
ከ 6 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ
በጦርነት ወቅት አሸናፊውን ጎራ ለመለየት በአብዛኛው አዳጋች ነው። ከፍተኛውን ዋጋ የሚከፍለው ግን ተራው ሕዝብ ነው።
ዓለም አቀፉ የነዳጅ ገበያ እና የአቅርቦት ሰንሰለት በመዘበራረቁ ምክንያት አንዳንድ አገራት ከባድ ኢኮኖሚያዊ ኪሣራ ለመጋፈጥ እየተዘጋጁ ነው። ከጦርነት የሚያተርፉ አገራት መኖራቸውም የሚጠበቅ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዓለም የነዳጅ ዋጋ መናር ከፍተኛ ምርት ላላት አገራቸው ትርፍን እንደሚያመጣላት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት በአካባቢው ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ብዙ መዘዞችን እያስከተለ ነው።
የባሕረ ሰላጤው አገራትን እንዳይረጋጉ አድርጓል። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘውን ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል።
ከጦርነት ቀጣናው ርቆም መዘዙ እየተሰማ ነው። የነዳጅ ዋጋ መጨመር እና በሆርሙዝ ሰርጥ እና በአካባቢው በተፈጠረው የባሕር ትራንስፖርት መስተጓጎል የሸቀጦችን ዋጋ እያናረው ነው።
ለመሆኑ በዚህ ጦርነት የትኞቹ አገራት ይጠቀማሉ? ተጎጂዎቹስ?
ሩሲያ

ኢራን የሩሲያ ቁልፍ አጋር ስትሆን ጠንካራ ወታደራዊ ትብብር አላቸው። ሩሲያ ወዳጄ ከምትላቸው አገራት የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደል፤ የሶሪያ በሻር አል አሳድ ከሥልጣን መወገድ እና አሜሪካ ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ስር ማዋሏ ለሞስኮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሰናክል ተደርጎ ተቆጥሯል።
የኪዬቭ አጋር የሆነችው አሜሪካ ወታደራዊ ሀብቷን ወደ ኢራን በማዞሯ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ከዩክሬን ጋር ለጀመረችው ጦርነት ግን ጥቅም ሊሰጣት ይችላል።
“የፓትሪዮት ሚሳዔሎች እና የፀረ ሚሳዔሎች መሟጠጥ ለሩሲያ ጠቃሚ ነው። ዩክሬን በገበያ ላይ መሣሪያዎቹን የማግኘት ዕድሏን ይገድበዋል” ሲሉ በፓሪስ የፖለቲካ ጥናት ተቋም የዓለም አቀፍ ጥናት ማዕከል ተባባሪ ፕሮፌሰር ኒኮል ግራጄውስኪ ለቢቢሲ ኒውስ ራሺያ ተናግረዋል።
ቴህራን የሻሂድ ድሮኖችን በብዛት መፈለጓ በሞስኮ አቅም ላይ ጉልህ ተጽእኖ እንደማያሳድር ባለሙያዎች ይናገራሉ።
“ዩክሬን ጦርነት በተጀመረበት ወቅት ሩሲያ በኢራን የሻሂድ ድሮኖችን እና ለድሮኖቹ የማምረቻ ቴክኖሎጂ ፈቃድ እስከምታገኝበት ወቅት ድረስ በቴህራን ላይ ጥገኛ ነበረች” ሲሉ በአሜሪካ የሚገኘው የጥናት ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ሃና ኖት ለቢቢሲ ኒውስ ተናግረዋል።
“አሁን ሩሲያ የዩክሬን ጦርነትን ለመቀጠል ኢራንን የማትፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ሩሲያ የሻሂድ ድሮኖችን በራሷ ማምረት ጀምራለች።”

ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን በመዘጋቷ የነዳጅ እና የጋዝ ዝውውርን በመቀነስ የነዳጅ ዋጋን እንዲያሻቅብ አድርጓል። ይህ ደግሞ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ለነበረችው ሩሲያ ከጋዝ ሽያጭ የምታገኘው ገቢ የተወሰነ የገንዘብ እፎይታ ሊሰጣት ይችላል።
