ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ነዳጅ ማደያ

ከ 3 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የኢትዮጵያ ነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን፤ የነዳጅ አቅርቦት ለፀጥታ እና ደኅንነት ተቋማት እንዲሁም ለሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች በቅድሚያ እንዲሰጥ ለኩባንያዎች እና ለማደያዎች ትዕዛዝ አስተላለፈ።

ነዳጅ ማደያዎች “ተጨማሪ ሳልቫቲዮ አስገጥመው ነዳጅ ለመቅዳት” የሚሞክሩ ተሽከርካሪዎችን ለፀጥታ አካላት እንዲጠቁሙም ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይህንን ውሳኔ የገለጸው ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 8/2018 ዓ.ም. በአገሪቱ ለሚገኙ ሁሉም የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች እና ነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች በጻፈው ደብዳቤ ነው።

በመሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ መኳንንት የተጻፈው ደብዳቤ፤ እነዚህ የቁጠባ እርምጃዎች የተላለፉት በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት “የነዳጅ አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት” ለመከላከል እንደሆነ ያስረዳል።

ሦስተኛ ሳምነቱን የያዘውን የኢራን ጦርነት ተከትሎ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። በዛሬው ዕለት አንድ በርሜን ድፍድፍ ነዳጅ ከ103 ዶላር በላይ በሆነ ዋጋ እየተሸጠ ነው።

የፌደራል መንግሥት በመካከለኛውም ምሥራቅ በተከሰተው ቀውስ ምክንያት የተፈጠረው የነዳጅ ዋጋ መናር እና የአቅርቦት መስተጓጎል የሚያመጣውን ችግር ለመከላከል ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ማሳሰቢያ ሲሰጥ ነበር።

ባለፈው ሳምንት መግለጫ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ “በቅርቡ በተጠና ሁኔታ ተጨማሪ [የነዳጅ] የቁጠባ እርምጃዎች” ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀው ነበር።

በትናንትናው [ሰኞ] ዕለት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ነዳጅን በቁጠባ እና ለመሠረታዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት” ጥቅም ላይ እንዲውል ለነዳጅ አከፋፋዮች፣ ማደያዎች እና ተጠቃሚዎች ማሳሰቢያ ሰጥተዋል

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማሳሰቢያ የጠቀሰው የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን ደብዳቤ፤ “የተፈጠረው ችግር በአገራችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አንድምታ ከወዲሁ ለመከላከል እንዲያስችል” የቁጠባ እርምጃዎች ይፋ መደረጋቸውን ጠቅሷል።

ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቱ ለነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች በጻፈው ደብዳቤ “ማንኛውንም የነዳጅ ጭነት በሚመለከት በቅድሚያ ለፀጥታ ተቋማት” ቅድሚያ እንዲሰጥ አሳስቧል። “ቁልፍ ለሆኑ የመንግሥት ፕሮጀክቶች በተለይም በመጠናቀቅ ላይ ላሉ የልማት ሥራዎች ቅድሚያ እንድትሰጡ” ብሏል።

ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ከተዘረዘሩ ተቋማት መካከል፤ “ኢንዱስትሪዎች እና መሠረታዊ ሸቀጦችን ሚያመርቱ አምራች ድርጅቶች” ይገኙበታል። በዚህም ምድብ ውስጥ “ወደ ውጭ የሚልኩ ኢንዲስትሪዎች” እና “ሰፋፊ የእርሻ ልማቶች” ተጠቅሰዋል።

ኩባንያዎች ነዳጅ የሚያከፋፍሉባቸውን አካባቢዎች በተመለከተም ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል። በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አዲስ አሠራር መሠረት “ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ቦታዎች” እንዲሁም “ከፍተኛ የአገር አቋራጭ የትራንስፖርት ፍሰት ያለባቸው የኮሪደር አካባቢዎች” ትኩረት ይሰጣቸዋል።

ዛሬ የተጻፈው ደብዳቤ ነዳጅ በችርቻሮ ለሚያቀርቡ ማደያዎችም ተመሳሳይ ትዕዛዝ አስተላልፏል። ነዳጅ ማደያዎች “ለሕዝብ ትራንስፖርት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ መስጠት” እንዳለባቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም “ማንኛውም ተሽከርካሪ በፋብሪካው ከተገጠመለት ሰልቫቲዮ [የነዳጅ መያዣ] ውጭ ተጨማሪ ሳልቫቲዮ አስገጥሞ ነዳጅ ለመቅዳት” የሚመጣ ከሆነ እንዳያስተናግዱ ታዝዘዋል። ይህን ፈጽሞ የተገኘ ተሽከርካሪን በአቅራቢያቸው ለሚገኙ ለፀጥታ አካላት እንዲጠቁሙም ተነግሯቸዋል።

የክልል መንግሥት እና የከተማ አስተዳደር መዋቅሮችም “በደብዳቤ ለሚስተናገዱ ቀጥታ ተጠቃሚዎች የሚሰጠው ነዳጅ በጥንቃቄ እና ለታለመለት ዓላማ” መዋሉን እንዲቆጣጠሩ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አሳስቧል።

በተጨማሪም አከፋፋይ ኩባንያዎች “በነዳጅ አጓጓዥ ተሽከርካሪዎች ብልሽት እና በሹፌሮች ልምድ ማነስ” በሚፈጠሩ አደጋዎች ምክንያት ነዳጅ እንዳይባክን በትኩረት እንዲሠሩ አሳስቧል።

የነዳጅ ግብይት ተዋናዮች እነዚህን የቁጠባ እርምጃዎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያሳሰበው የኢትዮጵያ ነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን፤ ትዕዛዙን የማይፈጽሙ አካላት ተጠያቂ እንደሚሆኑም አስጠንቅቋል።

ኢትዮጵያ፤ በኢራን ጦርነት ምክንያት በደረሰው የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል እና የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ውድመት ምክንያት የነዳጅ ቁጠባ እርምጃ የወሰደች ብቸኛዋ አገር አይደለችም። በኢራን በተዘጋው የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ነዳጅ የሚያስገቡት የእስያ አገራት የግል ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ከመገደብ እስከ የሥራ ቀናትን መቀነስ የደረሱ ውሳኔዎችን አስተላልፈዋል።