ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ፋኖ የሚል ጽሁፍ ያለበት ቲሸርት ለብሰው አሜሪካ ውስጥ ተቃውሞ የወጡ ኢትዮጵያውያን

13 መጋቢት 2026

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የአሜሪካ ኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ሕግ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤት “ራሱን የፋኖ አባል አድርጎ” የገለጸን ሰለሞን ቦጋለ የተባለ ግለሰብ ወደ ኢትዮጵያ ማባረሩን አስታውቋል።

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ እየወሰደ ያለውን ጠንካራ እርምጃዎች የሚያስፈጽመው ይህ መሥሪያ ቤት፤ ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ግለሰቡ ላይ ከባድ ውንጀላዎችን አቅርቧል።

መሥሪያ ቤቱ ሐሙስ መጋቢት 4/2018 ዓ.ም. የግለሰቡን ፎቶግራፍ አያይዞ ባሠራጨው ልጥፍ ሰለሞንን የገለጸው፤ “የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፈጻሚ፣ የታጣቂ ቡድን አባል እና የዘር ማጥፋት ተጽዕኖ ፈጣሪ” በሚል ነው።

ግለሰቡ “ስደተኛ በመሆን የሚገኙ ጥቅሞች እንደተከለከለ” የገለጸው መሥሪያ ቤቱ፤ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የካቲት 26/2017 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ እንደተባረረ አስታውቋል።

ሰለሞን የተባረረው የኢሚግሬሽን መኮንኖች “በርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶችን” ካገኙ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።

በእነዚህ አካውንቶች “በይፋ ራሱን የደረጃ ሦስት የሽብር ቡድኑ ፋኖ አባል አድርጎ ገልጿል” ብሏል። “የ[ሰለሞን] ቦጋለ ልጥፎች የትግራይ ተወላጆችን ከኢትዮጵያ ‘በማጽዳት’ መሳደድ እና ጥቃት እንዲፈጸምባቸው ጥሪ አቅርበዋል” ሲልም ወንጅሏል።

በፌስቡክ ላይ ከ100 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት ሰለሞን፤ የትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም አነሳስተዋል ከተባሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎች ጋር በተያያዘ ስሙ ሲነሳ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

‘ዘ ቢሮ ኦፍ ኢንቨስቲጌቲቭ ጆርናሊዝም’ የተባለው ለትርፍ ያልተቋቋመ የምርመራ ጋዜጠኝነት ማዕከል ላይ በአውሮፓውያኑ 2022 የወጣ አንድ የምርመራ ዘገባ ሰለሞንን ጠቅሶታል።

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።Accept and continue

ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።

የ X ይዘት መጨረሻ

ዘገባው፤ ፌስቡክ የማኅበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔር ተኮር ግድያ እንዲፈጸም እንዲያነሳሱ አስችሏል በሚል በተጎጂዎች ስለቀረበበት ክስ ያትታል።

ዘገባው ውስጥ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ውስጥ የተገደሉ አንድ የትግራይ ተወላጅ ታሪክን በማሳያነት የተጠቀሰ ሲሆን፣ ቤተሰቦቻቸው ግድያ እንዲፈጸም “አነሳስቷል” በሚል ካነሷቸው ልጥፎች አንዱ የሰለሞን ቦጋለ ነው።

ቢቢሲ፤ በአሜሪካ ኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ሕግ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤት የቀረበውን ውንጀላ በተመለከተ የሰለሞንን አስተያየት ለማካተተት ያቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘም። ይሁን እንጂ ሰለሞን ሐሙስ ምሽት ‘ዘ ሃበሻ’ ለተባለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን በሰጠው ቃለ ምልልስ የቀረቡበትን ክሶች ውድቅ አድርጓል።

ሰለሞን፤ “ለሁለት ወር ገደማ” ታስሮ ወደ ኢትዮጵያ መባረሩን ያረጋገጠ ሲሆን፣ በቁጥጥር ስር የዋለው “ለጥገኝነት ጥያቄ ቀጠሮ” ወደ ፍርድ ቤት በሄደበት ወቅት እንደሆነ ተናግሯል።

“የሐሰት መረጃ” እንደቀረበበት እና “ዘመቻ” እንደተደረገበት የገለጸው ሰለሞን፤ “እንደ ሕዝብ” ጥቃትን የሚያነሳሳ ጽሑፍ እንዳላጋራ በመግለጽ አስተባብሏል።

ታጣቂው ኃይል ፋኖ የተገለጸበት “ደረጃ ሦስት የሽብር ቡድን” ምንድነው?

የአሜሪካው የስደተኞች ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት፤ ሰለሞን “አባል የሆነበት” የፋኖ ኃይል “በደረጃ ሦስት የሽብር ቡድንነት” የተመደበ እንደሆነ መግለጹ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ ሆኗል።

የአሜሪካ የዜግነት እና ኢሚግሬሽን አገልግሎት መረጃ እንደሚያመለክተው እዚህ ምድብ ውስጥ የተካተቱ ቡድኖች አባል የሆኑ ግለሰቦች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ ሊከለከሉ እና በስደተኝነት የሚሰጡ ጥቅሞችን እንዳያገኙ ሊደረጉ ይችላሉ።

ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዙ ድርጊቶች “በአንጻራዊነት ሰፊ” እንደሆኑ የሚጠቅሰው የመሥሪያ ቤቱ መረጃ፤ “ብዙውን ጊዜ ከሽብርተኝነት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በማይታሰቡ ግለሰቦች እና እንቅስቃሴዎች ላይም ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል” አስፍሯል።

