DireTube 

የመሲሑ ልደት አብሳሪ፤ የአይሁዳውያን ጠበቃ የያኔዋ ፋርስ የአሁኗ ኢራን!!

እንደ መንደርደሪያ፤

በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ከ72 አርድዕት መካከል የሚመደበው ወንጌላዊው ሉቃስ- በመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ዘንድም፤ “ባለመድኃኒቱ/ሐኪሙ እና የታሪክ አዋቂው/መርማሪው” ቅዱስ ሉቃስ በስሙ የተመዘገበለትን የሉቃስ ወንጌልን እና ግብረሐዋርያትን (የሐዋርያት ሥራ) መጻሕፍትን እንደጻፈ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ሊቃውንት ያረጋግጡልናል።

ወንጌላዊው እና ታሪክ አዋቂው ቅዱስ ሉቃስ፤ በስሙ የተመዘገበውን የሉቃስ ወንጌልን ሲጽፍ እንዲህ በሚል ኃይለ-ቃል ነው የሚጀምረው።

“የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች “ታሪክን” በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ “በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ።”

(የሉቃስ ወንጌል ፩፤:፩-፬)

ቅዱስ ሉቃስ ከወንጌላዊነቱ ባሻገር “የታሪክ አዋቂ/መርማሪ” የሚለውን ስያሜ እንዲያገኝ ያደረገው ምክንያት አለ። ይኸውም የጌታችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን- ከልደቱ እስከ እርገቱ የተፈጸመውን ታሪክ የጻፈበት መንገድ ከሌሎቹ ወንጌላውያን የተለየ መሆኑ ነው። ቅዱስ ሉቃስ እያንዳንዱን ክስተት በጊዜ፤ በቦታ፤ የታሪኩ ተዋንያን የሆኑ ሰዎችን ስም፣ ዘመንና የትውልድ ስፍራ በጥንቃቄና ዘርዘር ባለ አኳኃን በመጻፉ ነው።

እናም ቅዱስ ሉቃስ በዘመኑ ስለሆነው ነገር በጥንቃቄ ታሪክን ለማዘጋጀት/ለመጻፍ እንደተጋው ሁሉ፤ እኔም እንደ ታሪክ ተማሪ- ታሪክን በጥንቃቄ በመመርመር በዚህ የእሳቤ ማሕቀፍ /Historical Framework “የሰው ልጅ/የዓለም ታሪክ የመለኮታዊው ዕቅድ አካል ነው” በሚል የሰሞኑን እስራኤልን እና የኢራን ጦርነት መነሻነት በታሪክ ሰረገላ አብረን ወደኋላ ጥቂት እንጓዝ ዘንድ ፈልጌ ነው።

“ታሪክን በቅጡ የመረመረ፤ ታሪክን ያወቀ፤ ከታሪክ የተማረ ብልህ ሰው፤ ላለፉት ትውልዶች ጓደኛ፤ ለዘመኑ ትውልድ መምህር፤ ለሚመጣው ትውልድ ደግሞ ነቢይ ነው፤” እንዲሉ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት።

የአይሁዳውያኑ ጠበቃ ኢራን/ፋርስ!!

ስመጥር ፈላስፋ እና የሂፖው ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ አውግስጢኖስ፤ “ታሪክ በቀላሉ ያለፈው ዘመን አይደለም፤ በጊዜ ውስጥ የተጻፈ የመለኮታዊ ዕቅድ አካል/ታሪክ ነው፤” ይለናል። በርግጥም የሰው ልጅ፤ የዓለም ታሪክ ከአምላክ/ከመለኮታዊው ዕቅድ ጋር ጥብቅ የሆነ ቁርኝት አለው።

ይህን እውነታ በደንብ ለመፈተሽ ያግዘን ዘንድ ሰሞኑን አሜሪካና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ጥቃት/ጦርነት መነሻ አድርገን ወደኋላ ተጉዘን ታሪክን ለመፈተሽ እንሞክር እስቲ፤

