ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

በሀይገር ባስ የሚጓዙ ሰዎች

ከ 9 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በአዲስ አበባ ከተማ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ታሪፍ ላይ ከአምስት እስከ 20 ብር የሚደርስ ጭማሪ ተደረገ። በአዲሱ ተመን ከፍተኛ ጭማሪ የተደረገው የከተማ አውቶብስ ዋጋ ላይ ሲሆን ከፍተኛው የባስ ታሪፍ ከ50 ወደ 70 ብር ከፍ ብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ዛሬ እሁድ መጋቢት 6/2018 ዓ.ም. ይፋ የሆነውን የዋጋ ጭማሪ ያደረገው ከአንድ ዓመት ከአራት ወራት በኋላ ነው። የመጨረሻው የታሪፍ ጭማሪ በተደረገበት ጥቅምት 2017 ዓ.ም. የቤንዚን እና ነጭ ናፍጣ ዋጋ 91 እና 90 ብር ገደማ ነበር።

የታሪፍ ማሻሻያ ሳይደረግ በቆየበት አንድ ዓመት ከመንፈቅ የሚጠጋ ጊዜ ውስጥ የቤንዚን ዋጋ በ41 ብር ገደማ ጨምሯል። ነጭ ናፍጣ ደግሞ የ49 ብር ገደማ ጭማሪ አሳይቷል።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የመጨረሻውን የነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ጭማሪ ይፋ ያደረገው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ መጋቢት 1 ቀን ነበር። በአዲሱ ዋጋ መሠረት ቤንዚን 132 ብር ከ18 ሳንቲም የተተመነለት ሲሆን ነጭ ናፍጣ ደግሞ 139 ብር ከ84 ሳንቲም እየተሸጠ ነው።

በአዲስ አበባ የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ጭማሪ የተደረገው “በወቅታዊ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ የተደረገውን የዋጋ ማስተካከያ” ምክንያት እንደሆነ የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ ዛሬ ባወጣው መረጃ ላይ ጠቅሷል።

ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው ታሪፍ ለሚኒባስ ታክሲዎች፣ እንደ “ሃይገር እና ቅጥቅጥ” ላሉ ሚድ ባሶች እንዲሁም ለከተማ አውቶብስ የተዘጋጀ ነው።

የሚኒባስ ታክሲ ተጠቃሚዎች እስከ 2.5 ኪሎ ሜትር ሲከፍሉት ነበረው የ10 ብር ተመን ባለበት እንዲቀጥል ተደርጓል። እስከ አምስት ኪሎ ሜትር የሚደረግ ጉዞ ደግሞ ከነበረበት 15 ብር ወደ 20 ብር ከፍ ብሏል።

እስከ 15 ኪሎ ሜትር ለሚደርሱ ጉዞዎች የተዘጋጁ የታሪፍ ተመኖች በተመሳሳይ የአምስት ብር ጭማሪ ተደርጎባቸዋል።

ከ15.1 እስከ 17.5 ኪሎ ሜትር ለሚደርስ ጉዞ ሲከፈል የነበረው የታክሲ ተመን የ10 ብር ጭማሪ ተደርጎበት 50 ብር ገብቷል። የመጨረሻው ከፍተኛ የታክሲ ታሪፍም ተመሳሳይ ጭማሪ ተደርጎበት ወደ 55 ብር አድጓል።

በአዲሱ ታሪፍ መሠረት ዝቅተኛው ‘የሃይገር እና ቅጥቅጥ’ ተመን 15 ብር ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 45 ብር እንዲሆን ተደርጓል።

እስከ 20 ብር የሚደርሰው ከፍተኛ ጭማሪ የተደረገው በከተማ አውቶብስ የዋጋ ተመን ላይ ነው።

ዝቅተኛው የአውቶብስ ክፍያ ባለበት 10 ብር እንዲቀጥል ቢደረግም በዚህ ታሪፍ መጓዝ የሚቻለው ከፍተኛው የጉዞ ርዝመት ከነበረበት 12 ኪሎ ሜትር ወደ 7.5 ኪሎ ሜትር ተቀንሷል።

በአንጻሩ 7.5 እስከ 12 ኪሎ ሜትር ያለው ርቀት አዲስ ምድብ ተዘጋጅቶለት 15 ብር ገብቷል። እስከ 17 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርቀትም ዋጋው 25 ብር ደርሷል።

ከዚህ ቀደም ከ30 እስከ 45 ኪሎ ሜትር ለሚደርስ የአውቶብስ ጉዞ ሲከፈል የነበረው 40 ብር የ20 ብር ጭማሪ ተደርጎበታል። የመጨረሻው ከፍተኛ የአውቶብስ ዋጋም በተመሳሳይ የ20 ብር ጭማሪ ተደርጎበት ከ50 ብር ወደ 70 ብር ከፍ ብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በተመኑ መሠረት ተገልጋዮችን እንዲያጓጉዙ ያሳሰበ ሲሆን ተጠቃሚዎችም “ከሕጋዊ ታሪፍ ውጪ” የሚያስከፍሉ አግልግሎት ሰጪዎችን እንዲጠቁሙ ጠይቋል።