
17 መጋቢት 2026, 07:44 EAT
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ኬንያዊያን ላለመመልመል መስማማቷን የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጹ።
በሞስኮ ካደረጉት ውይይት በኋላ ከሩሲያ አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ ጎን ሆነው መግለጫ የሰጡት ሙሳሊያ ሙዳቫዲ፤ ሁለቱም ወገኖች ኬንያውያን በሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር በኩል እንደማይመለመሉ መስማማታቸውን አስታውቀዋል።
“ከእንግዲህ ለመመዝገብ ብቁ አይሆኑም” ሲሉ ተናግረዋል።
ላቭሮቭ በስምምነቱ ዙሪያ አስተያየት ባይሰጡም ሁሉም የውጭ አገር ተዋጊዎች “የሩሲያን ሕግ ሙሉ በሙሉ በመቀበል” በፈቃዳቸው መቀላቀላቸውን አበክረው ተናግረዋል።
የካቲት ላይ የወጣ የኬንያ የስለላ ሪፖርት ከአንድ ሺህ በላይ የአገሪቱ ዜጎች ዩክሬን ውስጥ ለሩሲያ ለመዋጋት መሰለፋቸውን ይፋ አድርጓል።
አንዳንድ ኬንያውያን በጥሩ ክፍያ የሲቪል ሥራዎችን እንደሚሠሩ ቃል ቢገባላቸውም ከሩሲያ ጎን በዩክሬን ለመዋጋት መገደዳቸውን አስታውቀዋል።
ሙዳቫዲ ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚፈልጉ ኬንያውያን እንዲመለሱም ጠይቀዋል።
ባለፈው ወር ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ በውጭ አገር ሥራ ስም ዜጎችን በማታለል የተጠረጠሩ ከ600 በላይ የሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎችን መዘጋታቸውን ተናግረው ነበር።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አክለውም አንዳንድ ሥርዓት አልባ የመንግሥት ባለስልጣናት ዜጎቻቸው ከሩሲያ ጎን ተሰልፈው እንዲዋጉ ከሰው አዘዋዋሪ መረቦች ጋር እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁን በሩሲያ ሲዋጉ የነበሩ 27 ኬንያውያን ወደ አገራቸው መመለሳቸውን እና የደረሰባቸውን ጉዳት ለመቅረፍ የሥነ ልቦና ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ሙዳቫዲ ተናግረዋል።
ለሩሲያ ጦር ሲዋጉ ከነበሩ ኬንያውያን ምን ያህሉ እንደሞቱ ግልፅ አይደለም፤ ሩሲያም እንደዚህ አይነት ሪፖርቶችን በይፋ አላቀረበችም።
ለጥያቄያቸው መልስ ለማግኘት ናይሮቢ ወደሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ያመሩ ቤተሰቦች ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በዩክሬን እየተዋጉ ያሉ ኬንያውያን ቤተሰቦች የካቲት ላይ በአገሪቱ ፓርላማ ተገኝተው መንግስት እርምጃ በመውሰድ ዜጎቹን እንዲያስመልስ የሚጠይቅ ሰልፍ አካሂደዋል።
ሙዳቫዲ በሞስኮ ጉብኝታቸው ኬንያውያን በቀላሉ የሩሲያን የሥራ ገበያ እንዲቀላቀሉ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም ዕቅድ ይዘዋል።
“በምንም መልኩ ከሩሲያ ጋር ያለን አጋርነት ከልዩ ዘመቻ አጀንዳ መነፅር ብቻ እንዲታይ አንፈልግም። በኬንያ እና በሩሲያ መካከል ያለው ግንኙነት ከዚህ የዘለለ ነው” ብለዋል።
በዩክሬን የስለላ ግምገማ መሠረት ከ36 የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ከ1,700 በላይ ሰዎች ለሩሲያ ለመዋጋት ተመልምለዋል።
ደቡብ አፍሪካ፤ ተታልለው ለሩሲያ እንዲዋጉ መደረጋቸውን የተናገሩ 17 ዜጎቿ በዩክሬን ዶንባስ ግዛት ውስጥ ከተያዝ በኋላ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን የካቲት ላይ አስታውቃ ነበር።
ዩክሬንም አፍሪካውያንን ጨምሮ የውጭ ዜጎችን ከጎኗ አሰልፋ ለማዋጋት በመሞከሯ ከዚህ በፊት ትችት ደርሶባታል።
