ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ጄነራል አል ቡርሐን እና ከጀርባቸው ደብዝዘው የሚታዩ እስማላዊ ታጣቂዎች

13 መጋቢት 2026

ተሻሽሏል ከ 6 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሱዳኑን ሙስሊም ብራዘርሁድ ቡድን በተለየ ሁኔታ ዓለም አቀፍ ሽብርተኛ በማለት ከመጋቢት 7/2018 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የውጭ የሽብር ቡድን በሚል እንደፈረጀው አስታውቋል።

አሜሪካ በጄነራል አል ቡርሐን ከሚመራው የሱዳን ጦር ኃይል ጋር ግንኙነት ያለውን ይህንን ቡድን በሽብርተንነት መፈረጇ በአገሪቱ በሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ባሉ ተሳታፊዎች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል።

የሱዳን ሙስሊም ብራዘርሁድ (ሙስሊም ወንድማማችነት) ቡድን በአሜሪካ የሽብር ቡድን ለመባል ካበቁት ምክንያቶች አንዱ “በሰላማዊ ሰዎች ላይ ገደብ የሌለው ጥቃት በመፈጸም በአገሪቱ ያለውን ግጭት ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት ማደናቀፉ” እንደሆነ ተገልጿል።

“ኃይል የተቀላቀለበት እስላማዊ ርዕዮተ ዓለም” ያራምዳል የሚለውም በምክንያትነት ተጠቅሷል።

በተጨማሪም የቡድኑ ተዋጊዎች ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ሥልጠና እና ሌሎች ድጋፎችን እያገኙ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል። ሰላማዊ ሰዎችን በጅምላ በመግደልም ተከስሷል።

የቡድኑ አል-ባራ ቢን ማሊክ ብርጌድም በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ባለው ሚና ተመሳሳይ ፍረጃ ተጥሎበታል።

ቡድኑ በአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድን እና የውጭ ሽብርተኛ ድርጅት በመባሉ የተለያዩ የምጣኔ ሀብት ማዕቀቦች የሚጣሉበት ሲሆን፣ ይህ እርምጃ የትኛውንም ድጋፍ ለቡድኑ ማቅረብንም ሕገወጥ ያደርገዋል።

በሱዳን የሥልጣን የበላይነትን ለመያዝ በሚል በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና በአገሪቱ ጦር መካከል መካሄድ በጀመረው እና ሦስት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው ጦርነት ውስጥ የሙስሊም ብራዘርሁድ ቡድን ከጦር ኃይሉ አዛዥ ከጄኔራል አል ቡርሐን ጎን ተሰልፎ ይዋጋል።

መጠነ ሰፊ የጅምላ እልቂት እና ግፍ ተፈጽሞበታል በሚባለው የሱዳን ጦርነት ውስጥ ተፋላሚ ወገኖች በተለይም ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በመንግሥታቱ ድርጅት ጭምር ዘር ማጥፋት የሚመስሉ ግድያዎችን በመፈጸም ይከሰሳል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና ደጋፊዎቹ የአል ቡርሐንን ሠራዊት ብቻ ሳይሆን የሙስሊም ብራዘርሁድን ጭምር እየተዋጉ መሆናቸውን የሚገልጹ ሲሆን፣ አሜሪካ በቡድኑ ላይ ያሳለፈችውን ፍረጃ ደግፈውታል። የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ትደግፋለች ተብላ በስፋት የምትከሰሰው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስም የአሜሪካንን ውሳኔ ደግፋለች።

ሙስሊም ብራዘርሁድ እና ሱዳን

በአውሮፓውያኑ 1928 በግብፃዊው የእስልምና ምሁር ሐሳን አል-ባና የተመሠረተው ሙስሊም ብራዘርሁድ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ እና የማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ጨምሮ በርካታ ወኪሎች እና ቅርንጫፎች እስከ መመሥረት ደርሶ ነበር።

ሙስሊም ብራዘርሁድ እና ከቡድኑ ጋር ቁርኝት ያላቸው ወገኖች የእንቅስቃሴው ዋነኛ ትኩረት በአገራት ውስጥ ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ መሆኑን ይናገራሉ።

