ቦርከና ደስክ

World Wide Travel Group

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
መጋቢት3፣2018

መግቢያ

የዛሬ 130 ዓመት በአፄ ምኒልክና በውድ ባለቤታቸው በእተጌ ጣይቱ ብጡል የሚመሩት ጀግኖች እናቶቻችንና አባቶቻችን በወራሪው የኢጣሊያን ኃይል ላይ የተቀዳጁት ድል ለህብረ-ብሄር መሰረት፣ ወይም ኢትዮጵያን እንደ አገር በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት ወይም ወደ ዘመናዊነት ለማሽጋገር መሰረት እንደጣለ ይታወቃል። የዛሬ 130  ዓመት ወራሪው የኢጣሊያን ኃይል ቢሳካለትና የመጨረሻ መጨረሻም ጠቅላላውን ኢትዮጵያን በመቆጣጠር የቅኝ ግዛት ቢያደርጋት ኖር በልዩ ልዩ መልኮች የምትገለጽና የህዝባችንም መለያ የሚሆኑ ባህሎችን መገንባት ባልቻልን ነበር። ባህልም ሲባል በስነ-ጽሁፍ፣ በሰዋስውና ራሱን በቻለ ፊደል የሚገለጽ፣ ልዩ ልዩ የምግብና የመጠጥ ዐይነቶችን በመፍጠር የጠቅላላው ህዝብ መገለጫ ማድረግ፣ የሃይማኖት መዳበርና ልዩ ዐይነት የሙዚቃ አቀኛኘት መፍጠርና ማስፋፋት…ወዘተ. እነዚህ ሁሉ ነገሮች በሙሉ ወደድንም ጠላንም ራሳቸውን የቻሉ የዕድገት ምልክቶችና ህዝባችንንም ያስተሳሰሩ ናቸው። ስለሆነም አፄ ምኒሊክና የተቀሩት ጀግኖች እናቶቻችንና አባቶቻችን በአደዋ በወራሪው የጣሊያን ኃይል ላይ የተቀዳጁት ድል ህዝቡን በማስተሳሰርና የአንድነትን መንፍስ በማነቃቃት ለዘመናዊቱ ኢትዮጵያ በር በመክፈት ልዩ ዐይነት የባህል ዕምርታ እንዲዳብር ያደረገ ነው ማለት ይቻላል። ከዚያ በኋላ ስልጣንን የያዙት ሌሎችን አገዛዞች እረሰተን የአፄ ኃይለስላሴን አገዛዝ ብንወስድ በዚህ ድል ላይ በመመስረት ነው ኢትዮጵያን እንደ ህብረ-ብሄር ለመመስረት የሚያስችል መሰረት መጣልና ማስፋፋት የቻሉት። 

ይህ ዐይነቱ አንድን አገር የመመስረት ወይም ህብረ-ብሄርን የመገንባት አካሄድ በሌሎች አገሮችም፣ በተለይም በአውሮፓ ምድር ውስጥም የተከናወነና የመጨረሻ መጨረሻም ለካፒታሊዝም ዕድገት በር የከፈተ ነው ማለት ይቻላል። የአውሮፓውን የህብረ-ብሄር አመሰራረት ስንመረመር ከኢትዮጵያው ለየት የሚያደርገው በከፍተኛ ደረጃ በኃይል ላይ የተመሰረተና የመጨረሻ መጨረሻም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሲፈጠርና ሲስፋፋ ለኢንዱስትሪ አብዮት በር በመክፈቱ ነው። ይሁንና ግን በተለያዩ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተሰበጣጥሮ ይኖር የነበረውን ህዝብ እንዲሰባሰብና በንግድ አማካኝነት እንዲገናኝ ቀደም ብለው መንደሮችና ከተማዎች በአማረ መልክ ተገንብተዋል፤ እንዲሁም የስራ-ክፍፍልም ዳብሯል። ይህም ለካፒታሊዝም ማደገ መሰረት ሊሆን ችሏል። ከዚህም በላይ  የተገለፀላቸው ኃይሎች ወይም ምሁራን ብቅ  በማለታቸውና ከፍተኛ የጭንቅላት ስራ በመስራታቸው  ከሞላ ጎደል ፖለቲካዊ አስተሳሰብ እንዲዳብርና ለዘብ ያለ አካሄድም እንዲለመድ መስመር ለማሲያዝ ተሞክሯል። ይሁንና ግን በአውሮፓ ምድር ውስጥ እስከ አስራ-ዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ድረስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢስፋፉምና ፖለቲካዊ አስተሳሰብ እንዲዳብርና ስልጣንን የሚጨብጡ ኃይሎች በአርቆ-አሳቢነት አገሮቻቸውን እንዲያስተዳድሩ መስመር ለማሲያዝ በተገለፀላቸው ምሁራን ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም የአገዛዞች ዋናው ዘዴ ጦርነት ማካሄድና ህዝቡን ማስጨነቅ ነበር። ይህ ሁሉ ከፍተኛ የጭንቅላት ስራ ቢሰራም፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂም ቢዳብሩም በ19ኛውና በ20ኛ ክፍለ-ዘመን ስልጣንን የያዙት የአውሮፓ የገዢ መደቦችና በመዳበር ላይ ይገኝ የነበረው የከበርቴው መደብ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጸውን አዲሱን ስልጣኔ ወደ ሌሎች አገሮች፣ ለምሳሌ ወደ አፍሪቃ አህጉር ከማስፋፋት ይልቅ የበላይነት ስለተሰማቸውና በዘረኝነት መንፈስ በመነሳሳት የአፍሪቃን አሁጉር፣ ጥቁሩን ህዝብ ወደ ቅኝ-ግዛትነት መለወጥ ፈለጉ። ይህም ስለተሳካላቸው እስከዚያን ጊዜ ድረስ በማቆጥቆጥ ላይ ይገኝ የነበረውን የአፍሪካን ስልጣኔ ድምጥማጡን ማጥፋት ቻሉ። ቀስ በቀስ እያለ እየዳበረ የመጣውን የስራ.-ክፍፍልልና ንግድ አወደሟቸው። ባጭሩ አፍሪካን የጥሬ-ሀብት አምራች አህጉር በማድረግ ዕድገቷን ለማቀጨጭ ቻሉ። ከዚህም በላይ የበላይነት የተሰማው የካፒታሊስቱ ዓለም አንደኛውንና የሁለተኛውን ዓለም ጦርነቶች በመቀስቀስ በራሱ አህጉር ውስጥ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ህይወቱ እንዲጠፋ  ተደረገ። ይህም ማለት አንድ አገዝዛና ህዝብ መንፍሱ በሚገባ እስካልታነፀ ድረስ የግዴታ ስራው ሁሉ ተንኮል መሸረብና ጦርነትን መቀስቀስ ይሆናል ። ከዚህ ዐይነቱ ዕጣም እኛም በመማራችንና በዚህ ዐይነቱ መጥፎ መንፈስ እንድንታነፅ በመደረጋችን ከሃምሳ ዓመታት በላይ የፈጀ ጦርነት በማካሄድ አገራችንን በማፈራረስና ህዝባችንን መቆሚያና መቀመጫ በማሳጣት የሰለጠን ስራ እንዳይሰራ አግደነዋል።

