
14 መጋቢት 2026, 07:29 EAT
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ
በኦሮሚያ ክልል፣ በሰሜን ሸዋ ዞን በአንዲት የሰባተኛ ክፍል ታዳጊ ተማሪ ላይ የተፈጸመው ድርጊት የአካባቢውን ነዋሪ ከማሳዘን አልፎ ስጋት ውስጥ ከትቶታል።
ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ በቅርቡ አንዲት የ17 ዓመት ታዳጊ ተጠልፋ ወደ ገደል በመወርወሯ ከሞት ብትተርፍም የጀርባ አጥንቷ ተሰብሮ እጅ እና እግሯን ማዘዝ የማትችልበት ከባድ የአካል ጉዳት ስለደረሰባት ነው።
የነዋሪው ፍርሐት ምንጭ የሆነው ጉዳይ ከዚህም ከፍ ይላል፤ በአካባቢው ያለው የፀጥታ ችግር እና ከእርሱ ጋር ተያይዞ እየተስፋፋ የመጣው ጠለፋ ታዳጊ ሴቶችን ከትምህርታቸው ከማስተጓጎሉ ባሻገር ለአካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት መዳረጉ ነው።
ተምራ ለትልቅ ቦታ ትደርስልኛለች ብለው የሚጠብቋት ልጃቸው በጠላፊዎች በተፈጸመባት ጥቃት ለከባድ አካል ጉዳት የተዳረገችባቸው እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት አባት ልጃቸው መንቀሳቀስ የማትችል ጉዳተኛ ሆናለች።
አባት ልጃቸው አስፈላጊው ሕክምና እንድታገኝ ቢጥሩም በለጋ ዕድሜዋ ቦርቃ ያልጠገበችው ልጃቸው ስብራቷ ተጠግኖ፣ ጤናዋ ተመልሶላት ከዊልቸር ላይ ተነስታ ከእኩዮቿ ጋር ወደ ትምህርት ቤቷ ልትመለስ አልቻለችም።
የዞኑ ትምህርት ቢሮ እንዳለውም በአካባቢው ትምህርት ቤቶች እየተዘጉ ያሉት እየጨመረ ባለው የሴቶች ጠለፋን ጨምሮ በፀጥታ ስጋት ነው።
በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ኩዩ ወረዳ በጠላፊዎቿ ወደ ገደል የተወረወረችው ታዳጊ ተማሪ ጉዳይ በአካባቢው ቁጣ የፈጠረ ክስተት ሆኗል። ወላጅ አባቷ እንደሚናገሩት ድርጊቱን የፈጸሙትን ግለሰቦች “በድፍረት ለሕግ ለማቅረብ የሞከረ” የለም።
“ልጄ በትምህርቷ 1ኛ ነበረች። ወንጀለኞች በአጭር አስቀሯት እንጂ” ሲሉ አባትየው በቁጭት ተናግረዋል።
ልጃቸው ወደ ትምህርት ቤት እየሄደች ሳለ “ሰባት ጎረምሶች በጩቤ አስፈራርተው እንደጠለፏት” ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“ልጄ በወቅቱ ከተማሪዎች እና ከአስተማሪዎቿ ጋር ነበረች። ወንጀለኞቹ ግን ሁሉን አስፈራርተው ካባረሯቸው በኋላ እሷን እየጎተቱ በግድ ይዘዋት ሄዱ። መንገድ ላይ አልሄድ ብላ ስታስቸግራቸው ግን በዚያው ወደነበረ ገደል ወረወሯት።”
ልጃቸው በሕይወት ብትተርፍም የጀርባ አጥንቷ ተሰብሮ እጅ እና እግሯን ማዘዝ እንደማትችል ገልጸዋል።
“በሕይወት ተረፈች። ራሷ ስታ ስለነበረ ሞታለች ብለው ቅጠል ላይዋ ላይ አስቀምጠው ሄዱ። እኛ ጉዳዩን ሰምተን ወደ ቦታው ሄደን ተረባርበን ወደ ሐኪም ቤት ወሰድናት” ብለዋል።
የወረዳው ጤና ጣቢያ ከአቅሙ በላይ ስለሆነ ልጃቸው ወደ ፍቼ ሆስፒታል እንደተወሰደች ገልጸዋል።
“እዚያም አልተቻለም። ወደ ሌላ ሆስፒታል ተወሰደች። እኔ እርሻዬን ትቼ እሷን ለማሳከም ተንከራተትኩ። ያለኝን ጥሪት ጨረስኩ” ብለዋል አባት።
ይህን ወንጀል የፈጸሙት ወጣቶች በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዳልዋሉ እና እንዲያውም ቤተሰቡን እያስፈራሩ እንደሆነ ወላጅ አባት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በሕግ ቁጥጥር ሥር አልዋሉም። እያስፈራሩን ነው። ቤተሰቡንም ያስፈራራሉ። አሁን ልጄ በዊልቸር ላይ ነው ያለችው። ተቸገርን። የጀርባ አጥንቷ ነው የተሰበረው። ጭንቅላቷም ሦስት ቦታ ተፈንክቷል። ከባድ ጉዳት ነው የደረሰባት። እጇም እግሯም አይንቀሳቀስም።”
የሰሜን ሸዋ ዞን የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሹ አክሊሉ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ በዞኑ ዘጠኝ ወረዳዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት በብዙ ቦታዎች የመማር ማስተማር ሂደት መስተጓጎሉን ተናግረዋል።
