March 6, 2026

በኦሮሚያ ክልል ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ ባለው ግጭት ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነሰ) ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን፤ “የጦር ወንጀሎች” ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸሙን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ። ሰራዊቱ በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ “በቡድን አስገድዶ መድፈር” የደረሰ ጾታዊ ጥቃት፣ “የወሲብ ባርነት”፣ “ከህግ ውጭ ግድያ”፤ “ስቅየት” እና “የሲቪል ንብረት ውድመት” መፈጸሙን ድርጅቱ ገልጿል።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይህን ያስታወቀው፤ ዛሬ አርብ የካቲት 27፤ 2018 ይፋ ባደረገው የምርመራ ሪፖርት ነው። የምርመራ ሪፖርቱ በኦሮሚያ ክልል፣ በቄለም ወለጋ ዞን፣ ሳዮ እና አንፊሎ ወረዳዎች፤ በሰላማዊ ሰዎች በተለይም በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የኦነሰ ታጣቂዎች ፈጽመዋቸዋል የተባሉትን “የጭካኔ ድርጊቶች” የሰነደ ነው።
የሰራዊቱ ታጣቂዎች “የጭካኔ ድርጊቶቹን” የፈጸሙት ከ2012 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት እንደሆነ የአምነስቲ የምርመራ ሪፖርት ያመለክታል። ኦነሰ ከመከላከያ ሰራዊት እና በአጋርነት ከተሰለፉ የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር እያደረገ ያለው ውጊያ የተጀመረው በ2011 ዓ.ም ነው።

በአራት ዓመት ውስጥ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ብቻ ላካተተው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምርመራ ሪፖርት፤ የቡድን አስገድዶ መድፈር የደረሰባቸው 10 ሰለባዎች ቃለ መጠይቅ እንደተደረገላቸው ድርጅቱ ገልጿል። በምርመራው ወቅት የጤና ባለሙያዎች ምስክርነቶች መቀበሉን እና የተጎጂዎቹን የህክምና መዝገቦች መፈተሹን አምነስቲ አስታውቋል።
ከተጎጂዎቹ ውስጥ ዘጠኙ በኦነሰ ተዋጊዎች ጥቃት እንደደረሰባቸው የገለጸው ድርጅቱ፤ አንዷ ከታጣቂዎች በተጨማሪ በመከላከያ ወታደርም ጥቃት የደረሰባት መሆኑን አመልክቷል። ከእነዚህ መካከል ሰባቱ ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት ከ18 ዓመት በታች እንደነበሩም ድርጅቱ አክሏል።
ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው 10 ሴቶች መካከል አምስቱ ለጾታዊ ባርነት መዳረጋቸውን በምርመራ ሪፖርቱ ላይ ያሰፈረው አምነስቲ፤ ሁለቱ በተፈጸመባቸው የጾታዊ ጥቃት ምክንያት ማርገዛቸውንም በሪፖርቱ ላይ አስፍሯል። የጥቃቱ ሰለባዎች “ለቀናት፣ አንዳንዴም ለሳምንታት የዘለቀውን አስከፊ ጥቃት” በዝርዝር ገልጸዋል ተብሏል።

ከጥቃቱ ሰለባዎች አንዷ የሆነችው ላሊስቱ* እና በወቅቱ የ12 ዓመት ታዳጊ የነበረችው ልጇ ሰቦንቱ*፤ እጆቻቸው ከዛፍ ጋር ታስረው ለሶስት ሳምንታት በአንድ ዋሻ ውስጥ በበርካታ የኦነሰ ታጣቂዎች መደፈራቸውን የአምነስቲ ሪፖርት በማሳያነት ጠቅሷል።
አሁን 17 ዓመት የሞላት ሰቦንቱ “በየዕለቱ፣ በቀን ሁለት ጊዜ፣ ከቀኑ 5 ሰዓት እና 12 ሰዓት አካባቢ ይደፍሩን ነበር። በየዕለቱ በዚህ ሰዓት ፍርሃት ይሰማኝ ነበር። ‘ትሞቻለሽ። ወደ ቤትሽ አትመለሺም’ ይሉኝ ነበር” ስትል ታጣቂዎቹ ያደረሱባትን የጭካኔ ተግባር ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተናግራለች።
የሰቦንቱ እናት በበኩላቸው “ለሶስት ሳምንታት 15 ወንዶች ልጄን እና እኔን ይደፍሩን ነበር። ተራ በተራ ነበር የሚያደርጉት” ሲሉ ድርጊቱ እንዴት ይፈጸም እንደነበር አስረድተዋል። አኒሳ* የተባሉ ሌላ የጥቃት ሰለባም የኦነሰ ታጣቂዎች፤ በተደጋጋሚ ከቤታቸው ወደ ጫካ እየወሰዷቸው በቡድን አስገድደው እንደደፈሯቸው መናገራቸው በሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።

በ2016 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በኦነሰ ተዋጊዎች “የወሲብ ባርያ” ተደርገው የነበሩት እኚህ ተጎጂ፤ ታጣቂዎቹ ወሲባዊ ጥቃቱን ያቆሙት ባጋጠማቸው የህክምና እክል እንደነበር አስረድተዋል። ተጎጂዋ ቃለ መጠይቁ በሚደረግላቸው ወቅት፤ በተፈጸመባቸው ወሲባዊ ጥቃት ምክንያት ነፍሰ ጡር እንደነበሩ አምነስቲ አመልክቷል።
ጥቃት የደረሰባቸው የተረፉት ሴቶች ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በሰጡት ቃል፤ በኦነሰ ተዋጊዎች የተደፈሩት “ባሎቻቸው፣ ወንድሞቻቸው ወይም አባቶቻቸው በመንግሥት ኃይሎች ውስጥ በመኖራቸው ምክንያት” እንደሆነ ተናግረዋል። ወሲባዊ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው በኋላ ቤታቸውን ለቀው እንዲሄዱ መገደዳቸውን የገለጹት ተጎጂዎቹ፤ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑት ቤታቸው መቃጠሉን አብራርተዋል።
አስሩም ተጎጂዎች፤ በተፈጸመባቸው ጥቃት ምክንያት ከደረሰባቸው አካላዊ ጉዳት ጋር እስካሁን ድረስ እየታገሉ መሆኑን መናገራቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል። ተጎጂዎቹ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች ምርመራን ጨምሮ የህክምና እርዳታ ለማግኘት ፍራቻ እንዳለባቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል። ፍራቻው የኦነሰ ታጣቂዎች በሚያደርሱባቸው የበቀል እርምጃ እና ጾታዊ ጥቃት በደረሰባቸው ሰዎች ላይ ባለው መገለል የመጣ እንደሆነም ተገልጿል።

የጥቃቱ ሰለባዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ እንዲቆሙ እንዲሁም ፍትህ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን እንደሚሹ አምነስቲ አስገንዝቧል። ከተጎጂዎቹ መካከል አንዷ “እነሱን [ወንጀለኞቹን] ማግኘት ከተቻለ፣ በእኔ እና በሌሎች ላይ የደረሰው ነገር እንዲቆም የሚያደርግ ፍትህ እንደሚገኝ ተስፋ አደርጋለሁ” ማለቷን ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ድርጅት ጠቅሷል።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ፤ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ተዋጊዎች የፈጸሟቸው “ተደጋጋሚ ጥቃቶች አሰቃቂ ብቻ ሳይሆኑ የጦር ወንጀሎች ሊሆኑ ይችላሉ” ብለዋል። የሰራዊቱ አባላት ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የፈጸሟቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፤ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እንዲመረምሩም ጠይቀዋል።
ዓለም አቀፍ እና የአፍሪካ የመብት ተቆጣጣሪዎች “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ወንጀለኞቹን ተጠያቂ ለማድረግ እና ተጎጂዎች እና ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ፍትህ እንዲያገኙ ለማድረግ በጭካኔ ድርጊቶቹ ላይ ፈጣን፣ ገለልተኛ እና ጥልቅ ምርመራ እንዲያካሂዱ መጠየቅ አለባቸው” ሲሉም ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ ያደረጋቸው በኦሮሚያ ውስጥ የተፈጸሙ የጭካኔ ድርጊቶች “ከተጠያቂነት ውጭ” በሆነ ድባብ ውስጥ የተፈጸሙ እንደሆኑ የገለጹት ቻጉታህ፤ ሁኔታውን በዝምታ መተው “የሲቪሎችን ስቃይ የሚያስቀጥል” እንደሆነ አመልክተዋል። በሲቪሎች በተለይም በሴቶች እና በልጃገረዶች ላይ የሚፈጸመው የጥቃት ዑደት መቆም እንዳለበት ያሳሰቡት ዳይሬክተሩ፤ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ሊወስዳቸው የሚገባቸውን እርምጃዎችም ጠቁመዋል።
“የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት፤ ሁሉም ተዋጊዎቹ ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግን እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግን እንዲያከብሩ ወዲያውኑ ትዕዛዝ መስጠት አለበት” ብለዋል ቻጉታህ። የሰራዊቱ አመራሮች “ጾታዊ ጥቃትን፣ ሌሎች የማሰቃየት ተግባራትን፣ ግድያ፣ አስገድዶ ማፈናቀል እና በዓለም አቀፍ ሕግ ስር የተመለከቱ ሌሎች ወንጀሎችን የፈጸሙ” ተዋጊዎችን እና ቡድኖችን “ትጥቅ ማስፈታት እና ማሰናበት አለባቸው” ሲሉም ዳይሬክተሩ ምክረ ሃሳባቸውን አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[ * አምነስቲ ኢንተርናሽናል በምርመራ ሪፖርቱ ላይ የጠቀሳቸው ተጎጂዎች፤ ማንነታቸው እንዳይታወቅ ስማቸው ተቀይሮ መቅረቡን አስታውቋል።]