የሩሲያ የፌዴራል በጀት በበርሜል በ59 ዶላር በምትሸጠው ነዳጅ ላይ የተመሠረተ ነው። አሁን የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል ወደ 120 ዶላር የተጠጋበት አጋጣሚም ተፈጥሯል።
ዋና ዋና የባሕረ ሰላጤው ነዳጅ አምራች አገራት ምርታቸውን በመቀነሳቸው ሩሲያ እንደ ቻይና እና ሕንድ ላላሉ አገራት ኤክስፖርት ለማድረግ ዕድል ይከፍትላታል።
“ሕንድ ቀደም ሲል ከሩሲያ የምትገዛውን ነዳጅ እንድትቀንስ ስትወተወት ቆይታለች። በኋላም ቢያንስ እስከሚቀጥለው ወር ድረስ ከሩሲያ ነዳጅ እንድትገዛ ከአሜሪካ ፈቃድ ተሰጥቷታል” ሲሉ የአርገስ ዋና ኢኮኖሚስት ዴቪድ ፋይፍ ተናግረዋል።
“የነዳጅ ገበያ ጫናን ለማቃለል በሩሲያ ነዳጅ ላይ የተጣሉትን አንዳንድ ማዕቀቦች ስለማቃለል የተጀመሩ አንዳንድ ውይይቶችም አሉ።”
ቻይና
ቻይና በኢራን ላይ በተከፈተው ጦርነት ምክንያት ይህ ነው የሚባል ውጤት እስካሁን አላየችም። ነገር ግን ወላፈኑ መሰማቱ የሚቀር አይመስልም።
በዓለም አቀፍ የኢነርጂ ፖሊሲ ማዕከል መረጃ መሠረት ቻይና ከምታስገባው ድፍድፍ ነዳጅ ውስጥ 12 በመቶውን ከኢራን ታገኛለች።
በተጨማሪም ቻይና ለብዙ ወራት የሚበቃትን ነዳጅ አከማችታለች፤ ተጨማሪ ካስፈለጋትም ፊቷን በቀላሉ ወደ ሩሲያ ማዞር ትችላለች።
የቻይና “በውጭ ንግድ ላይ የተመሠረተው የኢንዱስትሪ ዘርፍ” ግን ይጎዳል ሲሉ ፋይፍ ተናግረዋል።
ከቻይና አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) 20 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው የወጭ ንግድ የኢኮኖሚዋ ቁልፍ መሠረት ነው።
በሆርሙዝ ወሽመጥ እና በአካባቢው ያለው የባሕር ትራንስፖርት መስተጓጎል ለቻይና ያን ያህል ችግር የሚፈጥር አይሆንም። ወደ ምዕራብ ለሚሄዱ የቻይና ምርቶች ግን ወደ አትላንቲክ መድረስ ወሳኝ ነው።
በአረቢያ ባሕረ ገብ መሬት በኩል እስያን፣ አውሮፓን እና አፍሪካን የሚያገናኘው የባብ ኤል-ማንደብ ሰርጥ፣ በኢራን በሚደገፉት ሁቲዎች ጥቃቶችን አስተናግዷል።

“የቀይ ባሕር መስመር እንደገና ክፉኛ የመጎዳት ዕድሉ ሰፊ ነው። ከእስያ የሚነሱ የጭነት መርከቦች ወደ አትላንቲክ ለመጓዝ በደቡብ አፍሪካ እና በደቡብ አፍሪካው ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በኩል በመዞር ዙሪያ አቅጣጫቸውን መቀየርን ይመርጣሉ” ሲሉ ፋይፍ ለቢቢሲ ኒውስ ተናግረዋል።
“ይህ ጉዞ ደግሞ ከፍተኛ ወጪ አለው” ሲሉ በለንደን የሚገኘው የቻታም ሐውስ የመካከለኛው ምሥራቅ ባለሙያ የሆኑት ኒል ኩሊያም ተናግረዋል።
“ጉዞው ከ10 እስከ 14 ቀናት ይጨምራል። እንደ እቃዎቹ መጠን፣ ለአንድ መካከለኛ መርከብ እስከ 2 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ያስወጣል።”
በኢራን ላይ የተከፈተው ጦርነት ለቻይና ዲፕሎማሲያዊ ዕድሎችን ሊፈጥር ይችላል። ከአሜሪካ አንጻር እራሷን “ኃላፊነት እንደምትወስድ ተገዳዳሪ” አድርጋ ለመቅርብ እየሞከረች ነው ሲሉ የዩናይትድ ኪንግደም ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት ባልደረባው ፊሊፕ ሼትለር-ጆንስ ለቢቢሲ ኒውስ ተናግረዋል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተቃራኒ የተረጋጉ እና ሊገመቱ የሚችል ዓለም አቀፍ መሪ አድርገው ራሳቸውን መግለጻቸውን ይቀጥላሉ።
