March 7, 2026

በፌዴራል የስፖርት ልማት እና አስተዳደር የአዋጅ ረቂቅ ላይ የስፖርት ውርርድን በተመለከተ የሰፈረው ድንጋጌ፤ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከብሔራዊ ሎተሪ አገልግሎት ስልጣን ጋር “ግጭት የሚፈጥር ነው” የሚል ጥያቄ አስነሳ። ድንጋጌው የሀገሪቱ የስፖርት ልማት ከስፖርት ውርርድ በሚገኝ ገቢ እንዴት መደጎም እንዳለበት የሚያመለክት እንጂ፤ የሌሎች መስሪያ ቤቶችን ስልጣን የማይቃረን እንደሆነ ምላሽ ተሰጥቷል።

ይህ ምላሽ የተሰጠው፤ የአዋጅ ረቂቁን በተመለከተ ትላንት አርብ የካቲት 27፤ 2018 በፓርላማ በተካሄደ የህዝብ ውይይት መድረክ ላይ ነው። የውይይት መድረኩን የጠራው፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው። 

በውይይቱ ላይ ጥያቄ ከተነሳባቸው የረቂቅ አዋጁ ድንጋጌዎች መካከል “የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ውርርድ በሀገሪቱ ውስጥ ስለሚተዳደርበት ስርዓት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የአሰራር ስርዓት ይዘረጋል” የሚለው አንዱ ነው። በዚህ ድንጋጌ ላይ ጥያቄ ያነሱት የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ወ/ት ቤዛ ግርማ ናቸው።

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ የስፖርት ውርርድን ጨምሮ ሎተሪ ወይም የእድል ጨዋታ ስራ ፈቃድ የመስጠት፣ የመሰረዝ፣ የመቆጣጠር፣ የሎተሪ ጨዋታዎችን ለማካሄድ የሚያስፈልጉ የመሳሪያ አይነቶችን የመወሰን፣ ወደ ሀገር እንዲገቡ ፍቃድ የመስጠት እና የመቆጣጠር ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው ለገቢዎች ሚኒስቴር እንደሆነ አስታውሰዋል። 

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በጉዳዩ ላይ “ዝርዝር ህግ እስኪወጣ ድረስ” እነዚህን ስራዎች እንዲያከናውን ስልጣኑን “በውክልና” የሰጠው ለኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት እንደሆነም ገልጸዋል። የስፖርት ውርርድ  “የሎተሪ ስራ” መሆኑ በብሄራዊ ሎተሪ ማቋቋሚያ አዋጅ በግልጽ መደንገጉንም ያመለከቱት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ መስሪያ ቤቱ በተሰጠው ውክልና መሰረት ይህንን ስራ ሲያከናውን መቆየቱን አብራርተዋል።

በፌዴራል የስፖርት ልማት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ይህ ስራ ለባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር መሰጡትን የጠቆሙት ቤዛ፤ ይህ ማለት “አንድን ስራ ለሁለት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት መስጠት” እንደሆነ ተናግረዋል። ይህ መሆኑ ስራውን ለመቆጣጠር፣ ለማስፈጸም እና ተጠያቂነት ለማስፈን “አስቸጋሪ” እንደሚያደርገውም አስረድተዋል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የስፖርት ውርርድን ስራ መቆጣጠር ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መሰጠቱ፤ ተቋሙ “ከስራ ዘርፉ ውጭ እንዲሠራ መፍቀድ ነው” ሲሉም የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሞግተዋል። መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት የተሻለ የቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት የውጭ አማካሪዎችን ቀጥሮ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር እየሠራ መሆኑንም በማንሳትም፤ የአዋጅ ረቂቁ ከዚህ የሪፎርም ስራ ጋር የሚቃረን መሆኑን አስገንዘበዋል።

የስፖርት ውርርድን በተመለከተ ያለው የቁጥጥር ስርዓት ስራ በተለያዩ ተቋማት የሚመራ መሆኑ፤ ከገቢ አሰብሰብ አንጻር “ክፍተት የሚፈጥር” እንደሆነም ወ/ት ቤዛ አክለዋል።  ከዚህ ዘርፍ የሚገኝ ገቢ በቀጥታ እንደ ገንዘብ ሚኒስቴር ላሉ ተቋማት “ሙሉ ለሙሉ ፈሰስ ተደርጎ” በመንግስት ለታቀዱ “ትልልቅ” ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳ ላላቸው እንዲሁም ማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ እንደምታ ላላቸው ተግባራት ማስፈጸሚያነት መዋል እንዳለበትም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በማጣቀስ አብራርተዋል።

ለጥያቄ ምላሽ የሰጡት የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ፤ የስፖርት ውርርድን በተመለከተ “የሚመለከተቻው አካላትን በማሳተፍ የሚመራ የአሰራር ስርዓት” እንደሚዘረጋ በረቂቅ አዋጁ ላይ መስፈሩን ተናግረዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስፖርት ነክ ለሆኑ ጉዳዮች ህግ እና የአሰራር ስርዓት የመዘርጋት ስልጣን እንዳለውም ሚኒስትሯ አስታውሰዋል።    

