
14 መጋቢት 2026, 07:51 EAT
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ
ተጨማሪ የአሜሪካ የባሕር ኃይል ወታደሮች እና የጦር መርከቦች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ይንቀሳቀሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሁለት ባለሥልጣናት ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሲቢኤስ ኒውስ አረጋገጡ።
ባለሥልጣናቱ እነዚህ አጋዥ ኃይሎች ከባሕር ኃይል ሠራዊት የሚውጣጡ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን፣ አንድ ባለሥልጣን ደግሞ ቡድኑ የሚመራው በጃፓን በሚገኘው ዩኤስኤስ ትሪፖሊ የባሕር ኃይል ክፍል መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
በዩኤስኤስ ትሪፖሊ የሚመራው ክፍል በተለምዶ በበርካታ የጦር መርከቦች የተደራጀ ሲሆን፣ ወደ 5,000 የሚጠጉ መርከበኞችን እና የባሕር ኃይል ወታደሮችን ያቀፈ ነው።
የጦር መርከቦቹ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንደሚሄዱ የተሰማው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ጦር የዓለም አቀፉ ወሳኝ የነዳጅ ማመላለሻ መስመር በሆነው በሆርሙዝ ወሽመጥ ውስጥ በሚገኘው በካርጅ ደሴት ላይ የሚገኘውን የኢራን ወታደራዊ መሠረተ ልማት “ሙሉ በሙሉ” እንዳወደመ ከገለጹ በኋላ ነው።
በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የእስራኤልን እና የአሜሪካን ወታደራዊ ካምፖች ላይ ያነጣጠሩ የኢራን የአጻፋ ጥቃቶች የዓለም አቀፍ የአየር ጉዞ ዋና ዋና ማዕከላትን ያስተጓጎሉ ሲሆን የነዳጅ ዋጋም ከፍ እንዲል ምክንያት ሆነዋል።
አርብ ዕለት ትራምፕ የአሜሪካ የባሕር ኃይል መርከቦችን በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል መቼ ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ማጀብ እንደሚጀምሩ ሲጠየቁ “በቅርቡ ይሆናል” ብለው ነበር።
የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ሥፍራው እንደሚመንቀሳቀሱ መጀመሪያ የዘገበው ዎል ስትሪት ጆርናል ነበር።
በቀጣናው አጋዥ ጦር እንዲሰማራ የጠየቀው በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ ጦር ኃይል አካል በሆነው የአሜሪካ ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ ሲሆን፣ በመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴትም ጸድቋል።
ምነም እንኳ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በይፋ የሚነገሩ ባይሆኑም ቢቢሲ የአሜሪካን ጦር እና ፔንታጎንን በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቆ ምላሽ አላገኘም።
ዋሽንግተን ፖስት እና የደቡብ ኮሪያ የዜና አውታሮች እንደዘገቡት ከሆነ አሜሪካ በደቡብ ኮሪያ ያላትን የሚሳዔል መከላከያ ሥርዓት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እያዛወረች ነው።
ትራምፕ ቀደም ብለው ኢራን በሚቀጥለው ሳምንት “በጣም ከባድ” ጥቃት እንደሚሰነዘርባት ተናግረው ጦርነቱ እንደሚያበቃ “እጅግ እርግጠኝነት ይሰማኛል” ብለዋል።
ሄግሴት የአሜሪካ ጦር “ለጠላቶቻችን ምንም ዓይነት ርህራሄ አያሳይም” ሲሉ ዝተዋል።
ፔንታጎን በዚህ ለሁለት ሳምንታት በዘለቀው ጦርነት 6,000 የኢራን ዒላማዎችን መደብደቡን አስታውቋል።
አሜሪካ እና እስአኤል የካቲት 21/2018 ዓ.ም. በጋራ በኢራን ላይ በከፈቱት ጥቃት የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገድለዋል።
የኢራን አዲሱ ጠቅላይ መሪ የ56 ዓመቱ ሞጅታባ ኻሜኒ ሐሙስ ዕለት ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር ቴህራን የሆርሙዝን የባህር ወሽመጥ መዝጋቷን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
በኢራን የመንግሥት ቴሌቪዥን ላይ በተነበበው በዚህ መግለጫ፣ በጦርነቱ የተገደሉትን ኢራናውያንን “ደም ለመበቀል” በመዛት ጎረቤት አገራት የአሜሪካን ጦር ማስተናገዳቸውን እንዲያቆሙ አስጠንቅቀዋል።
