
”ውድ ኢትዮጵያውያን! ለዚህ ክብራችሁ ከልብ አመሰግናለሁ። ሚስጥረስላሴ ታምራት ”
ሰሞኑን በምርጫ ጉዳይ ባደረግነው ክርክር የህዝብ ጥያቄዎችን በድፍረት ማንሳታችንን በመጥቀስ አክብሮታቸውን እየገለጹልን ያሉ ኢትዮጵያውያን ብዙ መሆናቸውን ተመልክቻለሁ።
ለዚህ ክብራችሁ ከልብ አመሰግናለሁ።
ሆኖም እኔ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄዎች ብዛት እና አንገብጋቢነት ጋር ተያይዞ ከተሰጠው ጊዜ አንፃር በበቂ ሁኔታ አንስቼ ሞግቻለሁ ብዬ አላስብም፤ ተጀመረ እንጂ አላለቀም።
እኔና ፓርቲዬ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ጥያቄዎች እንዳሉት እንረዳለን። እነዚህን እንደ ዜጋ የእኔም፣ እንደ ፓርቲም የጋራችን የሆኑትን ጥያቄዎች ባገኘነው እድል ሁሉ ለማንሳትና ለመሞገት እንደምንንቀሳቀስ አረጋግጥላችኋለሁ።
ውድ ኢትዮጵያውያን!
የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱት በጠነከረ ትግል እንደሆነ እናምናለን። ለዚያም እኔም ሆንኩ ፓርቲዬ ወቅቱ የሚፈልገውን ጠንካራ ትግል በጽናት እንደምንገፋበት ዛሬም በድጋሚ ቃል እንገባለን።
የምናነሳቸው የጋራ አጀንዳዎች በወቅታዊ ድጋፍ ብቻ ታጅበው እንዳይቀሩ የጋራ ትግላችን እስከ መጨረሻው እንዲሆን ጥሪ አቀርባለሁ።
በዋናነት ይህ ድጋፋችሁ ትግላችን ውጤት በሚያመጣበት አግባብ እንዲቀጥል እየጠየቅሁ ላሳያችሁን አጋርነት በድጋሚ አመሰግናለሁ ስትል በማህበራዊ ሚዲያ በኩል መልዕክቷን አጋርታለች።