ወደ አውሮፓ ስንመጣ  በአጭሩ በአውሮፓ ምድር ውስጥ መረጋጋት ሊመጣና የፓርሊሜንተሪ ዲሞክራሲ ሊለመድ የቻለውና፣ ካፒታሊዝምም ዕምርታን በማግኘት ዓለምን ለመቆጣጠር የቻለው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ነው ማለት ይቻላል። ይህንን ዐይነቱን የህብረ-ብሄረ አገነባብ ውስብስብና ጠመዝማዛ ሂደት ለመገንዘብ ያልቻሉና የማይችሉ በፖለቲካ ስም የሚንቀሳቀሱ የአገራችን ተዋንያን ከፍተኛ ጭንቅት በመፍጠርና ጦርነትን ማካሄድ ዋናው ተግባራቸው በማድረግ በአደዋ ላይ የተገኘውን አኩሪ ድል ከፍተኛ አደጋ ላይ ጥለውታል ማለት ይቻላል። ለተሟላና አገራችንንም ሊያስከብር የሚችል በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለፅ ዕድገት ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ፈጥረዋል ማለት ይቻላል። በተለይም ባለፉት 37 ዓመታት በተከታታይ ስልጣንን የተቀዳጁት የህወሃት አገዛዝ፣ ካለፉት ስምንት ዓመታት ደግም ስልጣንን የተቀዳጀው በኦሮሞ ብሄረስብ ስም የሚነግደው የአቢይ አህመድ አገዛዝና ግብረ-አበሮች የህብረ–ብሄርን አመሰራረትና ቀስ በቀስ የግንባታ ሂደት ባለመገንዘባቸው የውጭ ኃይሎች መሳሪያ በመሆን አገራችንና ህዝባችንን የእርስ በርስ መራኮቻ መድረክ ለማድረግ በቅተዋል። ሳይገባቸው በውጭ ኃይል ተፅዕና ተግባራዊ ያደረጉት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ህዝባችንን  ከድህነት ከማውጣትና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ከማድረግ ይልቅ ወደ ድህነት ዓለም ውስጥ ገፍትረውታል። በዚህም ምክንያት የተነሳ የዛሬ 130 ዓመት አደዋ ላይ የተገኘው ድል በከፍተኛ ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ ተደርጓል። 

Advertise here _ borkena

                በአገራችን ምድር የህብረብሄር ግንባታ አመሰራረትና የተሰናከለ የዘመናዊነት ሂደት

በተለያዩ ጊዜያት ለማሳየት እንደሞከርኩት አፄ ምኒልክ በአደዋ ላይ ድል ከተቀዳጁ በኋላ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችሉ አንዳንድ ነገሮችን ተግባራዊ ቢያደርጉም በጊዜው የነበረው ያልተጠናከረው ኃይልና በተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶችም ውስጥ በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጽ ይሁንና ለተሟላ የአገር ግንባታ የሚያገለግል የዕደ-ጥበብና የንግድ እንቅስቃሴ ባለመኖሩና መንደሮችና ከተማዎችም ስርዓት ባለውና የህዝቡን አስተሳሰብ ለመሰብሰብ በሚያስችል መንገድ ባለመገንባታቸው አፄ ምኒሊክ ስልጣንን ሲይዙና ግዛታቸውን ሲያስፋፋ ከበፊታቸው ከፍተኛ ዕንቅፋት ተደቅኖ ነበር። ይህም ማለት አፄ ምኒልክ ኢትዮጵያን እንደ አንድ ህብረ-ብሄር ወይም አገር ለመገንባት ሲነሱና አንዳንድ መሰረቶችን ሲጥሉ ከዜሮ በታች መጀመር ነበረባቸው። ስለሆነም በአፄ ምኒልክ የመጀመሪያው የአገዛዝ ወቅት የተወሰዱት ዕርምጃዎች፣ መሰረተ-ትምህርት ቤቶችን በአንዳንድ ቦታዎች ማስፋፋት፣ ብሄራዊ ባንክ ማቁቋምና አንድ ዐይነት የመገበያያ ገንዘብ እንዲታተም ማድረግና የባቡር ሃዲድም መዘርጋት እነዚህ የማይናቁ መሰረቶች ቢሆኑም አንድን አገር በተሟላ መልክ ለመገንባት የሚያስችሉ አልነበሩም። ከላይ በተዘዋዋሪ መልክ ለማሳየት እንደሞከርኩት ይህ ዐይነቱ አካሄድ በአፄ ምኒልክና በአገዛዛቻው በፍጹም የሚሳበብ አይደለም፤ በፍጹምም ሊሆን የሚችል አይደለም። ምክንያቱም በአፄ ምኒልክም ዙሪያም ሆነ በጠቅላላው በአገሪቱ ውስጥ የተገለፀለት ምሁራዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩና፣ በዚህም ምክንያት የተነሳ ስለ ሳይንስና ስለ ቴክኖሎጂ፣ በአጠቃላይ ሲታይ ስለ ጥበብ የሚረዳ  የተገለፀለት ምሁራዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ በተለይም የሁለ-ገብነትን አስፈላጊነት በማይረዱ ያለተገለፀላቸው ኃይሎች ላይ ግፊት ማድረግ አይቻልም ነበር። ከዚህም ባሻገር በአገሪቱ ውስጥ የጥሬ-ሀብትንና የሰውን ኃይል ሊያሰባስብ የሚችልና ይህንንም ወደ ምርታማነት ወይም ወደ ሀብት በመለወጥ ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችል ተቋም ባለመኖሩ የተነሳ ሁሉም ነገር ከዜሮ በታች መጀመር ነበረበት። ባጭሩ ለማለት የምፈልገው የአንድ አገር ግንባታ በብዙ ምሶሶዎች ላይ መቆም ያለበትና መሰረቱም እየተጠናከረ መሄድ አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ሰለ አንድ ህብረ-ብሄር ግንባታ አመሰራረትና ተከታታይነት መኖር ግንዛቤ ሊኖረን የሚችለው።  ይህንን መረዳት የምንችለው በተለይም ከአውሮፓው የህብረ-ብሄር ግንባታ ታሪክ፣ ከ13ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ መዳበር የጀመረውን ምሁራዊ እንቅስቃሴ፣ በተለይም በመንፈስ ተሃድሶ የሚገለፀው፣ የኋላ ኋላ ላይ ደግሞ ሰለመንግስት አመሰራረትና በአንድ አገዛዝ ውስጥ ሰለሚኖር የስራ-ክፍፍልና የንግድ እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም የከተማዎችና የመንደሮች መገንባት፣ የህግ የበላይነትን የሚያሰመርና በጭንቅላትም ውስጥ እንዲቋጠር የሚያደርግ ሰፋ ካለ ምሁራዊ እንቅስቃሴና፣ ከዚያም በኋላ በእነ ሬኔ ዴካ፣ ኒውተንና ላይብኒዝና በሌሎችም የተስፋፋውንና የዳበረውን ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ መሰረት የሚሆነውን ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ጋር የተዋወቅን እንደሆን ብቻ ነው። ስለ ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገትና ስለ አገር ግንባታም ስናወራ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መሰረቶች እንደሆኑና፣ ይህ ዐይነቱ የአገር ግንባታ በጭንቅላት አማካይነት ሲካሄድና ሰፋ ያለውን ህዝብ ሲያስተሳስርና የአንድ አገዛዝ ዶክትሪም በዚህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የተገነዘብን እንደሆን ብቻ ነው ስለ አገርና ስለ ህብረተሰብ ማውራት የምንችለው። እነዚህ መሰረተ-ሃሳቦች እስካልገቡን ድረስና ለእንደዚህ ዐይነቶቹ ለአንድ አገር በተከታታይነት መኖርና መከበር አስፈላጊዎች ነገሮች ከሆኑ ነገሮች እስካልተዋወቅንና፣ እስካልታገልንም ድረስ አስር ጊዜ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ፣ ባንዲራዬ ባንዲራዬ እያሉ ማውራቱ የውሽት ወሬና ጩኸት መሆናቸውን መገንዘብ አለብን።

