ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

የጦር መሣሪያ

17 መጋቢት 2026, 08:31 EAT

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አንትሮፒክ የተሰኘው የአሜሪካው የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ኩባንያ፤ ሶፍትዌሩ “በአደገኛ ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዳይውል” ለመከላከል የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች እና ፈንጂ ባለሙያ ሊቀጥር ነው።

ኩባንያው የቅጥር እንቅስቃሴውን የጀመረው፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎቱን በመጠቀም የኬሚካል ወይም የራዲዮአክቲቭ መሳሪያዎችን እንዴት መሥራት እንደሚቻል ለማወቅ የሚጥሩ ተጠቃሚዎች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል እንደሆነ ታውቋል።

ኩባንያው ‘ሊንክዲን’ ላይ ባወጣው የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ፤ አመልካቾች ቢያንስ የአምስት ዓመታት “የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች እና/ወይም ፈንጂዎች መከላከያ” እንዲሁም “የራዲዮሎጂካል መሳሪያዎች” ወይም ቦምቦች እውቀት ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልጿል።

ድርጅቱ ለቢቢሲ እንደተናገረው ሥራው ቀደም ሲል ካወጣቸው ሌሎች ወሳኝ የሥራ መደቦች ጋር ተመሳሳይ ነው።

አንትሮፒክ ይህንን ስትራቴጂ የተከተለው ብቸኛው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ኩባንያ አይደለም።

የቻትጂፒቲ ባለቤት የሆነው ‘ኦፕንኤአይ’ም ተመሳሳይ የሥራ ቅጥር ይፋ አድርጓል። ኦፕንኤአይ “የባዮሎጂካል እና ኬሚካል ስጋት” ተመራማሪ ለመቅጠር ያቀረበው 455 ሺህ ዶላር የሚደርስ ደመወዝ አንትሮፒክ ሊከፍል ካቀደው በእጥፍ ገደማ ይበልጣል።

ዓላማው ተጠቃሚዎችን ለመቆጣጠር ቢሆንም አንዳንድ ባለሙያዎች ግን ይህ አካሄድ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ስለ ጦር መሳሪያዎቹ መረጃ እንዲያገኝ ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የቴክኖሎጂ ተመራማሪው ዶ/ር ስቴፋኒ ሃሬ፤ “ቦምቦችን እና ሌሎች የራዲዮሎጂ መሳሪያዎችን ጨምሮ ሚስጥራዊ ኬሚካሎችን እና የፈንጂ መረጃዎችን ለመቆጣጠር የሰው ሠራሽ አስተውሎት ስርዓቶችን መጠቀም ደኅንነቱ የተጠበቀ ነውን?” ሲሉ ጠይቀዋል።