
MistreSilasie Tamerat

ከሰሞኑ እየተካሄዱ ያሉ የምርጫ ክርክሮችን በተመለከተ የታዘብኳቸውን ነገሮች በተለይ ክርክሮቹን ከሚያቀርቡ ሚዲያዎች ጋር በተያያዘ የተመለከትሁትን ጉዳይ ላንሳ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የምርጫ ክርክር እንዲደረግ ያዘጋጁት ብልጽግና ፓርቲ በሕዝብ ሀብት የሰራቸው ነገር ግን ሕዝብ ተኮር ባልሆኑት፤ ይልቁንም የአዲስ አበባን ሕዝብ ለከፋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል በዳረጉት የኮሪደር ‘ልማት’ ትሩፋት በሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ነው። ትብብሩን ወክዬ በተገኘሁበትና ‘ቱሪዝም፣ ማዕድንና ኢንደስትሪ’ በተመለከተው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ያዘጋጀው ክርክር ላይ ተቋሙ ክርክሩን በሚመራው ባለሙያው በኩል መቶ በመቶ እነዚህን ፕሮጀክቶች ሲያስተዋውቅ እንደነበር ተመልክቻለሁ።
ብልጽግና ፓርቲም በተከራካሪው በኩል ‘ይህ የቆምንበት ቦታ…’ እና ወዘተ.. በማለት ስራውን ለማዋደድ መሞከሩ በሚዲያ ተቋሙ እና በገዢው ፓርቲ በኩል የቦታ መረጣው ታቅዶበትና ታስቦበት በመናበብ የተሰራ ስለመሆኑ አስረግጦልኛል። እኔ እንደ አንድ ጋዜጠኛ ቦታ አመራረጥ ከምንሰራው ዜና እና ዘገባ ያልተናነሰ non-verbal cue እንዳለው በደንብ አውቃለሁ። ኢቲቪ እና ባልደረቦቹም ይሄ ሊጠፋቸው አይችልም።
ማንኛውም የኮምኒኬሽን ባለሙያ ፍሬሚንግ፣ ቶን፣ የዕይታ ማረፊያዎች እና የቦታ መረጣ በዘገባዎች ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ ያውቃል። ስራዎቹን የሚሰራውም ያንን ታሳቢ በማድረግ ነው። በጠቀስናቸው መመዘኛ ማዕዘናት ሁለቱም የሚዲያ ተቋማት ከመጡት የገዢው ተከራካሪ ወኪሎች በተጨማሪ ተጨማሪ የብልጽግና ወኪል መሆናቸውን አስመስክረዋል።
ይህንን በተመለከተም በቀረጻው ወቅት አግባብነት እንደሌለው እና ቢያንስ በምርጫ ወቅት እንኳን እንደዚህ በይፋ ገለልተኛ አለመሆናቸውን ሊያሳዩ እንደማይገባ የተናገርኩበትን ክፍል ቆርጠው አውጥተውታል። በእርግጥ እንዳይተላለፍ ያደረጉት ይህንን ብቻ አይደለም።
አዲስ ቲቪ በምርጫ እና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ኢሕአፓን ወክዬ የሰጠሁትን ቃለመጠይቅ ሙሉ በሙሉ አፍኖ አስቀርቶታል። በእርግጥ በቃለ መጠይቁ ወቅት ‘ጋዜጠኛው’ ከጋዜጠኛ በማይጠበቅ መልኩ ያሳየውን ወገንተኝነት በመመልከቴ አለማስተላለፋቸው እምብዛም ያስገረመኝ ባይሆንም ይህ ድርጊት ስለ ሚዲያ ተቋሙ ግን ብዙ የሚናገረው ነገር የመኖሩን ሓቅ አይቀይረውም።
የህዝብ ሚዲያ የመንግስት ፕሮፓጋንዳ መሳሪያ መሆን አይገባውም። የዕለት ተዕለት እውነታው በተቃራኒው ቢሆንም ቢያንስ በምርጫ ወቅት ይህንን ግልጽ የገዢው ፓርቲ የፕሮፖጋንዳ መሳሪያነት ገታ ያደርጉታል የሚል ትንሽ ተስፋ ነበረን።
እንደሚታወቀው ፓርቲዬ ኢሕአፓ በዚህ የምርጫ ሂደት ውስጥ እስከመጨረሻው ለመቀጠል ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኝነት እና የሚዲያ ነጻነት አንዱ ነው። ከላይ በጠቀስኳቸው ማሳያዎች ደግሞ ይህ የሚዲያ ገለልተኝነት መርሕ በግልጽ ተጥሷል።
በዚህ አጋጣሚ ይህንን የክርክር መድረክ በመምራት እና በማስተባበር በኩል ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዲሁም ባለሙያዎቹ ላሳዩት ፕሮፌሽናሊዝም አክብሮቴን ለመግለጽ እፈልጋለሁ።
Via: የኢሕአፓ ዋና ጸኃፊ ሚስጥረሥላሴ ታምራት
