March 11, 2026

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በተከሰተ የመሬት ናዳ 35 ሰዎች ሲሞቱ፤ የ63 ሰዎች ደብዛ መጥፋቱን የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በመሬት ናዳው ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችልም ጽህፈት ቤቱ ስጋቱን ገልጿል።
የመሬት ናዳው የተከሰተው፤ በጋሞ ዞን ደጋማ አካባቢዎች ከትላንት ማክሰኞ መጋቢት 1፤ 2018 በጣለ “ከባድ ዝናብ” ምክንያት እንደሆነ የዞኑ አስተዳደር ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። የዞኑ አስተዳደር ዛሬ ባሰራጨው መረጃ፤ በጎርፍ እና በመሬት ናዳ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 35 መድረሱን አመልክቷል።
በዞኑ ስር የሚገኘው የጋጮ ባባ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዛሬ ጠዋት በፌስቡክ ገጹ ባጋራው መረጃ፤ ማዞ ዶይሳ እና ላካ በተባሉ ቀበሌዎች በደረሰ የመሬት ናዳ በአጠቃላይ የ96 ሰዎች ደብዛ መጥፋቱን ገልጿል። የመሬት ናዳው ሰለባ ከሆኑት መካከል “የሰላሳ ሶስቱ አስክሬን መገኘቱንም” የገለጸው ጽህፈት ቤቱ፤ የሟቾቹን አስከሬን የማፈላለግ ስራው መቀጠሉንም አስታውቋል።

በጋጮ ባባ ወረዳ፣ ማዞ ዶይሳ ቀበሌ የመጀመሪያው የመሬት ናዳ የተከሰተው በትላንትናው ዕለት ጠዋት አራት ሰዓት ገደማ ነበር። በዚህ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ የአራት ሰዎችን አስክሬን ለመፈለግ ወደ ቦታው ባቀኑ ሰዎች ላይ በድጋሚ የተከሰተው የመሬት ናዳ ለበርካቶች መሞት ምክንያት ሆኗል ተብሏል።
የጋሞ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ማኑቆ፤ በወረዳ በኩል የተገለጸውን የሟቾች ብዛት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ከተለያዩ ወረዳዎች መረጃዎች ለጽህፈት ቤታቸው እየደረሱ መሆኑንም የተናገሩት ኃላፊው፤ በጋጮ ባባ ወረዳ በኩል የተገለጸው “የተጠቃለለ መረጃ” እንዳልሆነ አስረድተዋል።
የዞኑ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት መረጃዎቹን እያጣራ እና እየገመገመ መሆኑን የገለጹት አቶ መስፍን፤ ትክክለኛው የሟቾቹ ቁጥር አሁን ከተገለጸው ከፍ ሊል እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል። የጋሞ ዞን አስተዳደር ዛሬ ረፋዱን ባሰራጨው መረጃ፤ “ጉዳቱ ሰፊ በመሆኑ የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገምቷል” ብሏል።

በጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ደምሴ አድማሱ የተመራ የዞኑ ከፍተኛ ልዑክ፤ ከፍተኛ የሞት መጠን ወደ ተመዘገበበት ጋጮ ባባ ወረዳ በዛሬው ዕለት አቅንቷል። የልዑኩ አባላት አደጋው በተከሰተበት ቦታ ተገኝተው ሃዘናቸውን እንደገለጹ እና የሟቾችን ቤተሰቦች እንዳጽናኑ የወረዳው እና የዞኑ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤቶች ያሰራጯቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