የሱዳናውያን እስላማዊ እንቅስቃሴ (ኤስአይኤም) በሚል ተጨማሪ ስም የሚታወቀው የሱዳን ሙስሊም ብራዘርሁድ እስላማዊ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ በሚካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ባለው ተሳትፎ ምክንያት ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቧል።

ቡድኑ በጦርነቱ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ በሆነው የሱዳን ጦር ኃይሎች ውስጥ ቁልፍ ሚና አለው። በጄነራል አል ቡርሐን ለሚመራው ጦር ኃይል ከ20 ሺህ በላይ ተዋጊዎችን በማሰለፍ ድጋፍ አድርጓል።

በተለይ የቡድኑ የሚሊሻ ቡድን የሆነው አል-ባራ ቢን ማሊክ ብርጌድ በጦርነቱ ውስጥ ፈጽሟቸዋል በሚባሉ ወንጀሎ ምክንያት ክስ የሚቀርብበት ሲሆን፣ ከአጠቃላይ ሙስሊም ብራዘርሁድ ቡድን ተለይቶ ማዕቀብ ተጥሎበታል።

የሱዳን ሙስሊም ብራዘርሁድ ከሚያደርገው ወታደራዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በተጨማሪ በጄኔራል አል ቡርሐን ጦር ሠራዊት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳለው ይነገራል። በዚህም የተነሳ ሱዳንን የጽንፈኛ እንቅስቃሴዎች ማዕከል ሊያደርጋት ይችላል የሚል ስጋት አለ።

አሜሪካ ከኢራን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ የሱዳን ሙስሊም ብራዘርሁድ ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት እንዳለው እና ድጋፍም እንደሚያገኝ በመጥቀስ በሽብር ድርጅትነት ፈርጃዋለች።

ከመፈጠሪያው ከግብፅ ጀምሮ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት እና በሕገ ወጥ ቡድንነት የሚታየው ሙስሊም ብራዘርሁድ፤ ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ መንግሥታትም በበጎ አይመለከቱትም። ሳዑዲ እና ኤምሬቶች ደግሞ ቡድኑን ለቀጣናዊ መረጋጋት ጠንቅ ነው ብለው ይከስሱታል።

የቡድኑ ዋና ፀሐፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አሊ ካርቲ አሜሪካ የሱዳን ሙስሊም ብራዘርሁድን በሽብር ደርጅትነት መፈረጇን ውድቅ አድርገዋል። እንቅስቃሴያቸው የአገሪቱ ሕዝብ የተሳሰረበት ማኅበራዊ ውቅር “የማይነጠል አካል ነው” እንደሆነ በመግለጽም የጉዳዩ መሠረት አስፍተውታል።

ነገር ግን በጦርነት ውስጥ የሚገኘው እና ከሙስሊም ብራዘርሁድ ጋር የጠበቀ ትስስር እንዳለው የሚነገርለት የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት የአሜሪካን ውሳኔ ደግፎታል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በኩል ፍረጃው መንግሥቱ ካለው ፀረ ዓለም አቀፍ ሽብርተኝንት አቋም ጋር የሚጣጣም ነው ብሎታል።

ይህ የመንግሥት አቋም ከቡድኑ በኩል በበጎ የሚታይ ካለመሆኑም በተጨማሪ ከጄነራል አልቡርሐን ጎን ተሰልፈው የሚዋጉትን የሙስሊም ብራዘርሁድ ታጣቂዎችን ድጋፍ የሚያሳጣው ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ቡድኑ የራሱን አሰላለፍ በመፍጠር ሌላ ተፋላሚ ኃይል ሆኖ እንዲወጣ ሊያደርገው ይችላል።

አል ቱራቢ እና ፕሬዝዳንት አል ባሺር
የምስሉ መግለጫ,አል ቱራቢ እና ፕሬዝዳንት አል ባሺር

ሙስሊም ብራዘርሁድ በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ

የሱዳኑ ሙስሊም ብራዘርሁድ በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ የረጅም ጊዜ ተሳትፎ እና ሚና አለው። ለሦስት አስርት ዓመታት በቆየው የኦማር ሐሰን አል ባሺር አስተዳደር ውስጥ ቡድኑ የአገዛዙ ቀዳሚ የርዕዮተ ዓለም እና ፖለቲካ አድራጊ ፈጣሪ ኃይል ሆኗ ቆይቷል።

