
Trotsky Wendessen Yirga ·Follow
ኢራን ለምን ሳዑዲን፣ UAEን፣ ባህሬንን እና ሌሎች የሙስሊም አገራትን ታጠቃለች?
ይህ ግጭት በምዕራባውያን እና በሙስሊሙ ዓለም መካከል አልያም ክርስቲያኖች እና አይሁዶች ከሙስሊሞች ጋር የሚያደርጉት ጦርነት ብቻ አይደለም። ኃያሏና የክርስቲያን አገር የሆነችው ሩሲያ፣ የኢራን ደጋፊ ነች። ኤምሬትስ፣ ባህሬን፣ ሳዑዲ፣ እና ዮርዳኖስ ከእስራኤል ጋር የቆሙት በሃይማኖት አንድ ስለሆኑ አይደለም። ኢቫንጀሊካን ወይም የወንጌል አማኝ ናቸው የሚባሉት ትራምፕ የእስልምና እምነት ማዕከል ከሆነችው ከሳዑዲ ጋር ተባብረው ከእስራኤል ጎን የቆሙት፣ ሳዑዲን ቸርች ላይ አግኝተዋት ተዋውቀው አይደለም።
ይልቁንም የሰሞኑ ሁኔታ በሺዓ እና በሱኒ ኃይላት መካከል ያለ የበላይነት ፋክክር ጭምር ነው። ብዙ ሰዎች የዚህን ጉዳይ እውነተኛ ገጽታ በተሳሳተ መንገድ እየተረዱት ይገኛሉ። ጦርነቱን “አሜሪካ + እስራኤል ከኢራን ጋር” በሚል ብቻ የሚያዩት ብዙ ናቸው። ምንም እንኳ ይህ 100% እውነት ቢሆንም፣ ከዚህ በስተጀርባ ግን ሌላ ትልቅ ምስጢር አለ። ላይ ላዩን ሲታይ ፖለቲካዊ ይመስላል፤ ውስጡ ግን ኢኮኖሚያዊና የእስልምናውን ዓለም ለመምራት የሚደረግ ፍልሚያ ጭምር ነው። እውነታው ግን የሚከተለው ይመስለኛል፦
1) የሺዓ እና የሱኒ ለበላይነት የሚደረግ ፍትጊያ
ይህ ግጭት ጂኦ-ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊም ነው። ነቢዩ መሐመድ(ሰዐወ) ከሞቱ በኋላ ተተኪ ስላልተሰየመ ክፍፍሉ ከዚያ ተጀመረ።
* ሺዓዎች፦ የኸሊፋው አመራር በዓሊ በኩል ማለፍ አለበት ብለው ያምናሉ።
* ሱኒዎች፦ ሌላ ዓይነት የተተኪነት ቅደም ተከተልን ይከተላሉ።
ይህ የታሪክ ሁነት እስከ ካርባላ ጦርነት እና ለዘመናት የዘለቀ የኑፋቄ ፍትጊያ ፈጥሯል። ዛሬ ላይ፦
* ኢራን፦ የሺዓ ፖለቲካዊ ኃይል ማእከል ነች።
* ሳውዲ አረቢያ፦ ራሷን የሱኒው ዓለም መሪ አድርጋ ትቆጥራለች።
ስለሆነም ኢራን በቀጠናው ስትጠነክር፣ ይህ በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በመላው መካከለኛው ምስራቅ ለሚገኘው የሱኒ አመራር ትልቅ ፈተና ነው። በአጭሩ ጉዳዩ “ሙስሊም ከምዕራባውያን ጋር” የሚደረግ ጦርነት ብቻ ሳይሆን፣ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚደረግ ትግል ነው፦
* ኡማውን (የእስልምናውን ማህበረሰብ) ማን ይመራል?
* የእስልምናን ሁኔታ በበላይነት የሚወስነው ማን ነው?
* በቀጠናው ላይ የበላይነት የሚኖረው ማን ነው?
አሜሪካ እና እስራኤል የዚሁ ፍትጊያ የስሌት አካል ናቸው፤ ነገር ግን በቴህራን እና በሪያድ መካከል ያለው የቆየ ባላንጣነት ከሁሉም በላይ የገዘፈ ነው።
2) የሳውዲ አረቢያ የሰሞኑ ዝምታ አንድምታው
በይፋ ሳውዲ አረቢያ “ውጥረት አይባባስ”፣ “የእኛን መሬት ለጥቃት አትጠቀሙ” እና “ከዚህ ጉዳይ ውጡ” የሚሉ ዲፕሎማሲያዊ ጥንቃቄዎችን ታሳያለች። ነገር ግን በቴሌቪዥን የሚነገረው እና እውነተኛው ፖለቲካ አንድ አይደሉም።
ኢራን ብትዳከም ሳውዲ አረቢያ ለምን ትጠቀማለች?
ምክንያቱም የኢራን መዳከም፦
* የሺዓን ቀጠናዊ መስፋፋት ይገታል።
* በቀጠናው ያሉትን የኢራን ወኪል ኃይሎች ያዳክማል።
* የኃይል ሚዛኑን ወደ ሱኒ መሪዎች ይመልሳል።
በኢራን ውስጥ የመንግሥት ለውጥ ከመጣ፣ የቀጠናው የሥልጣን ተዋረድ ይቀየራል። ይህ ደግሞ አንዳንድ የአረብ አገራት በይፋ ከሚናገሩት በላይ የሚጠቀሙበት ጉዳይ ነው።
3) የአረብ አገራት “ዝምታ”
ሰዎች ችላ እያሉት ያለው ሌላው ነጥብ ይህ ነው። ጉዳዩ “የእስልምና ዓለም ከምዕራባውያን ጋር” የሚደረግ ጦርነት ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ በሁሉም የእስልምና አገራት ግዙፍ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ይታዩ ነበር።
ነገር ግን አስተውሉ፦
* በሳውዲ አረቢያ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (UAE)፣ በኳታር፣ በዮርዳኖስ፣ በግብፅ ወይም በባህሬን የታየ ሰፊ ተቃውሞ የለም።
* በአንጻሩ ተቃውሞዎች የታዩት በሕንድ አንዳንድ ክፍሎች፣ በፓኪስታን፣ በአንዳንድ ምዕራባውያን ከተሞች እና በሺዓ አብዛኛው በሆነባት ኢራቅ ውስጥ ነው።
ይህ ግጭት የእስልምናውን ዓለም ልዩነቱን ፍጥጥ አድርጎ የሚያሳይ ትልቅ ምልክት ነው። በአረብ አገራት ዋና ከተሞች የታየው “ዝምታ” በፖለቲካው ዓለም እንደ ድጋፍ ይቆጠራል።
ማጠቃለያ
ይህ “ክርስቲያኖች እና አይሁዶች ከሙስሊሞች ጋር” የሚደረግ ጦርነት ብቻ አድርጋችሁ ካሰባችሁት፣ ሁነቶቹን እየፈጠሩ ያሉትን የውስጥ ስንጥቆች ሳታዩ ቀርታችኋል ማለት ነው። ይህ ግጭት ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ፤ የነዳጅ ቁጥጥርና፤ እንዲሁም የመካከለኛው ምስራቅን ወደፊት በበላይነት ለመምራት የሚደረግ ጦርነት ነው ።
