Advertisement


መርሃጽድቅ መኮንነን ዓባይነህ
በፖለቲካው አለም ጥበብ የተመላበት ውሸት እንግዳና ያልተለመደ ነገር አይደለም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ወገኖች ይህንን አይነቱን የረቀቀ ውሸት ስሙን በማሳመር ዲፕሎማሲ ነው ሲሉ ሊያንቆለጳጵሱት ይቃጣቸዋል፡፡ እኔ እንኳ በዚህ የተጋነነ አቀራረብና የተዛባ ግንዛቤ መስማማት አብዝቶ ይቸግረኛል፡፡
ለማናቸውም በዚህ ረገድ ምድራችን ቁጥራቸው የበዛ ውሸታሞችን አስተናግዳለች፡፡
የአነስተኛና ጥቃቅን መንግሥታት ዋሾ መሪዎችን ለጊዜው እናቆያቸውና የታላቂቱ አገር የU.S አሜሪካ አዛውንት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሳይቀሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በጥቁር አባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ከአሜሪካ በተገኘ የፋይናንስ ድጋፍ ነው በማለት ዓይናቸውን በጨው አጥበው በአደባባይ ሲዋሹ ተመልክተናቸዋል፣ አድምጠናቸዋልም፡፡
ቀድሞ ነገር በውጊያ ላይ እንደነበሩ ሁሉ ጦር የተማዘዙትን ግብጽና ኢትዮጵያን አስታርቄ በመካከላቸው ሠላም አውርጃለሁ ሲሉም በአራድኛው ልሳን አብዝተው ሲቀዱ ሰምተናቸዋል፡፡
– Advertisement –

ቁቅም ከምንትስ ተቆጠረች እንዲሉ አበው፣ በአንድ ጠባብ አካባቢ የሚስተዋል ችግር እንደመሆኑ መጠን ያን ያህል ለንጽጽር ባይበቃም የዚህ አጭር ጦማር ባለቤት ለአሁኑ ማተኮር የፈለገው ራሱን የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ት.ህ.ነ.ግ) እያለ በሚጠራው ታጣቂ ኀይል ግብዝ መሪዎች ማለቂያ የሌለው ቅጥፈት ላይ ነው፡፡
ዶሮ ብታልም ጥሬዋን ነው እንደሚባለው ትህነግ ፕሪቶያ ላይ የተፈረመውን የተኩስ ማቆምና የዘላቂ ሠላም ስምምነት አፈፃፀም እያነሳ ሌት ከቀን ሲያላዝን እንሰማለን፡፡
ከዚህ አልፎ ለውሉ አተገባበር አይነተኛ መሰናክል ሆኗል በማለት የፌደራል መንግሥቱን በኃላፊነት ሲከስና የስምምነቱን አደራዳሪዎችና ታዛቢዎች ጭምር አዎንታዊ ተጽእኖ በማሳደር ረገድ የበዛ ዳተኝነት አሳይተዋል እያለ አብዝቶ ሲወቅስም በጥሞና እንከታተላለን፡፡
ሆኖም በዚያ ስምምነት ውስጥ ጎላ ተደርጎ የተሰነደው አቢይ ነጥብ በአንድ አገር ውስጥ ሊኖር የሚገባው አንድ የመከላከያ ኀይል ነው የሚል መሆኑን ልቦናው እያወቀ የትግራይ መከላከያ ኀይል (T.D.F) የተሰኘውና በግሉ ያደራጀው ሰራዊት ሳይነካ ጎን ለጎን አብሮ እንዲቆይለት ትህነግ ያለአንዳች ይሉኝታ ይሟገታል፡፡
– Advertisement –

ይህ አካሄድ ትክክል አይደለም፣ በውላችን መሠረትም ቢሆን ተቀባይነት የለውም ብለው ሲሞግቱት ደግሞ የትግራይ ህዝብ ህልውናና ደህንነት በአስተማማኝ ሊጠበቅ የሚችለው የራሴ ነው በሚለው የትግራይ ሰራዊት ብቻ መሆን አለበት በማለት ፍፁም የተንሸዋረረ አቋሙን እስከማስተጋባት ይዳፈራል፡፡