ከሰሞኑን አሜሪካና እስራኤል በጋራ በኢራን ላይ የተከፈቱት መጠነ ሰፊ ጥቃት የዓለማችን ትልቅ ዜና፤ በአንዳንዶች ዘንድ ደግሞ 3ኛው የዓለም ጦርነት መባቻ ይሆን እንዴ?! በማለት እያንዳንዱን ክስተት በጥንቃቄ እየተከታተሉት ይገኛሉ።

በነገራችን ላይ፤ አሜሪካና እስራኤል በጋራ በጥንታዊቷ አገር ኢራን ላይ የከፈቱን ጦርነት እንዲህ ሲሉ ነው የገለጹት፤

“The goal of these strikes is to remove the existential threat posed by the terrorist regime in Iran.”

በተቀራኒው የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚ/ር ደግሞ፤

The strikes were “a pre-planned and unprovoked act of armed aggression against a sovereign state.” በማለት የዓለም አቀፉን ሕግ የጣሰ ጥቃት መሆኑ በማስረገጥ አምርረው ኮንነውታል።

“እስራኤል ከምድረ-ገጽ፤ ከካርታ ላይ መፋቀ አለባት፤” የምትለው ኢራን የዛሬን አያድርገውና በጥንቱ ዘመን የአይሁዳውያኑ ጠበቃ ነበረች። የዛሬዋ ኢራን/ፋርስ በአምላክ መለኮታዊ ዕቅድ መሠረት አይሁዳውያንን ከባቢሎን መንግሥት ባርነትና ግዞት ነጻ ያወጣች የታላቅ ሥልጣኔ እና የገናና ታሪክ ባለቤት ናት።

እንዴት የሚለውን በደንብ ለማየት ያስችለን ዘንድ ከቅዱስ መጽሐፍ በማጣቀስ አሁንም ጥቂት አብረን እንዝለቅ።

እስራኤላውያን በበደላቸውና በኃጢአታቸው ምክንያት የአባቶቻቸውን አምላክ በማሳዘናቸው የተነሳ ከምድራቸው ተነቅለው፤ ተግዘው በባቢሎን ምድር ለ70 ዓመታት በባርነት ቆይተዋል። መጽሐፍ እንዲህ እንዲል፤

“እኔ ግን በደሉን ለያዕቆብ፥ ኃጢአቱንም ለእስራኤል እነግር ዘንድ በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይልንና ፍርድን ብርታትንም ተሞልቻለሁ።

ፍርድን የምትጠሉ ቅን ነገርንም ሁሉ የምታጣምሙ እናንተ የያዕቆብ ቤት አለቆችና የእስራኤል ቤት ገዦች ሆይ፥ እባካችሁ ይህን ስሙ።

ጽዮንን በደም፥ ኢየሩሳሌምንም በኃጢአት ይሠራሉ።

አለቆችዋ በጉቦ ይፈርዳሉ፥ ካህናቶችዋም በዋጋ ያስተምራሉ፥ ነቢያቶችዋም በገንዘብ ያምዋርታሉ፤ ከዚህም ጋር። እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ክፉ ነገር ምንም አይመጣብንም እያሉ በእግዚአብሔር ይታመናሉ።

ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌምም የድንጋይ ክምር ትሆናለች፥ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል፤” እንዲል።

(ትንቢተ ሚክያስ ምዕ. ፬)።

አይሁዳውያኑ አያልቁ እልቂትን አልቀው፤ ጎበዛዝቶቻቸው በሰይፍ ወድቀው፤ ደናግላውያኑ በሃፍረት አንገታቸውን በአደባባይ ደፍተው… እንደ ነፍሳቸው የሚሳሱለትም ቤተ-መቅደሳቸው ፈርሶ፤ በሕይወት የተረፉት በምርኮ ወደ ባቢሎን ምድር ተግዘው ነበር።