በአብዛኛዎቻችን በተለይም በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተን ይህንንም ሆነ ያንን ዝም ብለን የምናወራ፣ እስካሁን ድረስ እንደተከታተልኩትና ለመመራመርም እስከቻልኩት ድረስ ከአስራ ሶስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአውሮፓው ምድር ውስጥ እየዳበረና እየተስፋፋ ከመጣው በልዩ ልዩ መልክ ከሚገለፀው ምሁራዊ እንቅስቃሴ ጋር የተዋወቅን አይመስለኝም። አብዛኛዎቻችን ስለፖለቲካና ስለአገራችንም ጉዳይ በምናወራበት ጊዜ ባለፉት ሃምሳ ዐመታት በአገራችንም ምድር የሚካሄደውን ምስቅልቅል ሁኔታ በምሁራዊ፣ በተለይም በተገለፀለት የምሁራዊ  እንቅስቃሴ መነፅር ለማየትና ለመገምገም አልቻልንም። ይህም ማለት ስለ ፖለቲካ በምናውራበት ጊዜና የአገራችንም ሁኔታ ያሳስበናል ብለን ጭንቀት ውስጥ በምንገባበት ጊዜ የምናወራቸው ነገሮችና ጭንቀታችንም በሙሉ የአገራችንና የህዝባችንን ችግር ለመረዳት፣ በተለይም ደግሞ በፖለቲካው መድረክ ላይ የሚታየውን ቀውስና መዘላበድ ለመረዳት የሚያስችለን ምሁራዊ መሰረትና ኃይል እንዲኖረን ያስፈልገናል። ስለሆነም በስሜት ላይ በመመርኮዝ የምናደርጋቸው እዚህና እዚያ መሯሯጦች በልዩ ልዩ መልኮች የሚገለፁትን የአገራችንን ችግሮች ለመረዳት በፍጹም አያስችሉንም። በተለይም በአሁኑ በግሎባላይዜሽን ዘመን፣ አብዛኛው ነገሮች በተዘበራረቁበትና ብዙ ነገሮችም ተትረፍርፈው በሚገኙበት ዓለም ውስጥ ሃሳባችንን ሰብሰብ ለማድረግና በስልት ላይ በመመስረትና በመደማመጥ ለመስራት ተቸግረናል።

ነገሩን መልክ ለማሲያዝ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የተሰነዘረባትን አደጋ መክታ በመመለስ እንደ አገር ለመገንባት በአፄ ምኒልክ አጭር ጊዜ የአገዛዝ ዓመታት አንዳንድ መሰረቶች ቢጣሉም እነዚህ ነገሮች ሰፋ ላለና ለጠነከረ የአገር ግንብታ የማያማቹ ነበሩ። በተለይም ደግሞ በስልጣን አካባቢ ያለው ኃይል ከአፄ ምኒልክና ከባለቤታቸው እተጌ ጣይቱ ብጡል  በስተቀር  አርቆ የሚያስብ የተገለፀለት ኃይል ባለመኖሩ የአፄ ምኒልክንና የባለቤታቸውን ምኞትና ፍላጎት ስርዓት ባለው መልክ ተግባራዊ የሚያደርግ ኃይል አልነበረም። አፄ ምኒልክም ከሞቱ በኋላ የስልጣን ክፍተት በመፈጠሩና የእሳቸውም ምኞት ተከታታይነት እንዲኖረው ለመደረግ ባለመቻሉ የተነሳ ኢትዮጵያ እንደገና ለሌላ አደጋ የተጋለጠች ነበረች ማለት ይቻላል። የኋላ ኋላ ላይም የፋሺስቱ የኢጣሊያን ወራሪ ኃይል አደዋ ላይ በከፍተኛ ደረጃ በመማቱና በመሸነፉም የተነሳ ይህንን ቁጭት ለመወጣት ሲል እንደገና በመደራጀትና በዘመናዊ መሳሪያም በመታጠቅ ጠቅላላውን አገራችንን ለመውረር ከፍተኛ ሙከራ አደረገ። አንዳንድ ቦታዎችንም ለመቆጣጠርና ኃይልንም ለመከፋፈል የሚያስችል ዕድል አገኘ። ይሁንና በቆራጥነት የሚንቀሳቀሱ አርበኞቻችን በከፍተኛ ተጋድሎ አምስት ዓመት ያህል ክተዋጉ በኋላና የኢጣሊያንን ፋሺስታዊ ወራሪ ኃይል መቆሚያና መቀመጫ ስላሳጡት የመጨረሻ መጨረሻ ህልሙን ተግባራዊ ሳያደርግ ሀፍረትን ተከናንቦ አገራችን ጥሎ እንዲወጣ ተገደደ። ይሁንና ግን  በዚያን አጭር ጊዜ ውስጥ በቀላሉ ተተኪ የማይገኝላቸውን እያደጉ የመጡ ምሁራዊ ኃይሎችን በመጨፍጨፉ የተነሳ አፄ ኃይለስላሴ ከእንግሊዝ ስደት ተመልሰው ስልጣንን ሲይዙ ሀ ብለው መጀመር ነበረባቸው። ጣሊያንም ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን ሲወር በአብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገሮችና በአሜሪካንም በይፋ ባይሆንም የተደገፈ በመሆኑ የተነሳ ኢትዮጵያ የጃፓንን የዕድገት ፈለግ እንዳትከተል የፈፀመው ፋሺስታዊ ድርጊት በተለይም የነቁ ኃይሎችን የመጨፍጨፉ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ተሳክቶለታል ማለት ይቻላል። 