ግለሰቦች ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ከሚያስከለክሏቸው ምክንያቶች መካከል በሰዎች ላይ “ከፍተኛ ጉዳት ወይም ሞት ለማድረስ በማሰብ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴን ማነሳሳት” የሚለው ይገኝበታል። “የሽብርተኛ ድርጅት ተወካይ ወይም አባል መሆን” እንዲሁም “የሽብር ድርጊቶችን መደገፍ” ከምክንያቶቹ መካከል ናቸው።

በመሥሪያ ቤቱ አሠራር መሠረት የሽብር ቡድኖች በሦስት ደረጃዎች ይከፈላሉ። በደረጃ አንድ ላይ የሚቀመጡት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሽብርተኛ ተብለው የሚፈረጁ የውጭ ድርጅቶች ናቸው።

በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገቡት “የሽብር ድርጊቶች ውስጥ የሚሳተፉ” ወይም በእንደዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ “አቅም እና ዓላማው” ያላቸው መሆን አለባቸው። የሽብር ድርጊታቸው የአሜሪካ ዜጎችን ወይም የአሜሪካን ብሔራዊ ደኅንነት “አደጋ ላይ የሚጥል” መሆን አለበት የሚለውም ከመስፈርቶቹ መካከል ነው።

የአይስ ፖሊሶች
የምስሉ መግለጫ,የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር በኢሚግሬሽን ፖሊሶች አማካኝነት ስደተኞች ላይ የሚወስደውን እርምጃ ያጠናከረ ሲሆን የጸጥታ ኃይሎቹ እንቅስቃሴ በበርካታ ስፍራዎች ተቃውሞ ገጥሞታል

ደረጃ ሁለት ላይ የሚቀመጡት ለኢሚግሬሽን ዓላማ ሲባል በሽብርተኝነት የሚፈረጁ ቡድኖች ናቸው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጋር በመመካከር ወይም በዐቃቤ ሕግ ጥያቄ ሊፈርጃቸው ይችላል።

በዚህ ደረጃ ከሚፈረጁ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸው የውጭ ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ይታገዳሉ።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው የፋኖ ኃይል በተጠቀሰበት ሦስተኛ ደረጃ ውስጥ የሚካተቱ ቡድኖች ደግሞ ሁለቱ ምድቦች ውስጥ ከሚገቡት ድርጅቶች በተለየ ሁኔታ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የተፈረጁ አይደሉም።

በዚህ ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ድርጅቶች “ያልተፈረጁ የሽብር ድርጅቶች” ተብለውም እንደሚጠሩ የአሜሪካ የዜግነት እና ኢሚግሬሽን አገልግሎት መረጃ ያመለክታል።

“ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ግለሰቦችን የያዘ ቡድን” በዚህ ውስጥ እንደሚካተት የሚገልጸው መረጃው፤ “ተደራጁ ወይም ያልተደራጁ” ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቅሷል። በሽብር ድርጊት ውስጥ “የሚሳተፉ ወይም የሚሳተፍ ንዑስ ቡድን” ያላቸው ድርጅቶች እዚህ ምድብ ውስጥ እንደሚገቡ ተገልጿል።

“ልክ እንደ ደረጃ አንድ እና ደረጃ ሁለት ድርጅቶች መደበኛው የፍረጃ ሂደት ውስጥ ባያልፉም ድርጊቶቻቸው ብቻውን እንደ ሽብር ድርጅት ለመቆጠር ያበቋቸዋል” ሲል ያብራራል።

መሥሪያ ቤቱ እንደሚያስረዳው፤ አንድ ቡድን ‘ደረጃ ሦስት የሽብር ድርጅት’ ተብሎ ይጠራ አይጠራ የሚለው የሚወሰነው በአጠቃላይ ፍረጃ አይደለም።

ይልቁንም “የኢሚግሬሽን ጥቅም ለማግኘት የሚቀርብ ማመልከቻ ላይ ከሚደረግ ግምገማ ጋር በተያያዘ በእያንዳንዱ ኬዝ ላይ” ውሳኔ እንደሚሰጥ የመሥሪያ ቤቱ መረጃ ይገልጻል። “የደረጃ ሦስት ድርጅቶች [ምደባ] በየጊዜው የሚነሳ እና የሚለወጥ” እንደሆነም ተብራርቷል።

ሰለሞን በሰጠው ቃለ መጠይቅ በቁጥጥር ስር የዋለው የስደተኝነት ማመልከቻውን በተመለከተ ለተሰጠው ቀጠሮ ፍርድ ቤት በተገኘበት ሰዓት እንደሆነ ተናግሯል። ውንጀላው የቀረበበትም በትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዙ የፌስቡክ ልጥፎች እንደሆኑ ጠቁሟል።

በስደተኞች ላይ ጠንካራ እርምጃዎች እየወሰደ ያለው የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር፤ ከዚህ ቀደም ቪዛ የተሰጣቸው ሰዎችን የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎች እየተከታተለ እርምጃ ለመውሰድ ይጠቀማል የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር።

ይህንን ክስ ያቀረቡት የአሜሪካ የሠራተኛ ማኅበራት እርምጃው ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ይጋፋል ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቦ ነበር።

በወቅቱ ለዚህ ክስ ምላሽ የሰጡት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ምክትል ቃል አቀባይ፤ “ሽብርን የሚደግፉ” የውጭ ዜጎችን የመቀበል ግዴታ የለብንም ብለዋል።