መጨረሻ የተሻሻለው : March 10, 2026

 4 ደቂቃ ንባብ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1/ 2018 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣ በመሐል ሳይንት ወረዳ በሚገኘው ርዕሰ አድባራት ወታዕካ ነገሥት አትሮንሰ ማርያም ገዳም ላይ በተፈጸመ “የከባድ መሣሪያ ጥቃት” ስድስት ሰዎች መገደላቸውን እና ከ20 በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት መግረሱን የገዳሙ አስተዳዳሪ እና የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ገለጹ።

የርዕሰ አድባራት ወታዕካ ነገሥት አትሮንሰ ማርያም አስተዳዳሪ መክብብ አባ ገብረእግዚአብሔር ኃይለማርያም፤ ባሳለፍነው ቅዳሜ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. ከረፋዱ 3፡30 አካባቢ “የሞርታር ጥቃት እንደተፈጸመ” ተናግረዋል።

ጥቃቱ ሲፈጸም በቦታው የነበሩት የገዳሙ አስተዳዳሪ፤ “ሦስት [መሣሪያ] ተወረወረ። አንደኛው ከእኛ በታች አምባ ሥር አረፈ። ሁለተኛው አልፎ ሄደ። ሦስተኛው ደብሩ ላይ አረፈ” ብለዋል።

ከዕለቱ ቅዳሴ በኋላ በደረሰው ጥቃት የገዳሙ አበው መነኮሳት፣ ዲያቆናት እና የድጓ ተማሪ መገደላቸውን የገዳሙ አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

በተፈጸመው ጥቃት የተደገሉት መክብብ አባ ሞገስ ፍስሐ (የደብሩ ቀዳሽ)፣ ዲያቆን ከናፈርግብ አንዳርጌ (የዕለቱ ቀዳሽ)፣ እማሆይ ድንቄ ታከለ (የደብሩ ዐቃቢ)፣ ዲያቆን በለጠ አስቻለው (የዕለቱ ቀዳሽ)፣ ዲያቆን በአማን ገብረማርያም (የድጓ ተማሪ) እና ዲያቆን አይመረ መርሻ (የዕለቱ ቀዳሽ) መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከተገደሉት መካከል የሦስቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት የካቲት 29 ቀን 2018 ዓ. ም. እዚያው ገዳሙ ውስጥ ተከናውኗል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላ የአካባቢው ነዋሪ እና የዐይን እማኙ በበኩላቸው፤ ገዳሙ በደን የተከበበ በመሆኑ “ጫካ ውስጥ ታጣቂዎች ይኖራሉ በሚል ሆነ ተብሎ [የተፈጸመ] ነው ብዬ ነው የምገምተው” ብለዋል። ቅዳሜ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ. ም ጥቃቱ ከተፈጸመ አንስቶ በመሐል ሳይንት አካባቢ “በተከታታይ ሲተኮስ ነበር” ሲሉም አክለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተፈጸመው ጥቃት አባታቸው እንደተገደሉባቸው የገለጹት መሪ ጌታ ስሙር፤ “ከቤተ ክርሰቲያኑ ጩኸት ሲሰማ እየሮጥኩ ብሄድ እንደዛ ሆኖ አገኘሁ። ብዙ አስክሬን ተመለከትኩ. . . አስከሬኖቹን አንስቼ ለቤተሰቦቻቸው ሰጠሁ” ብለዋል።

የገዳሙ አስተዳዳሪ በበኩላቸው፤ የገዳሙ መሪ ጌታ፣ የድጓ አድራሽ እና በዕለቱ ለሙት ዓመት መታሰቢያ መባ ይዘው ወደ ገዳሙ የሄዱ አዛውንት ሴት “እግራቸው እና እጃቸው እንደተቆረጠ” የተናገሩ ሲሆን፤ የደብሩ ጥበቃ ደግሞ “ዐይናቸውን እና እግራቸውን” እንዳጡ አስረድተዋል።

በተጨማሪም “የመሣሪያ ፍንጣሪ የመታቸው” 21 ሰዎች መቁሰላቸውን አስተዳዳሪው ገልጸዋል። በወረዳው በሚገኙ እንዲሁም ደሴ ከተማ ባሉ ሆስፒታሎች ሕክምና ላይ እንደሚገኙ አክለዋል።

ከቅዳሴ በኋላ የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋዮች ለመባ በተሰባሰቡበት ወቅት ጥቃቱ እንደተፈጸመ እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም ካህናት፣ መነኮሳት፣ የአብነት ተማሪዎች እና ዲያቆናት እንደሆኑ ለዜና ምንጩ ተናግረዋል።

“አሁን ደብሩ ላይ ያለሁት እኔ ብቻ ነኝ። ከ100 ያላነሱ አገልጋዮች ነበሩ” ያሉት አባ ገብረእግዚአብሔር፤ የተቀሩት አገልጋዮች “እንደሸሹ” እና ሌሎች አገልጋዮች ደግሞ በሕክምና ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የገዳሙ አስተዳዳሪ የቤተ ክርስቲያኑ አዳራሽ፣ የቤተ ክርሰቲያኑ ቆርቆሮ እና የምዕመናን ቤት ላይም ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪ እና የዐይን እማኙ በጥቃቱ ከተገደሉት አንደኛው የባለቤታቸው አባት መሆናቸውን ገልጸዋል።

“ከቅዳሴ በኋላ ከጓሜዳ ወደ አትሮንሰ በተተኮሰ ሞርታር የስድስት ሰዎች ሕይወት አልፏል። 28 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል” ብለዋል። በጥቃቱ ሳቢያ የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች “ግማሾቹ እጃቸው ተቆርጧል፣ ግማሾቹ እግራቸው ተቆርጧል፣ ሌሎቹ ዐይናቸው ጠፍቷል” ሲሉም አክለዋል።