አይሁዳዊው ነቢዩ ኤርምያስ ይህን የሕዝቡን ግዞት፤ የወገኖቹን ሰቆቃ፣ ምሬትና መከራ – “ሰቆቃወ ኤርምያስ” በሚለው መጽሐፉ እንዲህ ከትቦታል፤

“እስራኤል አለቀሰች፥ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ በምድርም ላይ ጨለሙ፤ የእናቶች ጩኸት ከፍ ከፍ ብሎአልና፤ ሽማግሌዎች ዝም ብለው በመሬት ላይ ተቀምጠዋል፤ ትቢያን በራሳቸው ላይ ነሰነሱ፥ ማቅም ታጠቁ፤ ደናግላን ራሳቸውን ወደ ምድር አዘነበሉ።

ወደ ዓመት በዓልም የሚመጣ የለምና የጽዮን መንገዶች አለቀሱ፤ በሮችዋ ሁሉ ፈርሰዋል ካህናቶችዋም እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ ደናግሎችዋም ተጨነቁ፤ እርስዋም በታላቅ ምሬት፤ ስብራት ውስጥ አለች።

ሴቶችን፥ በከተሞቿም ደናግልን አጐሰቈሉ፤ አለቆች በእጃቸው ተሰቀሉ፤ በመቅደሱ የካህናት፣ በአደባባይም የሽማግሌዎች ፊት አልታፈረም።

ጕልማሶች ወፍጮን ተሸከሙ፥ ልጆችም ከእንጨት በታች ተሰናከሉ። ሽማግሌዎች ከአደባባይ፥ ጕልማሶች ከበገናቸው ተሻሩ። አቤቱ፥ ተጨንቅናል፥ አንጀታችም ታውኮብናልና፤ ተመልከት፤ ልባችን በውስጣችን ተገላበጠብን፤ በሜዳ ሰይፍ ልጆቻችንን አጠፋ በቤታችንም ሞት አለ።

ድንጋጤና ቍጣ፥ ጥፋትና ቅጥቃጤ ሆነብን። ስለ ወገናችን ሴት ልጆች ቅጥቃጤ ዓይንምቼ የውኃ ፈሳሽ አፈሰሰች። እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጐበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይኖቼ ሳያቋጡ፤ ዝም ሳይሉ እንባን ያፈሳሉ።

የልባችን ደስታ ቀርቶአል፤ ዘፈናችን ወደ ልቅሶ ተለውጦአል፤ ዓይናችን በእንባ ደከመች፥ አንጀታችንም ታወከ፤ ስለ ወገኖቼ ቅጥቃጤ ጉበቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ።

እስራኤል ሆይ፥ ምን እመሰክርልሻለሁ? በምንስ እመስልሻለሁ? አጽናናሽ ዘንድ በምን አስተካክልሻለሁ? ስብራትሽ እንደ ባሕር ታላቅ ነውና፤ የሚፈውስሽ ማን ነው?! ነቢያቶችሽ ከንቱና ሐሰተኛ ራእይ አይተውልሻል፤ ምርኮሽንም ይመልሱ ዘንድ በደልሽን አልገለጡም፤ ከንቱና የማይረባ ነገርንም አይተውልሻል።

አቤቱ የሆነብንን አስብ…!!”

በታላቅ ምሬት ውስጥ ሆነው ወደ ምድራቸው የሚመለሱበትን ዘመን በናፍቆትና በሰቀቀን ይጠባበቁ የነበሩትን አይሁዳውያን- የአባቶቻቸው አምላክ ሊታደጋቸው ወደደ። እናም ከዚህ የባርነት የፅልመት ዘመን ይታደጋቸው ዘንድ የፋርስ ንጉሥ የሆነውን ቂሮስን አስነሳላቸው።

ቂሮስ የመለኮት በቀል ማስፈጸሚያ በትር . . . የሰው ልጆች የመውደቅና የመነሳት ታሪክ ጉዞ ትልቅ ማሳያ!!

ይቀጥላል . . .

(ዲያቆን ተረፈ ወርቁ)