

አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)
ክፍል አንድ የዐቢይ አህመድ አስር ቀይ ስህተቶች
የብልጽግናው ሊቀመንበር ዐብይ አህመድ አሊ በስህተት የተሞላ ፖለቲካዊ ርዕዮት እና በጥፋት የታወቀ ውሳኔ ሰጪነታቸው ተለይተው ይታወቃሉ፡፡
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ከጦርነት፣ ከድህነት፣ ከኋላቀርነትና ከጭቆና ወጥታ ባታውቅም፤ የብልጽግናው ሊቀመንበር ግን፤ የሁሉንም ክፉና ጨካኝ መሪዎችን ክፋትና ጭካኔ ደምሮ ወርሶታል፡፡ ራሱም፤ ‹‹መደመር›› እንደሚለው፤ የሀገሪቱን እሴትና የህዝብ መስተጋብር ከመደመር ይልቅ፤ የጨካኝ መሪዎችን ጭካኔ ደምሮ፤ ‹‹ያለፉትን የሚያስንቅ፤ አስናቀ›› ሆኗል፡፡
በክፍል አንድ የማቀርበው ‹‹የዐቢይ አህመድ ዘጠኙ ቀይ ስህተቶች›› በሚል የለየኋቸውን በጣና ቲቪ ለህዝብ የተላለፍውን ትንታኔ ነው። የችግሩን ጥልቀትና ክብደት እንድንገነዘበው ለማድረግ ነው። ይህ ትንተና ለምን አስፈለገ?

የዚህ ትንተናና ምክረ ሃሳብ ዓላማ በንኡስና ግዙፍ ማንነት ዙሪያ እንዲበታተን ጫና የተደረገበት የኢትዮጵያ ድህረ-ኢህአዴግ ወጣት ትውልድ ለራሱና ለመላው ሕዝብ ህይወት፤ ደህንነት፤ የኑሮ መሻሻል፤ ሰብአዊ መብት፤ ክብር፤ አብሮነት እና ሕዝቡን የሥልጣን ባለቤት ለሚደረገው የወቅቱ ትግል፤ ለዚህ እምቅ ኃይል ያለው ወጣት ትውልድ መረጃዎችን ለማቅረብና ወጣቱ ትውልድ ከጎሳ ልዩነቶች በላይ እንዲያስብና መፍትሄዎችን በጋራ እንዲፈልግ ለመቀስቀስ ነው።
ጠቅላላው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ስእልና ገጽታ በማንኛውም መስፈርት ስገመግመው፤ ዐብይ አህመድ ጠቅላይ ሚንስትር ከሆነ በኋላ፤ የኦህዴድ ብልጽግና ስኬት ምንድን ነው? ብለው ቢጠይቁኝ የሚከተሉትን አቀርባለሁ።
አንደኛ፤ በአሁኑ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚኖረው በሁለት ዓለም ውስጥ ነው። ባንድ በኩል የገዢው መደብና ደጋፊ የሆነው የተወሰነ ክፍል ባስደናቂ ምቾትና የድሎት ዓለም ውስጥ ይኖራል፡፡ በሌላ በኩል አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ እንደ መምህራን ያሉትን ባለሙያዎች ጨምሮ፤ የዕለት ከለት ኑሮው ፈተና በሆነበት ዓለም ውስጥ ይኖራል።
ሁለተኛ፤ የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ ኢትዮጵያ የተባለችውን ታሪካዊት፤ ጥንታዊት፤ የሃገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ያላትን፤ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የሆነችውን አገር፤ ኦሮማዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ተቋማትን፤ ባንኮችን፤ የከተማ መሬት ይዞታን፤ የፌደራል ባጀት ፈሰስን፤ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምን ወዘተ…ማን በበላይት ይዟቸው ይቆጣጠራቸዋል? ያዝባቸዋል? ብዬ ራሴን ስጠይቅ፤ መልሱ ቀላል ነው፡፡ ኦህዴድ፤ ማለትም የአንድ ጎሳ አባላት፡፡ ኦፊሻል ባይሆንም፤ ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እየጠፋች ኦሮምያ የምትባል አገር እየተተካቻት ነው፡፡ ይህ ስር ነቀል የሃገረ መንግሥት ለውጥ ነው፡፡

ሶስተኛ፤ የሚዲያ ነጻነት ሙሉ በሙሉ ስለተከለከለ፤ የገዢው ፓርቲ የሳይበር ፕሮፓጋንዳውን በመደጎም፤ ከፍተኛ ቦታ ይዞ በመሬት ላይ ያለውን መንግሥት መር ግፍና በደል እንዳይታወቅ ሸፍኖታል። የዓለም ሚዲያም እንዳይከታተለው አድርጎታል። የኦህዴድ ብልጽግናን መረን የለቀቀ የፈጠራ ወሬን በማስተጋባት ለሚሰሙትና ለሚያምኑት ሁሉ ኢትዮጵያ በታሪኳ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ እድገትና ልማት እያሳየች ነው ይላል። ይህ ቢሆን ደስተኛ ነበርኩ፡፡ እውነታው ግን፤ ኦህዴድ ብልጽግና በተለይም ሊቀመንበሩ ዐቢይ አህመድ፤ እየተከለ ያለው ሥርዓት፤ የሰሜን ኮሪያውን ፍጹም ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓትን ነው፡፡ “አስናቀ” ያልኩበት ምክንያት ይኼው ነው።
አራተኛ፤ ሰላምና እርጋታ፤ አስደናቂ የኮሪዶር ልማት፤ የስራ እድል፤ በውስጧ የአብሮነት ተግባራዊነትን ያስመሰከረች፤ ከጎረቤት አገሮች ጋር በሰላም የምትኖር፤ ዲሞክራሳዊ ምርጫ የምታካሂድ ወዘተ አገር ሆናለች ይሉናል፡፡ ይህ ቢሆን ደስተኛ ነበርክ፡፡ የሚነግሩንና የመሬቱ እውነታው ፍጹም የተለያየ ነው፡፡
አምስተኛ፤ በዚህ ዓመት ዐብይ አህመድ ሲናገር “ኢትዮጵያ ከጨለማ ዘመን ወደ አዲስ ዘመን በማንሰራራት ተሸጋግራለች” ብሏል። በእንግሊዘኛው ባስቀምጠው “Ethopia entered the age of Renaissance under Abiy Ahmed.” ይህ ሃቅ ወይንስ ትርክት? የድህነት እርከን በዐብይ ዘመነ መንግሥት ከ24% ወደ 43% ንሯል። ድህነት ተባብሷል ማለት ነው፡፡ በሁሉም የድህነት መስፈርት ሲታይ–ትምህርት፤ ጤና፤ ምግብ፤ መጠለያ፤ ንጹህ ውሃ፤ መጠለያ፤ ኤሌክትሪክ ወዘተ የኢትዮጵያ
Multidimensional poverty index 76 በመቶ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በመውደቅ ላይ ካሉት አገሮች (Fragile states) መካከል አንዷ ናት፡፡ በዘመናዊ ቤት የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከ20 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህም ማለት ከ130 ሚሊዮኑ ህዝብ 26 ሚሊዮን የሚሆነው ብቻ ነው በጥሩ መጠለያ ውስጥ የሚኖረው ማለት ነው፡፡ ቀሪው 104 ሚሊዮን ህዝብ በምን መልኩ እየኖረ ነው? የሚለው ከዓለም ተደብቆ አይደለም፡፡ እዘህ ላይ ልብ ሊባል የሚችለው፤ መጠለያ የሌለው ወይም ከደረጃ በታች በሆነ መጠለያ የሚኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት፤ ከኤርትራ፣ ከጅቡቲ፣ ከሶማሊላንድ፣ ከሶማሊያ፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከኬንያ አጠቃላይ ድምር ህዝብ በላይ መሆኑን ነው፡፡
ስድስተኛ፤ በአሁኑ ዘመን የትምህርት እድል የሌለው ሕዝብ ራሱን አይችልም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለትምህርት ፈሰስ የሚያደርገው በጀት፤ የተባበሩት መንግሥታት ከተመነው ከጂዲፒው ከአራት እስከ ስድስት ያነሰ ነው፡፡ ይህም ማለት በብልጽግና መንግሥት ለአጠቃላይ ኢትዮጵያ ህዝብ የትምህር በጀት የተመደበው ገንዘብ፤ ከአጠቃላይ የአገሪቱ ጂዲፒ፤ ከሶስት ነጥብ አራት በመቶ በታች ነው። በዚህ የተነሳም፤ ከ11 ሚሊየን በላይ የሚገመት ወጣት ትውልድ፤ ከትምህርት ገበታ ውጭ ነው፡፡ ለጤና ፈሰስ የሚሆነው ደግሞ የአፍሪካ አማካይ በታች ነው፡፡
ሰባተኛ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ እምነት ስለሌለ የውጭ ኢንቬስትሮች ወደ ኢትዮጵያ አይገባም፡፡ አንድ ሁነኛ የዓለም ባንክ ዘገባ፤ “Foreign Direct Investment (FDI) is weaker than anticipated ይላል፡፡ ተጨማሪው ችግር የዐብይ መንግሥት አገሪቱን የጦርነት ምድር ስላደርጋት ሲሆን፤ የችግሩ እምብርት ደግሞ፤ በአገር ውስጥ ሰላምና አለመረጋጋት መኖሩ ነው፡፡ የፈለገውን ያህል በዐብይ ዘመነ መንግሥት ታዕምራዊ ልማት አለ ተብሎ እንዲነገር ቢደረግም፤ ሃቁን አይቀይረውም፡፡ ፖሊሲው ሳይቀየር ዓለም ባንክና አይኤምኤፍ የሚለግሱት ድጋፍ ፋይዳ ሊኖርው አይችልም፡፡
ድህነትን ሊቀርፍ የሚችለው ሕዝቡ ቢሆንም፤ ዐብይ አህመድ ግን በሕዝቡ እምነት የለውም። ሕዝቡም በመንግሥቱ እምነት የለውም፡፡ ሕዝቡ ከታፈነ ለመንቀሳቀስ፤ ለመስራት፤ ለማምረት፤ ለመግዛት፤ ለመነገድ አይችልም፡፡ ማነቆው የብልጽግና ሥርዓት ነው። በአጭሩ ህዝብና የዐቢይ መንግሥት አይተማመኑም ብቻ ሳይሆን፤ ሁለቱም አይፈላለጉም፡፡ ዐቢይ ህዝቡን ይጠለዋል፣ ይንቀዋል በፍጹም አያምነውም፡፡ ህዝቡም በዐቢይና በመንግሥቱ ላይ እምነት የለውም፤ ምክንያቱም የዐቢይ መንግሥት ተፈትኖ ወድቋልና፡፡
ስምንተኛ፤ ‹‹ይህንን ሁሉ ተአምራዊ ለውጥ ስኬታማ ያደረገው “እንኳን ኢትዮጵያን ቀርቶ መላውን አፍሪካ ለመምራት ብቃት ያለው ዐብይ አህመድ ጠቅላይ ሚንስትር ስለሆነ ነው›› ይሉናል የዐቢይ አህድ ሊቀመኳሶች፡፡ የፖለቲካ ሊቀመኳሱ ደግሞ የራሱ ቅኔም ሆነ ዜማ የለውም፤ ከሌሎች የሚቀዳ፤ የተነገረውን የሚደግም፤ የታዘዘውን የሚፈጽም፤ ዝለል ሲባል ስንቴ ልዝለል ብሎ የሚጠይቅ እንጂ፤ ‹ለምን እዘላለሁ› ብሎ የማይጠይቅ ሰው ነው፡፡
የዐቢይ ሊቀመኳሶች ‹‹ታዕምራዊ ለውጥ›› የሚሉት፤ በዋና ዋና ከተሞች የተሰቀሉትን አምፖሎችና፤ መንገድ ዳር የተተከሉትን ዛፎች መሆኑን በተደጋጋሚ ጊዜ የተነገረ ስለሆነ፤ የዐቢይን የልማት አፈጻጸም፤ ውጤታልባነቱን ለማስረዳት ጊዜ አላጠፋም፤ አንባቢያንንም አላደክምም፡፡
ዐብይ አህመድ እንደ ኔልሰን ማንዴላ ሰርዓቱን ቀይሮ ተአምር ቢሰራ ኖሮ እኔም ደስታዬ ክፍ ይል ነበር። ለመሆኑ ዐብይ አህመድ ምን አይነት የሕዝብ ቅቡልነት፤ ማህበረሰባዊና ፖለቲካው መሰረት ቢኖረው ነው ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ለመግዛትና ለመቆጣጠር የቻለው? ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ባንድ ወቅት፤ አንድ ሁነኛ ባለሥልጣን አዲስ አበባ ሆነን የነገረን ትዝ ይለኛል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር እንዲሆን ያመቻቹለት እንደነ ደመቀ መኮንን ያሉ የብአዴን ባለሥልጣንት ቁልፍ ሚና መጫዎታቸውን ነበር ያጫወተኝ፡፡
ሥልጣኑን ካደላደለ በኋላ ግን፤ ዐብይ አህመድ ዋና ጠላት ያደርገው አማራውን ነው። ባንድ ወቅት እንደፈለገ በሚያዝት ፓርላማ ቀርቦ፤ “በአዲስ አበባ ብዙ ኦሮሞ ጠል ሕዝብ አለ” ብሎ ተናግሯል። ይህ ዲስኩር ፈረንጆች እንደሚሉት ‹‹ጥላቻ ፈጣር›› ነው፡፡ ኦሮሞው በአማራው ላይ እንዲነሳ ቀሰቀሰ ማለት ነው፡፡ እሱ ብቻ አይደለም፡፡ ባንድ ቃለ ምልልስ ኤታማዦር ሹሙ ብርሃኑ ጁላ፤ ስለ ተተኪነት ሲጠየቅ “ምን አለበት፤ ተተኪነት የተለመደ ነው” ሲል አስታውሳለሁ፡፡ ይህ የባለሥልጣናቱ የአፍ ወለምታ ሳይሆን፤ ዐቢይ አህመድ የተከለው ሥርዓት ቋሚ መገለጫው ነው፡፡
ዘጠንኛ፤ በአፉም ሆነ በድርጊቱ ዐብይ አህመድ ጸረ-አማራ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፤ የሚመራው ፓርቲና መንግሥት የአማራውን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ በሁሉም ዘርፎች በማሳደድ እያመከነው ነው። ይህ የአደባባይ ምስጢር መላውን ኢትዮጵያዊና ዓለም አሳስቦታል።
መረጃዎች የሚያሳዩት ባለፉት ሰባት ዓመታት ከመቸውም በባሰ ደረጃ የዐብይ አህመድ ብልጽግና አገዛዝ በኢትዮጵያ ንጹህ ሕዝብ፤ በተለይ በአማራው ላይ በተከታታይ መንግሥት መር የሆነ ጭፍጨፋ አካሂዷል፤ አሁንም በማካሄድ ላይ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ ካውንስል ይህ እልቂት እንዲያቆም ጥሪ ቢያደርግም የዐብይ መንግሥት እልቂቱን አባባሰው እንጅ አልቀነሰውም። Ethiopia: Violence in Amhara region በሚል ርእስ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዊ መብት ካውንስል ቃል አቀባይ Seif Magango 17 November 2023 በአማራው ክልል ስለ ድሮን ጥቃት የሚከተለውን ዘገባና ማስጠንቀቂያ አቅርበው ነበር።
“Continued human rights violations and abuses, including arbitrary arrests, in Ethiopia’s northwestern Amhara region and other parts of the country are deeply concerning. They undermine any ongoing efforts by the Government of Ethiopia on the peace process, including transitional justice.
