ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የኩባ ፕሬዚዳንት ሚጌለ ዲያዝ-ካነል በብሪክስ ጉባዔ ላይ
የምስሉ መግለጫ,የኩባው ፕሬዚዳንት ዲያዝ-ካነል የአገራቸው የኤሌክትሪክ ማከፋፈያዎች እጅግ በጣም “ይዋዥቃሉ” ሲሉ አገሪቱ የገጠማትን ችግር ያስረዳሉ

14 መጋቢት 2026, 07:41 EAT

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኩባ ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ-ካኔል የካሪቢያን አገራት አሜሪካ ባደረገችው የነዳጅ እቀባ የተነሳ ተጽዕኖዎች እየገጠሟት በመሆኑ፣ የሁለቱን አገራት ልዩነት ለመፍታት መንግሥታቸው ከትራምፕ አስተዳደር ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ተናገሩ።

ዲያዝ-ካኔል ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ምንም ዓይነት ነዳጅ ወደ ኩባ አለመግባቱን ተናግረዋል።

አርብ ዕለት በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ በተላለፈ ንግግራቸው በሁለቱ አገራት መካከል የተጀመረው ውይይት ገና መጀመሩን እና የአገራቸውን ተደራዳሪ ልዑክ የሚመሩት ፕሬዝዳንት ዲያዝ-ካኔል ለሕዝባቸው ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ዕለት የኩባ መሪዎች “በፈቃደኛ ሥልጣናቸውን ያስረክቡ” ሲሉ ባስፈራሩበት ወቅት አገሪቱ “ከባድ ችግር ውስጥ ገብታለች” ብለው ነበር።

ኩባ ከአሜሪካ በሚደርስባት ጫና የተነሳ የገጠማት የነዳጅ እጥረት በተደጋጋሚ በአገሪቱ የኃይል መቆራረጥ እንዲፈጠር አድርጓል።

ትራምፕ ዳግመኛ ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ የኩባን አመራር የመቀየር ፍላጎታቸውን በግልጽ ተናግረዋል። በተጨማሪም ለኩባ ነዳጅ ከሚሸጥ ማንኛውም አገር ወደ አሜሪካ የሚገቡ እቃዎች ላይ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚጣል አስጠንቅቀዋል።

ዋይት ሐውስ አርብ ዕለት ለቢቢሲ “ፕሬዝዳንቱ ከኩባ ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል፤ መሪዎቿ ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው፤ ይህም ስምምነት ‘በቀላሉ ሊደረስበት የሚችል ነው’ ብለው ያምናሉ” ብሏል።

ሃቫና ለኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታዋ ከውጭ በምታስገባው ነዳጅ ላይ የምትተማመን ቢሆንም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሜሪካ ወደ አገሪቱ የሚሄዱ በርካታ የነዳጅ መርከቦችን በቁጥጥር ስር አውላለች።

ቬንዙዌላ ወደ ኩባ በቀን 35,000 በርሜል ዘይት ትልክ እንደነበር ይታመናል። ይህም የደሴቲቱን የነዳጅ ፍላጎት ግማሽ ያህሉን ይሸፍናል። ነገር ግን በጥር ወር መጀመሪያ ላይ ዋሽንግተን ቬንዙዌላን መውረር እና የፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በቁጥጥር ሥር ማዋል በርካታ ነገሮቸን አስተጓጉሏል።

ዲያዝ-ካኔል በቴሌቪዝን በተላለፈው ንግግራቸው ባለፉት ሦስት ወራት ነዳጅ ወደ ኩባ አለመግባቱ የናፍጣ እና የነዳጅ ዘይት ክምችት ቀስ በቀስ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል ብለዋል። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ማሠራጫ ከጊዜ ወደ ጊዜ “ያልተረጋጋ” እንዲሆን አድርጓል ብለዋል።

ኩባ ይህ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የአገር ውስጥ የነዳጅ እና የጋዝ ምርት እንዲሁም የፀሐይ ኃይል ማመንጫን ከፍ ማድረጓን ገልጸዋል።

አሜሪካ እና ኩባ የኮሚኒስት መሪ ፊደል ካስትሮ በአውሮፓውያኑ 1959 በአሜሪካ የሚደገፍ መንግሥትን ከገለበጡ ወዲህ ግንኙነታቸው ሻክሮ ቆይቷል።

ከ1960ዎቹ ጀምሮም አሜሪካ ማዕቀቦች እና የንግድ እገባዎችን በኩባ ላይ ተግባራዊ አድርጋለች።

ደሴቲቱ አገር ኩባ ከፍሎሪዳ በስተደቡብ 145 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች። ከቅርበቱ የተነሳ በሃቫና ፖለቲካ የማይስማሙ ብዙ ኩባውያን ወደ አሜሪካ ይሰደዳሉ፣ ይህም የፍሎሪዳ ዋና ከተማ ማያሚ በርካታ ትውልደ ኩባውያን መኖሪያ አድርጓታል።

አሜሪካ እና ኩባ በጀመሩት ድርድር ላይ ትራምፕ ከኩባ ተሰድደው ከመጡ ቤተሰቦች የተወለዱት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ተሳታፊ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሩቢዮ በየካቲት ወር ባደረጉት ንግግር ኩባ መለወጥ እንዳለባት ተናግረዋል።

“በከፍተኛ ሁኔታ መለወጥ አለባት፤ ምክንያቱም የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ያለው ብቸኛ ዕድል ይህ ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በተጨማሪም፣ ኩባ ከቫቲካን ጋር ከተነጋገረች በኋላ “መልካም ፈቃዷን” ለማሳየት በሚል በሚቀጥሉት ቀናት 51 እስረኞችን እንደምትለቅ የሃቫና መንግሥት አስታውቋል።

አገሪቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪጌዝ በቫቲካን ከሊቀ ጳጳስ ሊዮ ጋር ከተገናኙ ሳምንታት በኋላ ነው።

ኩባ የሚፈቱት ሰዎች የፖለቲካ እስረኞችን ያካትት እንደሆነ ባትገልጽም ሁሉም “ለረዥም ጊዜ ታስረው እንደቆዩ እና በእስር ቤት እያሉም መልካም ምግባር እንዳላቸው” ተናግራለች።

የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአውሮፓውያኑ 2010 ጀምሮ ሃቫና ለ9,905 እስረኞች ይቅርታ ማድረጓን አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ሌሎች 10,000 እስረኞች ተፈትተዋል ብሏል። መንግሥት ውሳኔው “ሉዓላዊ” እና በክርስቲያኖች የቀን አቆጣጠር ውስጥ ከሚጠበቀው ቅዱስ ሳምንት ጋር የሚስማማ ነው ብሏል።