Advertise here _ borkena

ስለሆነም አፄ ኃይለስላሴ ከእንግሊዝ ከተመለሱና ስልጣን ላይ ሲወጡ ከበፊታቸው ከፍተኛ እንቅፋት እንደተደቀነ መገመቱ ከባድ አይሆንም። አፄ ኃይለስላሴም እንደ አፄ ምኒልክ አገዛዝ ሰፋ ባለ በተገለፀለት፣ በሰለጠነና በተቀላጠፈ ተቋም የማይደገፉ ስለነበረና ስለሌለም ሁሉም ነገር በልምድና በሙከራ መካሄድ ነበረበት። ይሁንና ይህ ዐይነቱ ኢትዮጵያን በአዲስ መልክ መገንባትና በጠንካራ መሰረት ላይ እንድትቆም በማድረግ ሰፋ ባለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ ኢኮኖሚንና ህዝብን ሊያስተሳስር የሚችል ምሁራዊ እንቅስቃሴ ለማስፋፋት ደግሞ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ አዲስ የተፈጠረው ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ አሰላለፍ፣ በተለይም ደግሞ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአሸናፊነት መውጣትና ቀስ በቀስም እንደኛ በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ የተሟላ ዕድገት እንዳይተገበር የሚያስችል ልዩ ልዩ የማሰናክያ ዘዴዎቹን በመፍጠሩ የተነሳ  ኢትዮጵያን እንደ አንድ የተሟላ ህብረ-ብሄር(Nation-State) ለመገንባት ቀላል አልነበረም። በደንብና በጥልቀት ተከታትለን እንደሆን ይህ ዐይነቱ የአገሮችን የተሟላ ዕድገት ማሰናከልና ኃይልን በመከፋፈል ብጥብጥ እንዲኖር ማድረግ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በአብዛኛዎቹ ጠንካራና የተገለፀለት መንግስትና ምሁራዊ እንቅስቃሴ በሌለባቸው በአጠቃላይ አነጋገር የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩት አገሮች ውስጥ ተሳክቶለታል ማለት ይቻላል።  በተለይም የመንግስትን መኪና፣ ማለትም የወታደሩን፣ የስለላ-መዋቅሩን፣ ቴክኖክራቶችንና ቢሮክራቶችን በመቆጣጠርና በአዕምሮ ወይም በአስተሳሰብ ላይ ተፅዕኖ በማድረግ ብሄራዊ ባህርይ እንዳይኖራቸው በማድረግ በረቀቀ መልክ ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት እንዲለወጡ በማድረግ ወደ ውስጥ ያተኮረ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ፣ እንዲያም ሲል ሰፊውን ህዝብ ከድህነት የሚያወጣውና የተከበረችም አገር እንዳትገነባ ለማድረግ ቻለ።

          በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የተሰራው የዘመናዊነት ሂደት ስህተት!!  

አፄ ኃይለስላሴ በተለይም ከስደት ከእንግሊዝ አገር ከተመለሱ በኋላ ኢትዮጵያን እንደ አገር የሚያስጠራት፣ አንዳንድ “ዘመናዊ” ነገሮችን ተግባራዊ ቢያደርጉምና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ሊዳብሩ ቢችሉም፣ በተለይም በትምህርት መልክ ይሰጥ የነበረው “ዕውቀትና” ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለተሟላ ወይም ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚያመቹ አልነበሩም። የትምህርት አሰጣጡን ስንመለከት ሰብአዊነትን የሚያስቀድምና፣ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገትና፣ እንዲሁም ህዝቡን የሚያስተሳስሩ በሚያማምሩና ለህዝቡም መኖሪያ የሚያገለግሉ ከአገራችን የምድር አቀማመጥና የአየር ጠባይ ጋር የሚስማሙ የቤት አሰራሮች፣ እንዲያም ሲል መንደሮችና ከተማዎች ለመገንባት ባለመቻላቸው የዘመናዊነት አካሄዱ ለጠራ አስተሳሰብና ለአገር ወዳድነት ስሜት የሚያመች አልነበረም ማለት ይቻላል። ከዚህም በላይ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ለተሟላ የአገር ግንባታ የሚያመች የኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ ትምህርት ለመሰጠት ባለመቻሉ በአገራችን ምድር ተትረፍርፎ የሚገኘውን የጥሬ-ሀብትና ለልዩ ልዩ ሰብሎችና ፍራፍሬዎች  መዘራትና መተከል የሚያገለግለውን ለምለም መሬትና የተትረፈረፈ ውሃ በሳይንሳዊ መንገድ ለመጠቀም ባለመቻላችን በፈረንጆች አቆጣጠር በ1973 ዓ.ም የተከሰተው ረሃብ ከግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በላይ የሚቆጠር ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ ለመደረግ በቅተዋል። ለስራ ፈላጊው የስራ ዕድል የሚከፍቱ መጠነኛና ማዕከለኛ እንዲስቱሪዎች በየቦታው ባለመተከላቸውና ባለመስፋፋታቸው የተነሳ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በድህነት ዓለም ውስጥ ይገኝ ነበር፤ አሁንም ይገኛል። ከዚህ ዐይነቱ ግልፅ ሁኔታ ስንነሳ በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን ተግባራዊ የሆነው “የዘመናዊነት” ፖሊሲና የትምህርት አሰጣጡ ለተሟላ ዕድገት፣ ማለትም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ለሚገለጽ ዕድገት የሚያመቹ አልነበሩም። በተለይም ለቲኮኖሎጂ ፈጠራ የሚያመቹ ልዩ ልዩ የምርምር ተቋማት (Research and Development Center)ለመገንባት ባለመቻላቸው አገራችንና ህዝባችንን ከድህነት ሊያላቅቁ የሚችሉ ልዩ ልዩ የማምረቻ መሳሪያዎችን መፍጠርና መስራት አልተቻለም። እንደሚታወቀው በአንድ አገር ውስጥ በእርሻውም ሆነ በኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት በተከታታይነት ሊያድጉ የሚችሉት የማምረቻ መሳሪዎች በተቀላጠፈ መልክ ተመርተው ሲቀርቡ ብቻ ነው። ይህንን ዐይነቱን ሳይንሳዊ ጥራት የሌለውን የዘመናዊነት አካሄድ ከጃፓን፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከሲንጋፖርና አሁን ደግሞ ከቻይና ጋር እያነፃፀርን ማየተ እንችላለ።  የአንድንም አገር ኋላ-ቀርነት ሁኔታ መገንዘበ የምንችለው በንፅፅር መነፅር(Comparative Studies) ማወዳደር ስንችል ብቻ ነው። ከዚህም በላይ የተገለፀለት ምሁራዊ እንቅስቃሴ ማለት ምን ማለት ነው? አንድንስ ህዝብ ከኋላ-ቀርነት የሚያወጣው የትኛው የዕድገት ፈለግ ነው? የመንፍስ ተሃድሶ በምን መልክ መካሄድ አለበት? የሚሉትን ጥያቄዎች ስናነሳና መልስም ለማግኘት ስንጥር ከሞላ ጎደል ስለ ዕድገት የተወሰነ ግንዛቤ ሊኖረን ይችላል። በተለይም ከተለያዩ የዕድገት ሞዴሎች ጋር ስንትዋወቅና፣ በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ(IMF) ድርጅትና በዓለም ባንክ የሚስፋፋውንና እንደ እኛ የመሳሰሉ አገሮች ስለ ዕድገት ምንም ዐይነት ግንዛቤ ሳይኖራቸው ዝም ብለው ተግባራዊ የሚያደርጉት ኢ-ሳይንሳዊ ከሆነውና ድህነትንና ብልግናን ከሚያስፋፋው የኒዎ-ክላሲካልና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር የተዋወቅንና ጥልቅ ጥናትም ካካሄድን ስለ አንድ አገርና ህዝብ ዕድል፣ እንዲሁም ተከታታይነትና ሰላም ስለሚሰፍንበት ህብረተሰብ የተወሰነ ግንዛቤ ሊኖረን ይችላል። ከእነዚህ መሰረታዊ ነገሮች ስንነሳ ሰለህብረተሰብና ስለ ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንም ዐይነት ግንዛቤ ሳይኖረን ስለፖለቲካና ስለ አገር የምናደርገው እንቅስቃሴ የዝብርቅርነቱንና የድኽነቱን ዘመን ከማራዘም በስተቀር ምንም የሚያስጨብጠን ፍሬ ነገር የለም። ወደ ዋናው ነጥብ እናምራ። 

ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ዓመታት ጀምሮ በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን አዲስ ዐይነት የዕድገት ዕምርታ ቢታይም በተለይም በአዲስ አበባና በተቀሩት ከተማዎችም መሀከል ያለውን የዕድገት ልዩነት ስንመለከት ዕድገቱ ያልተስተካከለና(Unequal Development) ብሄራዊ ነፃነትንም የሚያስከብር አልነበረም። በራሱ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥም ከአራት ኪሎና ከብሄራዊ ቲአትር አካባቢ እርቀን ስንሄድ አብዛኛው ህዝባችን በቆሻሻና መፀዳጃ ቦታዎች በሌሉባቸው ግቢዎች ወይም ቤቶች ውስጥ ነበር ተጨናንቆ ይኖር የነበረው፤ አሁንም በዘመነ ግሎባላይዜሽን ዘመን ከደርግ ከስልጣን መወገድ በኋላ ስልጣንን የተቀዳጁች አገር አፍራሽ አገዛዞች በተከተሉትና በሚከተሉት በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እየተነደፈ የሚመጣው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፓሊሲ መተገበር የተነሳ ሁኔታው በከፍተኛ ደረጃ ተባብሷል ማለት ይቻላል። የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች ተስፋፍተዋል። በሌላው ወገን ደግሞ ለሰፊው  የስራ መክ የማይከፍቱና ሰፋ ያለ ሀብትም የማይፈጥሩና ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት የማያመቹ ሆቴል ቤቶች ተስፋፍተዋል። የሆቴል ቤቶችና የትላልቅ መደብሮች መሰራት በራሱ የዕድገት ምልክት ሳይሆን እንዲያውም ሀብት በከፍተኛ ደረጃ የሚባክንበትና ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትም የሚያስከትል ነው።

ለማንኛውም ለሁላችንም ግልጽ እንዲሆንልን ይህን ዐይነቱን ለተሟላ ወይም ለሁለ-ገብ ዕድገት የማያመቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የምትክ ኢንዱስትሪ(Import-Substitution-Industrialization) ብለን እንጠራዋለን። የምትክ ኢንዱስትሪውም የፍጆታ ዕቃዎችን በማምረት ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ስኳር ማምረት፣ የትምባሆ ተከላና የሲጋራ ፋብሪካ ማስፋፋት፣ የቀዝቃዛ መጠቶችና የቢራ ፋብሪካዎች መገንባትና ማስፋፋት ሲሆኑ፣  አልፎም አልፎም ቀላል የሆኑ የጫማና የጨርቃ ጨርቅ እንዲስትሪዎች፣ የከረሜላ ፋብሪካዎች ተተክለዋል። እነዚህም እንዱስትሪዎች በተወሰኑ ቦታዎች የተተከሉና በጣም ጥቂት ለሆነው 5% ለሚሆነው ህዝብ ብቻ፣ ይህም ማለት የመግዛት ኃይል ላለው ብቻ ተመርተው ለገበያ የሚቀርቡ ነበሩ፤ አሁንም ናቸው።  በተለይም አሜሪካን አገር ረቅቆ በመጣው የዕድገት ሞዴል(Growth Model) አማካይነት ይህ ዐይነቱ የኢንዱስትሪ ተከላ በመጀመሪያ ደረጃ በጣም ጥቂት የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል የፍጆታ ፍላጎት ማሟላትና አዲስ ዐይነትን የፍጆታ አጠቃቀም የሚያስተምር ሲሆን፣ በቲዎሪው መሰረት ቀሰ በቀስ እያለ ወደ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል የመዳረስ(Trickle Down Effekt) ዕድል ይኖረዋል የሚል ነው። በሌላ ወገንና ከሌሎች አገሮች ልምድ ስንነሳ ይህ ዐይነት የኢንዱስትሪ ተከላ ዘዴ ሰፋ ላለና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ለተመሰረተ ጠንካራ የአገር ውስጥ ገበያ(Home Market) የሚያመች አይደለም። ከካፒታሊስት አገሮች ልምድ ስንነሳና ተጨባጩም ሁኔታ እንደሚያረጋግጠው ማንኛውም የካፒታሊስት አገርና ኋላ ላይም የተነሱት እንደ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ሲንጋፖር፣ እንዲሁም ታይዋን፣ ቻይናና የስካንዲኔቪያንም አገሮች ይህንን የተኮላሽ አንድን አገር በተሟላ መንገድ ወይም መልክ ሊያሳድግና ኢኮኖሚውን ሊያሰፋ የማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በፍጹም ተግባራዊ አላደረጉም። ቀድም ብሎ የካፒታሊስት አገሮች፣ የኋላ ላይ ደግሞ የተቀሩት ጠንካራ የአገር ውስጥ ገበያ መገንባት የቻሉት አገሮች በሙሉ በውጭ ኃይሎች ሳይታለሉና ሳይመከሩ ነው በራሳቸው ጥረትና ምርምር፣ እንዲሁም በመኮረጀ አገራቸውን በጠንካራ የኢኮኖሚ መስረት ላይ ለመገንባት የቻሉት። ስለሆነም ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ ድህነትንና መዝረክረክን የሚያስወግድ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ መሰረት በመጣል የሚከበሩ፣ ወይም በቀላሉ ሊሸወዱ የማይችሉ አገሮች ለመሆን በቅተዋል። በዓለም አቀፍ ገበያ ላይም ተወዳዳሪ በመሆን በቀላሉ የማይገበሩ ለመሆን በቅተዋል። ራሺያ ኋላ ላይ ደግሞ ሶቭየት ህብረትም አንዳንድ የማያስፈልጉ ወንጀሎች ቢፈጸሙም፣ ሌላ ዐይነት የዕድገት ፈለግ በመከተላቸው ነው ህዝባቸውን ከድህነት ማላቀቅ የቻሉት። ወደ አገራችንና ወደ ሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ስንመጣ ፈረንጆችን የማምለክ አባዜ ስላለና፣ አንድን የተሳሳተ ቲዎሪና ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲን የሙጥኝ ብሎ የመያዝ ባህል ስላለ በአጠቃላይ ሲታይ የፖሊሲ አውጭዎችም ሆነ አዳዲስ ከዩኒቨርሲቲ´ እየተመረቀ የሚወጣው ወጣት በተሳሳተ ስልት በመመራት በድህነትና በመዝረክረክ ላይ ሌላ እየጨመሩበት ውስብስብ ሁኔታዎችን ሲፈጥሩ ይታያሉ። ፖሊሲ አውጭዎችና አዳዲስ ምሁራዊ ኃይልና፣ በአጠቃላይ ሲታይ በመንግስት መኪናው ውስጥ የተሰገሰጉት ኃይሎች በራሳችው ዓለም ውስጥ ስለሚኖሩና የፈለጉትንም ነገር ስለሚያገኙ በምድር ላይ ያለውን ሁኔታና የህዝባችንን የተዝረከረከና የተጎሳቆለ ኑሮ በፍጹም አይታያቸውም። አዕምር ከተዘጋ ዐይን ማየት ይሳነዋል እንደሚሉት የግሪክ ፈላስፋዎች አነጋገር፣ ለቴክኖክራቶችና ለቢሮክራሲዎች፣ በአጠቃላይ ሲታይ ተማርኩኝ ለሚለው የህዝባችን የድኽነትና የተዝረከረከ ኑሮ በፍጹም አይታያቸውም። ባጭሩ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን በተለይም በኢኮኖሚ ፖሊሲውና በትምህርት መስኩ የተሰራው ስህተት አደዋ ላይ አያቶቻችንና ቅድመ-አያቶቻችን የተጎናፀፉትና ከፍተኛና ታሪካዊ ድል ወደ ተግባር መመንዘር በፍጹም አላስቻለም።