It is imperative that all parties refrain from unlawful attacks and take all necessary measures to protect civilians. Security operations by the Ethiopian National Defence Forces (ENDF) and its allies
must be conducted in full compliance with Ethiopia’s human rights obligations.” ጥቃቱን ያካሄደው የዐብይ ጦር ሰራዊት መሆኑንና ይህ ሁኔታ ባስቸኳይ ካልታገደ እልቂቱ እንደሚቀጥልና ንጹሃን እንደሚሞቱ አሳስበው ነበር። መረጃውን እንደሚከተለው ዘግበውታል።
“On 6 November, a drone allegedly launched by Government forces struck a primary school in the Wadera district, killing seven people, including three teachers. Reports also suggest Fano militias had occupied some parts of the campus. Another drone attack hit a bus station in Waber town on 9 November, killing 13 people who were waiting to board a bus. …..Such attacks amount to arbitrary deprivation of life under international human rights law.
In an earlier incident, six people were killed and 14 others injured when Government forces shelled residential areas in Chuahit town, in Central Gondar Zone on 4 November. Many of the victims were killed in their homes.”
የዐብይ ሰራዊት የሚጨፈጭፈው ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን እንደ ትምህርት ቤት ያሉትን ተቋማትን ጭምር ነው።
በዚህ ወር፤ በተባበሩት መንግስታት ሰብአዊ ካውንስል 61ኛ መደኛ ጉባኤ 41 የአውሮፓ የጋራ ማህበር ድርጂት ተወካይ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
“As Ethiopia prepares for the general elections in June, we underline the importance of safeguarding the rights to freedom of expression, peaceful assembly and association in the country. We regret the further shrinking of the closed civic space in Ethiopia, including continued intimidation and harassment, arbitrary arrests and detentions of human rights defenders and independent media and journalists, while many have been forced into exile. Full respect for civil and political rights for all and a free civil society and media environment are preconditions for the conduct of free and fair elections, and we call on Ethiopia to abide by its international human rights obligations and reverse the current negative trend.
We have been following with great concern recent developments in Northern Ethiopia that have included military confrontations and clashes. Immediate deescalation by all parties is imperative to prevent a renewed conflict that would have serious consequences for civilians and regional stability. We call on the Government of Ethiopia and all other actors to take concrete action to end ongoing human rights violations and abuses in areas of conflict, including in Amhara, Oromia, and Tigray.”
የመግለጫው ይዘት ተደጋጋሚ የሆነና ወደ ባሰ ቁልቁለት የሚሄድ የስብአዊ መብት ሁከት ወይንም ክራይሲስ እንዳለ ያሳያል። ይህ ሁኔታ ለሰላምና እርጋታ ጠንቅ መሆኑን ያመለክታል። ለዚህ በሃላፊነት ተጠያቂ ጠቅላይ ሚንስትሩና የብልጽፍና መንግሥት መሆናቸውን አሰምርበታለሁ።
አስረኛ፤ በጥቅሉ ሲታይ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢቀበለውም ባይቀበለውም፤ ቢወደውም ባይወደውም፤ ቢያምነውም ባያምነውም በዐብይ አህመድ የሚመራው የኦህዲድ ብልጽግና መንግሥት ከጀመረው የአንድ ጎሳ የበላይነት መስመር ፈቀቅ የሚል አይመስለኝም። ለዚህ ነው፤ የተባበሩት መንግሥታት በተደጋጋሚ የሚያቀርበው ጥቲ ሰሚ የሌለው። ዐብይ አህመድ ከያዘው መርህ ንቅንቅ አይልም።
ዐብይ አህመድ ኢትዮጵያን መምራት ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ፤ ከብልጭልጭ (Glitzy projects that grab attention) ውጭ የኢትዮጵያን ሕዝብ መሰረታዊና መዋቅራዊ ችግሮች አባባሳቸው እንጂ የኢሚንት ያክል አላሻሻለውም፡፡ የድህነቱ መጠን፤ የኑሮ ውድነቱ መጠን፤ የውጭ እዳው መጠን ብቻ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የዐብይ አህመድ ደጋፊዎች ትርክት ተረት ተረት መሆኑን ለመገንዘብ ዓለም ባንክና አይኤምኤፍ ያወጡትን አንድ መረጃ ብቻ አቀርባለሁ።
በመለስ ዜናዊ ዘመነ መንግሥት በአንጻራዊነት ከፍተኛ አድገት ስለነበረ፤ በ2018 የድህነት እርከን ዝቅ ብሎ 24 % ደርሶ ነበር፡፡ ይህ የድህነት እርከን (ፍጹም ድህነት ወይም Absolute Poverty) በዐብይ አህመድ ዘመነ መንግሥት ከፍ ብሎ 43 በመቶ ደርሷል፡፡ ታዲያ የብልጽግናው መንግሥት ሊቀመኳሶች፤ ‹‹እድገትና ብልጽግና ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ መንጥቆ ዓለምን ማርኳል›› የሚለው ዲስኩራቸው ከየት መጣ? በምን መረጃ?
