ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ራፐሩ እና ፖለቲካኛው የአርኤስፒው ባሌንድራ ሻህ

ከ 4 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

በወጣቶች በተመራው የባለፈው ዓመት ተቃውሞ የኔፓል መንግስት ከስልጣን ከተወገደ በኋላ በተካሄደ የመጀመሪያ ምርጫ፤ ራስትሪያ ስዋታንትራ ፓርቲ (አርኤስፒ) በከፍተኛ ድምጽ አሸነፈ።

ውጤቱ ከራፐርነት ወደ ፖለቲካ የመጣው የአርኤስፒው ባሌንድራ ሻህ የአገሪቱ ቀጣይ መሪ እንዲሆን በር ይከፍትለታል ተብሏል።

አርኤስፒ 182 መቀመጫዎችን ማሸነፍ እንደቻለ ታውቋል። ውጤቱ በአስርት ዓመታት ውስጥ በኔፓል የተመዘገበ የአንድ ፓርቲ ትልቁ ድል ሆኗል።

የኔፓል ኮንግረስ 38 መቀመጫዎችን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፣ የኔፓል ኮሚኒስት ፓርቲ ዩኤምኤል (ሲፒኤን-ዩኤምኤል) ደግሞ በ25 መቀመጫ ሦስተኛ ሆኗል። ወደ 19 ሚሊዮን ከሚጠጉ መራጮችን ውስጥ 60 በመቶዎቹ መምረጣቸው ታውቋል።

አዲሱ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ ቢያንስ አንድ ሳምንት እንደሚፈጅ ይጠበቃል።

ውጤቱ በአውሮፓውያኑ 2022 ለተመሰረተው እና በዚያው ዓመት በተካሄደው ምርጫ አራተኛ ደረጃ ላይ ለተቀመጠው አርኤስፒ ፓርቲ አስደናቂ እድገት ተደርጎ ተወስዷል።

እንደ ፓርቲው ሁሉ ለፖለቲካ አዲስ ሆነው ሻህ እስካሁን ድረስ ያለው ብቸኛው የፖለቲካ ልምድ የዋና ከተማዋ ካትማንዱ ከንቲባ ሆኖ ማገልገሉ ነው።

ውጤቱ በምርጫ ዘመቻ ወቅት የታየውን የለውጥ ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ነው ተብሏል። ፓርቲዎች በኔፓል ቁልፍ የወጣቶች ጥያቄ የሆኑትን ሥራ አጥነት፣ የኢኮኖሚ መዳከም እና የኢኮኖሚ ደረጃ ልዩነትን ጨምሮ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ቃል ገብተዋል።

እነዚህ ችግሮች ባሉበት ባለፈው ዓመት የማህበራዊ ሚዲያ ላይ እገዳ መጣሉ ወጣቶች የሚመሩት ተቃውሞ እንዲባባስ አድርጓል። ሰልፈኞቹ የኔፓልን የፖለቲካ ስርዓት እና የመደብ አለመመጣጠን በማንሳት አገዛዙን ተችተዋል።

በተቃውሞዎቹ ወቅት 77 ሰዎች ተገድለዋል። የቢቢሲ ምርመራ እንዳመለከተው የአገሪቱ የፖሊስ አዛዥ በሺህዎች በሚቆጠሩ ያልታጠቁ ተቃዋሚዎች ላይ ኃይል እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ተቃውሞው የወቅቱ መሪ ኬፒ ሻርማ ኦሊ ከስልጣን እንዲወርዱ አስገድዷቸዋል። በኋላም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመወዳደር ዕጩ ሆነው ቀርበዋል።

ፓርቲያቸው ሲፒኤን-ዩኤምኤል በምርጫው ሦስተኛ ደረጃን ከመያዙም በተጨማሪ፤ የደጋፊ መሠረታቸው እንደሆነ በሚነገረው ጃፓ 5 የምርጫ ክልል ጭምር በሻህ በተሸንፈዋል።

አንጋፋ የሆነው የኔፓሊ ኮንግረስ አዲሱ መሪ ጋጋን ታፓም በአርኤስፒ ተሸንፈው መቀመጫቸውን አጥተዋል።