የስፖርት ውርርድ ዘርፍ ከዚህ በፊት በተገቢው መንገድ ያልተመራ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ሸዊት፤ በአዋጁ ላይ የተካተተው ድንጋጌ የትኛውንም የአስፈጻሚ ተቋማት ስልጣን ለመጋፋት ታስቦ እንዳልሆነ አስረድተዋል። የእርሳቸውን ሃሳብ ያጠናከሩት የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ መክዩ መሐመድ፤ ረቂቅ አዋጁ ከገቢዎች ሚኒስቴር ስልጣን ጋር የሚጋጭ ድንጋጌ እንዳልያዘ ተከራክረዋል። 

የገቢዎች ሚኒስቴር ስልጣን “ከየትኛውም ተቋም የሚገኘውን ገቢ መሰብሰብ ነው” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ድንጋጌው በረቂቅ አዋጁ የተካተተው “የስፖርት ፈንድን” ለመደገፍ መሆኑን አስገንዝበዋል። የፌደራል ስፖርት ልማት ፈንድ በአዲሱ አዋጅ መሰረት የተቋቋመ ነው።

ስለፈንዱ የገቢ ምንጭ፣ ስለ ገቢ አሰባሰብ እና አከፋፈል፣ ስለ ድጋፍ መስክ እንዲሁም ስለ ፈንዱ አስተዳደር የሚመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮች የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወደ ፊት በሚያወጣው ደንብ እንደሚወሰን በአዋጅ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል። ሆኖም አቶ መክዩ በትላንቱ ውይይት ላይ፤ ከስፖርት ውርርድ የሚገኘው ገቢ “በፐርሰንት” ተሰልቶ የስፖርት ልማትን ለማሻሻል ሊውል እንደሚችል ጥቆማ ሰጥተዋል። 

የስፖርት ውርርድን የተመለከተው ድንጋጌው በአዋጅ ረቂቁ ላይ የተካተተው፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከስፖርት አኳያ ጉዳዩ የሚመለከተው በመሆኑ እንጂ የገቢዎች ሚኒስቴርን ገቢ የመሰብሰብ ስልጣን ለመጋፋት እንዳልሆነ አቶ መክዩ በድጋሚ አጽንኦት ሰጥተዋል። ከስፖርት ውርርድ ጋር በተገናኘ ያለውን “ከፍተኛ ሕገ-ወጥነት” መንግስት ገምግሞ ጥናት እያደረገበት መሆኑንም አስረድተዋል። 

Post

Ethiopia Insider

@ethiopiainsider

የስፖርት ውርርድን የተመለከቱ መመሪያዎች እና ደንቦች “ጥናትን መሰረት አድርገው ሊታገዱ እንደሚገባ”

የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር አሳሰበ። በስፖርት ውርርድ ምክንያት “ብዙ ቤተሰብ እየፈረሰ” መሆኑንም ገልጿhttps://ethiopiainsider.com/2024/13008/

“ለመንግስት ገቢ መሆን የነበረበትን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰወር” ወንጀል የተጠረጠሩ የስፖርት አወራራጅ ድርጅት ባለቤቶች እና ተባባሪዎቻቸው፤ ባለፈው ህዳር ወር በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጋቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት የ22 የስፖርት ውርርድ ድርጅቶችን ፈቃድ ማገዱን አስታውቆ ነበር።

የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ የስፖርት ውርርድ “ጎጂ ነው ወይም ቁማር ነው” በሚሉ አስተያየቶች ላይ በሀገር ደረጃ ተገምግሞ የሚወስን መሆኑን በትላንቱ ውይይት ላይ ተናግረዋል። ቴክኖሎጂን መካድ ወይም ዘርፉን ሙሉ በሙሉ “block ማድረግ” አሁን ባለው የዓለም ሁኔታ “የማይቻል” መሆኑን የገለጹት አቶ መክዩ፤ “ህግ እና አሰራር ስርዓት አበጅተንለት ሀገር ከእዚህ ዘርፍ እንዴት መጠቀም እንዳለበት ነው ማስቀመጥ [ያለብን]” ሲሉ ተደምጠዋል። 

የሀገሪቱ የስፖርት ልማት ከስፖርት ውርርድ በሚገኝ ገቢ እንዴት መደጎም እንዳለበት በአሰራር መመሪያ ማስቀመጥ አንደሚቻል ሚኒስትር ዴኤታው እምነታቸውን ገልጸዋል። “ስፖርትን በዘላቂነት እና በሁለንተናዊነት ለማሳደግ” የሚከናወን ማንኛውም ተግባር፤ “የስፖርት ልማት” ሊባል እንደሚችል በአዋጅ ረቂቁ የትርጓሜ ክፍል ላይ ተቀምጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)