ያው ሁላችንም እንደምናውቀው የበሬ ወለደ ድርሰታቸው ወይም፤ ደጋግመው እንደሚነግሩን፤ ‹‹ካመንክና እሱን ከተከተልክ፤ የምትመኘውን ታገኘዋለህ›› በሚለው ቅዠታቸው እንደሚሆን ለማንም ተሰወረ አይደለም፡፡ ‹‹ልጅ እያለሁ ስኳር ግዛ ተብዬ ሱቅ ስላክ፤ መኪና ሳይኖረኝ መኪና እንደሚነዳ ሰው እቩቩቩ… እያልኩ እሮጥ ነበር›› ብሎ የነገረን ራሱ ዐቢይ አህድ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ አያጣውም፡፡
በአሁኑ ፈታኝ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ አማራው በመኖር አለመኖር አውድ ውስጥ ይገኛል፡፡ ሕዝቡ ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ አይችልም፡፡ በሰብአዊ መብት፤ በፖለቲካና ኢኮኖሚ ተሳትፎ፤ በእምነት፤ በባህል፤ በስነልቦና ወዘተ ስገመግመው፤ በተለይ በአማራው ሕዝብ ላይ በኢትዮጵያ ረዢም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ መንግሥት መር እና መንግሥት መር ያልሆነ ጭካኔ፤ ጥቃትና እልቂት እየተካሄደበት ነው። በደቡብ አፍሪካ ነጮችና ጥቁሮች ቢያንስ በሰላም በአንድ አገር ለመኖር ከቻሉ፤ የብልጽግና አገዛዝ እንዴት ከደቡብ አፍሪካ ለመማርና ስርዓቱን ለመቀየር ፈቃደኛነት አያሳይም? ብዬ ራሴን ስጠይቅ የማገኘው መልስ፤ ለዚህ እኩይ ተግባሩ ምክንያት አለው፤ እሱም የበላይነት።
ይህ ድንቁርናና ጭካኔ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ የአንድ ብሔር የበላይነት የተጫናት ለማድረግ ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጋር፤ ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ አጥፊ እንጂ አልሚ የሆነበት አገር ፈልጌ ለማግኘት አልቻልኩም፡፡ ሩዋንዳ ፈጣን እድገት የምታሳየው መንግሥቷ ከዘወግ በላይ ስለሚያስቡና ስለሚሰሩ ነው፡፡ የማቀርበው መሰረታዊ ጥያቄ “አፍሪካን ለመምራት ብቃት አለው የምትሉት ዐብይ ለምን መጀመሪያ በራሱ አገር ያለውን ስር የሰደደ ጎሳዊነት አባባሰው? ለማን ጥቅም? ማን እያዘዘው? ለምን ጦረኛ ሆነ? ለምን ለውጭ መንግሥት ታዛዢ ሆነ? ›› የሚሉ ጥያቄዎች ሊቀርበት ይገባል፡፡
የብልጽግና ሥርዓት፤ የሚናገረውና በመሬት ያለው ማህበረሰባዊ ሁኔታ እጅግ በጣም የተራራቀ ነው። የኦህዴድ ብልጽግናው ጸረ-ሕዝብ አገዛዝ ሁሉን አገራዊ ቀውስ በጦርነት እፈታዋለሁ የሚል ፖሊሲ ስለሚከተል፤ ኢትዮጵያ ሰላምና እርጋታ እንዳይኖራት አድርጓታል። የዚህ አገዛዝ አሉታዊ ውጤት ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ይመለከታል፤ ኦሮሞውን ጭምር፡፡
ለታላቁ የኦሮም ሕዝብ ጥሪ የማደርገው ‹‹ጎሳዊነትን አንቀበልም ብላችሁ፤ ከወገኖቻችሁ ጋር ለፍትህ ተሰለፉ›› ነው። የዐብይ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፤ በተለይ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የመሰረተው የግልና የቤተሰብ ግንኙነት፤ እና የቀጠናው የጦርነት እንቅስቃሴ፤ የሃገሪቱን ዘላቂ ጥቅም በመበከል ወደ ህልውና አደጋ አሽጋግሮታል፡፡ ከኤምሬትስ ጋር ሆኖ ለሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ለጀኔራል ሃምዳን ዳጋሎ ድጋፍ ሲሰጥ፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ደህንነት የሚያስከተለውን ሁከት ተገንዝቦታል? ታዛዢነቱ ለኢትዮጵያ ነው ወይንስ ለኤምሬትስ? ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ የሚታወቅ ነው፡፡
በዐቢይ አህመድ የተመሠረተው የኦህዴድ ብልጽግና ሥርዓት ዋናው መርህ፤ ጸረ-ሕዝብ፣ ጸረአማራነትና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት መሆኑ አከራካሪ አይደለም። ዐብይ አሕመድ ብልጽግና የሚል ስያሜ የሰጠው ብቸኛ ገዢ ፓርቲ፤ አዲስ ተጠቃሚ መደብ መስርቷል። አብዛኛው የአንድ ጎሳ ተወካይ ቢሆንም፤ ስርዓቱን አገር አቀፍ በሆነ ደረጃ እንዲደግፉ ለማድረግ ከሁሉም ብሄር፤ ብሄረሰቦችና እምነቶች የተወጣጣ አድርጎታል። ዐብይ አህመድ ‹‹ለገንዘብና ለግል ጥቅም የማይገዛ ሰው የለም›› የሚል እምነት አለው፡፡ እርካብና መንበር የሚለውን ድርስቱን ተመልከቱ፡፡
ለምሳሌ፤ በአማራ ክልል በአብዛኛው፤ ድሮ የብአዴን አባል የነበሩት አማራዎች፤ የብልጽግና አባልና ደጋፊ ሆነዋል። በተመሳሳይ ይህ “ከፋፍለህ ግዛው፤ አዳክመው፤ ብላው” ብዬ የምጠራው ዘዴ፤ በትግራይ ክልልም፤ በደቡብም፤ በጋምቤላም፤ በአዲስ አበባም፤ በኦሮሚያም ድጎማ በመለገስ የበላይነቱን በመተግበር የኦሮሙማ አጀንዳውን ስኬታማ በማድረግ ላይ ነው። በዐብይ አህመድ የበላይነት የሚያንቀሳቀሰው የኦህዴድ ብልጽግና አባላት ቁጥር፤ እስከ 15 ሚሊየን ይገመታል ተብሎ ሲገለጽ የሚያስታውሰኝ፤ በደርግ ዘመነ መንግሥት ኢሰፓ ተብሎ የተሰየመውን የመንግሥት አካል የነበረውን ገዢ ፓርቲ ብዛትና ሚና ነው።
