
14 መጋቢት 2026, 07:30 EAT
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ
የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫን ከመሠረቱ አገር መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት።
በአውሮፓውያኑ 1957 የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ካርቱም ላይ ሲዘጋጅ ተሳታፊ የሆኑት ሦስቱ አገራት ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና ግብፅ ነበሩ።
የአፍሪካ ዋንጫ ከሦስት አገራት ተነስቶ አሁን 24 የአፍሪካ አገራት ብሔራዊ ቡድኖችን የሚሳተፉበት ቢሊዮኖች በተለያዩ አማራጮች የሚመለከቱት አህጉራዊ ውድድር ሆኗል።
አፍኮን 2025 በሞሮኮ ሲካሄድ 6 ቢሊዮን ሰዎች በዲጂታል አማራጮች እንደተመለከቱት የአህጉሪቱ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ የሆነው ካፍ መረጃ ያሳያል። ይህ ቁጥር ክብረ ወሰን የሰበረ ነው።
የአፍሪካ ዋንጫ በሚቀጥለው የአውሮፓውያኑ ዓመት በኬንያ፣ በታንዛኒያ እና በኡጋንዳ በጥምረት ይዘጋጃል። የአፍሪካ ዋንጫ በ2028 ድጋሚ ይካሄዳል። ይህ በየሁለቱ ዓመቱ የሚዘጋጀው የአህጉሪቱ የእግር ኳስ ውድድር የመጨረሻው መርሃ ግብር ይሆናል። ካፍ ከ2028 በኋላ ውድድሩን በየአራት ዓመቱ ለማድረግ ወስኗል።
ኢትዮጵያ ለብቻዋ ደቡብ አፍሪካ እና ቦትስዋና ደግሞ በጥምር የ2028ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ያላቸውን ፍላጎት ይፋ አድርገዋል።
ለመሆኑ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የማዘጋጀት አቅም አላት? ካፍ የሚጠይቀው መስፈትስት ምንድነው?
ኢትዮጵያ የካፍን መስፈት ታሟላለች?
በአውሮፓውያኑ 2030 የዓለም ዋንጫን በጋራ ለማዘጋጀት እየተዘጋጀች ያለችው ሞሮኮ የታደሱ እና አዲስ የተገነቡ 9 ስታድየሞችን አሳይታለች።
የፈረንሳዩ ሌ ሞንድ ጋዜጣ ሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት 21 ቢሊዮን የሞሮኮ ድርሀም አሊያም 2.1 ቢሊዮን ዶላር እንዳወጣች ዘግቧል። ከዚህ ውስጥም 2 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነውን ወጪ መንግሥት ከኪሱ የሸፈነው ነው።
የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ የሆነው ካፍ አዘጋጅ አገር መሥፈርት የሚያሟሉ ቢያንስ 6 ስታድየሞች እንዲኖሯት ይጠይቃል። ሁለቱ ስታድየሞች 40 ሺህ እና ከዚያ በላይ ተመልካች ማስተናገድ አለባቸው። አልፎም ከስታድየሞቹ አቅራቢያ የመለማመጃ ሜዳዎች እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች መገንባት አለባቸው።
ስታድየሞች የመገናኛ ብዙኃን ማዕከል፣ የቪኤአር ክፍል እንዲሁም የሕክምና መስጫ ሥፍራዎች ሊኖራቸው ግድ ይላል።
ደረጃቸውን እና ደኅንነታቸውን የጠበቁ አየር ማረፊያዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ሆቴሎች እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎቶች አዘጋጅ አገር ልታሟላቸው የሚገቡ መሥፈርቶች ናቸው።
ኢትዮጵያ በ2028 ሊካሄድ የታቀደውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ፍላጎት እንዳላት በይፋ ማሳወቋን ተከትሎ የተደበላለቁ አስተያየቶች ሲሰጡ ይሰማሉ።
ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ እና ለሌሎች ኤፍኤም የሬዲዮ ጣቢያዎች ላለፉት በርካታ ዓመታት በስፖርት ጋዜጠኝነት ያገለገሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን ግለሰብ የሞሮኮን የዝግጅት ሰነድ “ተመልክቸው ነበር” ይላሉ።