በመሠረቱ ይሆናል መስሏቸው T.D.Fን ያደራጁትና እ.ኤ.አ ከ2020 ኣስከ2022 ድረስ ከፌደራል መንግሥቱ የአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት የያኔውን የጥፋት ዘመቻ በበላይነት የመሩት በአሁኑ ወቅት ተለዋጭ ሸሚዝ አጥልቀው የአራት ኪሎውን ቤተ-መንግሥት ያለሀፍረት የተቀላቀሉት እነሌተና ጄኔራል ጻድቃን ገብረ-ትንሳኤ እንደነበሩ የምንዘነጋው ጉዳይ አይደለም፡፡
የዛሬውን አያድርገውና ጻድቃንማ በያኔው የአማራ ልዩ ኀይልና አጋሮቹ ፈጥኖ ደራሺነት እስከተቀለበሰበት ጊዜ ድረስ በውጊያው ድል ቀንቶት እስከደብረ-ሲና ለመዝለቅና ወደመዲናዋ አዲስ አበባ መቃረቡን ሲረዳ ድርድር ለምኔ፣ ከማንስ ጋር ነው የምደራደረው፣ ጦርነቱ እንደሆነ አልቋል እኮ፤ በማለት አለቅጥ ሲዘባበትና በውጭ መገናኛ ብዙህኃን ዘንድ በየጊዜው እየቀረበ የተአብዮ መግለጫዎችን በመስጠት ሲያላግጥ የነበረ ሰው ነው፡፡
እንግዲህ ያ ሁሉ አለፈና ለጊዜውም ቢሆን በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በተለይ ደግሞ በትግራይ ክልል የጥይት ድምጽ መሰማት ካቆመና የባሩድ ሽታ ተወግዶ ተናፋቂ የነበረው የሠላም ድባብ መፈጠር ከጀመረ በኋላ ዋንኛው የኀይል አጠቃቀም ኃላፊነትና ተግባር (monopoly and use of violence) ሊያዝ የሚገባው በማእከላዊው መንግሥት ብቻ ነው ተብሎ በእማኞች ፊት ከተደመደመና የጋራ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ እንኳ ትህነግ ወደትግራይ እንደተመለሰ የወከላቸው ተደራዳሪዎች በሰነዱ ላይ የፈረሙበት ቀለም ገና በቅጡ ሳይደርቅ የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ሲል ተደምጧል፡፡
– Advertisement –

ቡድኑ ከናካቴው ትጥቅ የመፍታቱና ታጣቂውን ኀይል በትኖ ወደልማት ሥራ የማዞሩ እውነታ አንድም ቀን ቢሆን ተውጦለት አያውቅም፡፡
ይልቁንም ይኸው ሀኬተኛ ቡድን ድህረ-ጦርነት በጁ የቀሩትንና መሬት እየማሰ ለክፉ ቀን ያገለግሉኛል በማለት በየስፍራው አርቆ የቀበራቸውን የተለያዩ ከባባድ መሳሪያዎች በውሉ ላይ ቃል በገባው መሠረት ለማእከላዊው መንግሥት ወዲያውኑ ከማስረከብ ይልቅ በአዳዲስ የሰራዊት ምልመላና ሥልጠና ፕሮጀክቶች ክፉኛ መጠመዱን ቀጥሎበት ቆይቷል፡፡
እንደእውነቱ ከሆነ ትህነግ የሞት አፋፍ ላይ ከደረሰ በኋላ አፈር ልሶ ከተነሳና በነማይክ ሀመር እሽኮኮ ባዪነት ወደደቡብ አፍሪካ ተጓጉዞ ቀላል ከማይባል ድንጋጤ ጋር የፈረመውን የፕሪቶርያውን ውል በዝርዝር ያውቀዋል ለማለት ያዳግታል፡፡ ያውቀዋል ቢባል እንኳ የዚያን ሰነድ ድንጋጌዎች እየመረጠ ነው የሚያነባቸው፡፡ ለአጭበርባሪነቱና ለቀጣፊነቱ ፈፅሞ ለከት የለውም፡፡
ለምሳሌ ትህነግን በጊዜው ጨርሶ በወታደራዊ እርምጃ ከመደምሰስና ታሪክ ከመሆን በታደገው የፕሪቶርያው ውል አንቀጽ 10 ንኡስ አንቀጽ (4) ድንጋጌ መሠረት ሁለቱ ክልሎች፣ ማለትም አማራና ትግራይ የሚዋሰኑባቸው ግዛቶች አወዛጋቢ አካባቢዎች (contested areas) ናቸው፡፡