ወደ ሌሎች ነገሮች ስንመጣ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የመንግስቱ መኪና ውስጥ የሚቀጠሩ ሰዎች፣ ተክኖክራሲውና ቢሮክራሲው፣ የሚሊተሪና የፀጥታው ኃይል፣ እንዲሁም ፖሊሱ በአሜሪካና በእስራኤል፣ የተቀሩትም በአንዳንድ የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች በመሰልጠናቸው የተነሳ ንቃተ-ህሊናቸው በጣም ደካማ ስለሆነ አገዛዙን ከመከላከል በስተቀር ለዕድገት የሚያመቹ አልነበሩም። ንጹህ በንጹህ የመጨቆኛና ሀብት መምጠጫ መሳሪያዎች ናቸው። ሰለ ዕድገትና ስለ-ኋላቀርነት ጠለቅ ያለጥናት  ያደረገው የፓኪስታኑ ምሁር አላቪ እንደሚያስተምረን የአገራችን የመንግስት መኪና እንደሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች የመንግስት መኪና አወቃቀር በምድር ላይ ከሚታየው የማቴሪያል ሁኔታ ወይም ኋላ-ቀር ከሆነው የኢኮኖሚ ዕንቅስቃሴ ጋር የማይጣጣም ነበር(Overdeveloped State)፤ አሁንም ነው ማለት ይቻላል።  በመንግስት መኪንና ውስጥ የተሰገሰጉት የተወሰኑት የሚሊታሪው፣ የፀጥታውና የሲቪሉ ቢሮክራሲ ሰዎች የኋላ ኋላ ላይ በደርግ የ17 ዓመታት የአገዛዝ ዘመን እንደተከታተልነው ብዙዎች ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ውስጥ ለውስጥ የሚሰሩና የቀይና የነጭ ሽብር የሚሉት በመሰረቱ ምሁሩን ሙጥጥ በሚያደርግ ግድያ ውስጥ የተካፈሉ ወንጀለኞች በመሆን ዛሬ አገራችን ለምትገኝበት አሳፋሪና አገር አውዳሚ ሁኔታ የማይናቅ አስተዋፅዖ ለማድረግ ችለዋል። ከሌሎች አገሮች፣ በተለይም ከማዕከለኛው አሜሪካና ከደቡብ አሜሪካ የመንግስታት መኪና አወቃቀርና የሚሊተሪና የስለላ አሰለጣጠን ታሪክ ስንነሳ የመንግስቱን መኪና የሚቆጣጠሩት እንዳለ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሎጂክና ለእሱ በሚስማማ መልክ በመሰልጠናቸው በተደጋጋሚ የመንግስት ግልበጣ በማካሄድ ከውስጥ የተሟላ ዕድገት እንዳይመጣ ለማድረግ የበቁ ናቸው። የነቃና የሰለጠን ምሁራዊ እንቅስቃሴም እንዳይዳብር ያገዱ ነቸው። ለዲሞክራሲና ለለተሟላ ዕድገት የሚታገለውን ሁሉ በኮሙኒዝም ስም በመፈረጅ አብዛኛውን ያሰሩና የገደሉ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚፈልገውን አገሮችን የማቆርቆዝ ጉዳይ በተግባር አሳይተዋል። የመንግስታቱን መኪናዎች የሚቆጣጠሩት የሲቪል ቢሮክራቶችም በዕውቅ አሜሪካን አገር ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች በመሰልጠን ስልጣን ላይ እንዲወጡ የሚደረጉ በመሆናቸው የየአንዳንዱን የማዕከለኛውንና የደቡብ አሜሪካን አገሮችን ሁኔታ ስንመለከት ከፍተኛ ውንብድናና ድህነት እንደተስፋፋ መገንዘብ እንችላለን። የአሜሪካንም ኢምፔሪያሊዝም በሚያስፋፋው ርዕዮተ ዓለም የተነሳ ኢሌት የሚባለው ጭንቅላቱ በተበላሽ ርዕዮተ-ዓለም የተያዘ በመሆኑ የራሱን ህዝብ የመጥላትና ፋሺዝምን የማስፋፋት ኃይሉ ከፍ ያለ ነው። ስለሆነም ሰፊውን የየአገሩን ህዝብ ከድህነት የሚያወጣውና የተሟላ ዕድገት እንዳይተገበር በማድረግ የተፈጥሮ ሀብት እንዲባክን ለማድረግ በቅተዋል።