“እነሱ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት የነበራቸው ዝግጁነት እና የእኛ ዝግጀት ልዩነት ሳየው ፍፁም መራራቅ አለበት” ይላሉ።
“የአፍሪካ ዋንጫን የሚያክል ትልቅ ውድድር ይቅርና አንዳንድ ጊዜ ትኩረት የሚስቡ ፕሮግራሞችን (ኢቨንቶችን) ለማዘጋጀት እንችላለን ወይ? የሚለውን ሳስብ ክፍተት እንዳለ አምናለሁ።”
እሳቸው እንደሚሉት የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት አንድ ወይም ሁለት ስታድየም የመገንባት ጉዳይ ብቻ አይደለም።
“ለምሳሌ የባሕር ዳር ስታድየም ቢጠናቀቅ ከተማዋ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የበቁ ሆቴሎች አሏት ወይ?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
“የመለማመጃ ሜዳ ያስፈልጋል፤ በዙሪያው ጂምናዚየሞች፣ መዋኛ ገንዳዎች፤ ብሔራዊ ቡድኖች ከጨዋታ በፊት እና በኋላ ልምምድ የሚያደርጉባቸው ቦታዎች፣ መዝናኛ ሥፍራዎች፣ የከተማ ትራንስፖርት፣ ኢንተርኔት፤ ባቡር. . . እኛ አሁን ያለን መሠረተ ልማት የተሳለጠ የሚባል አይደለም።”

በአሜሪካ ሜሪላንድ ቶውሰን ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት የስፖርት ሳይንስ ባለሙያው ጋሻው አበዛ (ዶ/ር) በተቃራኒው ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት የሚያስችል አቅም እንዳላት የሚያሳይ ዕቅድ ካስገባች ሊሳካለት ይችላል ይላሉ። ባለሙያው ዕቅዱ ሲገባ አንኳር ጉዳዮችን መዳሰስ እንዳለበት ያስረዳሉ።
“የመጀመሪያው አስተማማኝ የሆነ የመሠረተ ልማት ዕቅድን ማሳየት ነው። አንዱ የብቃት መመዘኛ መሠረተ ልማት ነው እና ካለ እሰየው ከሌለ ግን ዝግጅቱ ምንድነው የሚመስለው? ስታድየሞች፣ የመለማመጃ ሥፍራዎች፣ ሆቴሎች እና የመጓጓዣ አገልግሎቶች እንደሚዘጋጁ እርግጠኛ በሆነ እና ተዓማኒ በሆነ የጊዜ ሰሌዳ የሚያሳይ ሰነድ ማቅረብ ነው።”
ጋሻው (ዶ/ር) እንደሚሉት መንግሥት ለዝግጅቱ ያለውን ድጋፍ የሚያሳይ ከሆነ፤ አዘጋጅ ኮሚቴው ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ከተመራ፤ ውድድሩ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ዕድገት ጥሎ የሚያልፈው አዎንታዊ ፋይዳ በደንብ ከተንፀባረቀ እንዲሁም ደኅንነት ከተጠበቀ እና ቴክኖሎጂው እንዳለ ማሳየት ከቻለች ኢትዮጵያ የማዘጋጀት ዕድሏ የሰፋ ይሆናል።
የስፖርት ጋዜጠኛው ግን ለማዘጋጀት የተሰጠው ጊዜ አጭር በመሆኑ “ሰርገኛ መጣ ዓይነት ሩጫ እንዳይሆን” ሲሉ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።
“በእኔ እምነት የሚመጡት ሁለት ዓመታት ለዕቅድ ሳይሆን የዝግጅት ማጠናቀቂያ ጊዜ መሆን ነው ያለባቸው። የሚያስፈልጉ ሥራቸው የሚጠናቀቁበት ጊዜ ነው። የመጨረሻው አንድ ዓመት ደግሞ የልምምድ (ሪኸርሳል) ጊዜ ነው። እንግዶች እንዴት ነው የምንቀበለው? ምግብ እና መጠጥ የሚያቀርቡት እነማን ናቸው? ሌሎችም ዝግጅቶችን የሚፈተሹበት ጊዜ ነው።”
ጋሻው (ዶ/ር) የካፍን መስፈርት የሚያሟሉ ስታድየሞች አለመኖራቸው ፈታኝ መሆኑን ቢያምኑም፤ ዕቅዱን ከማቅረብ ሊያግደን ግን አይገባም ይላሉ።
“አንዲት አገር አህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ውድድር ለማዘጋጀት ስትነሳ የሚታየው የሚያስተማምን ዕቅድ ማቅረቧ ነው። ካፍ የሚያየው ያለንን ሳይሆን አገሪቱ የሚያስፈልገውን ነገር ውድድሩ እንዲካሄድ በተያዘለት ጊዜ ማሟላት ትችላለች ወይ የሚለው ነው” ሲሉ ይከራከራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት ቁርጠኛ ከሆነች ከዕቅድ በተጨማሪ መሥራች አገር መሆኗን፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንደሆነች፤ ደጋፊዎች ለእግር ኳስ ያላቸውን ፍቅር፤ የቱሪስት መስኅቦችን፤ ሰፊ ተደራሽነት ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ሚና እና የመሳሰሉ ጉዳዮችን አጉልታ በማሳየት ዕድሏን ማስፋት ትችላለች።