ወታደራዊ መኮንን የነበሩት አል ባሺር ወደ ሥልጣን ያስወጣቸውን መፈንቅለ መንግሥት የመሩት፤ የሙስሊም ብራዘርሁድ ዋነኛ የርዕዮተ ዓለም ቀራጺ በሆኑት ሐሳን አል-ቱራቢ በጥንቃቄ ተመርጠው ነበር።

በአል ባሺር የሥልጣን ዘመን ቡድኑ በናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ (ኤልሲፒ) እና በናሽናል ኢስላሚክ ፍሮንት (ኤንኢይኤፍ) ሥር ሆኖ ነበር። በወቅቱም ሸሪአ መንግሥታዊ ሕግ እንዲሆን በማድረግ እና ከአገሪቱ ሠራዊት እና የደኅንነት ተቋማት ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት የቡድኑ አባላት ለመሆን ችለው እንደነበር ይነገራል።

በዚህም ምክንያት ቡድኑ በሱዳን አጠቃላይ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ስፍራን በመያዝ የአል ባሺርን አስተደዳር ለ30 ዓመታት ያህል በሥልጣን ላይ እንዲቆይ አስችሎታል።

ከስድስት ዓመታት በፊት አልባሺር በተካሄደባቸው ሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን ወርደው ወደ እስር ቤት ሲገቡ፣ አመራሮቹ ከፖለቲካው መንበር ላይ ገለል ቢሉም በሠራዊቱ እና በደኅነንት ውስጥ ያሉት በቦታቸው ቆይተዋል።

የአል ባሺር ከሥልጣን መወገድ ቡድኑ ከአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ እንዲገለል አላደረገም። ከፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራሩ ጋር ባለው ጥብቅ ትስስር የተነሳ ኅልውናው ቀጥሏል። የወታደራዊው ቡድን አጋር በመሆንም እየተካሄደ ባለው ጦርነት ውስጥ ቁልፍ ሚና አለው።

በለውጡ ዓመታት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ፈላጊዎች እና በወታደራዊ ኃይሉ መሪዎች መካከል የዘለቀው ፍጥጫ መስመሩን ስቶ አል ቡርሐን ሥልጣን ለመያዝ በወሰዱት እርምጃ ሱዳን ወደ ከባድ ቀውስ አመራች። የጦር ኃይሉ መሪ ጄኔራል አል ቡርሐን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ሃምዳን ዳጋሎ የበላይነትን ለመያዝ የጀመሩት ፍልሚያ ሱዳንን አፈራረሳት ነው።

በዚህ መሃል ወደ ዳር ተገፍተው የነበሩት የአል ባሺር ታማኞች እና የሙስሊም ብራዘርሁድ አባላት ውግንናቸውን ከጦር ኃይሉ ጋር በማድረግ በሚካሄደው ጦርነት ውስጥ ወሳኝ ኃይል ሆነው ብቅ አሉ።

ወሳኙ እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተዋጊዎችን የያዘው የሙስሊም ብራዘርሁድ ቡድን አል-ባራ ቢን ማሊክ ብርጌድ፤ የአል ባሺር ደጋፊዎችን እና የሙስሊም ብራዘርሁድ አባላትን አጣምሮ የያዘ ኃይል ለመሆን ችሏል። ወታደራዊ ኃይሉ በጦርነቱ ውስጥ ከአል ቡርሐን ጎን ሆኖ ከመዋጋቱ በተጨማሪ በጦርነቱ ሂደት ላይ ትልቅ ተሰሚነት ያለው አካል መሆን ችሎ ነበር።

በዚህም የተነሳ በሰላማዊ ሰዎች ግድያዎች እና ከጦርነቱ ጋር በተፈጸሙ ድርጊቶች ውስጥ ባለው ሚና ከሙስሊም ብራዘርሁድ ተለይቶ በሽብር ቡድንነት ተፈርጇል።

አሜሪካ በቡድኑ ላይ የሽብር ድርጅትነት ፍረጃን ስታስተላለፍ ከጠቀሰቻቸው ምክንያቶች መካከል ጦርነቱ እንዳይቋጭ እንቅፋቶችን ፈጥሯል የሚል ይገኝበታል።

አል ቱራቢ
የምስሉ መግለጫ,አል ቱራቢ

አል ቱራቢ እና ሙስሊም ብራዘርሁድ

ለ30 ዓመታት ሱዳንን የገዙት ኦማር ሐሳን አል ባሺር ወደ ሥልጣን እንዲመጡ በማድረግ እንዲሁም በሱዳንን እና በቀጣናው ፖለቲካ ውስጥ ተጽእኖ የነበራቸው ሐሳን አል-ቱራቢ የሱዳን ሙስሊም ብራዘርሁድ መሥራች እና መሪ ነበሩ።

አል ቱራቢ ከአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ ጀምሮ የሱዳን ሙስሊም ብራዘርሁድ መሪ በመሆን ሰፊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን፣ ቡድኑ በተለያዩ ሂደቶች ውስጥ አልፎ ቅርጽ እንዲይዝ እና እንዲጠናከር አስችለውታል።

ቱራቢ የሙስሊም ብራዘርሁድ ዓላማን ይዘው ወደ ሱዳን የፖለቲካ መድረክ ከመጡ በኋላ በአገሪቱ መንግሥት ውስጥ ሥልጣን የነበራቸው ሲሆን፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በነበሩበት ጊዜ ጥብቅ እስላማዊ ሕግ ተግባራዊ እንዲሆን አድርገዋል።

የሙስሊም ብራዘርሁድ ተጽእኖ በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቀጣናው እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥም የሚሰማ ነበር። በዚህም ሳቢያ አሜሪካ ላይ ከተፈጸመው የመስከረም 11ዱ ጥቃት በኋላ ዓለም የፀረ ሽብር ዘመቻ ከመክፈቱ በፊት ሱዳን በአል ቱራቢ መሪነት የእስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች መናኽሪያ አስከመሆን ደርሳ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 1090ዎቹ መጀመሪያ ላይ አሜሪካ በተፈጸመባት ጥቃት ምክንያት አሳድዳ የገደለችው የአል ቃኢዳ መሪ እና ቡድኑ ከመታወቃቸው በፊት በአል ቱራቢ ጋባዥነት መቀመጫውን ሱዳን ውስጥ አድርጎ ነበር።

ቱራቢ በተለያዩ የአረብ እና ሙስሊም አገራት ውስጥ የሚገኙ ታጣቂ እና እስላማዊ ቡድኖችን ለማስተባበር የሚያስችል ፖፑላር አረብ ኤንድ ኢስላሚክ ኮንግረስ የተባለ መድረክ መሥርቶ ነበር።

በአገር ውስጥም የሱዳንን ማኅበረሰብ መልሶ ለማዋቀር በሚል “የማዘመን ፕሮጀክት” የሚል እንቅስቃሴን በመምራት በአገሪቱ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ የበላይነት አስፍኖ ነበር። በዚህም የእስላማዊ እንቅስቃሴው አካል ያልሆኑ ዜጎችን ከመንግሥት እና ከወታደራዊው መዋቅሩ አጽድተዋል።

ለሱዳን ሙስሊም ብራዘርሁድ መጠናከር ከፍተኛ ሚና የነበቸራው ሐሳን አልቱራቢ የኋላ ኋላ ከፕሬዝዳንት አል ባሺር ጋር አለመግባባት ውስጥ በመግባታቸው ወደ ዳር ተገፍተው የተቃዋሚነት ሚና ይዘው ነበር።

ከአል በሺር ውድቅት እና ከአል ቱራቢ ኅልፈት በኋላ የሱዳን ሙስሊም ብራዘርሁድ ለዓመታት በመንግሥት እና በሠራዊቱ ውስጥ በተቆጣጠራቸው ቁልፍ ቦታዎች አማካኝነት በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚናን ይዞ ቆይቷል።

በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ተከሰተ በኋላ ተጽእኖውን ማሳረፍ ከሚችልበት የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ወገን በመሰለፍ የጄነራል አል ቡርሐን ደጋፊ ሆኖ ቆይቷል።

ከኢራን አብዮታዊ ዘብ ጋር ባለው ግንኙነት እንዲሁም በጦርነቱ ሂደት ውስጥ በተፈጸሙ ወንጀሎች እና ጦርነቱ እንዳያበቃ እንቅፋት በመሆን በአሜሪካ መንግሥት በሽብር ቡድንነት ተፈርጇል። ይህም ቡድኑን ብቻ ሳይሆን የሱዳን ጦር ሠራዊት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል እየተባለ ነው።