ዳታን በመቆጠብ ጽሑፍ ብቻ ለማንበብ

ጆ ኬንት
የምስሉ መግለጫ,ጆ ኬንት

ከ 2 ሰአት በፊት

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር የፀረ ሽብርተኝነት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ጆ ኬንት የኢራንን ጦርነት በመቃወም ከኃላፊነታቸው ሲለቅቁ እና ፕሬዝዳንቱ በጦርነቱ ላይ የያዙትን “አካሄድ እንዲቀይሩ” አሳስቡ።

የብሔራዊ የፀረ ሽብርተኝነት ማዕከል ዳይሬክተር ጆ ኬንት በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት ደብዳቤ ኢራን ለአሜሪካ “ምንም ዓይነት ስጋት እንደማትደቅን” ገልጸው፤ የትራምፕ አስተዳደር ይህንን ጦርነት የጀመረው በእስራኤል እና አሜሪካ ውስጥ ባሏት ኃያላን ደጋፊዎቿ ግፊት ነው ብለዋል።

የ45 ዓመቱ ጎልማሳ ኬንት የአሜሪካ ልዩ ኃይል እና ስለላ ድርጅቷ ሲአይኤ የቀድሞ አባል የነበሩ ሲሆን፣ ባለቤታቸው የባሕር ኃይል ባልደረባ የነበረችው ሻነን ኬንት በአውሮፓውያኑ 2019 ሶሪያ ውስጥ በአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ተገድላባቸዋለች።

የኬንት ሥልጣን መልቀቅን በተመለከተ ቢቢሲ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስተያየት ጠይቋል።

ጆ ኬንት ሥልጣን ከመልቀቅ ባሻገር አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱትን ጦርነት በይፋ በመተቸት በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛው ባለሥልጣን ናቸው።

በደብዳቤያቸው ላይ ኬንት ቀደም ሲል ትራምፕ ለፕሬዝዳትነት ያቀረቡትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የመወዳደሪያ አጀንዳ ይደግፉ እንደነበር እንዲሁም እስከ ካለፈው ዓመት ድረስ ትራምፕ “በመካከለኛው ምሥራቅ የተደረጉ ጦርነቶች የአሜሪካውያንን ውድ ሕይወት የነጠቁ እና የአገራችንን ሀብት እና ብልጽግና ያሳጡ መሆናቸውን ብለው ይረዱ ነበር” የሚል እምነት እንደነበራቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኬንት “ከፍተኛ የእስራኤል ባለሥልጣናት” እና ተጽእኖ ፈጣሪ የአሜሪካ ጋዜጠኞች “የተሳሳተ መረጃ” አስፋፍተው ትራምፕ “ቅድሚያ ለአሜሪካ” የሚለውን አጀንዳቸውን ችላ እንዲሉ አድርገዋቸዋል ሲሉ ከስሰዋል።

የኃላፊነት መልቀቂያ ደብዳቤያቸው አክሎም “ይህ ሲስተጋባ የነበረው ነገር ኢራን በአሜሪካ ላይ የማይቀር ስጋት እንደጋረጠች እንዲያምኑ ለማሳሳት ጥቅም ላይ ውሏል፤ ነገር ግን ውሸት ነበር” ብለዋል።

የትራምፕ የረዥም ጊዜ ደጋፊ የነበሩት ኬንት ለአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልነት ሁለት ጊዜ ተወዳድረው ያልተሳካላቸው ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ በጠባብ ድጋፍ ነበር ሹመቸታው ተቀባይነት ያገኘው።

የአሜሪካ ብሔራዊ የፀረ ሽብርተኝነት ማዕከል ዳይሬክተርነት ሥልጣንን ለመቀበል ምክር ቤት በቀረቡበት ጊዜ ብዙ ዴሞክራቶች ኬንት ከአክራሪ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው በማለት ተችተዋቸው ነበር።

ሥልጣናቸው በጸደቀበት የሴኔቱ ስብሰባ ኬንት ትራምፕ በጆ ባይደን መሸነፋቸውን ተከትሎ በአሜሪካ ምክር ቤት ሕንጻ ውስጥ የተከሰተውን ግርግር የፌደራል ኃይሎች ቀስቅሰውታል የሚለውን ክስ እና ትራምፕ በ2020 ምርጫ አሸንፈዋል የሚለውን አቋማቸውን ለመቀየር ሳይፈቅዱ ቀርተዋል።

በብሔራዊ የፀረ ሽብርተኝነት ማዕከል ዳይሬክተር ሆነው ተጠሪነታቸው ለአሜሪካ ብሔራዊ መረጃ ዳይሬክተር ቱልሲ ጋባርድ ሲሆን፣ በዓለም ዙሪያ ሊከሰቱ የሚችሉ የሽብር አደጋዎችን ትንተና እና ምርመራን በበላይነት ይቆጣጠሩ ነበር።

በኢራቅ የሚገኘውን የአሜሪካ ጦር ልዩ ኃይል ጨምሮ ጆ ኬንት ቀደም ሲል ከአሜሪካ ጦር ሠራዊት ጋር 11 ጊዜ ወደ ባሕር ማዶ ለግዳጅ ተሰማርተዋል።

በኋላ ላይም ባለቤታቸው ሶሪያ ውስጥ ከተገደሉ በኋላ የመንግሥት አገልግሎትን ከመልቀቃቸው በፊት በአገሪቱ የስለላ ተቋም ሲአይኤ ውስጥ የፓራሚሊታሪ መኮንን ሆነው አገልግለዋል።

ኬንት የባለቤታቸውን ሞት እና በአሜሪካ ሠራዊት ውስጥ ስለሰጡት አገልግሎት በደብዳቤያቸው ላይ ከኢራኑ ጦርነት ጋር አያይዘው ጠቅሰዋል።

“ቀጣዩን ትውልድ የአሜሪካንን ሕዝብን በማይጠቅም እና አሜሪካውያን በሕይወታቸው የሚከፍሉትን ዋጋ ትክክለኝነት ወደማያረጋግጥ ጦርነት መላክን ልደግፍ አልችልም” በማለት አሜሪካ ከኢራን ጋር የገባችበትን ጦርነት ተቃውመዋል።

ከኢራን ጦርነት በፊት በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸው ይታወቃል።

ነገር ግን አንድ ዓመት ባለፈው ሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው እምብዛም የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ አላጋጠማቸውም።

ትራምፕ ከእስራኤል ጋር በማበር በከፈቱት ጦርነት ምክንያት ከተለያዩ ወገኖች ትችቶች እየቀረቡባቸው ሲሆን፣ ከከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ተቃውሞ እና ከኃላፊነት መልቀቅ ሲያጋጥማቸው ጆ ኬንት የመጀመሪያው ናቸው።

የዋይት ሐውስ ፕሬስ ክፍል ኃላፊ ካሮላይን ሌቬት ኢራን ምንም ስጋት አልደቀለችም የሚለውን “ዲሞክራቶች እና አንዳንድ ሊብራል መገናኛ ብዙኃን የሚያቀርቡትን ሐሰተኛ ክስ” ኬንት አስተጋብተዋል ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።

ቃል አቀባይዋ ጨምረውም “ፕሬዝዳንት ትራምፕ በግልጽ እንደጠቀሱት፣ ኢራን ቀድማ በአሜሪካ ላይ ጥቃት ልትፈጽም እንደነበረ ጠንካራ እና አሳማኝ ማስረጃ ነበራቸው” ብለዋል።

እንዲሁም ኬንት “ትራምፕ ውሳኔ ያሳለፉት በሌሎች ተጽእኖ እንዲሁም በአገራት ጫና ነው ማለት ስድብ እና የሚያስቅ ነገር ነው” በማለት ሌቬት ተችተዋል።

ወግ አጥባቂው የመገናኛ ብዙኃን ተንታኝ ተከር ካርልሰን ከኒው ዮርክ ታይምስ ጋር ባደረገው አጭር ቃለ ምልልስ፣ በግል የቀረበ ግንኙነት ያላቸውን ከሥልጣን የለቀቁትን ጆ ኬንትን አድንቋቸዋል።

“ጆ ከማውቃቸው ሰዎች ደፋሩ ነው፣ እንዲሁ በቀላሉ ችላ የሚባል ሰው አደይለም” ብሏል ካርልሰን።

“በጣም አስተማማኝ የደኅንነት መረጃ የሚስገኝለትን ሥራን ነው የሚለቅቀው። በዚህም የተነሳ አዲሶቹ ወግ አጥባዎች ሊያጠቁት ሊሞክሩ ይችላሉ” ብሏል።