
15 መጋቢት 2026, 07:51 EAT
የንባብ ጊዜ: 7 ደቂቃ
ስቴፋኒ ቤከር ከጓደኞቿ ጋር በዱባይ ውስጥ በዘንባባ ቅርጽ በተሠራው ሰው ሠራሽ ደሴት ላይ ከሚገኙ ቅንጡ ሆቴሎች እና የባሕር ዳርቻ መዝናኛዎች አንዱ በሆነው በፓልም ጁሜራህ በሚገኝ የመዝናኛ ሥፍራ የልደት በዓሏን እያከበረች ነበር።
ነገር ግን እርሷ እና ጓደኞቿ ወደ ሌላ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ቦታ ለመሄድ ወደ ውጭ ሲወጡ ጥርት ባለው የዱባይ ሌሊት ሰማይ ላይ ያልተለመደ ነገር ተመለከቱ።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ፣ እርሷ እና ጓደኞቿ ከቆሙበት ማዶ መንገድ ተሻግሮ የሚገኘው ፌርሞንት ሆቴል የድሮን ጥቃት ደርሶበት ስብርባሪዎች ከባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ላይ መውደቅ ጀመሩ።
“ሁላችንም ፈርተን ነበር” ትላለች። “እንደዚህ ዓይነት ነገር ማየት ያልተጠበቀ ነበር።”
ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ከተማዋ የመጣችው ብሪታንያዊቷ የሪል ስቴት አማካሪ ስቴፋኒ ቤከር፣ ዱባይን ሁልጊዜ በቀጣናው ውስጥ ካሉት እጅግ አስተማማኝ ቦታዎች አንዷ አድርጋ ትመለከት እንደነበር ትናገራለች።
ሆኖም ከኢራን ግጭት ጋር በተያያዘ ለሁለት ሳምንታት የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት ከተፈጸመባት በኋላም፣ ለቅቆ የመሄድ ምንም ዕቅድ እንደሌላት ተናግራለች።
“ሁኔታው የተያዘበት መንገድ የበለጠ ደኅንነት እንዲሰማኝ አድርጓል” ትላለች።

ዱባይ ከተለያዩ አገራት የመጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የውጭ ዜጎች መኖሪያ ናት። ከአጠቃላዩ ነዋሪ መካከል የውጭ አገር ዜጎች ከአገሬው በከፍተኛ መጠን ይበልጣሉ። የኤሚሬትስ ዜጎች ከጠቅላላው ሕዝብ 10 በመቶ ብቻ ናቸው።
ከተማዋ ለአስርተ ዓመታት ሰላሙ በሚዋዥቀው ቀጣና ውስጥ የመረጋጋት እና የደኅንነት ተምሳሌት ሆና ትታያለች።
ሰማይን ለመቧጠጥ የሚንጠራሩ መስታወት የደረቡት ሕንጻዎቿ፣ ከቀረጥ ነፃ የሆነው ደሞዟ እና ለግል ደኅንነት ያላት መልካም ስም በመካከለኛው ምሥራቅ እያደገ የመጣ የንግድ እና የቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን እርጓታል።
ይህም በመላው ዓለም የሚገኙ ምሁራን ሆኑ ወዛደሮች ማቄን ጨርቄን ሳይሉ መጥተው የተሻለ ሕይወት ለመገንባት የሚፍጨረጨሩባት ከተማ አድርጓታል።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ ግጭቶች አብዛኛውን የቀጣናውን ክፍል መልኩን ቀይሮታል። ነገር ግን ዱባይ በአብዛኛው አልተነካችም። ያ ደግሞ አሁን ፈተና ውስጥ ወድቋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ባለሥልጣናት እንደገለጹት፣ የኢራን ጥቃቶች ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ወደ አገሪቱ 285 የባለስቲክ ሚሳዔሎች፣ 15 የክሩዝ ሚሳዔሎች እና 1,567 ድሮኖችን መተኮሳቸውን እና የአገሪቱ መከላከያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት መክሸፉን ተናግሯል።
ነገር ግን አንዳንድ ስብርባሪዎች በዱባይ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ወድቀዋል፣ ከእነዚህም ውስጥ ዋና ዋና የመኖሪያ አካባቢዎች እና ከከተማዋ አየር ማረፊያ በቅርብ ርቀት የወደቁ ይገኙበታል።
በበይነ መረብ ላይ የተለቀቁ ምሥሎች ረዣዥም የመኖሪያ ሕንፃዎች፣ ቅንጡ ሆቴል እና አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የወደቁ ስብርባሪዎችን አሳይተዋል።
እስካሁን ድረስ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ 141 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ሲሉ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከ20 በላይ የዱባይ ነዋሪዎችን አነጋግሯል፤ አንዳንዶቹ በዱባይ ለአስርተ ዓመታት የኖሩ ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ በቅርቡ ወደ ከተማዋ እቅፍ የገቡ ናቸው።
አብዛኞቹ በቅርብ ቀናት በደረሱት ጥቃቶች እንደተደናገጡ አልሸሸጉም። ነገር ግን ሁሉም ማለት ይቻላል አገሪቱን ለቅቆ የመውጣት ዕቅድ እንደሌላቸው ይናገራሉ።
በቤተሰቧ ንግድ ውስጥ የምትሠራው እና ሕይወቷን ሙሉ በዱባይ የኖረችው ኤቲ ባሲን “እንዲህ ዓይነት ነገር ያየነው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው” ትላለች።
“ዱባይ በሚያስደንቅ ሁኔታ ትልቅ ከተማ ሆናለች። በአገሪቱ ባለሥልጣናት ላይ እምነት አለን። ይህ ቤቴ ነው። አብሬያቸው እቆማለሁ።”
ለአንዳንድ ነዋሪዎች፣ ያለፉት ሁለት ሳምንታት አስጨናቂ ነበሩ። አዳም ካሎው፣ ባለቤቱ እና ሁለት ትናንሽ ልጆቻቸው ከዩናይትድ ኪንግደም ወደ ዱባይ የወመጡት በ2024 ነው።
በጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ቤተሰቡ በአንድ ክፍል ውስጥ ተኝቶ ሳለ ነው በከተማዋ ዙሪያ ፍንዳታ የተሰማው። በወቅቱ ልጆቹ ከመስኮቶች አጠገብ ለመተኛት በጣም ፈርተው ነበር።
“ባለሥልጣናቱ እዚህ እንድንቆይ ደኅንነት እንዲሰማን ለማድረግ በቂ ጥረት እያደረጉ ነው፤ ነገር ግን መረጋጋትም አይሰማንም” ይላል ካሎው።
“ስጋታችን ይህ እንደማይቀጥል በምንም እርግጠኛ አለመሆናችን ነው።”
የዱባይ፣ ከትንሽ የባሕረ ሰላጤ የንግድ ወደብ ወደ ዓለም አቀፍ መዳረሻነት የተመነደገችው በግንኙነት ላይ ነው።
በሺህዎች የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ መንገደኞችን የሚያስተናግደው የዱባይ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ባለፈው ዓመት ብቻ ወደ 90 ሚሊዮን የሚጠጉ ተጓዦችን አመላልሷል።
ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሺዎች የሚቆጠሩ በረራዎች ተሰርዘዋል፤ ይህም በቀጣናው ውስጥ በረራዎች ከሚበዙባቸው የጉዞ ማዕከላት አንዱን ጭር እንዲል አድርጎታል።

በቅርብ ቀናት ውስጥ የተወሰኑ በረራዎች እንደገና ተጀምረዋል፤ ኤምሬትስ የበረራ መርሃ ግብሩን በመቀነስ ወደ ቀደመው እንቅስቃሴው ቀስ በቀስ ለመግባት ጥረት እያደረገ ነው።
እንዲህ ዓይነቱ መስተጓጎል የሚመጣው በዓመቱ ውስጥ ለጎብኚዎች በተጨናነቀ ወቅት ሲሆን፣ ኃይለኛው የበጋ ሙቀት ከመቀነሱ እና የጥቃት ጉዳቱ ግልጽ ከመሆኑ በፊት።
አገሪቱ አሁን ከግጭት ቀጣና ለመራቅ የሚፈልጉ ሰዎች የቆረጡትን የበረራ ቲኬት እና የያዙትን የሆቴል ክፍል ሲሰርዙ እየተመለከተች ነው።
በአንዳንድ የቅንጦት ሆቴሎች ውስጥ ያሉ ክፍሎች ከተለመደው ክፍያቸው በጣም ባነሰ ዋጋ አገልግሎት እየሰጡ ነው።
“እንደ አለመታደል ሆኖ እስከ ግንቦት ወር ድረስ የተያዙ ክፍሎች ሲሰረዙ እያየን ነው” ይላል የጌትስ ሆስፒታሊቲ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ናይም ማዳድ።
ማዳድ የመጣው ከአውስትራሊያ ሲሆን፣ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት መኖሪያውን በዱባይ አድርጓል።
“የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አጀማመር ካላማረ፣ የቀረው ዓመት ያንን ለማካካስ ሩጫ ይሆናል።”
ብዙ ጎብኚዎች በዱባይን ቅንጡ የአኗኗር ዘይቤ ይሳባሉ።
ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በረዣዥም ፎቆች ላይ የተሠሩ የመዋኛ ገንዳዎችን እና ከባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ውጪ የቆሙ ቅንጡ ዘመናዊ መኪናዎችን እንዲሁም በግል የባሕር ዳርቻዎች ላይ ፀሐይ የሚሞቁ ሰዎችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ያጋራሉ።
ነገር ግን ከዚያ ምሥል በስተጀርባ ሌላ እውነታ አለ።
የዱባይ ሌላ ገጽታ
የከተማዋ ዕድሎች በግልጽ ተቃራኖዎች የተሞሉ ናቸው። በድረ ገጾች በመስታወት እና በመብራት የተንቆጠቆጠች ዱባይ ስትታይ ይህንን ምጣኔ ሃብተ ለመገንባት ላባቸውን እና ወዛቸውን የከፈሉ ስደተኞች አነስተኛ ተከፋይ ናቸው። መኖሪያቸውም ከከተማው ወጣ ብሎ በሚገኝ ሥፍራ ነው።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሠራተኛ ኃይል በአብዛኛው የውጭ ዜጎች ናቸው። የደቡብ እስያ ዜጎች ብቻ በከተማዋ ውስጥ በፍጥነት እያደገ ካለው የሕዝብ ቁጥር ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ይይዛሉ፤ ብዙውን ጊዜ በግንባታ፣ በሎጂስቲክስ እና በዴሊቨሪ አገልግሎቶች ውስጥ ይሠራሉ።
ለብዙዎች፣ ጦርነቱ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ላይ ብዙም ለውጥ አላመጣም።
ከፓኪስታን የመጣው ዴሊቨሪ የሚሠራው ሃምዛ በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀናት ውስጥ ብዙ ሰዎች ቤት ውስጥ ስለቆዩ ትዕዛዞች መጨመራቸውን ይናገራል።
“ፍንዳታ ስንሰማ ወይም ፍርስራሾች ሲወድቁ ስናይ የተወሰነ ፍርሃት አለ” የሚለው ሃምዛ ግን ሥራ ማቆም አልችልም።
“በትውልድ አገሬ ያሉት ቤተሰቦቼ በእኔ ላይ የተደገፉ ናቸው። በፍርሃት ቤት ውስጥ የመቆየት ቅንጦት የለኝም።”
የመብት ተሟጋቾች በባሕረ ሰላጤው ውስጥ ባሉ አንዳንድ ዝቅተኛ ክፍያ የሚከፈላቸው ሠራተኞች አያያዝ እና የኑሮ ሁኔታ ላይ ያላቸውን ስጋት ሲገልጹ ቆይተዋል።
ሃምዛን ጨምሮ አብዛኞቹ ነዋሪዎች በዱባይ ለመቆየት ቢወስኑም በረራ ማግኘት የቻሉት ጥቂቶች ግን ከተማዋን ለቅቀው ሄደዋል።

ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀች አንድ የአየር መንገድ ሠራተኛ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ወደ አውስትራሊያ ሜልበርን ሄዳለች።
“በየቀኑ የማያቋርጥ ፍንዳታዎችን መስማት በጣም ያስጨንቀኝ ነበር” ትላለች። “አሁን ወደ አገሬ መጥቼ ሁኔታው ከተረጋጋ በኋላ ብመለስ ይሻለኛል” ስትል የመመለስ ዕቅድ እንዳላት ተናግራለች።
ብዙ ምዕራባውያን አገራት የኢሚግሬሽን ፖሊሲዎቻቸውን እያጠናከሩ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ ዱባይ የተለየ መንገድን ትከተላለች።
ኤሚሬትስ ራሷን ለዓለም አቀፍ ባለተሰጥኦዎች እና ለሀብታሞች መስህብ አድርጋ አስቀምጣለች። ከኮቪድ ወረርሽኝ ወዲህ በርካታ ሚሊየነሮች ወደ ከተማዋ ተምመዋል።
ከታዳጊ አገራት የመጡ የማደግ ብርቱ ፍላጎት ያላቸው ባለሙያዎች የሕንድ መሐንዲስ፣ የግብፅ ዶክተር ወይም የፊሊፒንስ ነርስ ከአውሮፓ ወይም ከሰሜን አሜሪካ ይልቅ በዱባይ የሥራ ቪዛ ማግኘት በጣም ቀላል ሆኖላቸዋል፤ አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ ደሞዝ የማግኘት ዕድልም አላቸው።
ቀድም ሲል ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እና የሕግ አስከባሪ ኤጀንሲዎች የሚያደረጓቸው ምርመራዎች አንዳንድ በተደራጁ የወንጀል ድርጊቶች የሚጠረጥሩ ሰዎች በዱባይ እንደሚከትሙ አጉልተው ቢያሳዩም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና በበርካታ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት በመጨመሩ ወንጀለኞች ተላልፈው ተሰጥተዋል።
የዱባይ ወርቃማ ምሥል ባለበት ይቀጥላል?
የከተማዋ ትልቁ መስህብ ሁሌጊዜ ሁከት በነገሠበት ቀጣና ውስጥ የተረጋጋች እንደሆነች የሚያሳየው ምሥል በመሆኑ፣ ይህ ምን ያህል ይዘልቃል ወይስ አደጋ ላይ ነው? የሚለው ጥያቄ መልስ ያሻዋል።
ስለ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሰፊው የጻፉት የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ክሪስቶፈር ዴቪድሰን ጥቃቶቹ የዱባይን ማራኪነት ለአጭር ጊዜ ያህል ሊያበላሹት እንደሚችሉ ያምናሉ።
“ነገር ግን መሠረታዊ ነገሮች መሠረተ ልማት፣ ደንብ፣ የአየር ሁኔታ እና መልክዓ ምድሩ አይለወጡም” ይላሉ።
“በረዥም ጊዜ ውስጥ ማራኪነታቸው ሳይለወጥ ይቆያል።”
ባለሥልጣናት በየጊዜው ስለሚፈጸሙ ጥቃቶች እና ስለደረሱ ጉዳቶች በፍጥነት መልዕክቶችን በማድረሳቸው ከነዋሪዎች እና ከቢዝነሶች ምስጋና ይቀርብለቸዋል።
ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አገሪቷ ለነዋሪዎቿ ጥበቃ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬት ደኅንነቷን አደጋ ላይ ለሚጥሉ “በቀላሉ ለአደጋ የምትጋለጥ” እንዳልሆነች በመገለጽ አስጠንቅቀዋል።
የአገሪቱ ከፍተኛ አመራሮችም በዱባይ መደበኛ ሕይወት መቀጠሉን ለማሳየት በአደባባይ በሕዝብ ፊት ታይተዋል።
ይሁን እንጂ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አገሪቱን ወይም አመራሩን ዝቅ የሚያደርግ ወይም የሚተች ንግግር የሚከለክል ሕግ በመኖሩ ትችት ያልተለመደ ነው።

ባለሥልጣናት ስለ ግጭቱ ያልተረጋገጠ ምሥል ማጋራት ከባድ ቅጣት ወይም እስራት ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ሐሙስ ዕለት የ60 ዓመት ብሪታኒያዊ የኢራን ሚሳዔሎች በከተማው ሰማይ ላይ ሲምዘገዘጉ የሚያሳይ ምሥል ከቀረጸ በኋላ ክስ ተመሥርቶበታል።
ለጥቂት ቀናት ባልተለመደ ሁኔታ ጸጥ ብለው የነበሩ የዱባይ ጎዳናዎች ዳግመኛ በሰዎች እና በተሽከርካሪዎች ተሞልተዋል።
ተንታኞች የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ጦርነት በዱባይ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላይ የሚኖረው የረጅም ጊዜ ተጽእኖ እንዴት ይቀጥላል የሚለው ላይ የተመሠረተ ነው። “የተዳከመች ኢራን የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ማራኪነት የበለጠ ልታጎላ ትችላለች” ይላል ዳቪድሰን።
ነገር ግን የኢራን አገዛዝ ከሚወርድበት ቦምብ እና ሚሳዔል ከተረፈ፣ ከባሕረ ሰላጤው ጎረቤቶቹ ጋር ያለው ውጥረት ሊጨምር እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
“ይህ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ባንኮች ወይም የፋይናንስ ተቋማት ከተጎዱ ያ የንግዶችን ስሜት ሊጎዳ ይችላል” ይላል።
ረቡዕ ዕለት የኢራን ባንክ ጥቃት ከተፈጸመበት በኋላ ነው የቴህራን ጦር በአካባቢው ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኢኮኖሚ እና የባንክ ተቋማትን ዒላማ እንደሚያደርግ ዝቷል።
ከዚያ በኋላም በዱባይ የሚገኙ ብዙ የፋይናንስ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን ቢሮዎቻቸውን ለቀው እንዲወጡ አዝዘዋል።
ለጊዜው በዱባይ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ጠንቃቃ ቢሆኑም ተስፋ አላቸው። ከተማዋ ከዚህ በፊት ከ2008ቱ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ቀውስ ጀምሮ እስከ ኮቪድ ወረርሽኝ ድረስ ቀውሶችን ተቋቁማ በጥንካሬ ቀጥላለች።
“ዱባይ ሁልጊዜ በፍጥነት ታገግማለች” ይላል ማዳድ። “ጽናት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ደም ውስጥ ያለ ቅመም ነው።”