በሌላ አነጋገር የጎንደሩ ወልቃሂትም ሆነ የወሎው ራያ ግዛቶች አለመግባባቱ በፖለቲካ ውይይትና በሠላማዊ ድርድር እስኪፈታ ድረስ በሕግ ረገድ የየትኛውም ክልል ይዞታዎች መሆናቸው ቀርቶ በአከራካሪነታቸው እውቅና አግኝተው ባሉበት ሁኔታ እንዲቆዩ ነው በግልጽና በማያሻማ ቋንቋ የተደነገገው፡፡ የቡድኑ መሪዎችና አፈ-ቀላጢዎቻቸው አብዝተው ሲቀጥፉ እንደምንታዘበው የተጠቀሱት አካባቢዎች የትግራይ ሉኣላዊ ግዛቶች ናቸው የሚል ብያኔ በውሉ ውስጥ ተፅፎ በጭራሽ አናገኝም፡፡
ለነገሩ ራሷ እንደአንድ አስተዳደራዊ ክልል በተፈጠረችበትና በምትተዳደርበት የሀገረ-ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሕገ-መንግሥት መሠረትም ቢሆን ትግራይ የኔ ብቻ ነው የምትለው ሉኣላዊ መሬት የላትም፣ ሊኖራትም ከቶ አይችልም፡፡ በርግጥ ይህ መርህ የሚሠራው ለሁሉም የፌደሬሽኑ ክልሎች እንደሆነም ጭምር መታወቅ አለበት፡፡
ትህነግ ግን ምንጊዜም ቢሆን የርሱ ብቸኛ አንጡራ ሀብት እንደሆነች ዘልአለሟን የምትቀጥል የምትመስለው ትግራይ ወደሉኣላዊ መሬቶቿ ስላልተመለሰችና የግዛት አንድነቷ ስላልተጠበቀ የፕሪቶርያው ውል ሙሉ ተፈፃሚነት አግኝቶ የወያኔ አስተዳደር እንደገና ካልተተከለ በስተቀር አከራካሪዎቹ ግዛቶች የኔ እስካልሆኑ ድረስ ሌላው ቀርቶ በጦርነቱ ሳቢያ ከቀያቸው የተፈናቀሉና እስካሁን ድረስ በትግራይ ክልል በተለያዩ መጠለያዎች ውስጥ አስከፊ ኑሮ የሚገፉ የትግራይ ተወላጅ ወገኖቻችን እንኳ ወደቀድሞ ይዞታዎቻቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ሊፈቀድላቸው አይገባም በማለት አጥብቆ ሲሟገትና አለም-አቀፉን ሕብረተ-ሰብ ሳይቀር በሀሰት ለማሳመን ዛሬም ድረስ ያለእረፍት ይቀጥፋል፣ ያጭበረብራል፡፡
ቢያንስ የግዛት ይገባኛል ጥያቄውን ለጊዜው በጠረጴዛ ላይ ለውይይት አቆይቶ እቆረቆርላችኋለሁ የሚላቸውንና በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩትን ተፈናቃዮች ወደቀያቸው መልሶ እንደገና የማቋቋሙ ተግባር ቅድሚያውን መስጠት የሚቻልና የሚገባም ሆኖ ሳለ ቡድኑ ዘመናትን በተሻገረው የደረቅ መሬት መስፋፋት አጀንዳው ላይ አለቅጥ ተቸንክሮ መቅረቱና እዚያና እዚህ የቅዠት ዳንኪራ እንደረገጠ መቀጠሉ ክፉኛ ያሳዝናል፣ ያስቆጫልም፡፡
በመጨረሻም እዚያና እዚህ ያልኩበት አይነተኛ ምክንያት በመቀሌ ተወሽቆ የሚገኘው አፈንጋጭ ቡድን፣ ለይስሙላ የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በሃራ መሬት ያለው አዲስ ተፋላሚ ኀይልም ሆነ ከመቀሌ ተባርሮ ወደአዲስ አበባ የኮበለለው ፍንካች ይህንኑ የአከራካሪ ግዛቶች ይገባኛል ጥያቄና ተፈናቃዮችን መልሶ የማስፈሩ ጉዳይ በተመለከተ ያላቸው አቋም እምብዛም የተለያየ ሆኖ ስላላገኘሁት ብቻ ነው፡፡
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ለመደገፍ/ለማገዝ :- ይሄንን ይጫኑ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News–Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena
