ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የኢራን የቀድሞው ጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ምስል

17 መጋቢት 2026

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

የአውሮፓውያኑ የ1979ኙን አብዮት ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጣው የኢራን አመራር ከአራት አስርት ዓመታት በላይ በኋላ እጅግ አስከፊ የሚባል ጊዜ እያሳለፈ ነው።

ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል በጋራ በከፈቱት ጥቃት ጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እና ሌሎች ከፍተኛ የጦር አዛዦችን ተገድለዋል፣ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል።

አሜሪካ እና እስራኤል የአገዛዝ ለውጥ እንደሚፈልጉ ከመግልጽ ባለፈ ኢራናውያን አስተዳደሩን እንዲያፈርሱ እየወተወቱ ነው።

ባለሙያዎች ግን የኢራን አገዛዝ ዘላቂ እና በቀላሉ የማይወድቅ የኃይል መዋቅር ፈጥሯል ሲሉ ይሞግታሉ።

ለመሆኑ ይህ ኢራን መንግሥት እንዴት ነው የተቋቋመው? ከሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚለየው እንዴት ነው?

ሲቆረጥ መልሶ የሚያቆጠቁጥ መዋቅር

የኢራንን ንጉሣዊ አገዛዝ ከተገለበጠ በኋላ፣ እስላማዊው ሪፐብሊክ ችግሮችን የሚቋቋም የፖለቲካ ሥርዓት ገንብቷል ሲሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ይህም በጥብቅ ቁጥጥር ስር ያሉ ተቋማትን፣ ርዕዮተ ዓለማዊ አስተምህሮዎችን፣ የልሂቃን አንድነትን እና የተበታተነ ተቃዋሚን ያካተተ ነው።

“ሥርዓቱ እንደ ሃይድራ ያለ መዋቅር ነው ያለው፤ ይህ እጸዋት አንድ ቅርንጫፉ ሲቆረጥ አዲስ ቅርንጫፍ ተመልሶ ይበቅላል” ይላሉ በቤልጂየም በሚገኘው የአውሮፓ ጂኦፖለቲካል ተቋም የመካከለኛው ምሥራቅ ተመራማሪ የሆኑት ሴባስቲያን ቡሶይስ።

የጠቅላይ መሪው የአሊ ኻሜኒ ልጅ ሞጅታባ ኻሜኒ አባታቸው ከተገደሉ ከሳምንት በኋላ ተተኪው ሆነው ለመንበሩ ተሰይመዋል።

የአባታቸውን የጠንካራ አገዛዝ እንደሚቀጥሉ በሰፊው ይጠበቃል።

ሰንጠረዥ

“ዘርፈ ብዙ-አምባገነንነትን”

ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ እንደ ቱኒዚያ፣ ግብፅ እና ሶሪያ ካሉ የቀጣናው አገራት በተለየ መልኩ ኢራን በርዕዮተ ዓለም በሚመራ የደኅንነት መዋቅሯ ምክንያት የውጭ አደጋዎችን መቋቋም ችላለች።

ኢራን በአንድ ሰው ላይ ካተኮረ አምባገነንነት ይልቅ “ዘርፈ ብዙ-አምባገነንነትን” ትከተላለች። ይህም “በፖለቲካዊ እስልምና ደጋፊዎች እና በጠንካራ የኢራን ብሔርተኝነት ጥምረት መካከል ነው” ሲሉ መቀመጫውን በቴህራን ያደረገው የፈረንሳይ የኢራን የምርምር ተቋም የቀድሞ ዳይሬክተር በርናርድ ሁርኬድ ተናግረዋል።

ሥልጣን በብዙ ማዕከላት ተከፋፍሏል፤ የሃይማኖት አባቶች፣ በጦር መሪዎች እና በትላልቅ የኢኮኖሚ ክፍሎች። ሥርዓቱ ከአንድ ​​አምባገነን መሪነት የወጣ በመሆኑ ለመጣል በጣም ከባድ ያደርገዋል።

ሥልጣን ካላቸው ሌሎች አካላት መካከል በሕግ ጉዳዮች ላይ ደምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን ያለው እና ለምርጫ ዕጩዎችን ማቅረብ የሚችለው ምክር ቤትን ይጠቀሳል።

ይህ ደግሞ የትኛውም ቡድን በመንግሥት ላይ ከባድ ፈተና የመፍጠር ዕድሉን የበለጠ ይቀንሰዋል።

ኢራን በሰፋት እንደ አምባገነንነት የምትታይ ቢሆንም፤ ኢራናውያን ፕሬዝዳንታቸውን ጨምሮ በአንዳንድ ምርጫዎች የመምረጥ ዕድል ይሰጣቸዋል።

ሂደቱ ግን በጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ሲሆን፣ ዕጩዎች ለእስላማዊ ሪፐብሊኩ ያላቸውን ቁርጠኝነት ጨምሮ በሌሎች መስፈርቶች በአገሪቱ ምክር ቤት ተመርምረው የሚያልፉበት ነው።

ሞጅታባ ኻሜኒ
የምስሉ መግለጫ,ተተኪው ጠቅላይ መሪ ሚጅታባ ኻሜኒ

የአብዮታዊው ዘብ ሚና

ከተቋማት ጎን ለጎን የፀጥታ ኃይሎች ለአገዛዙ የተሟላ ቁመናን ይሰጣሉ።

ከመደበኛው ጦር ጎን ለጎን የሚንቀሳቀሰው የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ብዙውን ጊዜ “የአገዛዙ የጀርባ አጥንት” እንደሆነ ይቆጠራል ይላሉ ኸርኬድ።

ከወታደራዊ ሚናው ባሻገር፣ ሰፊ የንግድ ፍላጎቶች እና ተጽዕኖ ያለው የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ኃይል ሆኗል። በበጎ ፈቃደኞች የተቋቋመው ባሲጅ የተባለ የሚሊሻ ቡድን አለው።

የፀጥታ ኃይሉ አለመረጋጋቶች ሲከሰቱ አንድ መሆኑን ደጋግሞ አሳይቷል። ቡሶይስ ይህንን ታማኝነት ከርዕዮተ ዓለም ጋር ያያይዙታል።

“ይህ በሺዓዎች እና እንደ ሐማስ እና ሄዝቦላህ ባሉ ቡድኖች ውስጥ የምናገኘው የሰማዕትነት ባህል የስኬት አካል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል” ብለዋል።

የኢራን ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ሬዛ ታላይኒኒክ በቅርቡ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እያንዳንዱ የአብዮታዊው ዘብ አዛዥ ሦስት ተተኪዎች አሉት።

በዩናይትድ ኒውከሌር ኢራን የምርምር ኃላፊ የሆኑት ካሳራ አራቢ በበኩላቸው የኢራን ያልተማከለ መዋቅር የተቀረፀው በአውሮፓውያኑ 2003 የአሜሪካ ጥምር ጦር በፈጸመው ጥቃት ወቅት የኢራቅ ኃይሎች ከወደቁበት ትምህርት በመውሰድ ነው።

ሥርዓቱ ከተረፈ “ጠባቂዎቹ የበለጠ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል” ብለው ያምናሉ።

የሞጅታባ ኻሜኒ እና የአባታቸውን ምስል የያዙ ኢራናዊያን

የትብብር መረቦች እና የልሂቃን ጥምረት

የኢራን ኢኮኖሚ ዋናዋና ክፍሎች እንደ ቦኒያድስ ባሉ ከመንግሥት ጋር በተያያዙ ድርጅቶች ቁጥጥር ስር ናቸው። ቦኒያድስ በኢኮኖሚው ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኩባንያዎችን በባለቤትነት የያዘ ድርጅት ነው።

