ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ሕንጻው ላይ የደረሰው ውድመት

15 መጋቢት 2026, 09:50 EAT

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የምግብ ሸቀጦች ዋጋ መናር እና የመብራት መቆራረጥን ለመቃወም አደባባይ የወጡ ኩባውያን የኮምኒስት ፓርቲ ሕንጻ ላይ ጉዳት አደረሱ።

ሕንጻው ላይ የደረሰውን ውድመት ተከትሎ አምስት ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በኩባ በተከታታይ መብራት ከመጥፋቱ በተጨማሪ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ እጥረት ተባብሷል። ለዚህም አሜሪካ የኩባ ነዳጅ ላይ የጣለችው ማዕቀብ ዋነኛው ምክንያት ነው።

የኩባ ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ-ካኔል ለተቃውሞ የወጣው ሕዝብ ጥያቄው “ተገቢ ቢሆንም ውድመት እና ዜጎችን የሚያውክ ነውጥን አንታገስም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ለመብራት መጥፋት ምክንያቱ የአሜሪካ ማዕቀብ መሆኑን በኤክስ ገጻቸው የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ማዕቀቡ “በጭካኔ ለወራት የቀጠለ ነው” ብለዋል።

ለሦስት ወራት ወደ ኩባ ነዳጅ አለመግባቱን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

አሜሪካ እና ኩባ እየተወያዩ መሆናቸው በተገለጸ በሰዓታት ውስጥ ነዋሪዎች ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኩባን አስተዳደር መለወጥ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።

ኩባ “በጣም ጥልቅ ችግር ውስጥ ናት” ያሉት ትራምፕ “በወዳጃዊ መንፈስ እንቆጣጠራታለን” ብለዋል።

የቬንዝዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን አሜሪካ በቁጥጥር ሥር ካዋለች በኋላ “ቀጣዩ አጀንዳ” ኩባ መሆኗ መገለጹ ይታወሳል።

ኩባ ከምትጠቀምበት ነዳጅ ግማሹ የሚጓዘው ከቬንዝዌላ ነበር። አሜሪካ በቬንዝዌላ የነዳጅ መርከቦች ላይ ማዕቀብ ከጣለች በኋላ ኩባ በነዳጅ እጥረት እየተፈተነች ትገኛለች።

ለኩባ ነዳጅ የሚሸጥ አገር ላይ ትራምፕ ታሪፍ ለመጣል ዝተዋል።

ኩባ ከዚህ ቀደምም ለዓመታት የዘለቀ የአሜሪካ የነዳጅ ማዕቀብ ሥር ቆይታለች። አሁን የተጣለባት ተጨማሪ ማዕቀብ ምጣኔ ሃብቷን እያሽመደመደው ነው።

ድንገተኛ አገልግሎት ሰጪ ሆስፒታሎች፣ የሕዝብ ማመላለሻዎች እና ትምህርት ቤቶችም ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ተስኗቸዋል።

የአገሪቱ መንግሥት የሚያስተዳድረው ጋዜጣ ኢንቫሶር እንደዘገበው፤ ያለፈው አርብ ዕለት የተነሳው ተቃውሞ መጀመሪያ ላይ ሰላማዊ የነበረ ቢሆንም “ወደ ውድመት ተሻግሯል”።

“ጥቂት ሰዎች የሕንጻውን መግቢያ ጥሰው እሳት አስነሱ” ይላል ዘገባው። ሌሎች የመንግሥት ፋርማሲዎች እና ገበያዎች ጥቃት እንደደረሰባቸውን ተገልጿል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተዘዋወሩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች “ነጻነት” በማለት ድምጻቸውን ያሰሙ የነበሩ ኩባውያን ሕንጻዎች ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ ያሳያሉ።

የደረሰው ውድመት በአገሪቱ ልዩ ኃይል እየተመረመረ እንደሆነ ተገልጿል።

በኩባ ሕዝባዊ አመጽ መመልከት ብዙም የተለመደ አይደለም። ሆኖም ግን የመብራት መጥፋት በርካቶችን አስቆጥቷል።

ነዋሪዎች ምሽት ላይ ድስት እና ብረት ምጣት በመደብደብ ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀምረዋል።

ባለፈው ሳምንት በሐቫና ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተሰብስበው ትምህርት መቋረጡን ተቃውመዋል።