ጦርነቱ ትራምፕ እንደ ታይዋን ላሉ ለሌሎች አንገብጋቢ ሁኔታዎች እንዴት ምላሽ እንደሚሰጡ ቤይጂንግ “ምልክቶችን የምታይበት” ዕድል ሊሆን ይችላል።
ታዳጊ አገራት
በመካከለኛው ምሥራቅ ነዳጅ እና ጋዝ ላይ በእጅጉ ጥገኛ የሆኑት የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት በጦርነቱ ከባድ ጉዳት ይደርስባቸዋል። አንዳንዶች ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖውን በፍጥነት ለመቀነስ ከባድ እርምጃዎችን ወስደዋል።
በቬትናም የናፍጣ ዋጋ ከጦርነቱ መጀመር ወዲህ በ60 በመቶ ጨምሯል። በተቻለ መጠን ሠራተኞች ከቤት ሆነው እንዲሠሩ መንግሥት እየጠየቀ ይገኛል።
ከመካከለኛው ምሥራቅ 95 በመቶ የሚሆነውን ድፍድፍ ነዳጅ የምታስገባው ፊሊፒንስ በበኩሏ፣ ከአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ውጪ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች በሳምንት ለአራት ቀናት እንዲሠሩ ተደርጓል።
ፓኪስታን ከባንኮች ውጪ ላሉት ተመሳሳይ ገደቦችን አስቀምጣለች። በተቻለ መጠን ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ትዕዛዝ ተላልፏል። ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን ወደ በይነ መረብ አዛውረዋል።
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ በቴሌቪዥን በተላለፈው ንግግራቸው የአገሪቱን የነዳጅ ክምችት መጠበቅ እና በጥንቃቄ መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በባንግላዲሽ ነዳጅ ሽያጭ ሌላ መልክ ይዟል። በነዳጅ ማደያዎች በተከሰተው ረጅም ወረፋ ምክንያት የነዳጅ ሽያጭ ላይ ኮታ ተቀምጧል። ለመኪኖች 10 ሊትር እና ለሞተር ሳይክሎች ሁለት ሊትር ብቻ ነው በቀን የተፈቀደው።

የጦርነቱ መዘዝ ከነዳጅ እጥረት በላይ ሊሆን ይችላል።
አርሶ አደሮች ለእርሻቸው የሚጠቀሙት ማዳበሪያ ዋጋ ሊየጨምር ይችላል። በመሆኑም ማንኛውም የማዳበሪያ ሽያጭ መስተጓጎል ዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትናን ሊያናገው ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
“30 በመቶ የሚሆነው የዓለም ዩሪያ ማዳበሪያ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ያልፋል። ዩሪያ የሚመረተው ከፔትሮኬሚካሎች ሲሆን፣ ይህም ከድፍድፍ ነዳጅ የሚገኝ ነው። ስለዚህ 30 በመቶ የሚሆነውን ዩሪያ ከዓለም ገበያዎች እያስወገዱ ከሆነ፣ ይህ በዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል” ብለዋል ኩሊያም።
በማሽኖቹ ላይ ከተሰነዘረው ጥቃት በኋላ፣ በዓለም ላይ ካሉት ትላልቅ የጋዝ ላኪዎች አንዱ የሆነው እና የዩሪያ ማዳበሪያ አምራቹ ኳታርኢነርጂ ኩባንያ ምርቱን ለጊዜው እንዲያቆም ተገዷል።
“በምግብ ዋስትና የዋጋ ግሽበት ረገድ ከስድስት ወይም ከዘጠኝ ወራት በኋላ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ማየት ትችላላችሁ” ብለዋል ኩሊያም።
“እስካሁን ላይታይ ይችላል ነገር ግን ሰብሎች ወይም ገበሬዎች ማዳበሪያ ማግኘት ካልቻሉ ተጽዕኖውን በረዥም ጊዜ እናየዋለን።”
