
7 መጋቢት 2026, 09:09 EAT
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ
ዶናልድ ትራምፕ ወሲባዊ ጥቃት እንዳደረሱባት የከከሰች ሴት የሰጠችውን ቃለ ምልልስ የያዘ የወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን የምርመራ ሰነድ ይፋ ተደረገ።
የተጎጂዋን ቃል ምልልስ ጭምቅ ሐሳብ የያዘ ሰነድ በአሜሪካው የወንጀል ምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ ሥር ነበር። የፍትሕ መሥሪያ ቤት ይፋ ካደረጋቸው ከወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር የተያያዙ ሰነዶች ውስጥ ተካትቷል።
ሰነዱ፤ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ከዚህ ቀደም ይፋ ያደረገው የኤፕስቲን ፋይል ውስጥ አለመኖሩ ጥያቄ አስነስቶ ነበር። ዴሞክራቶች፤ ሰነዱን ለመደበቅ ጥረት ተደርጓል ብለው መክሰሳቸውም ይታወሳል።
ሰነዱ “በድጋሚ የተካተተ” በሚል ዝርዝር ውስጥ እንደነበረ የገለጸው የፍትሕ መሥሪያ ቤት፤ ሰነዱ ይፋ ያልተደረገው “በስህተት” መሆኑን አስረድቷል።
ትራምፕን እና ኤፕስቲንን ከከሰሰችው ሴት ጋር በአውሮፓውያኑ 2019 የተደገ ቃለ ምልልስ በሰነዱ ውስጥ ይገኛል።
ትራምፕ ከኤፕስቲን ጋር በተያያዘ ማንኛውንም ወንጀል እንዳልፈጸሙ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ክሱን ያቀረበችው ሴት ለኤፍቢአይ እንደገለጸችው፤ በ1980ዎቹ ከትራምፕ ጋር ያስተዋወቃት ኤፕስቲን ነበር። በወቅቱ ከ13 እስከ 15 ዕድሜ ክልል ውስጥ ሳለች ሁለቱም ወሲባዊ ጥቃት እንደፈጸሙባት ከስሳለች።
ቃለ መጠይቁን ካደረገች በኋላ ኤፍቢአይ በድጋሚ አላነጋገራትም። ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባት በገለጸችበት ወቅት ላይ ትራምፕ እና ኤፕስቲን ስለመተዋወቃቸው ግልጽ አይደለም።