ከመካከላቸው ወደ 10 የሚጠጉት ሰዎች የደረሰባቸው “መጠነኛ ጉዳት” እንደሆነ ገልጸዋል። የተገደሉት ሰዎች አካላቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ስለነበር “ይሄ እከሌ ነው” ለማለት እንኳ እንዳልተቻለ የዐይን እማኙ አክለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው በሚገኝ “ጅምር ሆስፒታል” እና አጅባር በሚገኝ “ሙያ እና ቴክኒክ ተጠግተው” እንደሚገኙ የተናገሩት የዐይን እማኙ፤ “ከአጅባር ወጥተው፣ ዝቅ ብሎ ባለው ጓሜዳ የገጠር ቀበሌ ሆነው ሲያስወነጭፉ ነው የተተኮሰው” ብለዋል።

የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግሥት ኃይል በሚንቀሳቀሱበት በዚህ አካባቢ ቢቢሲ ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ በገለልተኛነት ለማረጋገጥ የሚችልበት ዕድል አለመኖሩን ገልጿል።

ይህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ላይ የተፈጸመው ጥቃት፤ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ በተፈጸመ አዲስ ጥቃት የ21 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትሎ የተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የካቲት 22 ቀን በሰጠው መግለጫ፤ በምሥራቅ አርሲ በተፈጸመ ጥቃት የ21 ንጹሐን ሰዎች ሕይወት በግፍ ማለፉን፣ በሕይወት የተረፉትም በታጣቂዎቹ መታገታቸውንና የደረሱበት አለመታወቁን፣ ከ10 የሚበልጡ አባውራዎች ቤትና ንብረት እንደተቃጠለ ከሀገረ ስብከቱ ሪፖርት እንደቀረበለት ገልጿል።

ጥቃቱ ከምንም ጉዳይ ጋር ንክኪ በሌላቸው ኦርቶዶክሳውያን ላይ መፈጸሙን የገለጸው ሲኖዶሱ፤ ይህን አስነዋሪ ድርጊት የፈጸሙት አካላትም ግድያውን በሃይማኖት ስም ይፈጽሙት እንጂ የሃይማኖት ስዎች ግን አይደሉም ብሏል፡፡

የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ተቀባይነት የሌለው አጸያፊ ድርጊት በመሆኑ በጽኑ ያወገዘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ገልጿል። አክሎም በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ያለው ሞትና መፈናቀልም የኦርቶዶክሳውያንን ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚጋፋ በመሆኑ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ ተከታትለው አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጡበት ቋሚ ሲኖዶስ በጥብቅ አሳስቧል፡፡

ፍርድን በመሻት የሚጮኸው የንጹሐን ደም ተገቢውን ፍትሕ ይፈልጋል ያለው መግለጫው፤ ይህን አስነዋሪ ድርጊት የፈጸሙት አካላት በሕግ እንዲጠየቁ፣ ወደፊትም ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት እንዳይጠፋ፣ የዜጐች ሀብትና ንብረት እንዳይወድም መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ተግባሩን እንዲያከናውን አሳስቧል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤትም በተናጠል ባወጡት መግለጫ ድርጊቱን በማውገዝ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

ከዚህ ቀደም በምስራቅ እና በምዕራብ አርሲ ዞኖች በተደጋጋሚ በተፈጸመ ጥቃት የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል። ለአብነም ጥቅምት ወር በምሥራቅ አርሲ ዞን በጉና፣ በመርቲ፣ በሸርካ እና በሆሎንቆ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ25 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ትናንት ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ አርሲ ዞን አስተዳደር በጉና፣ በመርቲ፤ በሸርካ እና በሆሎንቆ ዋቢ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች” ላይ “አሰቃቂ ግድያ” መፈፀሙን ገልጿል።

በዚህም “ጥቅምት 14 ለ15 ቀን 2018 ዓ.ም. በጉናና መርቲ ወረዳዎች 17 ክርስቲያኖች፣ ጥቅምት 17 ለ18 ቀን 2018 ዓ.ም. በሸርካ ወረዳ 3 ክርስቲያኖች እንዲሁም ጥቅምት 18 ለ19 ቀን 2018 ዓ.ም. በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ 5 ክርስቲያኖች በድምሩ በጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም. ብቻ 25 ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን አገራችንና ምድራችን ብለው በሰላም በተኙበት በድንገት ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን” አመልክቷል።

በዞኑ ሽርካ ወረዳ ሌላኛው ጥቃት የተፈጸመው ህዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም ሲሆን በትንሹ 9 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች በወቅቱ ገልጸዋል። በተመሳሳይ በዞኑ አሰኮ ወረዳ ጢጆ ቀበሌ በነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም በተፈጸመ አሰቃቂ ጥቃት የአካባቢውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ካህን ጨምሮ 6 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች መናገራቸው አይዘነጋም። በወቅቱ ጥቃቱን ተከትሎ የመኖሪያ ቤቶች መውደማቸውንና ከብቶች እና በጎችን ጨምሮ ከፍተኛ የንብረት ዘረፋ መፈጸሙንም የአካባቢው የሃይማኖት አባቶች ገልፀዋል።

እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል አርሲ እና ቄለም ውለጋ ዞኖች በህዳር ወር 2016 ዓ.ም  በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ሁለት ጥቃቶች 45 ሰዎች መገደላቸውን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል። ጥቃቱ ያነጣጠረው በአማኞች ላይ መሆኑን ነዋሪዎች እና ኃላፊዎች በወቅቱ ገልጸዋል፡፡አስ