በአውሮፓውያኑ 2010 የዓለም ዋንጫን ያስተናገደችው ደቡብ አፍሪካ ከቦትስዋና ጋር በመሆን የ2028 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት እንደምትፈልግ ማሳወቋ ፉክክሩን ለኢትዮጵያ ፈታኝ እንደሚያደርገው ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ ሞሮኮ ድጋሚ ዋንጫውን ለማዘጋጀት ፍላጎት እንዳላት ገልፃለች።
ከሰሜን አፍሪካዊቷ አገር በፊት የተካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ የምዕራብ አፍሪካ አገር ማስተናገዷ፤ የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ አገራት መዘጋጀቱ ምናልባት ካፍ ፊቱን ወደ ደቡባዊ አፍሪካ ሊያዞር ይችላል የሚል ግምት አጭሯል።

የ2032 የአፍሪካ ዋንጫ
የስፖርት ሳይንስ ባለሙያው ጋሻው አበዛ (ዶ/ር) “አዲስ አበባ ላይ የሚከናወነው የመሠረተ ልማት ግንባታ ስትመለከት የማዘጋጀት አቅም እንዳለን የሚያመላክት ነው” ይላሉ።
“ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም” ሲሉ ሐሳባቸውን ያፀናሉ።
የስፖርት ጋዜጠኛው ግን በተለይ አሁን ያለው የፀጥታ ስጋት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ እና ለማዘጋጀት ዝግጁ እንዳልሆነች ያሳያል ሲሉ ይሞግታሉ።
“ብሔራዊ ቡድኖች ብቻ አይደለም የሚመጡት፤ ደጋፊዎች ይመጣሉ። በዚያ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መኖሩ ሰዎች እንዲመጡ ቀላል ያደርገዋል። የጉዞ እግድ ብዙም የለም። የቪዛ ጉዳይ ብዙ አያሳስብም። ስለዚህ ብዙ እንግዶች እንደሚመጡ ይጠበቃል።”
ኢትዮጵያ የ2028 የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ብትመረጥ ውድድሩን ያስተናግዳሉ ተብለው የሚጠበቁት አዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር፣ ሐዋሳ እና ድሬዳዋ ስታድየሞች መሆናቸውን ጋዜጠኛው ያወሳሉ።
“ሁሉም ስታድየሞች የካፍን መስፈርት ሙሉ በሙሉ የሚያሟሉ አይደሉም። ጊዜው በጣም አጭር ነው። እኛ የመጨረሻ የዝግጅት ጊዜ ተብሎ በሚጠራው ወቅት ነው ዕቅድ እያወጣን ያለነው።”
የስፖርት ጋዜጠኛው ኢትዮጵያ በ2032 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ብትሞክር መልካም ነው ይላሉ።
“ነገር ግን ሥራችንን መቀጠል ይኖርብናል። ከዚያ በፊት ራሳችንንም ብንፈትን መልካም ነው። ለምን የቻን ዋንጫን (አፍሪካ ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚሳተፉበት) ለማዘጋጀት አንሞክርም? ሴካፋን ካዘጋጀን እኮ ቆየን። እነ ሩዋንዳ እኮ ጥለውን ሔደዋል።”
ጋሻው (ዶ/ር) የ2028 የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት እንችላለን ብለው ቢያምኑም፤ በጋዜጠኛው አማራጭ ሐሳብ ግን ይስማማሉ።
“ነገር እንደ አማራጭ የሚቀጥለውን [2032] ብናዘጋጅ የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ። ቢሆንም ሥራውን መጀመር ያለብን ግን ዛሬ ነው። የሚቀጥለውን ብናዘጋጅ የአገራችንን ገፅታ የበለጠ ገንብተን ለመጠበቅ ሊጠቅመን ይችላል። ማስመር የምፈልገው ግን ሥራውን መጀመር ያለብን ዛሬ ነው።”
ቢቢቢ ኢትዮጵያ የ2028 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ለካፍ ማመልከቻ ማስገባቷን በተመለከተ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