እነዚህ ተቋማት ለሥርዓቱ ታማኝ ለሆኑ ክልሎች የሥራ ዕድሎችን እና ጨረታዎችን ይሰጣሉ።

አብዮታዊው ዘብን ጨምሮ ከታም አል-አንቢያ የተሰኘው ተቋም ይህንን “የትብብር” የንግድ ሥርዓት ያጠናክራሉ።

የምዕራባውያን ማዕቀቦች የኢራንን ኢኮኖሚ ክፉኛ ቢጎዱም፤ እነዚህ ጥምረቶች ልሂቃንን ለማግለል እና በሥርዓቱ ኅልውና ውስጥ ያላቸውን ድርሻ ለመጠበቅ ይረዳሉ ሲሉ ባለሙያዎች ይሞግታሉ።

እንደ ቡሶይስ ገለጻ ከሆነ ሥርዓቱ “በጣም ጠንካራ ስለሆነ ምንም ዓይነት ክህደት አንመለከትም።”

ርዕዮተ ዓለም እና የአብዮት ውርስ

ሃይማኖት ሥልጣንን በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

አብዮቱ የመንግሥትን የዓለም ዕይታን በመቅረጽ የሚታወቁ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ እና የትምህርት ተቋማትን መረብ ፈጥሯል።

“በጣም የቆየ በጣም ጠንካራ የርዕዮተ ዓለም፣ የቢሮክራሲ፣ የአስተዳደር መዋቅር ያለው በመሆኑ ሥርዓቱን ጠንካራ ያደርገዋል” ይላሉ ቡሶይስ።

ርዕዮተ ዓለም “እንደ እውነተኛ የአንድነት፣ የሙያ እና የሥራ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል” ሲሉ ይከራከራሉ።

የእስላሚክ አብዮታዊ ዘብ አባል

የተከፋፈለው ተቃዋሚ

በታሪክ የኢራን ተቃዋሚዎች የተከፋፈሉ ናቸው።

እነዚህም የተሃድሶ አራማጆችን፣ የግራ ዘመም ቡድኖችን፣ እንደ ኢራን ብሔራዊ ምክር ቤት ያሉ የዲያስፖራ እንቅስቃሴዎችን እና የተለያዩ የጎሳ ድርጅቶችን ያካትታሉ።

ይህ መከፋፈል ለረጅም ጊዜ የቆየ ነው ሲሉ በአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት ከፍተኛ የፖሊሲ ባልደረባ የሆኑት ኤሊ ጌራንማዬህ ይገልጻሉ።

ከአብዮቱ በኋላ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስለመፍጠር የሚደረገው ክርክር ወደ ጎን ተብሏል ይላሉ። ኢራን በ1980 ከኢራቅ ጋር ጦርነት ጀምራ ለስምንት ዓመታት መዝለቁ አንደኛው ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ።

እነዚህ ቡድኖች በተለያዩ ጊዜያት በአገዛዙ እና በጠንካራ አንጃዎቹ “ተገድለዋል፣ ተፈርዶባቸዋል ወይም ታስረዋል” ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት እንደ 2009ኙ የአረንጓዴ ንቅናቄ እና በ2022 የማህሳ አሚኒን ሞት ተከትሎ የተካሄዱት ሰልፎች በሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞው ቀስቅሰዋል።

እነዚያ ተቃውሞዎች አመራር አልነበራቸውም፤ ከባድ የመንግሥት ክንድም አርፎባቸዋል።

ዘንድሮ እና ባለፈው ዓመት የተደረጉት የተቃውሞ ማዕበሎች ግን በሟቹ የሻህ መሪ ልጅ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ ተካሄደ ነው።

ኢራን በክልሉ ውስጥ ካሉ እጅግ ዘመናዊ የክትትል ሥርዓቶችን ትጠቀማለች። የኢንተርኔት መዘጋት፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚታገዝ የነቃ ክትትል እና የሳይበር ጥቃቶች በውጭ አገር ያሉ አንቂዎችን ዒላማ አድርገዋል።

