March 10, 2026

መደበኛ ፓስፖርት ለሚፈልግ አመልካች፤ 50 ሺህ ብር በመክፈል “በቤት ለቤት ልዩ አገልግሎት” በሁለት ቀናት ውስጥ እንዲያገኝ የሚያስችል ደንብ በስራ ላይ ዋለ። ደንቡ ለ10 ዓመታት የሚያገለግል የኢትዮጵያን “ወርቃማ ቪዛ” (Golden Visa) በ10 ሺህ ዶላር ክፍያ ማግኘት የሚቻልበትን አሰራርም በውስጡ አካትቷል።
ይህንን አዲስ አሰራር ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገው፤ ከየካቲት 17፤ 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በስራ ላይ የዋለው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የክፍያ ደንብ ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዚህ ደንብ ላይ ውይይት አካሄዶ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ የወሰነው፤ ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ነበር።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ተቋም ለሚሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች የክፍያ ተመኖችን የሚዘረዝረው ይህ ደንብ፤ በአራት ዓመት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ እንዲሻሻል የተደረገ ነው። የአሁኑ ማሻሻያ የተደረገው፤ በሐምሌ 2016 ዓ.ም. የወጣው ደንብ አተገባበር ላይ “የታዩ ክፍተቶችን ለማሻሻል” እንዲሁም “የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት እንዲያፈሩ የተደነገገውን አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ” እንዲያስችል እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።
Post
በኢትዮጵያ የውጭ ዜጎች በሊዝ የመሬት ባለይዞታ እንዲሆኑ የሚፈቅድ አዋጅ በነገው ዕለት ለፓርላማ
ሊቀርብ ነው። የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረትን በባለቤትነት ለመያዝ ቢያንስ 150 ሺህ የአሜሪካ
ዶላር ሊመድቡ ይገባል።
https://ethiopiainsider.com/2025/15956/

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው አዲሱ ደንብ ላይ፤ በሁለት እና በአምስት ቀናት ውስጥ ለሚሰጡ የመደበኛ ፓስፖርት አገልግሎቶች ሲጠየቅ የነበረው ከ5 ሺህ እስከ 25 ሺህ ብር የሚደርስ ክፍያ ሳይለወጥ ቀጥሏል። ሆኖም መደበኛ ፓስፖርትን “በልዩ አገልግሎት” ለማግኘት የሚፈልጉ ተገልጋዮች ከ40 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር መክፈል እንደሚጠበቅባቸው በአዲሱ ደንብ ላይ ሰፍሯል።
በደንቡ ላይ “ፕሪሚየም” በሚል ለተሰየመው አገልግሎት 40 ሺህ ብር የሚከፍል ተገልጋይ፤ መደበኛ ፓስፖርትን በስድስት ሰዓት ውስጥ ማግኘት እንደሚችል ተቀምጧል። በ“ቤት ለቤት አገልግሎት” መደበኛ ፖስፖርት በሁለት ቀናት ውስጥ ማግኘት የሚፈልግ ተገልጋይ ደግሞ 50 ሺህ ብር መክፈል ይኖርበታል።
ከሐምሌ 2016 ጀምሮ በስራ ላይ በቆየው ነባሩ የክፍያ ደንብ፤ በ“ልዩ አገልግሎት” የሚሰጥ ባለ 32 ገጽ ፓስፖርት የክፍያ መጠን 35 ሺህ ብር ነበር። በተለያዩ ምክንያቶች የተቀመጠውን ይህን ክፍያ መፈጸም ለማይችሉ እና በጤና ችግሮች ምክንያት ተቋሙ ድረስ መምጣት ለማይችሉ ተገልጋዮች፤ መደበኛውን ክፍያ ብቻ በመክፈል በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱበት አሰራር ተዘርግቶ ተግባራዊ እንደሚሆን በነባሩ ደንብ ላይ ተመልክቶ ነበር።

አዲሱ ደንብ ይህንን አሰራር በሁለት ከፍሎታል። የመጀመሪያው አሰራር በ“ልዩ አገልግሎት” የተቀመጠውን ክፍያ መክፈል የሚችሉ ነገር ግን በጤና ችግር ምክንያት ተቋሙ ድረስ መምጣት የማይችሉ ተገልጋዮችን የሚመለከት ነው።
እነዚህ ተገልጋዮች ተገቢውን የልዩ አገልግሎት ክፍያ በመክፈል ባሉበት ቦታ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ በአዲሱ ደንብ ተደንግጓል። በአንጻሩ በጤና ችግር ምክንያት ወደ ተቋሙ መምጣትም ሆነ “የልዩ አገልግሎት ክፍያ” መፈጸም ለማይችሉ ተገልጋዮች፤ የመደበኛውን አገልግሎት ክፍያ ብቻ በመፈጸም ተቋሙ ባሉበት ቦታ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚደረግ በአዲሱ ደንብ ላይ ሰፍሯል።
በውጭ ሀገር ለሚሰጥ የመደበኛ ፓስፖርት አገልግሎት የሚጠይቁ ዜጎች፤ ለመደበኛው አገልግሎት መክፈል የሚጠበቅባቸው 200 ዶላር እንደሆነም በደንቡ ላይ ተቀምጧል። ፓስፖርታቸውን ለማሳደስ በበይነ መረብ (ኦንላይን) የሚያመለክቱ ተገልጋዮች በበኩላቸው 250 ዶላር መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

