March 12, 2026

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጋሞ ዞን በደረሰው የመሬት ናዳ አደጋ በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን ባጡበት የጋጮ ባባ ወረዳ፤ ከአንድ ቤት እስከ “አምስት ሰዎች” መሞታቸውን የወረዳው አስተዳዳሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በአደጋው ከሞቱት ውስጥ እስካሁን ድረስ የ70 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል።
በጋሞ ዞን ባለፈው ሰኞ የካቲት 30 ምሽት እና በማግስቱ መጋቢት 1 “ከባድ ዝናብ” መጣሉን ተከትሎ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ፤ በአራት ወረዳዎች “ከፍተኛ ጉዳት” አድርሷል። አደጋው ከተከሰተባቸው ወረዳዎች መካከል፤ ከፍተኛው የሰዎች ሞት እና ጉዳት የተመዘገበው በጋጮ ባባ ወረዳ ነው።
በወረዳው ማዞ ዶይሳ እና ላካ በተባሉ ቀበሌዎች በደረሰ የመሬት ናዳ ደብዛቸው የጠፋ ሰዎች ቁጥር 120 መድረሱን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብሩክ ቡጻ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአደጋው እስካሁን የደረሱበት ካልታወቁ ሰዎች መካከል እስከ ዛሬ ሐሙስ ከቀኑ 10 ሰዓት ድረስ የ58 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

“ከአንድ ቤተሰብ አራትም፣ ሶስትም፤ ሁለትም፣ አምስትም የሞተ አለ” ያሉት አቶ ብሩክ፤ ከአንድ ግለሰብ በስተቀር በአደጋው ሰለባ የሆኑት ሁሉም የማዞ ዶይሳ ቀበሌ ነዋሪዎች እንደነበሩ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። በአደጋው ደብዛቸው የጠፋ 62 ሰዎችን የማፈላለግ ስራ አሁንም መቀጠሉን የተናገሩት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ፤ የሟቾች አስከሬን ተቆፍሮ የወጣው በአካባቢው ማህበረሰብ ትብብር እንደሆነ አብራርተዋል።
በአደጋው ለተፈናቀሉ ሰዎች ከፌዴራል፣ ከክልል እና ከዞን አካላት ሰብዓዊ ድጋፎች እየቀረቡ ቢሆንም፤ አስክሬን ቆፍሮ ለማውጣት ከሶስቱ አካላት እስካሁን የተላከ ግብረ ኃይል አለመኖሩንም አቶ ብሩክ አመልክተዋል። በጋጮ ባባ ወረዳ የመሬት ናዳ የተከሰተው በሰባት ቀበሌዎች ውስጥ መሆኑን የገለጹት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ፤ በአደጋው ከሶስት ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውንም ጠቁመዋል።
በጋሞ ዞን አራት ወረዳዎች በአጠቃላይ የተፈናቀለው ሰው ብዛት 3,480 እንደሆነ የደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይለማሪያም ተስፋዬ በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል። የደቡብ ክልል መንግስት በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ እንዲሁም የጤና አገልግሎት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ኃላፊው አስረድተዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፤ በጋሞ ዞን ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በዛሬው ዕለት በስፍራው በመገኘት አጽናንተዋል። ከርዕስ መስተዳድሩ ጋር የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ወ/ሮ አለምጸሐይ ጳውሎስ እና የፌደራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማሪያምም አብረዋቸው ወደ አካባቢው በመጓዝ ሃዘናቸውን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