ሁለቱም፤ ሌላውን ተፎካካሪ ፓርቲ ሁሉ አምክነው የበላይነቱን የያዙ አውራ ፓርቲዎች ናቸው። የኢሰፓው በሰራተኛው መደብ ስም፤ የብልጽግናው በአንድ ጎሳ ስም። ቁም ነገሩ፤ ተፎካካሪ ፓርቲ በሌለበት አገር አሉታዊ ውጤቱ አምባገንነት ነው። የምርጫው ውጤት ቀድሞ ሊተነብይ ይችላል፡፡ አሸናፊው ገዥ ፓርቲ ይሆናል፡፡ የዚህ አሉታዊ ውጤት ወደፊት የባሰ ትርምስ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢሰፓ ግዙፍ አባላትን ይዞ አምባገነንና ጸረ-ሕዝብ ስለ ነበረ፤ በመጨረሻ እንደ እምቧይ ካብ ፈርሷል። ብልጽግናም የእምቧይ ካብ እንደሚሆን እገምታለሁ። እኔን የሚያሳዝነኝ፤ ኦህዴድ ብልጽግና ከደርግ ውድቀት፤ ከሩዋንዳ እልቂት አለመማሩ ብቻ ሳይሆን በዚህ እብሪተኝነቱና ትእቢተኛነቱ ኢትዮጵያን የሚወስድበት አደገኛ መንገድ ስለታየኝ ነው፡፡
ይህ ፍጹም የሆነ የአንድ ፓርቲ፤ የአንድ ጎሳ የበላይነትና ተጠቃሚነት አብዛኛውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይመለከተዋል፤ ያሰቃየዋል፤ ያበሳጨዋል። ኑሮውን፤ ሰላሙን፤ በእርጋታ መኖሩን በክሎታል። በአእምሮው፤ በልቡ፤ ሕዝቡ ለፍትሃዊና ዲሞክራሳዊ ለውጥ ተዘጋጅቷል። ሕዝቡ ለመሰረታዊና መዋቅራዊ ለውጥ ተዘጋጅቷል ስል፤ በአገር ደረጃ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ የፖለቲካ ድርጅትና መሪዎች አሉት ማለቴ አይደለም። ይህ በሂደት እንደሚመሰረት ግን ተስፋ አለኝ።
በኢትዮጵያ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ አምናለሁ፡፡ ሕዝቡና ባለድርሻ አካላት የተገኘውን እድል በብልሃትና በአንድነት ካልተጠቀሙበት ግን፤ የምንወዳት አገራችን የመቀጠል እድሏ እየመነመነ እንደሚሄድ እሰጋለሁ። ጎሳዊነትና የአንድ ብሄር የበላይነት የኢትዮጵያን ሁኔታ እያባባሰው መሄዱን ለመረዳት፤ በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር ዙሪያ የተከሰተውን የኃይል አሰላለፍ ብቻ መገምገሙ በቂ ነው። የታወቁት አሜሪካዊት ደራሲ ማያ አንጀሎ ሲመክሩ “የት እንደ ነበርክ ካላወቅህ፤ ወደ የት እንድምትጓዝ አታውቅም” ያሉት ትዝ ይለኛል፡፡
የዐብይ ቡድን እኛ ከየት እንደመጣን እንድንዘናጋ እያስገደደን፤ ሌላ ትርትክት እየሰጠን፤ እሱና ግብረአበሮቹ የሚተርኩትን ከተቀበልን አገራችንን ወደ የት እንደሚወስዷት አናውቀውም፡፡ ኢትዮጵያን የሚያዋጣት ህበረሰባዊነት እንጂ የአንድ ጎሳ የበላይነት ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ጉዞ አፍራሽ ነው፤ ድንቁርና ነው፡፡ አምካኝ ነው፡፡ ከ21 ዘመን አካታችነትና የዜግነት መብት ቅቡልነት ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ መልካም ጉርብትና ለሕዝቦች ህይዎትና ደህንነት ወሳኝ ነው፡፡
የተለያየ ታሪክ ያላቸውና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩት የአውሮፓ አገሮች የጋራ የኢኮኖሚ ማህበር መስርተው ለታዳጊ አገሮች ድጋፍ ሲሰጡ፤ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ለምን ተስማምተው ለሕዝባቸው ኑሮ ትኩረት አይሰጡም? “አፍሪካን ለመምራት ብቃት አለው የምትሉት ዐብይ አህመድ አስተዋይነት ካለው ለምን ከአፍሪካ ቀንድ መሪዎች ጋር በጋራ ጥቅም ላይ አይወያይም? በውስጥም ሆነ ውጭ ለምን ሁል ጊዜ ለጦርነት ቅድሚያ ይሰጣል?” መልሱን ራሳችሁ ስጡ።
የቀጠናውን አደገኛ ክስትት በሚመለከት International Crisis Group፤ February 18, 2026 – Ethiopia, Eritrea and Tigray: A Powder Keg in the Horn of Africa የሚለውን ዘገባና ምክረ ሃሳብ መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ማርቲን ፕላውት የተባለው ለህወሓት ድጋፍ ያለው ‹‹ጋዜጠኛ››፤ ለህወሃት ደጋፊዎች ምክር ሲሰጥ “የተገኘውን እድል ተጠቀሙበት፤ የትግራይን ሃገረ መንግሥት ለመመስረት እድል አላችሁ” ብሏል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱም›› አንቀጽ 39 እንደሚፈቅድ ይናገራል።
ይህ ሕገ መንግሥት መቀየር አለበት እያልኩ ምክንያቶችን በተደጋጋሚ አቅርቤያለሁ፡፡ ለህወሃት የሚያደላው ማርቲን ፕላውት የሚሰብከውን ባልቀበልም እንኳን፤ አደጋው ግን ያሳስበኛል። በተለይ በአማራና በትግራይ ህዝብ የቆየ ወዳጅነት ላይ እንደ ትርፍ ጥርስ በመካከላቸው የበቀለውና ውበትም፤ ጤናም ምቼትም የነሳቸው ህወሓት ከእነ ህገ መንግሥቱ መቀየር አለበተ የምለው ለዚህ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ የህወሓት ህገ መንግሥትና አስተሳሰቡ፤ የአማራውና የትግራዩ ህዝብ እርስ በርሱ እንዲጨራረስ የሚያደርገው የብልጽግናና አጋሮቹ ሴራ መነሻው እሱ ስለሆነ ነው።
ዐብይ አህመድ ሁልጊዜ ልዩ ልዩ አጀንዳ እየፈጠረ እኛ ትኩረት መስጠት ላለብን እንዳናተኩር ያደርገናል፡ በዚህ ዐብይ ያለውን ስጦታ አደንቃለሁ፡፡ ‹‹ሞኞቹና አላዋቂዎቹ እናንተ ናችሁ›› እያለን ነው፡፡ ለምሳሌ፤ የባህርን በር በሚመለከት ከሶማሌላንድ ጋር ተዋዋለ፡፡ በውጭ የአረብ አገራት ግፊት፤ ይህ አልሆን ሲል አጀንዳውን ወደ ቀይ ባህር አዛወረ፡፡ የእሱ ደጋፊዎች የዛሬ ዓመት “ሬቻን የምናከብረው አሰብ ቀይ ባህር ነው” ብለው ነበር፡፡ የአሰብ ጉዳይ ዋና አጀንዳ ሆነ፡፡ ይህን ተከትሎም፤ ጃዋር ሞሃመድን እና ክራይሲስ ሴንተርን የመሰሉ በጉዳዩ ላይ ትንታኔ የሰጡ ሁሉ፤ ‹‹ጦርነት አይቀርም›› አሉ፡፡