ከሀገር ውጭ ሆነው ፓስፖርት “በአስቸኳይ” ለማግኘት ለሚጠይቁ ዜጎች፤ በአዲሱ ደንብ የሚጠየቀው ክፍያ 300 ዶላር ነው። ይህንኑ የ“አስቸኳይ አገልግሎት” በበይነ መረብ ለሚጠይቁ ተገልጋዮች ክፍያው ወደ 350 ዶላር ከፍ ይላል።
የይለፍ ሰነድ (ሊሴፖሴ) ለማግኘት የሚያመለክቱ ተገልጋዮች 120 ዶላር መክፈል እንደሚገባቸው የደነገገው አዲሱ ደንብ፤ “ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ” ለሚጠይቁ ጥገኝነት አመልካቾች መደበኛ ክፍያ 500 ዶላር እንደሆነ አመልክቷል። በሁለት ቀን የሚያልቅ “የጥገኝነት ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ” የሚጠይቀው ክፍያ ደግሞ 1,000 ዶላር ነው፡፡
ለአምስት አመታት የሚቆይ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት የሚጠየቀው ክፍያ፤ ቀድሞ ከነበረበት በሶስት እጥፍ ጨምሮ በአዲሱ ደንብ 3,000 ዶላር ገብቷል። ይህንኑ አገልግሎት “በአስቸኳይ” ማለትም በአንድ እና በሁለት ቀናት ለማግኘት ከ4,000 እስከ 4,500 ዶላር እንዲከፍሉ ይጠየቃሉ።

በሐምሌ 2016 ዓ.ም. በወጣው ነባሩ ደንብ፤ ለአንድ ዓመት የሚያገለግል ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት የሚጠየቀው 500 ዶላር ብቻ ነበር። አዲሱ ደንብ ከመኖሪያ ፍቃድ ባሻገር ለ21 ዘርፎች የሚሰጥ የቪዛ አይነት እና የክፍያ መጠንን በዝርዝር ይዟል።
ለኢንቨስትመንት አመልካቾች የሚሰጥ ቪዛ ከአንድ ወር እስከ አምስት ዓመት ድረስ ባለ የቆይታ ጊዜ ተከፋፍሎ የክፍያ ተመኑ በደንቡ ላይ ተቀምጧል። እነዚህ አመልካቾች ለአንድ ወር 60 ዶላር፣ ለሶስት ወራት 150 ዶላር እንዲሁም ለስድስት ወራት ቪዛ 250 ዶላር ይጠየቃሉ።
አመልካቾቹ ለሶስት ዓመት ቪዛ ሁለት ሺህ ዶላር ክፍያ የሚጠየቁ ሲሆን፤ አምስት ዓመት የቆይታ ጊዜ ላለው ቪዛ ደግሞ አራት ሺህ ዶላር መክፈል እንደሚጠበቅባቸው በአዲሱ ደንብ ላይ ሰፍሯል። ቤት የሚገዛ የውጭ ዜጋ እስከ አምስት አመት የሚቆይ ቪዛ በተመሳሳይ ክፍያ በአራት ሺህ ዶላር ማግኘት ይችላል። ቪዛው የሶስት ዓመት ብቻ ከሆነ የክፍያ መጠኑ ሁለት ሺህ ዶላር እንደሚሆን በአዲሱ ደንብ ላይ ተቀምጧል።
Post
በ2018 በጀት ዓመት 3 ወራት ጊዜ ብቻ 860 ኢትዮጵያዊን እና የውጭ ዜጎች ሀሰተኛ የጉዞ ሰነድ
በማቅረባቸው ተይዘው በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጋቸውን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና
ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ።
https://ethiopiainsider.com/2025/16712/

· 736Views
ለ10 ዓመታት የሚያገለግል የኢትዮጵያን “ወርቃማ ቪዛ” የሚፈልጉ አመልካቾች በበኩላቸው፤ አገልግሎቱን ለማግኘት 10 ሺህ ዶላር መክፈል ይጠበቅባቸዋል። ይህ የክፍያ መጠን በወቅታዊው መደበኛ የባንክ ምንዛሬ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ነው።
የ“ወርቃማ ቪዛ” ባለቤቶች ቪዛቸውን በመደበኛ አገልግሎት ለማራዘም 10 ሺህ ዶላር እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ ለማራዘም ደግሞ 12,500 ዶላር መክፈል እንደሚገባቸው በአዲሱ ደንብ ላይ ሰፍሯል። እነዚህን አገልግሎቶች የሚሰጠው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት ሶስት ወራት ካገኘው 10.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ከቪዛ እና ተያያዥ አገልግሎቶች የሚሰበስበው እንደሆነ ባለፈው ህዳር አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