“ሴት ልጆች ከትምህርት ቤት እንዲቀሩም ሆኗል። በጉልበት ሴት ልጆች በየጊዜው ይጠለፋሉ። ተከሰው በፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታየ ያሉም አሉ” ብለዋል።
በዞኑ ዘጠኝ ወረዳዎች ጠለፋን ጨምሮ በሌሎችም ስጋቶች 87 ተማሪዎች ትምህርት ማቆማቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ ችግሩ በስፋት የሚስተዋልባቸው ትምህርት ቤቶች የሚገኙት በደራ፣ ግራር ጃርሶ፣ ሂዳቡ አቦቴ፣ ሙሌ እና ወረ ጃርሶ ወረዳዎች እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከትምህርት ቤት የቀሩት ተማሪዎች በአጠቃላይ ምክንያታቸው ጠለፋ ባይሆንም ሴት ተማሪዎች ግን ጠለፋን ጭምር ፈርተው ትምህርት ማቋረጣቸውን ተናግረዋል።
“በኩዩ ወረዳ ከአንድ ትምህርት ቤት አምስት ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ተጠልፈዋል። በተመሳሳይ ያያ ጉለሌ ወረዳ ከትምህርት ቤት ውስጥ የተጠለፈች ሴት ልጅ አለች” ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም “ይሄ ብቻ ሳይሆን ተደፍረው የወለዱ አዳጊዎች አሉ። በዚህ የተነሳ ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ። እኔ ራሱ ተጠልፋ እንድትወልድ የተገደደች እና ትምህርቷን ያቆመች ልጅ አጋጥማኛለች” ሲሉ ተናግረዋል።
“ስትጠለፍ የፀጥታ አካላት ጠላፊዎቹን ተከታትለው ታጣቂዎች ያሉበት ቦታ ሲደርሱ ነው የተመለሱት። በጠራራ ፀሐይ ነው የጠለፏት” በማለትም ተናግረዋል።
ልጃቸው በጠላፊዎች ከገደል የተወረወረችባቸው አባት “ልጄ በትምህርቷ ጎበዝ ተማሪ ነበረች። ትምህርት እየወደደች ከትምህርቷ አፈናቀሏት። ወንጀለኞች ከጓደኞቿ በታች አደረጓት” ብለዋል።
የሰባተኛ ክፍል ተማሪ የነበረችው ልጃቸው “ሁልጊዜ 1ኛ ስለምትወጣ ትልቅ ደረጃ ትደርሳለች” ይሉ እንደነበር የገለጹት አባት “በአጭር አስቀሯት። በሰው ልጅ ላይ መድረስ የሌለበት ነገር ነው የደረሰባት” በማለት ሐዘን በተጫነው ድምጽ ተናግረዋል።
አባትየው አክለውም “ተወልደን ባደግንበት አገር ነው ይሄ የተፈጸመብን። ይህን የፈጸሙትን በሕግ ለመጠየቅም የደፈረ የለም። እነዚህ ሰዎች በሌላ ሴት ልጅ ላይም ተመሳሳይ ወንጀል ሊፈጽሙ ይችላሉ” ብለዋል።
“በዚህ አገር ሴቶች መብት አላቸው ይባላል። ምን መብት አላቸው? የታለ መብታቸው? ልጄ በተጠለፈችበት ቀን ሌሎች ሦስት ልጆች ተጠልፈዋል። ሦስቱም ከዚያው ትምህርት ቤት ነው የተጠለፉት። መንግሥት እንዲያግዘን ነው የምንፈልገው።”
ለአካል ጉዳት በተዳረገችው ታዳጊ ላይ ወንጀሉን የፈጸሙት በሕግ አለመጠየቃቸው በአካባቢው ነዋሪው ላይ ስጋት በመፍጠሩ የተጎጂዋን አባት ጨምሮ ሌሎችም ያሉበትን ሁኔታ በነጻነት ለመናገር እንኳን እንደማይደፍሩ ይናገራሉ።
የሰሜን ሸዋ ዞን የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሹ ጠለፋ “ትልቅ ጫና” እንደፈጠረ እና ሴት ልጆች ትምህርት ቤት መሄድ ማቆማቸውን አስረግጠው ገልጸዋል።
ኃላፊው እነዚህ የጠለፋ ወንጀሎች በስፋት የሚፈጸሙት ፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች እንደሆነም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም 234 ትምህርት ቤቶች ተዘግተው እንደነበር እና እስካሁን ያልተከፈቱት 96ቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
“አብዛኛዎቹ ያልተከፈቱት ትምህርት ቤቶች ያሉት ፋኖ በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች ናቸው። ቀሪዎቹ ደግሞ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ 18 ትምህርት ቤቶች የተዘጉት ደራ ወረዳ ነው። ወረ ጃርሶም እንዲሁ። በእነዚህ 96 ትምህርት ቤቶች ይማሩ የነበሩ ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ቀርተዋል” ብለዋል።