እየተሸረሸረ ያለው ተስፋ

ለዓመታት በርካታ ኢራናውያን በአፍጋኒስታን እና በኢራቅ የነበረውን የአሜሪካ መራሹ ጣልቃ ገብነትን ውጤት ከተመለከቱ በኋላ የአገዛዝ ለውጥ እንዲኖር ያላቸው ፍላጎት መመናመኑን ጌራንማዬህ ይገልጻሉ። የአረብ አብዮቶች መዘዝም ጥንቃቄውንየበለጠ እንዳጠናከረው አክለዋል።

ይህ ስሌት ግን አሁን ተቀይሯል። ብዙ ኢራናውያን መንግሥት ከሥራ ፈጠራ እስከ ንፁህ ውሃ ያሉ መሠረታዊ ፍላጎቶችን መስጠት እንደማይችል ከማሰባቸውም በላይ ተቃውሞን ለማፈን ጭካኔ የተሞላበት ኃይል መጠቀሙ እየጨመረ መጥቷል።

በጥር ወር በአገሪቱ ከታዩት ትላልቅ ሰልፎች በኋላ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት አዲስ ተቃውሞ ይህንን ለውጥ አፋጥኖታል ሲሉ አክለዋል።

ሁርኬድ በኢራናውያን እና ለሥርዓቱ ባላቸው አመለካከት መካከል “የትውልድ ክፍተት” እንዳለ ገልጸዋል።

የተማሩት እና በማኅበራዊ ሚዲያ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን የሚከታተሉት ወጣት ኢራናውያን አገዛዙ “ሙስና የተሞላበት፣ ጨቋኝ እና የማይገባቸው” አድርገው ይመለከቱታል በማለት ይሞግታሉ።

ኢራናውንያ ምርጫ ሲመርጡ
የምስሉ መግለጫ,በኢራን ምርጫ ሲካሄድ

‘ሁሉም አገዛዝ መጨረሻ አለው’

ተንታኞች እንደሚሉት አምባገነን ሥርዓቶች የሚወድቁት ሦስት ሁኔታዎች ሲጣመሩ ነው፤ እነሱም ሕዝባዊ ንቅናቄ፣ የገዢው ልሂቃን መከፋፈል እና የፀጥታ ኃይሎች መኮብለል ናቸው።

ባለፉት ጊዜያት ኢራን በአብዛኛው የመጀመሪያውን አጋጥሟት የነበር ቢሆንም፤ ቀሪዎቹ ሁለቱ አለመኖራቸውን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ሁርኬድ የኢስላማዊ ሪፐብሊክ ፍጻሜ የማይቀር ነው ብለው ቢያምኑም በቅርቡ ይሆናል በሚለው ላይ ግን ጥርጣሬ አላቸው።

“ሁሉም አገዛዝ መጨረሻ አለው። ዋናው ጥያቄ የጊዜው ቅደም ተከተል ጉዳይ ነው።”

የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ሞት ለገዥው አገዛዙ ትልቅ ጉዳት እንደሆነ ይከራከራሉ።

“እንደ እሱ ያለ ሌላ ሰው አይኖርም። የእሱ ተተኪ ኻሜኒ የነበረውን ዓይነት ሥልጣን በፍጹም አይኖረውም።”

ቡሶይስ ግን በእስላማዊ ሪፐብሊክ ውድቀት እርግጠኛ እንዳልሆኑ ይናገራሉ።

አገዛዙ ውጭ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ከተሳካ የሚከተለው ነገር የከፋ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል ለኒው ዮርክ ታይምስ እንደተናገሩት የአሜሪካ የቀድሞው የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን መያዟ ለኢራን “ትልቅ ማሳያ” እንደሚሆን ተናግረዋል።

ቡሶይስ ግን “ተቃራኒው ተፈጥሮ ልክ እንደ ሰሜን ኮሪያ ወይም ኩባ አደገኛ አገዛዝ ሊተካ ይችላል” ብለዋል።