ዐብይ አህመድ ኢትዮጵያዊያንን በሃገር ወዳድነት ለማባበል በሚል ሰበብ፤ በአንድ በኩል ኑሯቸውን እያመሰና እያመሰቃቀለ ባለበት ወቅት፤ አንድ ጊዜ ሶማሌላንድን በሚመለከት ከሶማሊያ ጋር፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ህዳሴ ግድብንና የዓባይ ወንዝን በሚመለከት ከግብጽና ሱዳን ጋር፤ ሱዳንን በሚመለክት ከሱዳኑ ወታደራዊ ጁንታ ጄኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡህራን ተፋላሚ የኢምሬትስ ወዳጅ ከሆነው የግመልና የወርቅ ነጋዴው ሌላኛው ጦረኛ ጄኔራል ሃምዳን ዳጋሎ ጋር፤ አሁን ደግሞ የባህር በርን በሚመለከት ከኤርትራ ጋር፤ ጋምቤላን በሚመለከት ከደቡብ ሱዳን ጋር ንትርክ ውስጥ ገብቷል። የዐብይ አህመድ መንግሥት ንትርክ ውስጥ ያልገባው የጎረቤት አገር ኬንያ ብቻ ናት። ኬንያዊያንንም ቢሆን በአንድ ወቅት ተንኩሷቸው፤ ‹‹በዚህ ጉዳይ ቀዩን መስመር አለፍክ›› ሲሉ ዊሊያም ሩቶ በግልጽ መናገራቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላም በኬኒያ በኩል የሚያደርገውን ትንኮሳና ማቡካት እጁን ሰበሰበ፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚገባት አምናለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ እኔ ብቻ ሳልሆን መላው ኢትዮጵያዊያንም የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማሪያም ያሉ ምሁር፤ ‹‹አሰብ የማናት›› በሚል ርዕስ የጻፉትን የባህር በር ቁጭት መላው ኢትዮጵያ እንዲያነበውና የመላው ኢትዮጵያዊያንን ስሜት እንዲረዳ በዚህ አጋጣሚ እጋብዛለሁ፡፡ ነገር ግን የባህር በርን አስመልክቶ፤ የውስጥ ጦርነቱ ያደከማትን አገር ወደ ውጭ ጦርነት መምራት ጤናማ ነው ለማለት አልችልም፡፡ ዝንጀሮ መጀመሪያ መቀመጫዬን እንዳለችው ሁሉ፤ ለአገር ውስጥ ሰላምና እርጋታ፤ አብሮና ተከባብሮ ለመኖር ትኩረት ቢሰጠው የውጩን አደጋ ለመከላከል ይቻላል። ታሪክችን የሚያስተምረን ይህንኑ ነው። ከፉከራ ውጭ (Bravado) አጀንዳውን መቀያየር አያዋጣም።
ጃዋር የሚናገረውን፤ የክራይሲስ ቡድንና ሌሎቸ ያቀርቡትን ትንተና ስመለከት፤ የትኛው አገር ከየትኛው ጋር ተሰልፏል? የኢትዮጵያ ወዳጅ አገሮች እነማን ናቸው? የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚታደግ አገር ወዳድ መንግሥትና አመራር አላት? እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡ የማይካደው ሃቅ፤ ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ በእልቂት እና በውጭ ከበባ ውስጥ እንደምትገኝ አልጠራጠርም። ለማንኛውም ከዚህ በፊት ብዙ እድሎች አምልጠውናል። ከአሁን በኋላ ሌላ እድል የምናገኝ አይመስለኝም። የራሱን ሕዝብ ቀን በቀን በድሮን የሚጨፈጭፍ አገዛዝ ኢትዮጵያን ሊታደጋት አይችልም፡፡ አገሩን ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ቡድን፤ ለአስር ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት አሳልፎ የሚሰጥ አመራር፤ ኢትዮጵያን ሊታደጋት አይችልም። ይህ እብሪተኝነት ያለው ክህደት ነው፡፡ ሕዝቡ ብሶቱን ያውቃል። ሁሉም በአገዛዙ የተገፉ ወገኖቻችን ለፍትህ-ርትእ፤ ለእኩልነትና ለዴሞክራሲያዊ አማራጭ ተዘጋጅተዋል።
ስርዓታዊና መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልጋል ስንል ምን አይነትና እንዴት፤ በምንና ለማን? ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ መጀመሪያ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግና ካለፉት ስህተቶቻችን መማር አለብን። ከጎጠኛነት፤ ከጎሰኛነት፤ ከጠባብ ብሄርተኛነትና ከብሄር ትምክህተኛነት በላይ ማሰብ አለብን። የአንድ ጎሳ የበላይነት እኮ ዘረኛነት ነው። ስር ነቀል ለውጥ ለማካሄድ የምንችለው በተናጥል፤ በፉክክር፤ በብልጣ ብልጥነት፤ በርስ በርስ ጥላቻ፤ በገመድ ጉተታና ባለመተማመን ሊሆን አይችልም። በብሄርተኛነትም ሊሆን እንድማይችል ያለፈውና የአሁኑ ታሪካችን ይመሰክራል። ዛሬ ኢትዮጵያን የበከላት ጠባብ ብሄርተኛነት፤ የብሄር ትምክተኛነት፤ ተስፋፊነት እና የአንድን ጎስ የበላይነት ትርክት ማስተጋባት ነው፡፡ ይህ የጠባብ ብሔርተኝነት ልምምድ፤ ሕዝብን አማሽ፤ አገርን አፍራሽ ጉዳት ነው ብል አልሳሳትም። ለዚህ ነው ያሰተሳሰብ ለውጥ ወሳኝ ነው የምለው።
ከሳምንታት በፊት ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፤ “ሃገርን ለመታደግ እና ለማሸጋገር ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል” የሚል ርዕስ አዘጋጅቶ ጋብዞን ነበር፡፡ በኔ ግምገማ ሃገርን ለመታደግ የሕዝብን ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ማስቀደም አለብን የሚል መሰረታዊ እሴት ይጨመርበት እላለሁ። የዜጎች ሰብአዊ መብት የማይከበርበት አገር ሰላምና እርጋታ ሊኖረውና አገርም ልትቀጥል አትችልም። ሰብአዊ መብት ካልተከበረ ሁልጊዜም ጦርነትን በጦርነት እየተካን ቀውሱ ይቀጥላል (war becomes a permanent fixture). ይህ ሁኔታ ለኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች መግቢያ ቀዳዳ ፈጥሯል፤ መሳሪያ ሆኗል። የውክልና ጦርነት አይቀርም። በጋራ ሆነን የሽግግር መንግሥት አማራጮችን የምናቀርብበት ወቅት ዛሬ ነው። ይህንን ለማድረግ ግን ብሄራዊ አንድነት ያስፈልጋል። ካለፈው ስህተታችን እንማር፤ የሕዝቡን ፍላጎት መሰረት እናድርግ። የሕዝቡን ፍላጎት ስል ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ማለቴ ነው። ሁሉንም ያላቀፈ አማራጭ አያዋጣነም፡፡
