ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የሶማሊላንዱ ፕሬዝደንት አብዲራህማን ኢሮ

15 መጋቢት 2026, 08:56 EAT

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

እስራኤል የሁቲ አማጺያንን ለመዋጋት በሶማሊላንድ የጦር ሰፈር ልትገነባ ነው መባሉን ሐርጌሳ አስተባበለች።

በአውሮፓውያኑ መጋቢት 11 ብሉምበርግ ባወጣው ዘገባ፤ እስራኤል እና ሶማሊላንድ የደኅንነት ስምምነት ለመፈራረም ውይይት እያደረጉ መሆኑን እና ንግግሩ በርበራ አቅራቢያ ለእስራኤል ይዞታ መስጠትን እንደሚያካትት ገልጾ ነበር።

እስራኤል የሁቲ አማጺያንን ለመታገል በቀይ ባሕር ዳርቻ ሶማሊላንድ ውስጥ የጦር ሰፈር ልትገነባ እንደምትችል ዘገባው ይጠቁማል።

በሶማሊላንድ እስራኤል የሚኖራት ይዞታ እንደ ወታደራዊ ዒላማ እንደሚወሰድ የሁቲ አማጺያን መሪ አብዱል-ማሊክ አል-ሁቲ ያለፈው ታኅሣሥ ላይ ተናግሯል።

ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያ አገር በሆነችው እስራኤል እና በሐርጌሳ መካከል ተደርጓል የተባለውን ውይይት ሞቃዲሹ ውድቅ አድርጋለች።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ በጥር ወር ከአል ጀዚራ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ እስራኤል በሶማሊላንድ ወታደራዊ ሰፈር ብትገነባ የሞቃዲሹን ሉዓላዊነት እንደምትጥስ አስጠንቅቀዋል።

ከቢቢሲ ማብራሪያ የተየጠቁት የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲራሒም ዳሂር አዳም፤ ከእስራኤል ጋር ያላቸው ግንኙነት በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጸዋል።

“ሁለቱ አገራት አንዳቸው ለሌላቸው ዕውቅና ስለሰጡ ዲፕሎማሲያዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር መፍጠር” እንደሚችሉ ተናግረዋል። ሆኖም ግንኙነታቸው ወታደራዊ ትስስርን እንደማያካትት ጠቅሰዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሶማሊያ የጦር ሰፈር የምትገነባበት ቦታ ከሶማሊላንድ አለመሰጠቱን ገልጸዋል።

እስራኤል በሶማሊላንድ የጦር ሰፈር እንድትገነባ ስምምነት ላይ ተደርሷል የሚሉ የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች “ከዐውድ ውጭ የተወሰዱ ናቸው” ሲሉም ተናግረዋል።

ሶማሊላንድ በምሥጢራዊ ስምምነቶች ውስጥ እጇን እንደማታስገባ የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ በድብቅ ውይይቶች ተደርገዋል የሚሉ ዘገባዎች “ሶማሊላንድን ለማጠልሸት ያለሙ ፕሮፓጋንዳዎች ናቸው” ሲሉም ከስሰዋል።

“እነዚህ ዘገባዎች ትክክል አይደሉም። ሁቲዎችን ስለማጥቃት የሚያትት ዘገባ የሶማሊላንድ ጠላቶች የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ነው” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሶማሊላንድ በየመን ውጥረት ውስጥ ተሳታፊ እንዳልሆነች እና ሁቲዎች ሐርጌሳ ላይ የተለየ ስጋት እንደማይደቅኑ ገልጸዋል።

ሶማሊላንድ ከእስራኤል ጋር ያላት ግንኙነት ከሌሎች የቀጣናው አገራት ጋር ካላት ትስስር ተለይቶ መታየት እንደሌለበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለዋል።

“ሶማሊላንድ ከእስራኤል ጋር የምጣኔ ሃብት እና ስትራቴጂክ ወዳጅነት ለመመሥረት ዝግጁ ናት። አሁን ላይ የተጀመረ ነገር የለም። ውይይት ሲኖርም በግልጽ ይካሄዳል” ብለዋል።

የጦር ሰፈር ግንባታን “ፍጹም ሐሰት” ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከዘገባው ጀርባ ያሉት “ሶማሊላንድ በዓለም አቀፍ መድረክ በተዛባ መንገድ እንድትሳል የሚፈልጉ ናቸው” ሲሉም አክለዋል።