
በአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣ መሐል ሳይንት ወረዳ የምትገኘው ጥንታዊቷ ታዕካ ነገሥት አትሮንስ ማርያም ገዳም የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በመንግሥት ኃይሎች በተፈጸመ የከባድ መሣሪያ ጥቃት አበምኔቱን ጨምሮ 6 የገዳሙ አገልጋይ አባቶችና እናቶች ሥርዓተ ቅዳሴ ሲወጡ የተገደሉ ሲኾን፣ 28 የሚኾኑ አባቶችና ምዕመናን ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። እንዲኽ ዓይነት የሃይማኖት አባቶችንና ቅዱሳት መካናትን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ከድግግሞሹና ኹኔታው በመነሳት በዓላማ የሚፈጸም ነው ብለን እንድናምን ተገደናል። ትብብራችን ድርጊቱን በጽኑ እያወገዘ ለሞቱት እረፍተ ነፍስን ለአካባቢው ማኅበረሰብም መጽናናትን ይመኛል።
በዚኹ አጋጣሚ ተመሳሳይ የግዴለሽነት ድርጊት ጥንታዊቷ ርእሰ አድባራት ወገዳማት ተድባበ ማርያም ቤተክርስቲያን ላይ ያነጣጠረ የከባድ መሣሪያ ጥቃት እየተፈጸመ እንዳለ መረጃ ደርሶናል፤ ይኽ በአስቸኳይ እንዲቆም እናሳስባለን።
*****
በሌላ በኩል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ትናንት ማክሰኞ የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ማለትም ከጋጮባባ ወረዳ- ማዞዶይሳ ቀበሌ፣ ላካ፣ ቦንኬ ወረዳ- የላ ቀበሌ፣ ካምባ ዙሪያ ወረዳ- ባልታ ቀበሌዎች
በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በደረሰ የናዳና የጎርፍ አደጋ የ30(ሠላሳ) ያኽል ወገኖቻችን ሕይወት አልፏል።
ትብብርችን በእልቂቱ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ፣ ለሞቱት እረፍተ ነፍስን፣ ለተጎዱ ማገገምንና ለአካባቢው ማኅበረሰም መጽናናትን ይመኛል። መላው ኢትዮጵያውያንም ተጎጂዎችን በማቋቋም እንዲረባረቡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
ትብብር ለኢትዮጵያአንድነት- ለኢትዮጵያ
መጋቢት ፪ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