የሕዝብ ቅቡልነት የሌለው፤ ሕዝብ ያልተሳተፈበትና ያልደገፈው ሽግግር ሊሰራ አይችልም። የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤትና መሰረት ሕዝብ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የስልጣኑ ባለቤት ሆኖ አያውቅም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ወደ አሜሪካ መጥቶ የተናገረውን አስታውሳለሁ፤ “እኔ አሸጋግራችኋለሁ፤ እመኑኝ” ብሎን ነበር። ዐቢይ ወደ የት እንዳሸጋገረን እናውቀዋለን፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ በሚገባ አሸጋግሮናል፡፡
ባንድ ወቅት “ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል” የሚል ጥያቄ የቀረበለት ዐብይ ሲመልስ፤ ‹‹እኛ ለአንድ ክልል ብለን የምናሻሽለው አንቀጽ የለም›› ነበር ያለው፡፡ ዐቢይ ለአንድ ክልል ሲል ለአማራው ማለቱን አንርሳ።
በዐብይ መሰሪ ሴራ ከሞቱት ወጣት የአማራ መሪዎች መካከል የማደንቀው ዶር አምባቸው መኮነንን ነበር። ስለ ሕገ መንግሥት ለውጥ አስፈላጊነት እና የዐብይ እምቢተኛነት የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን፤ ‹‹ለአንድ ክልል ብለን የምናሻሽለው ሕገ መንግሥት የለም› የሚባል ነገር ተቀባይነት የለውም፡፡ ትክክልም አይደለም፡፡ አንድ ስለተባለ ብቻ አንድ ክልል አይደለም፤ ሰፊ ህዝብ ነው፡፡ እንደገናደግሞየአንድክልልብቻጥያቄምአይደለም፡፡ሌሎቹምየሚያምኑበትናየሚቀበሉትማሻሻያሃሳብአለ፡፡ስለዚህህገመንግሥቱመሻሻልአለበት፡፡ሕገመንግሥቱየሰዎችንችግርመፍታትካልቻለእናየሰላምምንጭመሆንካልቻለ፤ሕዝብበሚፈልገውመንገድመሻሻልአለበት›› ሲሉየተናገሩትንማስታወስእፈልጋለሁ።መሪማለትእንደዚህነው።መሻሻልንየሚደግፍ።ከታችአቫሪውንበቪዲዮተመልከቱ።
ህገ መንግሥቱ ችግር የለበትም ለሚሉ ግለስቦች የማቀርበው ጥያቄ፤ ዜጎች በያሉበት የመኖር መብታቸው ከተነጠቀና ከቀያቸው ከተፈናቀሉ፤ የመገንጠል መብት እንዳለ ከቀጠለ፤ አንድ ጎሳ ብቻ የበላይነቱን እንዲይዝ ካመቻቸ፤ ይህ ህገመንሥት ኢትዮጵያን ሊወክላትና ሊሸከማታ ይችላል? ይህ ህገመንግሥት ነው የዐብይ አህመድን ኦሮሙሙማ አጀንዳ ስኬታማ ሊያደርግ የሚችለው፡፡ እኔ ይህ ህገመንግስት ኢትዮጵያን እየናዳት ነው እላለሁ፡፡ ሕዝብን ያማከለ እና የዜግነት መሰረት ያደረገ ህገመንግሥት ያስፈልጋል፡፡
ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለኢትዮጵያ የሚቆረቆረው ሁሉ መታገል ያለበት በጦርነት፤ በመፈናቀል፤ በድህነት፤ በረሃብ፤ በስራ አጥነት፤ በኑሮ ውድነት፤ በገፍ እስራት፤ በስደትና ሌላ ለሚሰቃየው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሃዊና ዘላቂ መፍትሄዎችን ማቅረብ የምሁራኑና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ኃላፊነት ነው። ይህንን የተቀደሰ ስራ ስኬታማ ለማድረግ የምንችለው ባንድነት ጸንተን ስንታገል ነው። ሃቁን ስንናገርና አቋም ለመውሰድ ስንደፍር ነው። ፍላጎትና ቅንነት ካለ ቢቻል በውህደት፤ ባይቻል ግን በትብብር ለመስራት እንችላለን፡፡ ለዚህ ምሳሌ ለመጥቀስ እፈልጋለሁ። የአማራ ፋኖ ውህደት
በቅርቡ፤ ከብዙ ውጣ ውረድና የገመድ ጉተታ በኋላ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅትና የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ኃይል ተመካክረውና ተነጋግረው የአማራ ፋኖ ውህደትን ለመላው ዓለም አብስረዋል። አዲሱ የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄ አንድ ተቋም፤ አንድ አመራር የመሰረተበት መሰረታዊ ምክንያት የአማራው ሕዝብ እልቂት የሚካሄድበት ጎንደሬ፤ ወሎየ፤ ጎጃሜ፤ ሸዋዬ፤ ከክልሉ ውጭ ወይም፤ ክርስቲያን፤ ሙስለም፤ ሴት፤ ወንድ፤ ድሃ ወይም ሃብታም ወዘተ ስለሆነ ሳይሆን፤ በብሄሩ ተለይቶ በአማራነቱ ስለሚጠቃ ነው። አማራነት ወንጀ ሆኗል ማለት ነው።
የህልውና ትግሉ የአማራ ብሄርተኛነትን መሰረት ያደረገበት ምክንያትም ይኼው ነው፡፡ በአማራነቴ እየለያችሁ አትጨፍጭፉኝ፤ አታሳዱኝ፤ አታፈናቅሉኝ፤ አትሰሩኝ፤ ሰብአዊ መብቴን አክብሩልኝ፤ ቤት፤ መሬትና ንብረቴን አትቀሙኝ የሚል የተቀደሰ ትግል ነው፡፡ ጥናትና ምርምሮች የሚያሳዩት በመሬት ላይ የሚታየው ሃቅ፤ አማራው የህልውና ጥቃት እየተካሄደበት ነው ሲባል ጥቃቱ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ለማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ ከቀየው በገፍ ይፈናቀላል፡፡ ለምሳሌ፤ በኮሪዶር ልማት ሰበብ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚገመት ሕዝብ ከአዲስ አበባ ከተማ ከቤቱና ከንብረቱ ተፈናቅሏል፡፡ በአማራነቱ ከወለጋና ሌሎች የኦሮሚያ ክልል፤ ከጉራ ፈርዳ ወዘተ ብዙ ሺህ አማራ ተፈናቅሏል፡፡ በደብረ ብርሃን በመጠለያ የሚኖረውን ሕዝብ ብቻ ማየቱ በቂ ነው፡፡ በአማራነቱ በማይካድራ ከ1650 በላይ የአማራ ሕዝብ ተጨፍጭፏል፡፡ ዐብይ አህመድ አስቸኳይ አዋጅ ካወጀ በኋላ በአማራው ክልል በተደጋጋሚ ጭካኔ የተሞላበት የድሮን ጭፍጨፋ አካሂዶ፤ የሞቱት አማራዎች ቁጥር በትክክል ባይታወቅም፤ ብዙ ሺህ ሕዝብ እንደ ተጨፈጨፈ መረጃዎች አሉ፡፡ በዐቢይ የሥልጣን ዘመን፤ የህዝብ ሞት ተራ የቁጥር ጨዋታ ከሆነ ቆይቷል፡፡
