
ከ 5 ሰአት በፊት
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ሌሎች የአሜሪካ ፖለቲከኞች የሚጠቀሟቸው “የዘረኝነት ጥላቻ ንግግሮች” የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እያባባሱ ነው ሲል የተባበሩት መንግስታት ተቆጣጣሪ ቡድን አስጠነቀቀ።
በተባበሩት መንግስታት የሚደገፈው እና የዘር መድልዎ የሚከላከለው ኮሚቴ (ሲኢአርዲ) ባወጣው ሪፖርት አሜሪካ ዓለም አቀፍ ሕግን እንድታከብር እና የሰብአዊ መብት ፖሊሲዎቿን እንድትገመግም አሳስቧል።
ስደተኞችን እና ጥገኝነት ፈላጊዎችን “እንደ ወንጀለኞች ወይም ሸከም በማድረግ በመንግስት ፓርቲ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ባሉ ፖለቲከኞች እና ተደማጭነት ባላቸው ሰዎች፣ በተለይም በፕሬዚዳንቱ” መገለጻቸው የዘር መድልዎ እና የጥላቻ ወንጀሎችን ሊያነሳሳ እንደሚችል አስታውቋል።
ዋይት ሃውስ ሪፖርቱን ውድቅ በማድረግ “የማይጠቀም” እና “አድልዎ የታየበት” ሲል ጠርቶታል።
“ያላቸው ከፍተኛ መድልዎ ለምን ማንም ሰው በቁም ነገር እንደማይመለከታቸው የሚያሳይ ነው” ያሉት የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ኦሊቪያ ዌልስ፤ ትራምፕ የአሜሪካን ድንበር ለማስጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት አስታውሰዋል።
“ማንም ሰው ‘ባለሙያዎች’ ስለሚባሉት የተባበሩት መንግስታት ‘ባለሙያዎች’ ግድ የለውም፤ ምክንያቱም አሜሪካውያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ደህንነቱ በተጠበቀ እና ጠንካራ በሆነ ሀገር ውስጥ እየኖሩ ነው” ብለዋል።
መቀመጫውን በጄኔቫ ያደረገው ኮሚቴ፤ የትራምፕን የኢሚግሬሽን ማስፈጸሚያ አጀንዳ በሪፖርቱ አጉልቶ አሳይቷል። ስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ሌሎችንም በተለየ መልኩ ዒላማ የሚያደርጉት የዘፈቀደ የማንነት ማረጋገጥ ተግባራት “በጣም ያሳስቡኛል” ብሏል።
ረቡዕ ዕለት የወጣው ሪፖርት የተለዩ አጋጣሚዎችን ባይጠቅስም ግን በሚኒሶታ ለስደተኞች እስራት ምክንያት የነበረውን ‘ዘመቻ ሜትሮ ሰርጅን’ አንስቷል። ሬኒ ጉድ እና አሌክስ ፕሬቲ ሁለት የተባሉ የአሜሪካ ዜጎች በመገደላቸው በመላ አገሪቱ ተቃውሞዎችን አስነስቷል።
ከዚያ ወዲህ የትራምፕ አስተዳደር በሚኒሶታ ስደተኞችን ማሳደዱን ቀንሷል።
የተባበሩት መንግስታት ዘገባ አክሎም ሁለቱ ግድያዎች “በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ህግ መሠረት ከፍተኛ ጥሰቶች” እንደሆኑ ገልጿል።
በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት እና በአምልኮ ቦታዎች አቅራቢያ ስደተኞችን ዒላማ ያደረጉ እንቅስቃሴዎችን አሜሪካ እንድታቆም ጥሪ አቅርቧል።
ፓከዚህ በተጨማሪ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን እንደ ወንጀለኛ ወይም እንደ ሸክም አድርጎ የሚገልጹ “የዘረኝነት እና ሰብአዊነትን የሚያዋርድ ቋንቋን ጨምሮ” እየጨመረ የመጣው የዘረኝነት የጥላቻ ንግግር “በጣም እንዳሳሰበው” አስታውቋል።
ተቋሙ ቀደም ሲል ባወጣቸው ሪፖርቶቹ ባራክ ኦባማ እና ጆ ባይደንን ጨምሮ በተለያዩ አስተዳደሮች ወቅት በአሜሪካ ይታያል ያለውን ዘረኝነት እና መድልዎ አውግዟል።
ትራምፕ በሁለተኛው የስልጣን ዘመናቸው ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞችን ለማባረር ሰፊ ጥረት ጀምረዋል። ይህ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል የገቡት ጉዳይ ሲሆን ከፍተኛ ድጋፍም አስገኝቶላቸዋል።
ይህንን ቃላቸውን ለመጠበቅ እና ስደተኞችን ለማስወጣት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ሚኒያፖሊስን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላትን ወደ አሜሪካ ከተሞች አሰማርተዋል።