ይህም ማለት አንድ አገር አስር ጊዜ ከውጭ የመጣባትን ወራሪ ኃይል እየመከትኩ የመለስኩኝ ነኝ ብላ ብትዝናና ቀረርቶም በየጊዜው ብታሰማም የተገለፀለት የመንግስት መኪናና ሰፋ ያለ የሰለጠነና ሰፊውን ህዝብ የሚያከብር ምሁራዊ ኃይልና ሰፋ ያለ የሰለጠነ ጠቋም እስካልተዘረጋና በየጊዜውም የማይሻሻል ከሆነ በአንድ ወራሪ ኃይል ላይ የተገኘ መክቶ የመመለስ ድል ትርጉም አይኖረውም። በተለይም በአሁኑ በግሎባላይዜሽን ዘመን ከፍተኛ እሽቅድምድሞሽ ብቻ ሳይሆን፣ አንዲሁም ዐይን ያወጣ ወረራና በትላልቅ ጀቶች በመታገዝ አገሮችን ማፈራረስ በሚካሄድበት ዘመን የአንድን አገር ህልውናን ለማስከበር ከፍተኛና በራሱ ላይ የሚተማመን ምሁራዊ ኃይል መኮትኮትና መገንባት ያስፈልጋል። አስቸጋሪው ነገር ግን ለዚህ ሁኔታ የሚዘጋጅ ኃይል የለም፤ ታዳጊውንም ትውልድ የሚኮተኮትና መንፈሱን የሚያንፅ አስተማሪ የለም። በአጭሩ የአገራችን ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ ህዝባችን የተሟላ ዕድገት የመቀዳጁ ዕድል በጣም የመነመነ ይሆናል። በሌላ አነጋገር ለአርባና ለሃምሳ ዓመት ሁኔታው በተዝረከረከ መልክ ይቀጥላል።  

በአደዋ ስም የሚነግዱ ስዎች የመብዛቱ ጉዳይ!!

በአገራችን ያለው ዋናው ችግር ዕውነተኛውን አገር ወዳድ ከከሃዲውና ለውጭ ኃይሎች ከሚሰልለውና አገርን በተለያየ መልክ ከሚያዳክመው ለይቶ ማወቁ ላይ ነው። በተለይም በአገራችንም ሆነ በውጭ አገር በሚኖረው ኢትዮጵያዊው ዘንድ ከፍተኛ የዕውቀት ክፍተት ስላለ ሀቀኛውንና ከህዝብ ጎን ቆሞ ሰፊውን ህዝብ ከድህነት ለማላቀቅ ከሚፈልገው በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ  በስም ብቻ ዝናን የተጎናፀፉትንና ይህንን በመጠቀም በተለይም ወጣቱን ትውልድ የሚያሳስቱትን ለይቶ ማወቅ በጣም አስቸጋሪ ሆኗል። ስለሆነም አብዛኛው ወጣትና በፖለቲካ ውስጥ እሳተፋለሁ የሚሉት በሙሉ ራሳቸውን ችለውና በዕውነተኛ ዕውቀት ላይ ተመስርተው ከመታገል ይልቅ በደፈናው ዝናን ያገኙትን በመከተልና በማምለክ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የኢትዮጵያን ህዝብ ሰቆቃ እያራዘሙት ነው።

ዋናው ምክንያት እንደዚህ ነው ብሎ ለመናገር በሚያዳግበት በተለይም እንደኛ ባለው አገር ውስጥ የባንዳዎች ቁጥር ከፍ ያለ ነው። ይህ የባንዳነት መንፈስ ድሮም ያለና አሁንም የሚከታተለን ነው። በድሮው ዘመን ከንቃተ-ህሊናና ከዕውቀት ማነስ የተነሳ አንዳንድ ሰዎችን በገንዘብ በመደለል ወደ ባንዳነት ወይም ወደ አገር ከሃዲነት መለወጡ ቀላል ነበር። በአሁኑ ወቅት በተለይም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘመንና ብዙ ነገሮችም ግልጽ በሆኑበት ዘመን አንዳንዶች ዝም ብለው የውጭ ኃይልን በተለይም የአሜሪካንን ኢምፔሪያሊዝምን በማመን የአገራችንን ህዝብ በዚያው በድህነትና በድንቁርና ዓለም ውስጥ ለዝንተ-ዓለም ታፍኖ እንዲቀር የማያደርጉት ሙከራ የለም። የሚያሳዝነው ነገር የዓለምም ሁኔታ ግልጽ በሆነበት ዘመንና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምም ሰይጣናዊ ባህርይውን በሚያሳይበት ወቅት እነዚህን አሳሳች ኃይሎች የሚያምነው ቁጥሩ ቀላል ነው አይባልም።

ነገሩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ እንደ ቻይናና አንዳንድ የኋላ ላይ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተን ሁለ-ገብ ዕድገት የተጎናፀፉ አገሮች አንዳንድ ሰዎችን በጭፍን በማመን ሳይሆን በቆራጥነት አሳሳች ኃይሎችን ነጥሎ በማውጣት ብቻ ነው። በእርግጥ ቀደም ብሎ ጃፓን፣ ኋላ ላይ ቻይናና ቬትምናም ውስጥ የፖለቲካ ክፍተት ስላልነበረና የአሜሪካንም ኢምፔሪያሊዝምም የሚገባበትና የሚያሳስትበት ቀዳዳ የጠበበ ስለነበረና፣ በተለይም ከማንም አናንስም በማለት አነሰም በዛም ቢሆን ትክክለኛውን የዕድገት ፈለግ የተከተሉ ኃይሎች ስትራቴጂያዊ ቦታዎችን በመያዝ ህዝባቸውን ከድህነት ለማላቀቅና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤትም ለመሆን በቅተዋል። ቀደም ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት በተለይም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የትምህርት መስኩ በአሳሳች መንገድ ስለተዋቀረና የመንግስቱም መኪና ለኢምፔሪያሊዝም ሰርጎ መግባት አመቺ እንዲሆን ሆኖ በመዋቀሩ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ቁልፍ ቁልፍ ሰዎችን በመመለምልና ወጣቱን እንዲያሳስት በማድረግ የተሟላ ዕድገትን የሚቀናቀኑ ኃይሎችን በራሱ ዙሪያ ለማሰባሰብ ችሎ ነበር። በሌላ አነጋገር፣ የጎላ ባይሆንም ልክ ማዕከለኛውና ደቡብ አሜሪካ ያለው ዐይነት የቀኝ አዝማሚያ፣ ወይም ደግሞ ህዝብን ከድህነተ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ የሚያወጣ ሰፋ ያለ በሳይንስ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ፕሮጀክት እንዳይተገበር ስር የሰደደ ዘመቻ ተካሂዷል። ለዚህ ደግሞ በአገራችንም ሆነ በውጭው ዓለም በሚኖረው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ሀቀኛውን ከአሳሳቹ መንገድ ለመለየት የሚያስችል ውይይትና በጽሁፍም መልክ የሚቀርብ ሀተታ ባለመኖሩ የተነሳ መንገዱ ለአሳሳቾችና ለባንዳ ኃይሎች አመቺ ነው። በተለይም በአሁኑ የፌስ ቡክና የቲክቶክ ዘመን አብዛኛው ያንን በመከታተል ጊዜውን ስለሚያሳልፍ ሀቀኛውን መንገድ ለመከተል ሳይንሳዊ ምርምር ከማድረግ ይልቅ በስንፍና ዓለም ውስጥ ሲዋዥቅ ይገኛል። ይህ አንደኛው አስቸጋሪ ጉዳይ ቢሆንም አንዳንድ በዕድሜያቸው የገፉ ከሞላ ጎደልም የተደላደለ ኑሮ ያላቸው ለምን ነገረ ዓለሙን በመተው አርፈው እንደማይቀመጡ ነው። ለምንድን ነው በአሳሳችና ሰፊውን ህዝባችንን ነፃ የማያወጣውን መንገድ በመከተል የስልጣኔውን መንገድ የሚዘጉት?  ስለሆነም እነዚህን ሰዎች የምንለምናቸው በአረጀና የተሟላ ዕድገትን የማያመጣውን የአጻጻፍ ዘዴን በመተው አርፈው እንዲቀመጡ ብቻ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ይኸኛው ነው ትክክለኛው የስልጣኔ፣ እንዲያም ሲል የሳይንሱና የቴክኖሎጂው መንገድ ብለው በጠራና በግልጽ ቋንቋ በሀተታ መልክ የሚያቀርቡ ከሆነ መከራክከር ይቻላል። አስቸጋሪው ነገር ሃሳብን ግልጽ ሳያደርጉና የሳይንሱንና የቴክኖሎጂውን መንገድ ሳያሳዩ በጭፍን የሚጻፉ ጽሁፎች፣ የፖለቲካ ውይይቶችና የቲክቶክ አነጋገሮች ህዝብን ከማደናበር በስተቀር የትም የሚያደርሱን አይደለም። ሌላው ደግሞ በአሁኑ ዓለም እንደ አሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ተከታዮቹ ሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ነገሮችን በጥቁርና በነጭ እየጻፉ ሰፊውን ታዳጊ ወጣት ማሳሳት ከፍተኛ ወንጀል እንደ መስራት ይቆጣራል። በሌላ አነጋገር፣ የአንድን ሰው ጽሁፍ በሚገባ ሳያናቡ፣ የአጻጻፍ ዘዴውንና ለማለት የሚፈለገውን ነገር በሚገባ ሳይገነዘቡ አንድን ሰው በኮሙኒስታዊ አስተሳሰብ መወንጀል  ለተሟላና ግልጽ ለሆነ ዕድገት የሚያመች አይደለም። እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች በአሜሪካንና በተቀረው የምዕራቡ የስለላ ድርጅት እንደሚራገበው የወዳጅና የጠላት ፖለቲካ ዐይነት የሚቀርቡትን ትንተናዎች ሳይረዱ በደፈናው ሰውን የሚወነጅሉ በአገራችንና በህዝባችን ላይ ከፍተኛ የሆነ ታሪካዊ ወንጀል እንደሚሰሩ ማወቅ አለባቸው። የአንድን ሰው የአጻጻፍ ስልት ለመረዳት የሚፈልጉ ከሆነ የፍልስፍናና የተፈጥሮ ሳይንስ መጽሀፎችን፣ እንዲሁም የኢኮኖሚና የሶስዮሎጂ መጽሀፎችን እየፈለጉ በማንበብ መንፈሳቸውን ማደስና ሀቀኛውን መንገድ መፈለግ ይችላሉ። 

ያም ተባለ ይህ የዛሬ 130 ዓመት በወራሪው የጣሊያን ኃይል ላይ የተጎናፀፍነው ድል በተሟላ ዕድገትና ድህነትን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በሚያስወግድ መልክ ሊገለጽ ያልቻለው የተሳሳተውን መንገድ በመከተላችን ነው። ኢ-ሳይንሳዊ በሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ኢ-ሰብአዊ በሆነ የትምህርት አሰጣጥ የተነሳ መንፈሳችን በጥሩ መልክ ለመቀረፅ ባለመቻሉ ውስጣዊ ጥንካሬ ለማግኘት አልቻልንም። ስለሆነም በሆነው ባልሆነው በመነታረክ ኃይላችንን እንድንጨርስና እንድንከፋፈልም ተገደናል። እንድሚታወቀው አንድ አገር በተሟላ መልክ የምታድገውና ብሄራዊ ነፃነቷም የሚከበረው ኃይልን በመከፋፈልና በመነታረክ አይደለም። ስለሆነም አብዛኛዎቻችን ዋናውን ችግራችንን ለመረዳት ጥረት ለማድረግ አንሞክርም። የምዕራብ አውሮፓን፣ በተለይም የጀርመንን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት ስንመረምር አንዳንድ ግለሰቦች በጊዜው የነበረውን አመቺ ሁኔታ በመጠቀም ማንም ሳይገፋፋቸው በራሳቸው ጥረት ምሁራዊውን መንገድ በመከተላቸው ነው አገራቸው በተሟላ መልክ እንዲገነባ ለማድረግ የቻሉት። እነዚህ በጣም ጥቂት የሆኑ ምሁራን ለጀርመንና ለምዕራብ አውሮፓ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው የዓለም ህዝብም የሚሆን ሳይንሳዊውንና የፍልስፍናውን መንገድ ለማሳየት ችለዋል። መሰረቱም በግሪክ ፈላስፋዎች የተጣለ ሲሆን ከአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ቀስ በቀስ በአውሮፓ ምድር ውስጥ በጥልቅ ምርምር ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ፣ እንዲያም ሲል ለህብረተሰብ ግንባታና ህብረ-ብሄር ምስረታ መንገዱን ያሳየ ነው። ይኸኛውን ሳይንሳዊውንና የፍልስፍናውን መንገድ ከአገራችን ሁኔታ ጋር ለማገናኘት ስንችልና በተግባርም ስንተረጉም ብቻ ነው እነ አፄ ምኒሊክና ሌሎች ጀግኖች አያቶቻችንና ቅድመ-አያቶቻችን የተመኙትን አንድን አገር በተሟላ መልክ መገንባትና ነፃ የማድረጉን ጉዳይ በእርግጥም ለማረጋገጥ የምንችለው። መልካም ግንዛቤ!!

fekadubekele@gmx.de

www.fekadubekele.com

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡ 

ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ  :-  ይሄንን ይጫኑ 

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian NewsBorkena English