ባንድ ወቅት፤ የአሜሪካ አምባሳዶር በኢትዮጵያ “የድሮን ጥቃቱ አስጊ” እንደሆነ ተናግረው በዐብይ መንግሥት ጫና “ስህተት ነው” የሚል ማስተባበያ አውጥተዋል፡፡ አምባሳደር ማሲንጋ ሃቁን መናገራቸው ለትችት ዳርጓቸዋል፡፡ የአማራው ወጣት ትውልድ ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆን
በማሰብ፤ በአማራው ክልል ከአራት ሚሊየን በላይ የሚሆን ወጣት የትምህርት እድል እንዳይኖረው ተደርጓል፡፡ ይህ ተከታታይ ትውልድ የማይረሳው ጭካኔ ነው፡፡ የዐብይን ጭካኔ የሚተቹ ብዙ ሺህ የሚሆኑ የአማራ ምሁራን፤ የፖለቲካ መሪዎች፤ ጋዜጠኞች፤ የሰብአዊ መብት ታዛቢዎች፤ ባለ ኃብቶች ወጣቶችና የከተማ ነዋሪዎች በዐብይ ወህኒ ቤቶች በመሰቃየት ላይ ይገኛሉ፡፡
ዐብይ አህመድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተውህዶንና የእስልምና እምነቶችን ፋይዳ ቢስ ለማድርግ በሚያደርገው ስልታዊ መዋቅር ፈረሳ፤ ብዙ የእምነት መሪዎችንና ተከታዮችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንዲገደሉ፤ እንዲቆስሉ፤ እንዲሳደዱ አድርጓል፡፡ በሱ ግምገማ እነዚህ እምነቶች ለሱ የብልጽግና ወንጌል የማስፋፋት አጀንዳ መሰናክል ናቸው፡፡ ‹‹እስልምና እና የኦርቶዶክስ ኃይማኖቶች፤ ለሥልጣኔና ለዴሞክራሲ ፈታኞች ናቸው›› ሲል በፓርው የንድፈ ሃሳብ መጽሔቱ ላይ ማስፈሩ ይታወቃል፡፡
በጥቅሉ ሲታይ፤ የአንድ ጎሳ የበላይነትን መርህ ያደረገው የዐብይ አህመድ አገዛዝ ጭካኔው፤ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ስለሆነም፤ የሚካሄደው ድርጊት ኢፍትህዊና አገር አፍራሽ ነው፡፡ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚካሄደው ዘርፈ ብዙ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት እና ዐብይ አህመድ በኦሮሞው ሕዝብ ስም የሚሰብከው ስኬታማነት እንዳለ ሆኖ፤ የማያከራክረውን የኢትዮጵያን የሀገረ መንግሥት መፈራረስ ባጭሩ ላቅርበው፡፡
በቀውስ የተበከለችው ኢትዮጵያ፤ ዐብይ አህመድ ጠቅላይ ሚንስትር ከሆነ በኋላ፤ በሁሉም ዘርፍ ማለትም፤ በሰላምና እርጋታ፤ በዜጎች የኑሮ ሁኔታ፤ በሰብአዊ መብት፤ በውጭ እርዳታ መጠን መቀነስ፤ በውጭ እዳ መጠን መጨመር፤ በመልካም ጉርብትና ግድፈት፤ በጦረኛነት፤ በሕግ የበላይነት ክፍተት፤ በስራ እድል እጥረት፤ በፍትህና ርትዕ ጉድለት፤ በፖለቲካ ተሳትፎ እጣ ፋንታ፤ በፖቲካ ውድድርና ምርጫ አለመኖር፤ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ 135 ሚሊየን ሕዝብ በቀውስ ተበክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት መሪዎች፤ ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ በጦር ወንጀል፤ በዜጎች እልቂት፤ በሴቶች መደፈር፤ በዜጎች መፈናቀል፤ በሌብነትና ሙስና የሚያስጠይቃቸውና የሚያስከስሳቸው ብዙ መረጃ አለ፡፡ ይህ መሆኑ አይቀርም፡፡ ይህ ዘርፈ ብዙ ቀውስ አልበቃ ብሎ፤ የዐብይ መንግሥት በአሁኑ ፈታኝ ወቅት ኢትዮጵያንና የአፍሪካን ቀንድ ወደ አላስፈላጊና አደገኛ ጦርነት እየወሰዳቸው ነው፡፡
ጦርነትን በጦርነት መተካት እብድነት ነው፡፡ አንድ ግለሰብ የዐብይን ስነ ልቦናና ባህሪ ሲገመግም እንዲህ የሚል ሃሳብ ነግሮኝ ነበር፡፡ “ፈጣን ምላስ ያለው፤ ውጤቱ ክስረት ነው፡፡” የሚያሳስበኝ ምላሱ ሳይሆን ክሰረቱ ለማን ይሆን የሚለው ነው፡፡ የኔ መልስ፤ ለሕዝቡ፡፡ ይህንን ግን ዐብይና ቡድኑ ረስትውታል፡፡ ሕዝቡን ንቆታል፡፡ ‹‹የራሴ ህዝብ›› ብሎ የሚጠራውንና በሱ የሚነግድበትን የኦሮሞን ሕዝብ ጭምር ነው የካደው፡፡
ለማጠቃለል፤
በህይዎቴ የማደንቃቸው ብዙ የሃገር መሪዎች አሉ። ለምሳሌ እንደ ኔልሰን ማንዴላ አይነቶቹ፤ ለእውነት፤ ለፍትህ፤ ለእኩልት የቆመ ስለሆነ የሚደነቅና የሚወደድ መሪ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሚናቁም መሪዎች አስታውሳለሁ፡፡ ኢዲ አሚን ዳዳ፡፡ ይህ የቀድሞው የዩጋንዳ ጨካኝና ግብዝ ‹‹መሪ››፤ የፈለገውን የሚያወራ፤ ጦርነት የሚወድ፤ የሚፎክር፤ ለእውነትና ለሰብአዊ ፍጥረት ደንታ የሌለው፤ ራስ ወዳድ እንደ ነበረ ትዝ ይለኛል።
ወደፊት፤ ዐብይ አህመድን ታሪክ የሚያወሳው ውሸትን እንደ እውነት የሚደጋግም፤ ያልሰራውን ሰራሁ የሚል፤ በሁሉም ነገር አዋቂ ነኝ የሚል ግን ደግሞ ከእውቀት፣ ከአዋቂዎችና ከእውቀት ፍሬዎችና የእውቀት ምንጮች ጋር የተጣላ፤ ንጹሃንን በገፍ የሚጨፈጭፍ፤ ከጦርነት ጋር ፍቅር ያለው፤ ልክ እንደ ኢዲ አሚን ለሰው ህይዎት ደንታ የሌለው መሆኑን እንደሚያካትት እገምታለሁ፡፡ ለዚህ ነው፤ አገዛዙ የሚመሰክረው ስኬት ትርጉመ ቢስ ነው የምለው፡፡
ይቀጥላል!!
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena
