፍታ :ከሽፍትነት ተግባር ተመልሼ የአገራችንን ጠላት እየተዋጋሁ እንድሞት ምህረትና ፈቃድ ይሰጠኝ :ብለው ለብሔራዊ ግዳጅና ክብር ንጉሱን ለምነው መዝማታቸውን ስናስታውስ ኢትዮጵያዊነት ምን ያህል እንደሚያኮራ እንገነዘባለን።
የመላው ኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ ክብር፣ ህይወትና አንጡራ ሃብት፣ እንዲሁም የመስዋዕትነት ዋጋ የሆነው ብሔራዊ አንድነታችንን በአድዋ ድል በማስመስከራችን የዓለምን ፖለቲካ መልክ እንደለወጠው ሁሉ :ቅድመ አድዋ ምንም ዓይነት የፖለቲካና የዲፕሎማቲክ ግንኙነቶችና: ስምምነቶችን : አሻፈረን ያሉት የምዕራባውያን ኃያላን መንግስታት በፋንታቸው ግንኙነታቸውን ከኢትዮጵያ ጋር ለማጠናከር ጠየቁ። ፈረንሳይ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር ውል ፈረመች። የኢትዮጵያ ህልውና፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ኃያልነት፣ በማያሻማ መልኩ ለዓለም ህብረተሰብ ተረጋገጠ። አንድነት ህይልን ይወልዳል:: ሀይል ድልን ያስገኛል:: ድል ያስከብራል::
መላው አፍሪካ፣ መላው እስያ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ ላቲን አሜሪካና ሌሎችም ዛሬ ህልውና ያገኙ አገሮች በኮሎኒያኒዝም ሲረገጡና ሲበዘበዙ፣ ኢትዮጵያችን ለተወሰነ ጊዜ የሰሜኑን ክፍል ብትነጠቅም ብቸኛና ነጻ ሃገር ሆና ኖራለች ። ከ 1884 ወዲህ አፍሪካን ለመከፋፈልና ለመቀራመት አዲስ ሴራ ( Scramble for Africa) በተደረገበት ወቅትና ዓለም በሞላ በአዲስ የብዝበዛ ስርዓት ውስጥ በወደቀበት ጊዜ፣ ኢትዮጵያ አዲስ ድል በአድዋ ላይ ተጎናጸፈች። የዓለም ሶስት አራተኛው ህዝብ በኮሎኒያሊዝም ስር ሲወድቅ ኢትዮጵያ ብቻዋን እንዴት ህልውናዋን ጠብቃ በነጻነት ልትኖር ቻለች? ምንድነው የእዚህ ህዝብ ምስጢሩ? ብለው ብዙውች ስጠይቁ: ብዙዎች ደግሞ ምስጥሩን ቢያውቁትም ይህንን ምስጢር በገሃድ አውጥቶ፣ በታሪክ መዝግቦ ለዓለም ማሳወቅ ሃፍረታቸውንና ውርደታቸውን ስለሚያስታውሳቸውና ለኢትዮጵያውያን የጀግንነት ስም መስጠቱ የሚያሳፍር መስሎ ሰለሚታያቸው፣ ይህ ድል በተወሳና በተከበረ ቁጥር ይዘገንናቸዋል።
ምስጢራችን የሃገር ፍቅርና ጀግንነትና አንድነታችን ነው። ምኒልክ ከተደራጀ የአውሮፓ ኃይል ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጠው የአድዋን ድል እንድንጎናጸፍ ያደረጉት: ዘርአይ ደረሰን እንድ እሳት አግሎ በሰው አገር የጠላቶቹን አንገት እንዲቆራርጥ ያስገደደው፣ ሞገስ አስገዶምንና አብርሃ ባህታን በፋሺስት የጦር መሪ በግራዚያኒ ላይ ቦንብ እንዲወረውሩ ያደረጋቸው፣ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያዊ ኩራትና በልበ ሙሉነት ኃያላን የአውሮፓ ኮሎኒያሊስቶች ላይ ተፍተውና ተዋግተው መቅደላ ላይ የክብር ሞት እንዲሞቱ ያደረጋችው : አሉላ ዶጋሊ : ቀይ ባህር የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ወሰን ነው፤እያለ ህይወቱን በሞላ እንዲዋጋ ያደረገው: በተንቤን፣ በመተማ፣ በኦጋዴን በአጠቃላይ በደቡብ ምስራቅ፣ በሰሜንና ም ዕራብ ለኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና እልፍ አእላፍ ጀግኖች እንዲሞቱ፣ እንዲሰውና እንዲቆስሉ ያደረጋቸው: ይህው ጀግንነታችን: አንድነታችውና ለሃገራችው ያላቸው ፍቅር ነው።
ይህንን የሚያክል ፍጹም ወደር የለሽ የትግልና የድል ታሪክ አለን። የአርበኝነትና የጦርነት ታሪካችንን : አብዛኛው የዘመኑ ህዝባችን ገና አያውቀውም:: ይህ እውቀት ነበር ወደ አንድነት ሊመልሰን የሚችለው:: ግን ከሚያውቀው የማያውቀው በዝቶ ይገኛል። ዛሬ ዘመኑ ያመጣብን የዘር ፓለቲካ : ታሪካችንን ፈልቅቀን በማውጣት እንደኢትዪጵያዉያን አያሰበ በየመድረኩ እንዳይኩራራበት: እንዳይፎክርበት ወጣቱን በዘር ፓለቲካ መርዞ ከለከለው እንጂ : አንድ ሆነን በእኩልነት : በነፃነት እንደገና መኖር ስንጀምር :ተከብረን: ስለኢትዮጵያዊነታችን የበለጠ አውቀን : አንገታችንን ቀና እድርገን : ደረታችንን እሳብጠን: ሳንሸማቀቅ በአለም ዙሪያ የምንታይበት ጊዜ ይመጣል:: ታሪክ የሌላቸው ታሪክ እየፈጠሩ፣ ትንሽ ታሪክ ያላቸው ደግሞ ተጋኖ እንዲጻፍላቸውና እንዲነገርላቸው ሲደረግ : ከሁሉ ልቆ የሚገኘው የኢትዮጰያ ሰፊ ህዝብ ታሪክ ግን: ገና ከተቀበረበት እየወጣ በሃቀኛ የታሪክ ሰዎች በሙሉ ነፃነትና ኩራት: በትክክለኛ ገጽታው እንዲቀርብ የሚያመቻች የአንድነትና የእኩልነት ማእከላዊ የፓለቲካ ስርአት እንዲፈጠር በጉጉት እንጠብቃለን::
አድዋ አንድ ውጊያ አልነበረም:: በአድዋም የተጎናጸፍነው አንድ ድል አልነበረም። የአድዋም ድል የኢትዮጰያ ህዝብ ድል ብቻ አልነበረም። ከአድዋ በፊት በኢትዮጰያ ሕልውና ላይ የተቃጡ ብዙ የወረራ ሙከራዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በጀግናው የኢትዮጵያ ህዝብ ድል የተመቱበት፣ የውጊያዎች ውጊያ፣ የድሎች ሁሉ ድል ነበር። ይህ ታሪካዊ ድርጊት የኢትዮጵያ ህዝብ ኮሎኒያሊስቶችን ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር ድባቅ በመምታት፣ ጀግንነቱን ለመላው ዓለም በይፋ በማሳወቅ፣ ከፍተኛ የፖለቲካ ክብር በመቀዳጀት፣ ላልተማሩት፣ ላላውቁት ትምህርት በመስጠት : ኢትዮጵያችን በአለኝታነት እንድትታይ ያደረገ ነው። በምሳሌነቱ፣ በአርአያነቱ፣ በኮሎኒያሊዝም አገዛዝ ስር ላሉ ለብዙ ጭቁን ህዝቦች ብሩህ ተስፋ ያበሰረ ታላቅ ድል ነው። የአድዋ ድል በጸረ ኮሎኒያሊስት የትግል ታሪክነቱ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለመላው አለም ታላቅ ትምህርት ያለው ድል ነው። ለብዙ የተጨቆኑና የተገፉ ህዝቦች የትግል አርአያ የሆነ ተጋድሎና ገድል ነው።
አባቶቻችንና እናቶቻችን የኢትዮጵያ ሕልውናን ለመጠበቅ ከፍተኛ ትግል አካሂደው ብዙ ድሎችን ተጎናጽፈዋል። ካሸበረቀ የትግልና የድል ታሪክ ጋር : ይችን ውብ አገር: በሂደት ሊቋጩ ከሚገባና ከሚቻሉ ችግሮች ጋር አስረክበውናል። ይህንን የመሰለ አኩሪ የጀግንነት ታሪክ በተረከብንበት ምድር ላይ ጥቂቶች ዛሬ ታሪክ ክደው፣ አዲስ ታሪክና ትርክት ፈጥረው፣ ግዙፍና ጠንካራ የአንድነት ታሪክ ባለው ህዝብ መካከል ሽብርና መከፋፈል የሚያራምዱ ቢኖሩም: ይህንን ድል እንድንጎናፅፍ ያስቻለን የአርበኝነት፣ የአንድነት ስሜትና ጠንካራ እምነትን ለመመለስ የሚያስችል: ለዘመናት ሲገነባ የኖረ ባህል : ታሪክና አቅም አለን። በእኩልነትና በነጻነት ላይ የተመሰረተ ህብረተሰብ ስናስገኝ ይህንን ሁሉ ፈተና ለመቋቋም ያስችለናል።
የእስልምናና የክርስትና እምነትን ከመላው የተባበሩት መንግስታት አባላት ከሆኑ አገሮች በፊት የተቀበለች: ክዚያን በፊት እንደ ኢትዮጵያም ባይሆን በአባይ ሸለቆና በቀይ ባህር ዳርቻ ለተገነባው ስልጣኔ: እንደ ህዝብ ከማንም የቀደመ ስልጣኔ የነበረው ህዝባችን :ዛሬ ያንን ክብር ተገፎ : የትናንትና መጤ መንግስታት : እኛ እናውቅልሀለን ብለው በዘር: በሀይማኖት : በፓለቲካ ከፋፍለው የእነሱ ጥቅም እስፈፃሚ ሲያደርጉን: ይህ ግዙፍ ህዝብ ሊቀበለው አይገባም:: ንቀት ነው:: ስድብ ነው: አለማወቅ ነው:: ሳናውቅ በከፈትነውወይም በጠላቶች አማካኝነት በፈጠርነው ስንጥቅ ገብተው እኛን ለመበተን የተደረገና በመደረግ ያሉ ሴራዎች ስለሆኑ : ህዝባችን ሆይ ! እስከዛሬ ያየኸው : የመስከርከው: የደረስብህ : ይበቃል :: እንደ ህዝብ: አንደ ሀገር ወደ ኢትዮጵያዊነት ተመለስ:: በአንድነት ለአንድነት ታገል::ሌሎች ትርክቶች ሁሉ እርስ በእርስ የሚያጫርሱህ አገር የሚያሳጡህ ናቸው:: አፄ ዮሀንስ እንዳሉት : ” ኢትዮዽያ የተባለች አንደኛ እናትህ ናት: ሁለተኛ ዘመድህ ናት: ሶስተኛ ሚስትህ ናት: አራተኛ ልጅህ ናት: አምስተኛም መቃብርህ ናት::”
ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጣጠር: ትናንትና የተወለዱት ሀገሮች : ኢትዮጵያ ካላት ብሄረሰብች ቁጥር እጅግ ከመብለጡም ባሻገር: ኮሎኒያሊስቴች ለመግዛት እንዲያመቻቸው እርስ በእርስ ሲይፋጁአቸው የነበሩት : ዛሬ ነፃ መንግስታት መስርተው በሰላም ሲኖሩ: ኢትዮጵያውያን ለብዙዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ: ሌላ አለም ውስጥ የሌለ ትርክት ፈጥረው ለምን አንድነታቸውን ያደፈርሳሉ? ለሚለው አንግብጋቢ ጥያቄ ስንቱ ሊቅ ቢመራመር መልስ ማግኘት አልቻለም:: መልሱ እኛ ውስጥ ነው ያለው:: በአሁኑ ዘመን እንድም ሎአላዊ አገር :በብሄረስቦች ልዩነት ምክንያት: የአገር ህልውና የማፍረስ ደረጃ ላይ የደረስ ስለሌለ : በድርጊታችን አፍረን: ባሸበረቀ ልዬነታችን ላይ አንዲት ኢትዮጵያን ማዋለድ አለብን::
ለምሳሌ ያህል:
ህንድ 2500: ብሄረስብ
ኢንዶኒዝያ 1340
ፓፑዋ ጊኒ የምትባል ትንሽ የደሴት ሀገር: 1000 :
ናይጀሪያ 300
ኮንጎ ኪንሻሳ 250:
ታንዛኒያ ፅ 130 :
ሜክሲኮ 65 ;
ኡጋንዳ 60 : ብሄረሰቦች ኣሉአቸው::
እነዚህ አገሮች ሌሎች ችግሮች ይኑርባቸው እንጂ የዘር ፓለቲካ የለባቸውም:: ተቻችለው መኖር እንዳለባቸው አምነው በእንድነት ጃንጥላ ሁሉን አቃፊ በሆነ የፖለቲካ ስርአት ውስጥ ይኖራሉ:: የሁሉም ፍላጎት በነፃነትና በእኩልነት ሊያስተዳድር የሚችል ማእከላዊ የፓለቲካ ስርአት መፍጠር እንጂ : ብሄርተኛነትን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ስርአት ለመፍጠር አይደለም::
ሀገር መኖሪያ ቤት ነው:: ሀገር ማለት: የተባበሩት መንግስታትና መላው አለም የሚያውቀው : በድንበር የተከለለ: በሀይማኖት : በዘር: በባህል: በቀለም: የተለያዪ ብሄረሰቦች በሰላም በእኩልነት በነፃነት የፓለቲካ ስርአትና መሪዎች እየመረጡ የሚኖሩበት የአለማችን አንድ አካል ነው:: ኢትዮዽያችን አንዷ ነች:: ኢትዮጵያ የብሄረሰብ ስም አይደለም:: የሀገራችን የመኖሪያችን ስም ነው:: አለጎጆአችን መኖሪያ ስፍራ የለንም:: ከእሷም ወጥተን ሌላ ሀገር ለመመስረትም ሆነ በሰላም ለመኖር አንችልም:: ህልውናችን እኩልነት: አንድነትና ነፃነት እንጂ ማንነት አይደለም:: ብሄርተኛነትን መስረት ያደረገ ስርአተ መንግስት ሊኖርም እይችልም:: ትርፋ ዘለአለማዊ ጦርነት ነው:: አለም የተፉው: ጤናማ አእምሮ ሊረዳው የማይችል : ሁዋላ ቀር አስተሳሰብ ለእኛም ለማንም ህዝብ የሚመጥን እይደለም:: ታሪክ በአንድ በኩል እንደ ታላቅ ህዝብ መዝግቦናል:: ከዚያ ከፍታ ከፍ ባንልም ዝቅ አንበል:: ህልውናችን : እድገታችን : ክብራችን: ሀብታችን አንድነት ብቻ ነው:: የአድዋ ድል አለምን ያነቃነቀ : ያስደነገጠ: ለጥቁር ህዝብ የነፃነት ትግል ጎህ የቀደደ : አቅጣጫ ያሰመረ : የሰሜን ኮከብ ሆኖ ይታውሳል:: ይህንን አስከፊ ስርአት በአንድነት ለውጠን ታሪካችንን እናድስ::
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena
